ነመድ

ከውክፔዲያ

ነመድአየርላንድ ልማዳዊ አፈ ታሪክ ዘንድ በአየርላንድ በጥንት የሰፈረ ንጉሥ ነበር። የነመድ ዘመድ ፓርጦሎን ወገን በቸነፈር ከሞተ 30 ዓመታት በኋላ የነመድ ወገን ከእስኩቴስ እንደ ደረሰ ይጻፋል። በነመድ ዘመን 4 ሐይቆች ከምድር መነጩ። ነመድ በሮስ ፍሬቃይን ውግያ የፎሞራውያንን አለቆች ጋንና ሰንጋንን ገደላቸው። አምባዎች በራይጥ ቂምባይጥና በራይጥ ቂንደይቅ እንደ ቆፈረ 12ም ሜዳዎች እንደ ተጠሩ ይጨመራል። በሌላ 3 ውግያዎች ደግሞ ነመድ ፎሞራውያንን አሸነፈ፦ ባድብግና በኮናሕት፤ ክናምሮስ በለይንስተር፣ ሙርቦልግ በዳልሪያታ። 9 አመት ከደረሰ በኋላ ነመድም ከቸነፈር ሞተ።

ነመዳውያን[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከዚያ የፎሞራውያን አለቆች ኮናንድና ሞርክ በነመድ ወገን ላይ ዕጅግ ጨቆኑባቸው። የፎሞራውያን አምባ የኮናንድ ግምብ በቶሪ ደሴት ላይ ነበር። ከነመዳውያን ምርት፣ ወተትና ልጆችም ሳይቀሩ 2 ሢሶዎች በየዓመቱ ለፎሞራውያን ማቅረብ ነበረባቸው። ከጊዜ በኋላ ግን ነመዳውያን አመጹ፣ 60,000 ነመዳውያን ተነሥተው ግንቡን አጠፉ፣ ኮናንድን ገደሉ። ከደሴቱ ሲመለሱ ግን መርከቦቻቸው በሞርክ ወገን ተሰመጡ። ሌቦር ጋባላ ኤረንጊላ ኮማይን ግጥም (1064 ዓም) ሲጠቅስው፣ ይህ የሆነው የነመድ ወገን ከደረሰው 217 ዓመት በኋላ ነበር። የቀሩት ነመዳውያን ተበተኑ፤ አንድ ወገን ወደ ታላቅ ብሪታንያ ገባ፤ አንዱም ወደ ስሜን ሄዶ ቱአጣ ዴ ዳናን ሆኑ፤ ሦስተኛውም ወገን ከነመድ ተወላጅ ስምዖን ጋራ ወደ ግሪክ አገር ገባ። ግሪኮች ግን ባርዮች አደረጉዋቸው፤ አፈር በቦርሳዎች ውስጥ ወደ ተራራ ጫፍ መሸከም ነበረባቸው። ስለዚህ ስማቸው «ፊር ቦልግ» (የቦርሳ ሰዎች) ተባለ። ከሌላ 200 ዓመታት በኋላ የነመድ ተወላጆች የነበሩት 5000 ፊር ቦልግ ከግሪክ አገር በ1,130 መርከቦች አመለጡ። መርከቦቹንም ወይም ከቦርሳዎች ፈጠሩ ወይም ከግሪኮች ሰረቁ፤ እንደ ልማዱ ዝርዝሩ ይለያያል። መጀመርያ በእስፓንያ ደርሰው ከዚያ ወደ ነመድ አገር ወደ አይርላንድ ተመልሰው በ፭ አለቆቻቸው ሥር ወረሩ። ዋና አለቃቸው ስላንጋ መጀመርያው የፊር ቦልግ ከፍተኛ ንጉሥ ሆነ።

ይህ ሁሉ ከአይርላንድ ታሪክ መጻሕፍት ውጭ አልተገኘም።