ስላንጋ

ከውክፔዲያ

ስላንጋ ወይም ስላይንገ (ስላይኔ) ማክ ዴላአየርላንድ ልማዳዊ አፈ ታሪክ ዘንድ ከፊር ቦልግ የአየርላንድ መጀመርያ ከፍተኛ ንጉሥ ነበር። ስላንጋ የዴላ ልጅና የነመድ ዘር ነበር። ሚስቱ ፉዋድ ተባለች።

ፎሞራውያን የነመድ ወገን ካሸነፉ በኋላ የቀሩት ነመዳውያን ተበተኑ፤ አንድ ሢሶ ወደ ታላቅ ብሪታንያ ገባ፤ አንዱም ወደ ስሜን ሄዶ ቱአጣ ዴ ዳናን ሆኑ፤ ሦስተኛውም ወገን ከነመድ ተወላጅ ስምዖን ጋራ ወደ ግሪክ አገር ገባ። ግሪኮች ግን ባርዮች አደረጉዋቸው፤ አፈር በቦርሳዎች ውስጥ ወደ ተራራ ጫፍ መሸከም ነበረባቸው። ስለዚህ ስማቸው «ፊር ቦልግ» (የቦርሳ ሰዎች) ተባለ። ከ200 ዓመታት በኋላ የነመድ ተወላጆች የነበሩት 5000 ፊር ቦልግ ከግሪክ አገር በ1,130 መርከቦች አመለጡ። መርከቦቹንም ወይም ከቦርሳዎች ፈጠሩ ወይም ከግሪኮች ሰረቁ፤ እንደ ልማዱ ዝርዝሩ ይለያያል። መጀመርያ በእስፓንያ ደርሰው ከዚያ ወደ ነመድ አገር ወደ አይርላንድ ተመልሰው በ፭ አለቆቻቸው ሥር ወረሩ። ዋና አለቃቸው ስላንጋ እንዲሆን ተመረጠ።

ስላንጋ እና አራት ወንድሞቹ — ሩድራይግጋንጌናንሴንጋን — ሻለቆች ሆነው አይርላንድን (ወይም የዛኔው ስም ኢኒስ ኤልጋ) በአምስት ክፍሎች ከፋፈሉ። የስላንጋ ወገን «ጋይሊዮይን» በስላይኔ ወንዝ አፍ በወክስፎርድ ወደብ ደሴቱን ገቡ። የስላንጋ ክፍል ሌንስተር የሚባል ክፍላገር ሆነ። ባብዛኛው ታሪኮች ዘንድ ስላንጋ ከአንድ አመት በኋላ ዓረፈና ወንድሙ ሩድራይግ ተከተለው። ከሁሉ ቀድሞ የተቀነባበረው ዝርዝር የላውድ አቆጣጠሮች (1021 ዓም) ፪ አመታት ይሰጠዋል።

ጊላ ኮማይን 1064 ዓም ግጥም (በሌቦር ጋባላ ኤረን እንደ ታተመ) እንዲህ አለው፦

«አንድ አመት ለስላይነ፣ ለጀግናው፤
ከባድ ድንገት በሽታ እስከ ገደለው ድረስ፣
በዱማ ስላይነ ተቀበረው፣
መጀመርያው የአይርላንድ ነጭ ፈረሶች ንጉሥ።»

የተቀበረበት ቦታ እስከ አሁን ስለይን፣ አይርላንድ ይባላል።

ቀዳሚው
ፎሞራውያን
አይርላንድ (ኤልጋ) ከፍተኛ ንጉሥ
1538-1536 ዓክልበ. ግድም (አፈታሪክ)
ተከታይ
ሩድራይግ