Jump to content

ፊር ቦልግ

ከውክፔዲያ

ፊር ቦልግአየርላንድ አፈ ታሪክ በአየርላንድ በጥንት የሠፈረ ብሔር ነበር።

ፎሞራውያንነመድ ወገን ካሸነፉ በኋላ የቀሩት ነመዳውያን ተበተኑ፤ አንድ ሢሶ ወደ ታላቅ ብሪታንያ ገባ፤ አንዱም ወደ ስሜን ሄዶ ቱአጣ ዴ ዳናን ሆኑ፤ ሦስተኛውም ወገን ከነመድ ተወላጅ ስምዖን ጋራ ወደ ግሪክ አገር ገባ። ግሪኮች ግን ባርዮች አደረጉዋቸው፤ አፈር በቦርሳዎች ውስጥ ወደ ተራራ ጫፍ መሸከም ነበረባቸው። ስለዚህ ስማቸው «ፊር ቦልግ» (የቦርሳ ሰዎች) ተባለ። ከነዚህም ውስጥ «ፊር ዶምናይን» አፈሩን የቆፈሩት ክፍል ሲሆን፣ ሌላውም «ጋሌዮይን» ተብለው ጦር የያዙት ዘበኞች ነበሩ፡

ከ200 ዓመታት በኋላ የነመድ ተወላጆች የነበሩት 5000 ፊር ቦልግ ከግሪክ አገር በ1,130 መርከቦች አመለጡ። መርከቦቹንም ወይም ከቦርሳዎች ፈጠሩ ወይም ከግሪኮች ሰረቁ። ከአንድ ዓመት በኋላ ከግሪክ ወደ እስፓንያ ደርሰው ከዚያም ወደ ወላጃቸው ነመድ አገር ወደ አይርላንድ ተመልሰው በ፭ አለቆቻቸው ሥር ወረሩ። ዋና አለቃቸው ስላንጋ እንዲሆን ተመረጠ። «የአይርላንድ ታሪክ» በተባለው መጽሐፍ ዘንድ፣ የአይርላንድ ስያሜ በፊር ቦልግ ሥር «ኢኒስ ኤልጋ» (ክቡር ደሴት) ተባለ።

የፊር ቦልግ ነገሥታት በጠቅላላ አይርላንድን ለ፴፯ ዓመታት ገዙ። ያንጊዜ ዘመዶቻቸው «ቱአጣ ዴ ደናን» ነገዶች ወደ አይርላንድ ተመለሱ፤ ፊር ቦልግ ግማሹን አገር ለማካፈል ፈቃደኞች ስላልነበሩ የቱአጣ ዴ ሃይላት በማግ ቱይሬድ ውግያ አሸነፏቸውና ስለዚህ ፊር ቦልግ የአይርላንድ ሩብ ብቻ (ኮናኽትን) ለመናርያቸው ተቀበሉ።

ጥንታዊው የአይርላንድ ስዋሰው መጽሐፍ አውራከፕት ና-ኔከስ (650-1050 ዓም ያህል የተቀነባበረው) ለፊር ቦልግ ቋንቋ ናሙናዎች «ዊንዲዩስ» (እሱ፣ ተባዕት)፣ «ዊንድሲ» (እሷ) እና «ኦንዳር» (እሱ፣ ግዑዝ) ይሰጣል።