ብሬስ

ከውክፔዲያ

ዮካይድ ብሬስአየርላንድ ልማዳዊ አፈ ታሪክ ዘንድ ከቱዋጣ ዴ ዳናን ወገን የአየርላንድ መጀመርያው ከፍተኛ ንጉሥ ነበር። አባቱ የፎሞራውያን ንጉሥ ኤላጣ ሲሆን እናቱ የቱዋጣ ዴ ልዕልት ኤሪው ነበረች።

የቱዋጣ ዴ ዳናን ወገን እንደ ፊር ቦልግነመድ ተወላጆች ነበሩ። በ1625 ዓ.ም. አካባቢ የታተመው የሴጥሩን ኬቲን ታሪክ መጽሐፍ የአይርላንድ ታሪክ እንዳለው፤ የነመድ ልጆች ከአይርላንድ ሲበተኑ ቱዋጣ ዴ ዳናን ደግሞ በግሪክ አገር (ቦዮቲያአቴና አካባቢ) ይቆዩ ነበር። በዚያ ሲኖሩ ጠንቋይና አስማት ተማሩ። በዚያን ጊዜ የሶርያ ሥራዊት በብዙ መርከቦች ውስጥ ለጦርነት በግሪክ ደረሱ። ሶርያውያን የቱዋጣ ዴ ጠንቋይ አሸንፈው ቱዋጣ ዴ ሁላቸው ከግሪክ ወደ «ሎቅላን» (የአሁኑ ኖርዌ) ሸሹ፤ በዚያ ስለ ዕውቀታቸው አራት ከተሞች ከሕዝቡ ዘንድ ተቀበሉ፦ ከተሞቹም ፋልያስ፣ ጎርያስ፣ ፊንያስና ሙርያስ ተባሉ። በያንዳንዱ ከተማ ሕዝቡን ለማስተምር ትምህርት ቤት ከመሠረቱ በኋላ፣ ከኖርወይ ወደ ስኮትላንድ ሔደው እዚያ ለ፯ ዓመት ቆዩ። መሪያቸውናንጉሣቸው ኑዋዳ ነበር።

በመጨረሻ በአይርላንድ ደረሱ፤ ነገር ግን ዘመዶቻቸው ፊር ቦልግ ግማሹን ደሴት ለማካፈል ፈቃደኞች አልነበሩም። ስለዚህ በአንድ ታላቅ ውግያ በማግ ቱይረድ ውግያ ፊር ቦልግ ተሸነፉ። የቱዋጣ ዴ ንጉሥ ኑዋዳ እጅ ስለ ተቋረጠ ዮካይድ ብሬስ ለ፯ አመት በአይርላንድ ነገሠ። እርሱ ግን ግማሽ ከፎሞራውያን ወገን ስለሆነ ለነርሱ ጥቅም ገዛቸው። በ፯ኛው ዓመት ኑዋዳ በጠንቋይ አዲስ የብር እጅ ስላገኘ ያንጊዜ እንደገና የቱዋጣ ዴ ንጉሥ ሆነ።

ኑዋዳ ለ፳ ዓመታት ገዝቶ በ1474 ዓክልበ. ብሬስ በፎሞራውያን እርዳታ ተመልሶ ኑዋዳን ተዋግቶ በሁለተኛው የማግ ቱይረድ ውግያ ተሸነፈ። ሆኖም ኑዋዳ በዚሁ ውግያ ተገድሎ ሌላ የፎሞራውያን ክልስ ሉግ ተከተለው። ብሬስ ተማርኮ ለሕዝቡ ግብርና ቢያስተምር እንዲኖር ተፈቀደ። በኋላ ግን ሉግ በተንኮል ብሬስን ገደለው። እንደ ትውፊቱ፣ ሉግ ፫ መቶ የእንጨት ላሞች ሠርቶ በፋንዲያ ሞላቸው፣ ብሬስንም ተጋብዞ ከዚህ ሲጠጣ ሞተ።

ቀዳሚው
ዮካይድ ማክ ኤይርክ
አይርላንድ (ባንባ) ከፍተኛ ንጉሥ
1501-1494 ዓክልበ. (አፈታሪክ)
ተከታይ
ኑዋዳ