ማርኮ ፖሎ

ከውክፔዲያ
ማርኮ ፖሎ

ማርኮ ፖሎ (1254 - ጥር 8፣ 1324) ጥንታዊው የጣሊያን ተጓዥ እና ነጋዴ ነበር። ታዋቂነትም ያተረፈው በተለይ ወደቻይና እና ሞንጎሊያ ከተጓዙት አውሮጳውያን ቀደምትነት ስለነበረው ነው። በዚህ ምክንያት ከሱ በኋላ ዘግይተው የተነሱት እነ ክርስቶፎር ኮሎምበስ ሳይቀር ለሱ ከፍተኛ ግምት እና አድንቆት እንደነበራቸው ታሪክ ይዘክራል። ት 1 17 አመት ሲሞላው ከጣሊያን ቬኒስ ከተማ በመነሳት፣ መጀመሪያ በጀልባ ከዚያም በእግሩና በግመል ተራሮችን በርሃን አቆራርጦ ቤይቺንግ ቻይና (በድሮ ስሟ ካቴ]) ለመድረስ ችሏል። በጊዜው ቻይና ትመራ የነበረው በሞንጎሉ መሪ ኩብላ ካህን የሚባለው የጌንጊዝ ካህን ልጅ ነበር። ስርዓቱም የዩዋን ሥርወ መንግስት ይባል ነበር። ለሚቀጥሉት 17 ዓመታት በኩብላ ካህን ቤተመንግስት አስተዳደር ተሰጥቶት መንግስቱን አገልግሏል። ከዚያም ወደ ጣሊያን በውቅያኖሶች አቋርጦ ተመልሷል። ወደ600 የሚሆኑ አብሮ ተጓዦች ግን በበሽታና በጥቃት ሞተዋል።

ይህ ተጎዥ ኑድል የተባለውን የቻይኖች የምግብ አይነት ወደ አገሩ ጣልያን በማምጣት የፓስታ ስራ አሰራርን ለጣሊያኖች ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋውቋል።

በጣሊያኖች እርስ በርስ ጦርነት ተማርኮ እስር ቤት ከገባ በኋላ ለእስር ጓደኛው ርስቲቸሎ የነገረውን ታሪክ ረስቲቸሎ ጽፎ በማሳተም ለማርኮ ፖሎ በአውሮጳ ዙርያ ታላቅ መታወቅን አስገኝቶለታል።

ማርኮ ፖሎ በነበረበት ዘመን ስለኢትዮጵያ የመዘገበው [1][ለማስተካከል | ኮድ አርም]

«አበሻ በሌላ አጠራር መካከለኛው ህንድ ወይም ሁለተኛው ህንድ ተብሎ ይታወቃል። ዋናው ልዑሉ ክርስቲያን ሲሆን በሱ ስር 6 ሌላ ንጉሶች አሉ። ሶስቱ ክርስቲያን ሲሆኑ ሶስቱ ደግሞ እስላም ናቸው። ሁሉም ግን በክርስቲያኑ ንጉስ ስር ይተዳደራሉ። ንጉሰ ነገስቱ በአገሪቱ መካከለኛ ስፍራ ይኖራል [ምናልባትም ተጉለት? ]። የእስላሙ ዋና ንጉስ የሚኖረው ኤደን አካብቢ ነው። የአቢሲኒያ ሰወች በጣም ጠንካራ ናቸው፣ ታላቅም ጦረኞች ናቸው፣ ከአዳል ሱልጣኔት፣ ከኑቢያ መንግስት እና ሌሎች መንግስታት ጋርም የማያቋርጥ ውጊያ ያደርጋሉ። በዚህ ምክንያት በህንድ ውስጥ ካሉ ወታደሮች ሁሉ ዋና ሃይለኞቹ እነሱ ናቸው።

እንደሰማሁት፣ በ1288 የሃበሻው ንጉስ ወደ እየሩሳሌም በመሄድ የኢየሱስ ክርስቶስን መቃብር ለመሳለም ፈልጎ የሱ መኮንኖች ይህ የሚያስከትለውን ችግር በተለይ የእስልምና ተከታይ መንግስታት በአካባቢ መብዛትን ግምት ውስጥ በማስገባት በሱ ምትክ በሃይማኖተኛነቱ ይደነቅ የነበረ ጳጳስ እንዲሄድ አድርጎ ይህ ጳጳስ እየሩሳሌም በመሄድ ስለት አስገብቷል። ጳጳሱ ሲመለስ ግን አዳል ውስጥ ተማርኮ የአዳሉ መሪ ጳጳሱ እስልምና እንዲቀበል ቢመክረው እምቢ በማለቱ ጳጳሱ እንዲገረዝ [እንዲሰለብ?] አደረገ። ከዚያም ጳጳሱ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ የተደረገበትን ግፍ ለንጉሱ ነገረው። ንጉሱም ወዲያው ፈረሱን አስጭኖ ከሰራዊቱ ጋር አዳልን ለማጥፋት ዘመተ። የአዳሉም ልዑል የአቢሲኒያ ጦር እንደዘመተበት በሰማ ጊዜ ሁለት ባለ ብዙ ሰራዊት እስልምና ተከታይ ንጉሶች ከእንዲረዱት ጥሪ አደረገ። ነገር ግን የሃበሻው ንጉስ ስላሸነፋቸው የኤደንን [አዳል?] ዋና ከተማ [ዘይላ?] በመቆጣጠር ከተማይቱን በዘበዘ። ይህም ለጳጳሱ የተደረገበትን ጉዳት ለመበቀል ነበር። [2]

የአቢሲኒያ ሰወች የሚበሉት ስንዴሩዝ፣ እና ወተት ነው። የምግብ ዘይት የሚሰሩት ከሰሊጥ ሲሆን የተትረፈረፈ ሰብልን ያመርታሉ። ዝሆኖችአንበሶችቀጭኔወች፣ እንዲሁም ፍየሎችና የተያዩ የወፍ ዝርያወች በአገራቸው ይገኛሉ። ሰውን የሚመስሉ ዝንጀሮወችና ጦጣወች እንዲሁም ብዙ የተለያዩ እንስሳቶች አሉ። ውስጠኛው የአገሪቱ ክፍል ብዙ ወርቅ አለው፣ ነጋዴወችም በራሳቸው ፈቃድ በአገሪቱ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ ምክንያቱም ብዙ ጥቅም ስለሚያገኙበት።»

ማርኮ ፖሎ ይህን ጽሁፍ የጻፈው በ1290 እ.ኤ.አ. ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ከተገኙ ገድላት ጋር አንድ አይነት ታሪክ እንደሆነ ሳልት የተባለው የእንግሊዝ ተጓዥ አረጋግጧል። የማርኮ ፖሎ ጽሁፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተገኙ ገድላት ጋር ተመሳሳይ ታሪክ ያስቀምጥ እንጂ የንጉሱን ስም ግን አልጻፈም። የማርኮ ፖሎን ጽሁፍ ያጠኑ ታሪክ ተመራማሪወች፡ ለምሳሌ ትሪንግሃም[3] እና ሪቻርድ ፓንክረስት [4] ንጉሱ አጼ ይግባ ጽዮን እንደነበር ለማረጋገጥ ችለዋል።

ማጣቀሻወች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ Extract from the Travels of Marco Polo. (Lib. iii. in Ramusio, page 59, c. 38.
  2. ^ [ ጄምስ ብሩስ የጻፈው መጽሃፍ ላይ Mr. Bruce's Travels, Vol. III. ማርኮ ፖሎን ሳይጠቅስ ኢትዮጵያዊ ገድልን አጣቅሶ ካለው ታሪክ ጋር ይስማማል ]http://www.archive.org/details/travelstodiscove03bruc
  3. ^ J. Spencer Trimingham, Islam in Ethiopia (Oxford: Geoffrey Cumberlege for the University Press, 1952), pp. 69f.
  4. ^ Richard P.K. Pankhurst, History of Ethiopian Towns (Wiesbaden: Franz Steiner Verlag, 1982), p. 55.