Jump to content

ሸለምጥማጥ

ከውክፔዲያ


?ሸለምጥማጥ

ሳይንሳዊ ደረጃ መስጫ
ስፍን: ጉንደ እንስሳ (Animalia)
ክፍለስፍን: አምደስጌ (Chordata)
መደብ: አጥቢ (Mammalia)
ክፍለመደብ: ስጋበል
አስተኔ: የጥርኝ አስተኔ Viverridae
ወገን: ሸለምጥማጥ Genetta
ዝርያ: 17 ዝርያዎች

ሸለምጥማጥ ኢትዮጵያና ሌላ አገር ውስጥ የሚገኝ አጥቢ እንስሳ ነው።

የእንስሳው ሳይንሳዊ ጸባይ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሸለምጥማጦች አጫጭር ቅልጥም ያላቸውና ሽንጠ ረጅም የሆኑ፣ በከፊል ዛፍ ላይ የሚኖሩ ሥጋ-በሎች ናቸው። በሙሉ ጀርባቸው በረጃጅም ተርታዎች ነጠብጣብ አላቸው። ረጅም ጅራታቸው ቀለበቶች የመሳሰሉ ጥቋቁር ክቦች አለው። ሁሉም እግሮቻቸው አምስት አምስት ጣቶች አሏቸው። ክብደታቸው ፪ ኪሎ ግራም ገደማ ነው። ዓይኖቻቸው ከፊት ለፊት ይገኛሉ። አፋቸው ጋ ረጃጅም ፀጉር አላቸው። ኮኮኔዎቻቸው የጎበጡና ስል፣ የሚወጡና የሚገቡ ናቸው።

ሸለምጥማጦች ቀልጣፋና በዛፍ ላይ ሆነ በምድር ብቁ አካላዊ እንቅስቃሴ ያላቸው አዳኞች ናቸው። አንዳንዴ አድፍጠው፣ አንዳንዴ አሯሩጠው ያድናሉ። የሌሊት እንስሳት ናቸው። ደማቅ የጨረቃ ብርሃን ሲኖርም ተግባራቸውን በቅልጥፍና ያካሂዳሉ። በኢትዮጵያ፣ በኦሞ ፓርክ በተደረገ ጥናት፣ ‹‹G. tigrina›› ብዙ ተግባሮቻቸውን የሚያካሂዱት፣ ፀሐይ ከጠለቀች ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት መሆኑ ተረጋግጧል።

ሸለምጥማጦች እጅጉን የተለያዩ ዓይነት ምግቦች ይበላሉ። አይጥየሌሊት ወፍ፣ ሜንጦዎች፣ አእዋፍ (ዶሮ የሚያህሉት ድረስ)፣ እንሽላሊትእባብእንቁራሪት፣ የእግዜር-ፈረስ፣ ጢንዚዛ፣ ሸረሪት፣ አርባ እግር፣ ጊንጥ፣ የሳት ራት የመሳሰሉትን ሁሉ ይበላሉ፡፡ ፍራፍሬና የአበባ ወለላም ይበላሉ። የታወቀ የዶሮ ሌባ ነው።

ሸለምጥማጦች የማሽተት ኃይላቸው እጅግ የዳበረ ነው። ሽንት፣ ዓይነ ምድር እና ከተለያዩ የአካል ክፍሎች ከሚወጡ እዦች፣ የአካባቢው ኗሪ ሸለምጥማጥ ወይንስ የእንግዳ መሆኑን መለየት ይችላሉ።

በዓይነ ምድር መውጫና በቆለጥ (ወይም ሴት ከሆነች በብልቷ) መካከል ዘይትነት ያለው ብጥብጥ እዥ የሚያወጣ ዕጢ አላቸው። በዚህ እዥ ነው ወይ ከኋላቸው ዝቅ ብለው፣ አሊያም ከቆመ ነገር ጋር ተሻሽተው ምልክት የሚያደርጉበት። መለስተኛ መዓዛ ያለው ይህ እዥ፣ ሲደርቅ ቡናማ ጥቁር ይሆናል። ተደጋግሞ የተጠረገበት ግንድ ከአራት ዓመት በኋላም የሸለምጥማጥ ጠረን ይኖረዋል።


አስተዳደግ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ማኅበራዊ አደረጃጀታቸው፣ ግለኛ፣ ዋነኞቹ ወንዶች የአያሌ ሴቶችን መኖርያ የሚጠብቁበት፣ ማለትም አንድ ወንድ ብዙ ሴቶችን የሚቆጣጠርበት ነው። ምንም እንኳ አንዳንዴ ወንድና ሴት ከልጆቻቸው ጋር እንደ አንድ ቡድን ሊታዩ ቢችሉም፣ ሸለምጥማጦች ግለኛ ቢባሉ ትክክል ነው። ትልቁ ቡድን እናትና ቡችሎቿ ናቸው። ይኸም የሚዘልቀው፣ ቢበዛ መንፈቅ ሞልቷቸው ጡት እስኪጥሉ ነው። ሆኖም የዳበረ አካል የሚኖራቸው በሁለት ዓመታቸው ግድም ነው። ወንዶቹ እስከ አምስት ካሬ ኪሎ ሜትር በሆነ ሥፍራ የሚዘዋወሩ ሲሆኑ፣ ሴቶቹ እጅግ በጠበበ ሥፍራ የተወሰኑ ናቸው። ሆኖም ግን ተይዘው፣ ከተጠመዱበት ሥፍራ ፴፭ ኪሎ ሜትር ርቀት የተለቀቁ ሴት ሸለምጥማጦች፣ በጥቂት ቀናት ከመኖርያ ሥፍራቸው ተመልሰዋል። ወንዶቹ በክልላቸው በሚዘዋወሩበት ጊዜ፣ የርምጃቸው ፍጥነት በሰዓት ሦስት ኪሎ ሜትር ይሆናል።


ሴቶቹ በዓመት ሁለት ጊዜ በአማካይ በአንድ ጊዜ ከሁለት እስከ ሦስት ግልገሎች ይወልዳሉ። የሚያረግዙት ከ፸ እስከ ፸፯ ቀናት ነው። በስሪያ ወቅት የሴቷን ብልት ወይም ሽንት ወይም እዥ ያሸተተ ወንድ፣ ሽቅብ ያንጋጥጣል። የደራች መሆኑን ይገነዘባል። ከዚያ እያጉረመረመና የጉንፋን የመሰለ ድምፅ እያሰማ ይከተላታል። በመጀመርያ ታፋና ጭራዋን ዝቅ አድርጋ ትሸሸዋለች። በኋላ ግን እንዲጠጋት ትፈቅዳለች። ፊታቸውንና ብልቶቻቸውን ተሸታትተው፣ ጉንጮቻቸውን ይተሻሻሉ። ሴቷ ጭራዋን ከፍ አድርጋና ወደ ጎን ብላ፣ ከታፋዋ ከፍ ብላ ትጋብዘዋለች። ደረትና ሆዱ ከታፋዋ ላይ አርፎ፣ በእጆቹ ከላይ በኩል ጭኖቿን ይዞ፣ ግንኙነቱን ይፈጽማል። አንዳንዴ አምስት ደቂቃ በሚፈጀው ስሪያ በመጨረሻዎቹ ሰኮንዶች፣ የአንገቷን ፀጉር ይነክሳል። ከዚያ ሴቷ በቂጧ ትንፏቀቅና በጀርባዋ ትንከባለላለች። በመጨረሻ ሁለቱም የየራሳቸውን ብልቶች ይልሳሉ።

ሸለምጥማጦች የሚወልዱት በጉድጓድ ውስጥ ወይም ከቅጠሎች በተሠራ ጎጆ ነው። እናቲቱ እየላሰቻቸውና ዓይነምድራቸውን እየበላች፣ ከግልገሎቿ ጋር ብዙ ቀናት ትቆያለች። ከቦታ ቦታ ስታዘዋውራቸው የጀርባቸውን ቆዳ ነክሳ አንጠልጥላ ነው። የግልገሎቹ ፀጉር ግራጫና ምልክቶቹ የማይለይ ነው። ዓይንና ጆሯቸው የሚከፈተው ወደ አሥረኛው ቀን ገደማ ነው። ከወተት ሌላ መመገብ የሚጀምሩት ከስድስት ሳምንቶች በኋላ የመንጋጋ ጥርሳቸው ሲወጣ ነው። አዳኝነቱን የሚማሩት ቀስ በቀስና ደረጃ በደረጃ ነው። ለማደን ጥረት የሚያደርጉት አሥራ-አንድ ሳምንት ገደማ ከሞላቸው በኋላ ነው። አደን ማደን ከጀመሩ በኋላ በእዥ ምልክት ማድረግም ይጀምራሉ።

ሸለምጥማጦች ሲጣሉ፣ ንክሻቸው የሚያነጣጥረው ራስ፣ አንገትና ደረት ላይ ነው። ባይቋሰሉም ፀጉር ይነጫጫሉ። ከዚያም ተሸናፊው ይጮሃል፣ ይሸናል፣ ቂጡ ጋ ካለው ከረጢት ውስጥ ያለውን ግም ፈሳሽ ይለቃል።

በብዛት የሚገኝበት መልክዓ ምድር እና ብዛቱ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የተለያዩ ብቸኛ ዝርያዎች፣ የተለያዩ ሥነ ምህዳራዊ ሁኔታዎች ስለሚፈቅዱ፣ ተለያይተው ይኖራሉ። በደን ውስጥ የሚገኙ የሸለምጥማጥ ብቸኛ ዝርያዎች ቢኖሩም፣ ‹‹G. tigrina, G. abyssinica, G. feline,›› የተባሉት የሚገኙት ዛፍ በሌለባቸው ገላጣ ሥፍራዎች ነው። ‹‹G. tigrina›› ሰው በሚኖርባቸው አካባቢዎች ይኖራል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ የሸለምጥማጥ ብቸኛ ዝርያዎች ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ሽለምጥማጦች፣ በዝርዝር የተጠኑት ሁለቱ ብቻ ናቸው። ጀኒታ ቲግሪና (Genetta tigrina) እና ጀኒታ ጀኒታ (Genetta genetta)። የሸለምጥማጦች ምንጭ የኮንጎ የዝናብ ደን ነው ቢባልም፣ ከሰሃራ በረሃ በስተቀር በአፍሪካ የሌሉበት ሥፍራ የለም። ከዚህም አልፈው በደቡባዊ ምዕራብ አውሮፓና በዐረብ ባሕር ሰርጥም ይገኛሉ። መደበቂያና ምግብ በሚያገኙባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ይገኛሉ። ገና በቂ ጥናት የተደረገባቸው ባይሆኑም፣ የተለያዩት ብቸኛ ዝርያዎች በመልክና በምግባር የተመሳሰሉ መሆናቸው ግልጽ ነው። ‹‹G.felina›› እና ‹‹G.tigrina›› ከሌሎቹ ሁሉ ሰፊ ስርጭት ያላቸው ከመሆናቸው በላይ ያሉበት ቦታ ተደራራቢ ነው። በአንድ ሥፍራ እየኖሩም ግን አንዱ ዓይነት ከሌላው የማይዋለዱ ናቸውና የተለያዩ ብቸኛ ዝርያዎች ለመሆናቸው የሚያጠራጥር ነገር የለም።

ዋቢ ምንጭ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • ሪፖርተር (የካቲት ፫ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም)፤ “ሸለምጥማጥ ‹‹Genet›› (Genetta feline, G.tigrina, G.abyssinica)”፤ በሰሎሞን ይርጋ (ዶር.) ‹‹አጥቢዎች›› (2000)