Jump to content

ሱሳ

ከውክፔዲያ
(ከሹሻን የተዛወረ)
ባለ-ክንፍ እስፊንክስ - ከታላቁ ዳርዮስ ቤተ መንግሥት በሱሳ።

ሱሳ (ፋርስኛشوش /ሹሽ/፤ ዕብራይስጥשושן /ሹሻን/፤ ጥንታዊ ግሪክΣέλεύχεια /ሰለውከያ/፤ ሮማይስጥSeleucia ad Eulaeum /ሰለውኪያ አድ ኤውላዩም/) በኢራን32°18922′ ሰሜን ኬክሮስ እና 48°25778′ ምሥራቅ ኬንትሮስ የሚገኝ እጅግ ጥንታዊ ከተማ ነው። በ1997 ዓ.ም. 64,960 ገደማ ሰዎች ይኖሩበት ነበር[1]

ሱሳ በድሮ ጊዜ የኤላም መንግሥት ዋና ከተማ ነበረ። በዓለሙ ከሁሉ ጥንታዊ ከተሞች አንድ ነው። በኤላምኛ ከተማው ሹሻን ተባለ። በሱመርኛ መዝገቦች ይታወቃል። ለምሳሌ ኤንመርካርና የአራታ ንጉስ በተባለው ትውፊት ለኡሩክ አምላክ ለኢናና እጅ የሰጠ ቦታ ይባላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ሱሳ (ወይም 'ሱሳ ግንብ') በተለይ በመጽሐፈ አስቴር ሲጠቀስ ደግሞ አንዴ በመጽሐፈ ነህምያ አንዴም በመጽሐፈ ዳንኤል ስሙ ይገኛል። ዳንኤልነህምያ ሁለቱ በ6ኛ ክፍለ ዘመን ዓክልበ.ባቢሎን ምርኮ ጊዜ በሱሳ ይኖሩ ነበር። አስቴርም እዚያ ንግሥት ሆና አይሁዶች ከእልቂጥ እንዲያመልጡ ቻለች። ከዚህ በላይ የነቢዩ ዳንኤል መቃብር በከተማው አካባቢ እንዳለ ይታመናል።

ሱሳ እንደገና በመጽሐፈ ኩፋሌ ይጠቀሳል። በቁ. 9፡10 እና 9፡16 መሠረት በሴምና በበኩሩ በኤላም ርስት ውስጥ ካሉት ቦታዎች አንድ ነው ይላል። በተጨማሪም በምዕ. 8፡34 'ሱስን' የኤላም ልጅ ይባላል።

ሱሳ በአዋን ሥርወ መንግሥት ሥር እንደ ተመሠረተ ይመስላል። በ2075 ዓክልበ. ገደማ ሱሳ በታላቁ ሳርጎን ወደ አካድ መንግሥት ተጨመረ። በአካድ ውስጥ የክፍላገሩ ዋና ከተማ ሆኖ ቀረ። በ2013 ገደማ ግን ኤላማዊው አገረ ገዡ ኩቲክ-ኢንሹሺናክ በአመጽ ተነሥቶ ነጻ አወጣው። በ1888 ዓክልበ. የኡር ንጉሥ ኢቢ-ሲን ሱሳን አሸነፈው። እንዲህ የኡር መንግስት በኤላማውያን እጅ እስከ ወደቀ ድረስ እስከ 1879 ቆየ። ያንጊዜ ሱሳ ዳግመኛ የኤላም ዋና ከተማ ሆነ።

በ1640 ዓክልበ. የባቢሎን ንጉሥ ሳምሱ-ኢሉና ሱሳን አጠፋው። በ1184 ዓክልበ. በንጉሳቸው ሹትሩክ-ናሑንተ መሪነት ኤላማውያን የባቢሎን ንጉስ የሐሙራቢ ሕገጋት የተቀረጹበት ጽላት በዝብዘው ወደ ሱሳ በምርኮ ወሰዱት። እዚያም በ1894 ዓ.ም. በሥነ-ቅርስ ይገኝ ነበር። ይሁንና የባቢሎን ንጉስ 1 ናቦከደነጾር ከአምሳ አመት ያሕል በኋላ ሱሳን በሱ ተራ ለመበዝበዝ በቃ።

በዚህ ቅርጽ የአስናፈር ግፈኛ ዘመቻ በ655 ክ.በ. ይታያል። ነበልባል ከከተማው እየተነሣ የአሦር ሠራዊት ሲያጠፉና ምርኮውን ሲበዘብዙ ነው።

በ655 አመት ከክርስቶስ በፊት የአሦር ንጉስ አስናፈር በጦርነት ከተማውን ፈጽሞ አጠፋ። በኋላ በ545 ክ.በ. የፋርስ ንጉሥ ታላቁ ቂሮስ ከተማውን ማረከ። በቂሮስም ልጅ በካምቡሴስ ዘመን ዋና ከተማው ከፓሳርጋዳስ እስከ ሱሳ ተዛወረ።

በ339 ክ.በ. የመቄዶን ንጉሥ ታላቁ እስክንድር ከፋርስ መንግሥት ጋር ሱሳን አሸነፈው። ከሱ በኋላ ሱሳ ለሴሌውቅያ መንግሥት ስለ ታደለ ስሙ ሰለውከያ ሆነ። ከመቶ አመት በኋላ የጳርቴ መንግሥት ነጻነቱን ከሴሌውቅያ አገኝቶ ሱሳና ካሲፍያ ሁለቱ ዋና ከተሞቹ ሆኑ። የሮማ ንጉስ ትራያን108 ዓ.ም. ሱሳን ይዞ በአመጽ ምክንያት ቶሎ መመለስ ነበረበት። ይህም ሮማውያን ከሁሉ ወደ ምሥራቅ የደረሱበት ወቅት ነበረ።

እስላም ሰራዊቶች በ630 ዓ.ም. ፋርስን በወረሩበት ጊዜ ሱሳ እንደገና በጥፋት ላይ ተጣለ። በሌላ ዘመን በ1210 ዓ.ም. በወራሪ ሞንጎሎች እጅ በፍጹም ጠፋች።

የዛሬው ከተማ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሱሳ ወይም ሹሽ ዛሬ በፋርስ ውስጥ በሑዚስታን ክፍላገር ይገኛል።

ሥፍራው በሥነ ቅርስ ረገድ አይነተኛ ቢሆንም በቅርቡ የሕገ ወጥ ቆፈራ ትልቅ ችግር ሆኖአል። [2]

ከቅርሶቹም በላይ ሱሳ ስለነቢዩም ዳንኤል ስመ ጥሩ ሆኖ የሺዓ እስላም ወገንም ሆነ የፋርስ አይሁዶች መቃብሩን በጣም ያከብሩታሉ።

ምንጮችና ነጥቦች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የውጭ መያያዣዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
በ"Wikimedia Commons"
(የጋራ ፎቶዎች ምንጭ)
ስለ Susa የሚገኛኙ
ተጨማሪ ፋይሎች አሉ።