Jump to content

ቀመር ዥብ

ከውክፔዲያ
?ቀመር ጅብ
ቀመር ዥብ
ቀመር ዥብ
ሳይንሳዊ ደረጃ መስጫ
ስፍን: ጉንደ እንስሳ (Animalia)
ክፍለስፍን: አምደስጌ (Chordata)
መደብ: አጥቢ (Mammalia)
ክፍለመደብ: ሥጋበል Carnivora
አስተኔ: ጅብ Hyaenidae
ወገን: ቀመር ጅብ Proteles
ዝርያ: ቀመር ጅብ P. cristata

ቀመር ጅብ (Proteles cristata) የጅብ ዝርያ ነው።

የእንስሳው ገጽታና ተፈጥሯዊ ጸባይ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ቀመር ጅብ፣ መልክና ቁመናው ሽልምልም ጅብን ይመስላል። በወንዱና በሴቷ መካከል የአካል መጠን ልዩነት የለም። በአማካይ ሁለቱም ጾታዎች ከ፰ እስከ ፲፪ ኪሎግራም ይመዝናሉ።

ቀመር ጅብ ቀጠን ብሎ ከትከሻው ከፍ ሲል ፣ ወደ ጀርባው እየወረደ ሄዶ ወደ ታፋው ዝቅ ያለ እንስሳ ነው። የፊት እግሮቹ አምስት አምስት ጣቶች አሏቸው። የኋላ እግሮቹ ደግሞ ባለአራት ጣት ናቸው። ረጅም ጋማና ጎፈሪያም ጅራት አለው። ከወደ ጀርባው ደረቅ-ሣር ከመሰለ ቡኒ-ቢጫማ ቀለም እስከ ዳማ ቀለም ሲኖረው፣ ከወደ ሆዱ ነጣ ይላል። ከጀርባው ወደ ሆዱ በኩል የሚዘልቁ ጥቋቁር መስመሮች አሉት። ጭኖቹ አካባቢ ደግሞ መስመሮቹ አግድም ይሄዳሉ።

ቡችሎቹ ጠቆር ከማለታቸው በስተቀር ትልልቆቹን ይመስላሉ። ሴቶቹ አራት ጡቶች አሏቸው። ቀመር ጅቦች በፀብ ጊዜ ሰውነታቸውን በመንፋት አካለ-መጠናቸውን በሰባ አራት በመቶ ማሳደግ ይችላሉ። እንዲህ ሲያደርጉ ግን ደካማ ጥርሶቻቸው እንዳይታዩባቸው ይመስል አፋቸውን አይከፍቱም።

በሰዐት ከሦስት እስከ አራት ‘ኪሎ ሜትር ድረስ ይጓዛሉ። ምናልባት ለአንድ ሰዓት ያህል ከተጓዙ በኋላ ሽንታቸውን ለመሽናት ይቆማሉ። የክልላቸውን ድንበር መከለላቸው ነው። አካሄዳቸው ወደ ንፋስ ሲሆን፣ አቅጣጫቸውን የሚቀይሩትም በድንገት ነው።

የቀመር ጅቦች ኩስ ብዛት አለው። አንዴ የሚጥሉት ኩስ የገዛ ክብደታቸውን ስምንት በመቶ ያህል ሲሆን ኩሳቸውን የሚጥሉት በተወሰነ የመጸዳጃ ሥፍራ ነው። በአንድ ክልል እስከ አስር የመጸዳጃ ሥፍራዎች ይገኛሉ። ኩሳቸውንም ቀብረው ይሄዳሉ።

የሚወልዱት በክረምት ሲሆን ከሦስት ወራት እርግዛት በኋላ ሁለት ወይም ሦስት ቡችላዎች ይወልዳሉ። ቡችሎቹ የሚወለዱት በአዋልዲጌሳ ጉድጓዶች ውስጥ ነው። ሲወለዱ ዓይናቸው ክፍት ከመሆኑ በስተቀር በግላቸው ምንም ማድረግ የሚችሉ አይደሉም። ከስድስት እስከ ስምንት ሳምንታት በጉድጓድ ውስጥ ከተቀመጡ በኋላ በአንደኛው ወላጅ ታጅበው ለምስጥ አደን ይወጣሉ። ጉድጓድ ውስጥ ሲኖሩ፣ አባቶቹ የሌሊቱን ስድስት ሰዐታት ያህል ይጠብቋቸዋል። በዚህ ጊዜ እናቶቹ ወጥተው ለምግብ ፍለጋ ይሠማራሉ። ቡችሎቹ በአራት ወራቸው ብቻቸውን ወጥተው ምስጥ ሊበሉ ይችላሉ። የሚተኙት ግን ከእናታቸው ጋር ነው። በዘጠኝ ወራቸው ለአካለ መጠን ይደርሳሉ። ዓመት ሲሞላቸው ደግሞ ከወላጆቻቸው አካባቢ ርቀው መሄድ ይጀምሩና እናታቸው ተተኪዎቹን ቡችሎች ወልዳ አዲሶቹ ቡችሎች ምስጥ መብላት ሲጀምሩ፣ ነባሮቹ ከአካባቢው ርቀው ይሄዳሉ።

ምግብ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ቀመር ጅብ ምግቡ ከሞላ ጎደል ምስጥ ብቻ ነው። የሚበላቸው ምስጦች ምግብ የማያከማቹትን ዓይነት ሲሆን፣ ሲመሽ የመሬት ውስጥ ጎጇቸው ሆነ ኩይሳቸውን ለቀው ለምግብ የሚሆናቸውን ሣር ለማምረት በብዙ ሺሕ ሆነው ሲወጡ ቀመር ጅብ ምግቡን የሚያገኘው። ከምስጥ በተጨማሪም ጉንዳን፣ የእሳት ራት፣ ጢንዚዛ፣ ወዘተ ይመገባል። እንዲሁም አንዳንዴ አይጦች፣ ጥንብ፣ እንቁላል፣ ወፎችና ትናንሽ ኤሊዎችን ይመገባል። አንዴ ምስጦቹን ካገኟቸው የሚያጣብቅ ምራቅ ባለው በሰፊው ምላሳቸው ላስ ላስ ያደርጓቸዋል። ሠራተኞቹ ምስጦች ቀመር ጅብ እንደመጣባቸው ሲያውቁ ወደ የጎሬአቸው ይመለሳሉ። በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ ምስጦች ከጎጇቸው ወጥተው፣ መርዛቸውን ይነሰንሳሉ። የወታደሮቹ ቁጥር ከሠራተኞቹ እኩል ሲሆን ቀመር ጅቦቹ መብላታቸውን አቋርጠው ይሄዳሉ።

ቀመር ጅቦች ምስጥ ሊበሉ ሲወጡ፣ በሣሩ ላይ ቀስ እና ለስለስ በሚል እርምጃ ነው። ሲራመዱ አንገታቸውን ከትከሻቸው በታች አድርገው (አቀርቅረው) ነው። ለምግብ የሚሆኗቸውንም ምስጦች የሚያገኟቸው በማዳመጥ ነው። ያሞጠሞጠው አፋቸው ሳይነቃነቅ፣ ትልልቅ ጆሮቻቸው ናቸው ወደፊትና ወደኋላ የሚንቀሳቀሱት። ዝናብ መዝነብ ሲጀምር ምስጥ አደናቸውን ያቆማሉ። ምናልባት የምስጦቹን ድምፅ መስማቱን ስለሚያውክባቸው ይሆናል።

በብዛት የሚገኝበት መልክዓ ምድር እና አኗኗር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ቀመር ጅብ ከኢትዮጵያ ምሥራቅና ሰሜን ምሥራቅ ቆላዎች አንስቶ፣ በሶማሊያ፣ በኬንያ እስከ መሐል ታንዛኒያ ይገኛል። በተጨማሪ ከአንጎላ አንስቶ በቦትስዋናናሚቢያደቡብ አፍሪካ ይኖራል፡፡

አደረጃጀቱ፣ ብቸኛ በምሽት የሚንቀሳቀስና ምናልባትም አንድ ወንድ ከአንድ ሴት ብቻ ሆነው የሚኖሩበት ዓይነት ሳይሆን አይቀርም። በአንድነት በአንድ ጉድጓድ በባልና ሚስትነት ባይኖሩም፣ ከ፩ እስከ ፪ ‘ካሬ ኪሎ ሜትር’ አካባቢ ይጋራሉ። ኑሯቸው ከመጨረሻ ቡችሎቻቸው ጋር ሲሆን፣ ወንዶቹ ቡችሎቻቸውን እንደሚጠብቁ ይታወቃል። የቀመር ጅቦችን የጉድኝት ጠባይ በዝርዝር ያልተጠና በመሆኑ ብዙም አልታወቀም።

ቀመር ጅቦች ጉድጓድ በመቆፈር ረገድ ደካማ ናቸው ተብለው ይመገታሉ። ሆኖም መሬቱ ለስላሳ ከሆነላቸው፣ የአዋልዲጌሳን፣ የቀበሮና የጥንቸል ጉድጓዶችን ካገኙ አስፍተው ይቆፍራሉ። ሥራው ያለቀለት የቀመር ጅብ ጉድጓድ ፪ ሜትር ከ፴ ሣንቲም ገደማ ጥልቀት ያለውና መጨረሻው እንደ ክፍል የሆነ ነው። አንድ የቀመር ጅብ የመኖሪያ አካባቢ እስከ አስር የተለያዩ ጉድጓዶች ይኖሩታል። ወደ ሌሎች ቦታዎች እስኪሄድ ድረስም ከነዚህ ውስጥ አንድ ወይም ሁለቱን በማዘውተር፣ ከአራት አስከ ስድስት ሳምንት ያህል ይኖርበታል። ሆኖም ለጊዜውም ሆነ ለድንገተኛ መደበቂያነት፣ ማንኛውንም ጉድጓድ ሊጠቀም ይችላል።

ዋቢ ምንጭ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

http://www.ethiopianreporter.com/index.php/other-sections/social-affairs/social/item/932-%E1%89%80%E1%88%98%E1%88%AD-%E1%8C%85%E1%89%A5-aardwolf-proteles-cristatus Archived ማርች 8, 2013 at the Wayback Machine