ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት
ቅዱስ እስጢፋኖስ | |
---|---|
ቀዳሚ ሰማዕት | |
የተወለደው | በ፩ኛው ክፍለ ዘመን |
የትውልድ ቦታ | ኢየሩሳሌም |
የእናት ስም | ማርያም |
የአባት ስም | ስምዖን |
የሚከበረው | በመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ሥንክሳር |
በዓለ ንግሥ |
ሲመቱ ጥቅምት ፲፭ ቀን ዕረፍቱ ጥር ፩ ቀን ፍልሰቱ መስከረም ፲፯ ቀን በግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ቶቢ ፩ ቀን በምዕራባውያን ዲሴምበር ፳፮ ቀን |
ያረፈበት ቀን | ጥር ፩ ቀን በመናፍቃን በድንጋይ ተወግሮ |
እስጢፋኖስ (በግሪክ: Στέφανος ሲነበብ ፡ Stéphanos ስቴፋኖስ ፤ በዕብራይስጥ ፡ הקדוש סטפנוס ፤ በእንግሊዘኛ ፡ Stephen ሲነበብ ፡ ስቴፈን) በሕገ ወንጌል (በክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው ።
ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እሥራኤላውያን አንዱ ነበር ። ይህም በወጣትነት ያለፈችው ሕይወቱ ስትሠራ የነበረው ታላቅ መንፈሳዊ ሥራ ይመሠክራል ።
የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ ። (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ) ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ት/ቤት ገባ ። የወቅቱ ታላቅ መምህር ገማልያል ይባል ነበር። ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፭፥፴፫ ላይ ተጠቅሷል ። በትውፊት ትምህርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን፣ ጳውሎስን ፣ ናትናኤልን፣ ኒቆዲሞስን...) አስተምሯል ። በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር ፤ በፍጻሜውም አምኗል ። ቅዱስ እስጢፋኖስም ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ ። ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር ።
በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ ። ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ። ለስድስት ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ ። ለስድስት ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በኋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ ። በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ መምህሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው ። "ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው ።" በሚል ላከው ። ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ እጅ ነስቶ ተማረ ። (ሉቃ. ፯፥፲፰) በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ ።
ጌታም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው ፤ አጋንንትም ተገዙለት ። (ሉቃ. ፲፥፲፯) ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ከዋለበት እየዋለ ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ ፤ ምሥጢር አስተረጐመ ። ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኳል ። በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን (ጵጵስናን) ተሹሟል ። በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት፣ ምሥጢርም የተገለጠለት የለም ። በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ ።
በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ሰባቱ ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር ። አልፎም የስድስቱ ዲያቆናት አለቃ እና የስምንት ሺው ማኅበር መሪ(አስተዳዳሪ) ሆኑዋል ። ስምንት ሺህ ሰውን ከአጋንንት መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አባቶቻችን መጠየቅ ነው ። አንድን ሰው ተቆጣጥሮ ለደኅንነት ማብቃት እንኳን እጅግ ፈተና ነው ። መጸሐፍ እንደሚል ግን መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ማኅደር እግዚአብሔር ነውና ለርሱ ተቻለው ። (ሐዋር፣ሥ፡፮ ቁ፡፭)
አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ሲባል እንደዘመኑ ይመስለን ይሆናል ። እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው ። ዲቁና ለእርሱ " በራት ላይ ዳርጎት" እንጂ እንዲሁ ድቁና አይደለም ።
ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ስምንት ሺውን ማኅበር እየመራ ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት "እጠፋ እጠፋ" አለች ። በዚህ ጊዜ "ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው " ብለው አይሁድ በማመናቸው አልቀረም ገደሉት ። እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው ። በመጨረሻውም ስለ እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት ። ደቀ መዝሙርቱም ታላቅ ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት ።
ቅዱስ እስጢፋኖስ ከአረፈ ከሦስት መቶ ዓመት በኋላ በኢየሩሳሌም የሚኖር አንድ ደግ ሰው ነበረ ስሙም ሉኪያኖስ ይባላል ። በተደጋጋሚ በራዕዪ ቅዱሱ እየተገለጠለት "ሥጋዬን አውጣ" ይለው ነበርና ሒዶ ለጳጳሱ ነገረው ። ጳጳሱም ደስ ብሎት ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ወደ አፀደ ገማልያል ማለት ወደ መምህሩ ሄደ ። ቦታውንም በቆፈሩ ጊዜ ታላቅ መነዋወጥ ሆነ ። መላዕክት ሲያጥኑም በጎ መዓዛ ሸተተ ። ዝማሬ መላዕክትም ተሰማ ። ሕዝቡና ጳጳሱም በቅዱስ እስጢፋኖስ ፊት ሰግደው በታላቅ ዝማሬና በሐሴት ዐፅሙን ከዚያ አውጥተው በጽርሐ ጽዮን (በተቀደሰችው ቤት) አኖሩት ። እለ እስክንድሮስ የተባለ ደግ ሰውም ቤተክርስቲያን አነጸለት ወደዚያ አገቡት ።
ከአምስት ዓመታት በኋላም እስክንድሮስ ሲያርፍ በሳጥን አድርገው በቅዱሱ ጎን አኖሩት ። የእስክንድሮስ ባለቤት ግን ወደ ሀገሩዋ ቁስጥንጥኒያ ስትመለስ የባሏ ሥጋ መስሉዋት የእስጢፋኖስን ቅዱስ ሥጋ በመርከብ ጭና ወሰደችው ። መንገድላይም ከሳጥኑ ውስጥ ዝማሬ ሰምታ ብታየው ያመጣችው የቅዱሱን ሥጋ ነው ። እጅግም ደስ አላት አምላክ ለዚህ አድሉዋታልና ። እርሷም ወስዳ ለታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጥንጢኖስ አስረከበችው ። በከተማው ታላቅ ሐሴት ተደረገ ። ሥጋውን ሊያኖሩት በበቅሎ ጭነው ሲወስዱትም በቅሎዋ በሰው ልሳን ተናግራ ማረፊያውን አሳወቀች ። በዚያም ላይ ትልቅ ቤተክርስቲያን ታንጾለታል ።[1]
ቅዱስ እስጢፋኖስ
- ሲመቱ ጥቅምት ፲፯ ቀን
- ዕረፍቱ ጥር ፩ ቀን
- ፍልሰቱ መስከረም ፲፭ ቀን ነው ።
- ^ ከስንክሳር የተገኘ መረጃ