Jump to content

ቆፋሪዎቹ

ከውክፔዲያ
አንድ ገጽ ከቆፋሪዎቹ ጽሑፍ

ቆፋሪዎቹ (እንግሊዝኛDiggers /ዲገርዝ/) ከ1641 እስከ 1643 ዓ.ም. ድረስ በእንግሊዝ አገር የቆየ ኅብረተሠባዊ እንቅስቃሴ ነበረ። በ1641 በኦሊቨር ክሮምዌል ዘመን የመሠረተው ሳባኪው ጄራርድ ዊንስታንሊ ሲሆን ደንበኛ ስማቸው «ዕውነተኛ አስተካካዮቹ» (/ትሩ ሌቨለርዝ/) ይባል ነበር። ሆኖም ከድርጊቶቻቸው የተነሣ «ቆፋሪዎቹ» ተብለው ይታወቁ ጀመር።

«ዕውነተኛ አስተካካዮቹ» የሚለው ስያሜያቸው የመጣ ከሐዋርያት ሥራ 4፡32 ቃል[1] መሠረት የምጣኔ ሀብታቸው እኩልነት እምነት ስለ ነበራቸው። ቆፋሪዎቹ ርስትን በ«ማስተካከል» የቆየውን ኅብረተሠብ ለማሻሻል ሞከሩ። ዋና ሃሳባቸው በትንንሽ እርሻ ሰፈሮች ላይ በግብርና ሁላቸው እኩል ሆነው ለመኖር ነበር። በዚሁ ዘመን ከተነሡት ከእንግሊዝ ቤተክርስቲያን ተቃራኒ እንቅስቃሴዎች አንዱ ናቸው።

1641 ዓ.ም. በእንግሊዝ አገር ኅብረተሠባዊ ሁከቶች የበዙበት አመት ነበር። የፓርላማ ወገን በጦር ሜዳ ላይ በሰፊው ድል አድርገው ቢሆንም የተሸነፈው ንጉሥ 1ኛ ቻርልስ ገና ስምምነት አልፈቀድም ነበር። በመጨረሻ ፓርላማና ሠራዊቱ እንደ አታላይ ይሙት በቃ ፈረዱበት።

የንጉሥ ጉባኤ በአዲስ መንግሥት ጉባኤ ወዲያው ተተካ። የፓርላማም ሥልጣን በጠብ ብዛት ስለ ተደከመ ይህ አዲስ ጉባኤ በሠራዊቱ ተገዛ። ብዙ ሰዎች በፖለቲካ ውስጥ ገብተው የአዲስ መንግሥት ለውጥ እንዴት እንደሚሻሻል ያላቸውን ልዩ ልዩ ሃሣቦቻቸውን እያቀረቡ ነበር። የቀደመውን ንጉሥ ልጅ 2ኛ ቻርልስ በዙፋን ላይ ማስቀመጥ የፈለጉ ወገን ሲኖር እንደ ክሮምዌል የነበሩት መሪዎች ደግሞ ባለ ሃብታሞች ብቻ የሚውከሉበት ፓርላማ ፈለጉ። በጆን ሊልቡርን መጻሕፍት ተጽእኖ የወጣ ተቃራኒ ወገን ደግሞ እያንዳንዱ አዋቂ ወንድ ባላቤት እንዲወከል እንጂ በሀብት መሠረት እንዳይሆን ጣሩ። እነኚህ «አስታካካዮቹ» (/ሌቨለርዝ/) ተባሉ። ከዚህ በላይ «አምስተኛው ንጉዛት ሰዎች» የሚባለው ወገን ሃይምኖታዊ መንግሥት (theocracy) ፈለጉ። ከነዚህ ወገኖች መካከል የዊንስታንሊ ቆፋሪዎች ሥርነቀል መፍትሔ አራመዱ።

ጄራርድ ዊንስታንሊና 14 ሌሎች እራሳቸውን ከአስተካካዮቹ ለመለየት ስማቸውን «ዕውነተኛ አስተካካዮቹ» ብለው አንድ ጽሑፍ አሳተሙ። ሃሳባቸውን ተግባራዊ አድርገው የጋራ መሬት ለማረስ ከጀመሩ በኋላ ሰዎች «ቆፋሪዎች» ይሉዋቸው ነበር። በቆፋሪዎቹ እምነት ተፈጥሮአዊ አኗርኗር አይነተኛ ነበረ። ዊንስታንሊ እንዳለው «ዕውነተኛ ነጻነት ሰው ምግቡንና ደህንነቱን ባገኘበት ይተኛል፣ ያውም በምድሪቱ ጥቅም ነው።»

በቆፋሪዎች አስተሳሰብ፣ ከኖርማኖች ወረራ (1058 ዓ.ም.) አስቀድሞ እንግሊዞች ቀና፣ ጻድቅ፣ እና በእኩልነት የኖረ ነገድ ሆነው ነበር። ኖርማኖች ከወረሩ በኋላ ግን መንግሥቱን በመያዛቸው መኳንንት ሆኑ፣ ኗሪ እንግሊዞች ግን ተራ ሕዝቦች ሆነው በኖርማኖች ሥር («የኖርማኖች ቀንበር») ተጨቆኑ። ዊንስታንሊ እንደ መሰለው የእንግሊዝ ንጉሥና የእንግሊዝ መንግሥት የኖርማኖች ተከታዮች ስለ ሆኑ መጣል ነበረባቸው።

ተግባር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ቅዱስ ጊዮርጊስ ኮረብታ፣ ወይብሪጅ፣ ሳሪ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በሚያዝያ 1641 ዓ.ም. ለመንግሥት ጉባኤ በቀረበው ደብዳቤ መሠረት፣ ብዙ ግለሠቦች በቅዱስ ጊዮርጊስ ኮረብታወይብሪጅ ላይ፣ በኮብሃም፣ ሳሪ ዙሪያ በጋራ መሬት ላይ አትክልትን ይተክሉ ጀመር፣ ይህም የምግብ ዋጋ ካለፈው ጊዜ ይልቅ ከሁሉ ከፍ ባለ ደረጃ ሲደርስ ነበር። የአቶ ሳንደርዝ ደብዳቤ እንዳወራው፣ «ሰው ሁሉ መጥቶ እንዲረዳቸው ሲለምኑ ምግብን፣ መጠትንና ልብስን በምላሽ እንዲያገኙ ቃላቸውን ሰጥተው ነበር።» አጥሮቹን ሁሉ በመፍረስ የዙሪያው ሕዝብ አንድ ላይ እንዲሠሩ ለማድረግ አሰቡ። በ10 ቀን ውስጥ ቁጥራቸው ብዙ ሺህ እንዲሆን አሳመኑ። «ዕቅድ በእጅ እንደ ያዙ የሚል ፍርሃት አለ።» በዚሁም ወር፣ ቆፋሪዎቹ «የእውነተኛ አስተካካዮቹ መርኅ ተራመደ» የሚባል ጽሑፍና አቤቱታ አሳተሙ።

በዙሪያው ባለርስቶች ጥያቄ፣ የአዲስ አራያ ሠራዊት አለቃ ሰር ቶማስ ፌይርፋክስ ከወታደሮች ጋር ደረሰና ዊንስታንሊንና ሌላ ቆፋሪ ዊልያም ኤቨራርድን በጥያቄ መረመራቸው። ኤቨራርድ ብርቱ ችግር እንደ ፈላ ስለ መሰለው ከእንቅስቃሰው ቶሎ ወጣ። ዳሩ ግን በፌይርፋክስ አስተያየት ቆፋሪዎች ጉዳት የሚያምጡ ስላልነበሩ፣ ባለርስቶቹ ጉዳዩን በችሎት እንዲቀጥሉት መከረ።

ዊንስታንሊ በሰፈሩ ላይ ቆየና ቆፋሪዎቹ ስላገኙት እንቅብቃቤ ለመጻፍ ቀጠለ። የርስቱ ጌታ ፍራንሲስ ድረይክ (ይህ የስመ ጥሩ ተጓዥ ፍራንሲስ ድረይክ አልነበረም) ሆን ብሎ በቅጥ ሊያሳድዳቸው ሞከረ። ወንበዶችን በቡድን አሰብስቦ ብዙ ጊዜ ከመደበደባቸው በላይ አንዴ የጋራ ቤታቸውንም አቃጠሉ። በችሎቱ ጉዳይ ቆፋሪዎች ለራሳቸው እንዳይመሰክሩ ተከለከለ። መረኑ የ«ዘላባጆቹ» (/ራንተርዝ/) ወገን አባላት ተብለው ተፈረደባቸው። (እንዲያውም ግን ዊንስታንሊ የዘላባጆች መሪ ላውረንስ ክላርክሶንን መረንንነትን ስለማስተማሩ ወቀሰው) በችሎቱ ጉዳይ ስለ ተሸነፉ፣ መሬቱን ለመልቀቅ እምቢ ካሉ ሠራዊት በእርግጥ ያስወጣቸው ነበር፤ ስለዚህ ለባለርስቶቹ ደስታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኮረብታን በነሐሴ 1641 ተዉ።

ሊተል ሂስ በኮብሃም፣ ሳሪ ዙሪያ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሳደዱት ቆፋሪዎች መካከል አንዳንድ በትንሽ ርቀት ወደ ሊተል ሂስ ፈለሱ። 4.5 ሄክታር የመሬት ስፋት ልክ ታረሰ፤ ስድስት ቤቶች ታሠሩ፣ የበጋ ሰብል ተመረተ፣ አንዳንድ ጽሑፍ ታተመ። መጀመርያ በርኅራኄ ያያቸው የኮብሃም ርስቱ ጌታ ካህን ጆን ፕላት በኋላ ዋና ጠላታቸው ሆነ። በሥልጣኑ አማካይነት የዙሪያው ሕዝብ እንዳይረዳቸው አሰናከለ፤ እንዲሁም ቆፋሪዎቹም ሆነ ንብረታቸው በግፍ እንዲበደሉ አደረገ። በሚያዝያ 1642 ዓ.ም. ፕላትና ሌሎች ባለርስቶች ከርስታቸው በፍጹም አባረሯቸው።

ዌሊንግቦሮ፣ ኖርሳምቶንሺር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሌላ የቆፋሪዎች ሰፈር ደግሞ በዌሊንግቦሮኖርሳምቶንሺር አካባቢ ቆመ። ይህ ማህበር በ1642 ዓ.ም. ያሳተመው አዋጅ እንዲህ ተባለ፦

«እኛ የዌሊንግቦሮ መንደር በኖርሳምቶን ድኃ ኗሪዎች በይርሻንክ በተባለው በዌሊንግቦሮ ኗሪዎች ጋራ ወና ምድር ላይ ለመቆፈር፣ ለማዳበርና እህልን ለመዝራት ፈቅደን የጀመርንበት መሠረቶችና ምክንያቶች አዋጅ...»

ይህ ሠፈር የተጀመረው ከሳሪ ቆፋሪዎች ግንኙነት የተነሣ ይመስላል። በመጋቢት 1642 ከሳሪው ሰፈር የደረሱ 4 ተልእኮዎች በባኪንግሃምሸር ታሠሩ፤ የያዙትም ደብዳቤ በጄራርድ ዊንስታንሊና በሌሎች ቆፋሪዎች ተፈርሞ ሰዎች በየቦታው ለራሳቸው የቆፋሪ ሠፈር ለማቆምና የሳሪን ሰፈር በስንቅ ለመርዳት የሚል ልማኔ ነበር። «ፍጹም በየዕለቱ» የሚባለው ጋዜጣ እንደሚናግረው፣ እነኚህ ተልእኮዎች ከሳሪ ወደ ሚድልሴክስህርትፎርድሺርቤድፎርድሸር፣ ባኪንግሃምሸር፣ ባርክሸርሃንቲንግደንሸር እና ኖርሳምቶንሸር አውራጃዎች ከተጓዙ በኋላ ታሠሩ።

በሚያዝያ 10 ቀን 1642 ዓ.ም. የመንግሥት ጉባኤ የኖርሳምቶንሸር ዳኛ አቶ ፔንትሎው በሚከተለው ችሎት «በአቅራቢያው ባሉት አስተካካዮች ላይ» ክስ እንዲያካሄድባቸው ታዘዘ። የአይቫ ቆፋሪዎች እንደ መዘገቡት፣ ከዌሊንግቦሮ ቆፋሪዎች 9 በወህኒ ታስረው ምንም ወንጀል በነርሱ ማረጋገጥ ባይቻልም ኖሮ ዳኛው ነጻ እንዳያስወጣቸው እምቢ ብለው ነበር።

አይቫ፣ ባኪንግሃምሸር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከሳሪና ከኖርሳምቶንሸር ሠፈሮች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሌላ ቆፋሪዎች ሰፈር በአይቫ፣ ባኪንግሃምሸር ተገኘ። ይህም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ኮረብታ በ14 ኪ.ሜ ይርቃል። የአይቫ ቆፋሪዎች አዋጅ እንዳለው፣ ሌሎችም ሠፈሮች ደግሞ በባርኔት፣ ህርትፎርድሸር፣ በኤንፊልድ፣ ሚድልሴክስ፣ በዳንስተብል፣ ቤድፎርድሸር፣ በቦስዎርስግሎስተርሸር እና እንዲሁም በኖቲንግሃምሸር ኖሩ። በተጨማሪ የሳሪ ሰፈር ከተሳደደ በኋላ፣ ቆፋሪዎቹ ልጆቻቸውን በአሳዳጊነት መተው እንደ ተገደዱ ይገልጻል።

የእንቅስቃሴው መጨረሻ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በመላ እንግሊዝ አገር የቆፋሪ ሰፈሮች በጠቅላላ ከጥቂት መቶ ሰዎች በላይ አልነበሯቸውም። በባለርስቶችና በመንግሥት ጉባኤ ማሳደድ ምክንያት እንቅስቃሴው በ1643 ዓ.ም. ጨረሰ።

ተጽእኖ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ጽሑፎች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ «ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም።» --ግብረ ሐዋርያት 4፡32
  2. ^ Loewenstein, David (2001). Representing revolution in Milton and his contemporaries: religion, politics, and polemics in radical Puritanism (illustrated ed.). Cambridge University Press. p. 315. ISBN 0521770327. 
  3. ^ Winstanley, Gerrard (2009). The complete works of Gerrard Winstanley. 2. Oxford University Press. p. 430. ISBN 0199576068.