ባቢሌ የዝሆን መጠለያ

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

ባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ (elephant sanctuary) ከአዲስ አበባ ወደ ጅጅጋ መስመር፣ ፭መቶ ፶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ይህ መጠለያ በቆዳ ስፋት ፮ሺ ፱መቶ ፹፪ ካሬ-ሜትር የሚመዘን ሲሆን፣ ከጠቅላላ ስፋቱም ውስጥ ፸፯ ከመቶ ያህሉ በአሁኑ አጠራር ”በሶማሌያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት” ሥር ሲካለል፤ ቀሪው ፳፫ ከመቶ ያህሉ ደግሞ ”በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት” ሥር ይገኛል።[1]

የአካባቢው የኦሮሚያ ብሔር ተወላጆች ‹‹ወረ-ሃርባ›› (ባለዝሆኖቹ) በማለት የሚጠሩትና በፌዴራል የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ሥር የሚተዳደረው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ-መንግሥት፣ በ፲፱፻፷፪ ነው የተመሠረተው። የምሥረታውም ዋነኛ ዓላማ፥ በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ የሚገኙትን “ሎክሶዳንታ አፍሪካና ኦርሊያንሲ” የተባሉትን ንዑስ የዝሆን ዝርያ ለማልማትና ለመጠበቅ ሲሆን ባሁን ጊዜ መጠለያው በተጨማሪም ከ፴ በላይ ጡት አጥቢ የዱር እንስሳት፣ ከ፪መቶ ፶ በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች፣ ፫መቶ ያህል የዕፅዋት ዝርያዎች የሚገኙበት ነው። [2]

ከሌሎች አዕዋፍ እና የዱር አራዊት ዝርያዎች ደግሞ ከገጸ ምድር የመጥፋት አደጋ ላይ ያለው ”የሳልቫዶሪ ዘረ-በል” (Serinus xantholaema) ወፍ እና ባለጥቁር ጎፈር አንበሳ በዚህ መጠለያ ይገኛሉ።

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ከተመሠረተበት ዘመን ወዲህ ለመቋቋም ከተገደደባቸው ክስተቶች መካከል የኢትዮጵያና የሶማሊያን ጦርነት ያስከተለው ቀድሞ በዳካታና ፋፈም ሸለቆዎች የነበሩ ዝሆኖች ወደ ኤረር ሸለቆ የሸሹበት ሁኔታ ነበር።

ሌላው አደገኛ ክስተት ደግሞ በመጠለያው ውስጥ የሰው ሠፈራ የተከለከለ ቢሆንም ከቁጥጥር ያለመኖር ምክንያት ባለፉት ፵ ዓመታት ቀስ በቀስ በሰው-ሠራሽ ተፅዕኖ መጠለያው ከፍተኛ ግፊት ላይ ወድቋል። በተለይም ከ፲፱፻፺፮ ዓ/ም ወዲህ በመጠለያው ውስጥ እየጨመረ የመጣውን ‹‹ሕገ-ወጥ›› ሠፈራና ሰው-ሠራሽ ተፅዕኖዎች ለመግታት በቂ የጥበቃ ኃይል ባለመሰማራቱና የሠፈሩትንም በሕጋዊ መንገድ የማስለቀቅ የፖለቲካዊ ቆራጥነትም ሆነ ከሙስና የጸዳ አሠራርም ባለመኖሩ የዱር አራዊቱ ስደት እና ዕልቂት እየተባባሰ እንደሆነ የቅርብ ጊዜ ዘገባዎች ያመላክታሉ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ይሄንን አስጊ ሁኔታ በተመለከተ በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የባህል፣ቱሪዝምና የብዙሃን መገናኛ ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ አባላት በስፍራው ተገኝተው ባደርጉት ምርምር ላይ የሰጡትን ገለጻ በመጥቀስ፣ ሕገ-ወጥ ሰፈራ፣ የመጠለያ ድንበር የማከለሉ ሥራ አለመተግበር፤ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን በመጠለያው ማኖር ለመጠለያው አደጋ ላይ መውደቅ ተጠቃሽ ምክንያቶች መህናቸውን ዘግቧል።[3]

ከሁሉም በላይ ግን ከፍ ያለ ውዝግብ እና ዓለም-አቀፍ ተቃውሞ ያስከተለው በ፲፱፻፺፯/፲፱፻፺፰ «ፍሎራ ኢኮ ፓወር» (Flora EcoPower Holding AG) ለተባለ የንምሳ ኩባንያ ለናፍጣ-ነዳጅ ማምረቻ የሚሆን የጉሎ ተክል ልማት ተብሎ በተፈቀደለት፤ ወደ አሥራ-ሁለት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ያደረሰው የመጠለያውን ደን ምንጠራ ነው። ኩባንያው በፌዴራል መንግሥቱ ቡራኬ ከኦርሚያ ብሔራዊ መንግሥት የተረከበው ይህ ‘የልማት’ መሬት ፹፯ በመቶው በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ክልል ላይ ያረፈ መሆኑን በፌዴራሉ መንግሥት ምርመራ ተረጋግጦ ቢሆንም ምርመራው የተካሄደው ኩባንያው ደኑን ከመነጠረ በኋላ ስለነበር የዝሆኖቹን የሽግግር ወቅት ያዛባበት፣ ከዚህ ቀደም ወደማይንቀሳቀሱበትና ከመጠለያው ክልል ውጪ ወደሆኑ ቦታዎች እንዲገፉ ተፅዕኖ እንዳደረገ ይገመታል። «ፍሎራ ኢኮ ፓወር» የጀመረው የጉሎ ልማት ስኬታማ ሳይሆንና አገሪቱም ከታሰበው ነዳጅ አንዳችም ጠብታ ሳታይ ኩባንያው ዕዳውንም ሳይከፍል ከአገር እንደወጣ በሰፊው ተዘግቧል። [4]

ማጣቀሻዎች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ ‹‹ወረ - ሃርባ››፤ ቁም ነገር መጽሔት ቅፅ ፲፪ ቁጥር ፻፴፱ ጥቅምት ፳፻፭ ዓ/ም
  2. ^ ‹‹ወረ - ሃርባ››፤ አክርማ መጽሔት፣ ቁጥር ፳፬ ፳፻፪ ዓ/ም
  3. ^ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3884&K=) ፤ “የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ አደጋ ላይ ነው”፤ ታኅሣሥ ፩ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም]]
  4. ^ DESALEGN SISAY ; http://www.afrik-news.com/article17480.html  ; “Ethiopia: German biofuel company fails as employees abscond with assets; TUESDAY 27 APRIL 2010

ዋቢ ምንጮች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]