Jump to content

ቦዩስ

ከውክፔዲያ

ቦዩስ (በጀርመንኛ Baier ባየር) በጀርመን አፈ ታሪክ ዘንድ በጥንት የጀርመን ፲፪ኛው ንጉሥ ነበረ። ከአባቱ ሄርኩሌስ አለማኑስ ዘመን በኋላ ለ60 ዓመታት (ምናልባት 1759-1699 ዓክልበ. ግድም?) ነገሠ።

አቬንቲኑስ እንደ ጻፈው ንጉሥ ባየር (ቦዩስ) የባየርን ሰዎች አባት ነበር። አባቱ አለማኑስ (አልማን) ካረፈ በኋላ ከወንድሞቹ ኖሪኩስሁኑስሄልቬቲዩስ መካከል ለጊዜው ትግሎች ነበሩ። ያንጊዜ በሬምስሉክሳምቡርግ የነገሠው ዘመዳቸው ራሙስ ዐርቆ የአልማን ግዛት አከፋፈላቸው ይላል። ከነዚህ ታናሹ ልጅ ቦዩስ ባየርንንና የጀርመን ከፍተኛ ንጉሥነቱን ተቀበለ።

ዋና ከተማው «ባየርቢንግ» በኋላ «ማርቦዲንግ» አሁንም ፕራግ የሚባለው ነበር። ስሙን ለአገሩ ባየርን እንዲሁም ለቦሄሚያ (አሁን ቼክ ሪፐብሊክ) የሰጠው ይባላል። በተጨማሪ ከተሞች በባየርብሩን (በሙኒክ ዙሪያ) እና በቦየርስዱም (አሁን ፓሣው) ሠራ።

ከአልማን ዕረፍት (1791 ዓክልበ. ግ.) በኋላ ትልልቅ የአሕዛብ እንቅስቃሴዎች (ፍልሰቶች) ይከሠቱ ጀመር። ከነዚሁ መጀመርያው የቦዩስ ወንድሞች ጦይርና አቢዩስ ከዳኑብ ወንዝ ደቡብ ያለቸውን ኢሉዋሪያን ወርረው ሠፈሩባት፤ ከዚህ ወደ ምሥራቅ በጥቁር ባሕር ዳርቻ ያለውን አገር እስከ ክሪሜያ ልሳነ ምድር ድረስ ያዙ። እነዚህ ጦረኞች ኪምብሪ ወይም ኪሜራውያን ሲባሉ፣ ስማቸውን ለክሪሜያ ልሳነ ምድር እንደ ሰጡ ጻፈ። ሚስቶቻቸውም ሥራዊት ሁነው «ማዘኖች» (አማዞኖች) ተባሉ። አቢዩስ በዚህ አገር ላይ ቆይቶ ጦይር ግን ከሥራዊቶቹ ጋራ ወደ ትንሹ እስያ ገቡ፤ በደብረ ኢዳ (በትሮይ አካባቢ) ሠፈረ። በዚህ ረገድ «ጦይር» በግሪክ አፈ ታሪክ ጀግናውን ቴውከርን ይመስላል። በዚህ ወቅት የጦይርም ሚስት ሃክስና አለቆቿ ሄርስግላይድሄርሽላግ ከአማዞኖች ጋራ በአውሮፓም ሆነ በአናቶሊያ እስከ አርሜኒያ ድረስ ወረሩ፤ ከተማቸውንም በኤፌሶን መሠረቱ።

ሌላው ትልቅ እንቅስቃሴ (ፍልሰት) በጣልያን አገር በዚህ ዘመን ስለ ተከሠተው ብሔራዊ ጦርነት የተነሣ ነበረ። በ1758 ዓክልበ. ግድም ዳርዳኑስ ወንድሙን የጣልያን (እና የፈረንሳይ) ንጉሥ ያሲዩስ ያኒጌናን ገደለው፤ ከዚያ ግን የእስፓንያ ንጉሥ ሲከሌውስ ዳርዳኑስን ከጣልያን አባረረው፤ ወደ ሳሞትራቄ ሸሸ። በ1736 ዓክልበ. ግድም ዳርዳኑስ ከማዮንያ (ልድያ) ንጉሥ አቲስ ርስት ተቀበለ፤ በዚያ ስመ ጥሩ ከተማውን ትሮይን መሠረተ። (ይህም በቦዩስ ፴ኛው ዓመት እንደ ሆነ ይጽፋል።) በምላሽ ዳርዳኑስ የሱን ይግባኝ መብት በጣልያን ለአቲስ ልጅ ለቲሬኑስ ተወው። ቲሬኑስ ወደ ጣልያን ሄዶ አስተዋይና የተወደደ ንጉሥ ሆነ፤ በዚህም ወቅት ፲፪ ነገዶች ከጣልያን ወደ ልድያ ፈለሱ። ሌሎችም ከልድያ ወደ ጣልያን ፈለሱ።

ሦስተኛው ትልቅ እንቅስቃሴ ወይም ፍልሰት፣ በስዊድንጎጣውያን ዘንድ የነበሩት ሕዝቦች ከስካንዲናቪያ ሲፈነዱ በንጉሣቸውም ቤሪግ ሥር መሬትን በአሁኑ ፖላንድ ሲይዙ ነበር። ከዚያ ቀጥሎ ብዙ ምድር ከቫንዳሎችና ከሌሎች ጀርመናውያን፣ ደግሞ ከሳርማትያና ከእስኩቴስ ይይዙ ጀመር። የድሮ ታሪክ ጸሐፊዎች ከሰጡት መረጃ፣ በ1683 ዓክልበ. ግድም ባልቲክ ባሕርን ተሻግረው ወደ ፖላንድ ገቡ፣ በ1600 ዓክልበ አካባቢ እስከ ዳክያ (አሁን ሮማኒያ) ድረስ ደረሱ፤ ከኪሜራውያንም ጋራ ተባበሩ። እነዚህ ጎጣውያን ደግሞ ጌታያውያን ወይም ዳክያውያን ተባሉ።

በአቨንቲኑስ መጽሐፍ፣ የቦዩስ ተከታይ ልጁ ኢንግራም ይባላል። ነገር ግን በኢንግራም ዘመን የጎጣውያን ንጉሥ ታናውሲስ ሕዝቡን ወደ ክሪሜያ ወሰዳቸው ሲለን ይህ ታናውሲስ የገዛው ከጊዜ በኋላ በ1563 ዓክልበ. ግድም ይመስላል። ስለዚህ ከቦዩስ ዘመን በኋላ 1699-1563 ዓክልበ. በጎጣውያን፣ ኪሜራውያንና አማዞኖች ምክንያት መዝገቦች እንደ ጠፉ ይቻላል።

ቀዳሚው
ሄርኩሌስ አለማኑስ
አለማኒያ/ባየርን ንጉሥ
1759-1699 ዓክልበ. ግድም?
ተከታይ
ጎጣውያን? (ኢንግራም)