Jump to content

አምባሰል

ከውክፔዲያ
አምባሰል
ውጫሌ ተራራ
ከፍታ 3567 ሜትር (አምባሰል ተራራ)
የሕዝብ ብዛት
   • አጠቃላይ 121,899
አምባሰል is located in ኢትዮጵያ
{{{alt}}}
አምባሰል

11°45′ ሰሜን ኬክሮስ እና 39°15′ ምሥራቅ ኬንትሮስ

አምባሰልደቡብ ወሎ ዞን የሚገኝ ወረዳ ሲሆን፤ ስሙ በዚህ ወረዳ ውስጥ ከሚገኝ አምባ ስም ይመነጫል። አምባሰል ወረዳ፣ በደቡብ ምዕራብ የባሽሎ ወንዝ ከተንታ ወረዳ ሲለየው፣ በደቡብ የባሽሎ ገባሪ የሆነው ወላኖ ወንዝ ከኩታበር፣ እንዲሁ የ ሚሌ ወንዝ ደግሞ በስተ ደቡብ ምስራቅ ከተሁለደሬ ወረዳ ይለየዋል። 44% የሚሆነው የወረዳው ክፍል ተራራማ፣ 36% ወጣ ገባ፣ 12% ገደላማ ሲሆን 7.5% ብቻ ለጥ ያለ ሜዳ ነው። ስለሆነም በዚህ ወረዳ አራት አይነት የአየር ንብረቶች ይገኛሉ፦ ውርጭደጋወይና ደጋ እና ቆላ፣ እያንዳንዳቸው .47%፣ 29.53%፣ 49.64%፣ 20.36% ይይዛሉ። የዚህ ወረዳ ታላቁ ከተማ ውጫሌ ሲሆን በአካባቢው በሚገኝ የተፈጥሮ ከሰል ክምችት ይታወቃል። የኢጣሊያ ወራሪ ሃይል ይህን የከሰል ክምችት አገር እስከለቀቀበት ዘመን ድረስ ይጠቀም ነበር[1]

የአፄ ይኩኖ አምላክ እናት ከሰገረት እንደመጣች ሲነገር፣ አባቱ ደግሞ ከዚህ ቦታ እንደተገኘ ይጠቀሳል። በዚህ ምክንያት ይመስላል፣ የዚህ አምባ ባለስልጣኖች ጃንጥራር በሚል ልዩ ማዕረግ ከጥንት ጀምሮ እስከ ንጉሳዊው ስርዓት ፍጻሜ አካባቢውን ያስተዳድሩ ነበር ( ከቅርብ ምሳሌ እቴጌ መነንጃንጥራር አስፋው ልጅ ነበሩ)። የይኩኖ አምላክ የልጅ ልጅ የሆኑት አፄ ጅን አሰግድ ስልጣን ተገዳዳሪ የነገሥታት ወንድ ልጆችን በዚህ ወረዳ በሚገኘው አምባ ግሸን ላይ ማሳሰር እንደጀመሩ ታሪክ ጸሐፊው ዋሊስ ባጅ ይጠቅሳል። እኒህ የሚታሰሩት ሰዎች ቤተ እስራኤል ወይንም በቀላሉ እስራኤላውያን ይባሉ ነበር። ስለሆነም ከአምባ ግሸን አጠገብ የሚገኘው ተራራ አምባ እስራኤል ወይንም አምባ ሰል መባል ጀመረ[1]

በ1682 ዓ.ም. የታተመው የቪቼንዞ ኮሮኔሊ ካርታ አምባሰልን በአምሃራ ግዛት የሚገኝ ተራራ እና የንጉሳዊ ቤተሰቦች ማቆያ እንደሆነ ያሳያል[2]። ከጊዜ በኋላ፣ የጣሊያን ወራሪዎች ከመምጣታቸው በፊት አምባሰል ከተራራ ስምነት ባሻገር የአስተዳደር ክፍል ስም በመሆን ከዋና ከተማው ማርየ ስላሴ ይተዳደር ነበር። በጣሊያን ወረራ ጊዜ የአምባሰል ዋና ከተማ ጎልቦ ሆነ፣ ለዚህም ምክንያቱ ጎልቦ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ለሚወስደው አውራ ጎዳና ስለሚቀርብ ነበር። ጣሊያኖች ሲባረሩ ዋና ከተማው ውጫሌ ተብሎ በወረዳነቱ ጸና። ቀጥሎ የአውራጃ ስርዓት ሲተገበር፣ ተሁለደሬ እና ወረ ባቦ ወረዳዎች አንድ ላይ ሆነው የአምባሰል አውራጃን መሰረቱ። የአውራጃው ዋና ከተማ ሐይቅ ነበር። የደርግ ስርዓት በአውራጃነቱ ካስቀጠለው በኋላ የዞን ስርዓትን ሲተገብር አውራጃውን ወደ መሰረቱት ወረዳዎች በመክፍል አምባሰል በወረዳነቱ ጸና[3]። ወረዳው በአሁኑ ወቅት 23 ቀበሌዎችን አቅፎ ይገኛል። ይሄው ቀደም ባሉ ዘመናት ከነበረው 34 ጭቃዎች ዝቅ ያለ ነው።

የአምባሰል ሕዝብ ቁጥር [2][3]
ዓ.ም.** የሕዝብ ብዛት የተማሪዎች ብዛት
1986
111,172
1999
121,899


  1. ^ "Local History in Ethiopia" The Nordic Africa Institute website (accessed 15 February 2008)
  2. ^ Census 2007 Tables: Amhara Region, Tables 2.1, 2.4, 2.5, 3.1, 3.2 and 3.4.
  3. ^ 1994 Population and Housing Census of Ethiopia: Results for Amhara Region, Vol. 1, part 1, Tables 2.1, 2.7, 2.10, 2.13, 2.17, Annex II.2 (accessed 9 April 2009)


አምባሰል አቀማመጥ
ዳውንትና ደላንታ ጉባ ላፍቶ ሐብሩ
ዳውንትና ደላንታ
አምባሰል
አምባሰል
ወረባቦ
ጠንታ ኩታበር ተሁለደሬ