Jump to content

አሪያኒስም

ከውክፔዲያ

አሪያኒስም ወይም የአሪያን ቤተ ክርስቲያን በአንድ ክርስቲያን ቄስ አሪዩስ (250-328 ዓም) ትምህርቶች የተመሠረተ በሥላሴ የማያምን ሀረ ጤቃዊ የተባለ እምነትና እንቅስቃሴ ነበር።

አሪዩስ እንዳስተማረ ኢየሱስ ክርስቶስ ወይም ወልድ ከእግዚአብሔር አብ በታች የተለየና የተፈጠረ አምላክ እንደ ነበር አለ፣ እንጂ ሥላሴን አላስተማረም። እግዚአብሔር ከዓለም በፊት ኢየሱስን ቢፈጥርም፣ ኢየሱስ ግን ያልኖረበት ጊዜ ነበር፤ ከአብ በታች የተለየ ንዑስ አምላክ ነው ብሎ ያስተምር ነበር።

አሪዩስ ካረፈ በኋላ አሪያኒስም ለጊዜው በምሥራቁ የሮሜ መንግሥት እየተደገፈ እምነቱ ወደ አንዳንድ ጀርመናዊ ብሔር ተስፋፍቶ ነበር፤ ለጥቂት ዘመናት እስከ 663 ዓም ድረስ ቆየ። የ«አሪያኖች» ስም ከመሥራቹ አሪዩስ የተሰየመ ሲሆን፣ አሁን አንዳንድ ያልተማሩ ሰዎች «አርያኖች» ከሚለው ሕንዳዊ-ኢራናዊ ስያሜ ጋራ ተስተዋቸዋል፤ በውኑ ግን «አሪያኖች» ከ«አርያኖች» ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም።

ታሪክ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ራቬና ጣልያን ከ500-550 ዓም ግድም ከአሪያን ቤተክርስቲያን፤ ከዚህ ናሙና በቀር ብዙ ኪነታቸው አይተርፍም።
 • 250 ዓም - አሪዩስ በስሜን አፍሪካ ሊብያ ተወለደ።
 • 252 ዓም - የአንጾኪያ ጳጳስ የሆነው ጳውሎስ ዘሳሞሳታ ኢየሱስ እንደ ተራ ሰው ተወልዶ በኋላ በሕይወቱ ሳለ እንደ አምላክ ወይም መሢህ ተቀባ በማለት አስተማረ።
 • 260 ዓም - ጳውሎስ ስለዚያው ተቃራኒ ትምህርት በሲኖዶስ ተሻረ። አንድ ቄስ ሉቅያኖስ ዘአንጾኪያ ደግሞ በዚህ ምክንያት ተወገዘ።
 • 277 ዓም - ሉቅያኖስ ከቤተ ክርስቲያን ጋራ ተራርቆ እንዲመለስ ተፈቀደ። አሪዩስ በአንጾኪያ የዚሁ ሉቅያኖስ ተማሪ እንደ ሆነ ይታመናል።
 • 295 ዓም - የሮሜ ቄሣሮች ዲዮቅሌጥያንጋሌሪዩስ ክርስትናን እንደገና ከለከሉ፣ ክርስቲያኖች ተሰቃዩ።
 • 297 ዓም - አንድ የግብጽ ኤጲስ ቆጶስ ሜሌቲዩስ ዘሊኮፖሊስ ክርስትናን በስቅይ ምክንያት የካዱት ሰዎች ፪ኛ ወደ ምዕመናን እንዳይገቡ መከልከል ስለ ፈለገ፣ ለዚህ ከባድ አስተያየት እንደ ረባሽ ተሻረ። ቄሱ አሪዩስ ድግሞ በዚሁ ጉዳይ ተከተለው።
 • 303 ዓም - ቀሣሩ ጋሌሪዩስ ሊሞት ሲል ጸጽቶ ክርስትናን እንዲታገሥ ፈቀደ። አሪዩስ የሜሌቲዩስ ደጋፊ ስለ ነበር በእስክንድርያ ጳጳስ ጴጥሮስ ተወገዘ።
 • 305 ዓም - የጴጥሮስ ተከታይ አቡነ አኪላስ አሪዩስን ይቅር ብሎ እንደ ቄስ አስመለሰው። ቄሣሮቹ ቆስጠንጢኖስሊኪኒዩስ የሚላኖ ዓዋጅ አውጥተው ክርስትና እንዲታገሥ ንብረታቸውም እንዲመለስ አዘዙ። አኪላስ ከጥቂት በኋላ ዓርፎ አቡና አሌክሳንደር ተከተሉት።
 • 312 ዓም - አሪዩስ የአሪያኒስም ትምህርት በግልጽ አስተምሮ አቡና አሌክሳንደር የእስክንድርያ ሲኖዶስ ጠርቶ ሥላሴን ስለ መካዱ አሪዩስን ወገዘው።
 • 317 ዓም - የአሪያኒስም ክርክር ስላልጠፋ መላው ቤተ ክርስቲያን በንቅያ ጉባኤ ሥላሴን ደግፈው የንቅያ ጸሎተ ሃይማኖት አወጡ።
 • 328 ዓም - ቤተ ክርስቲያን አሪዩስን ይቅር ብሎ አሪዩስ ወደ ቁስጥንጥንያ ተጉዞ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሳይገባ በኩራቱ ሠልፍ አደረገ፤ በዚህም ሠልፍ ሆድ ዕቃው ዝም ብሎ ወድቆ ሞተ።
 • 329 ዓም - ቆስጠንጢኖስ ሊሞቱ ሲሉ ተጠመቁ፤ የተከታያቸው በምሥራቁ መንግሥት ቆስጠንቲዩስ ዝንባሌ ለአሪያኖች ወገን ነበር።
 • 343 ዓም - ቆስጠንትዩስ በመላው ሮሜ መንግሥት ቄሣር ሆኖ በምዕራብም አሪያኒስምን ይገፋ ጀመር።
 • 347 ዓም - ቆስጠንትዩስ በሮሜ ፓፓ ሊቤሪዩስ ፈንታ ለትንሽ ጊዜ የአሪያን ፓፓ ፪ ፌሊክስ አስገባ።
 • 349 ዓም - የሲርሚዩም ጉባኤ አርያኒስምን ደግፎ አብ ከወልድ በላይ ነው በማለት በየነ። ይህ የአሪያኒስም ጫፍ ነበረ።
 • 353 ዓም - የቆስጠንቲዩስ ተካታይ ዩሊያኖስ ከሓዲ የድሮ አረመኔነት ወዳጅ ሲሆን ክርስትናን ለመቃወም በወገኖቹ መካከል የነበረውን ክርክር አስነሳሳ።
 • 355 ዓም - ዩሊያኖስ በጦርነት አርፎ ክርስቲያን ወታደር ዮቪያኑስ ቄሣር ሆኑ።
 • 356 ዓም - ዮቪያኑስ አረመኔነትን ከልክለው ክርስትናን የመንግሥት ሃይማኖት አደረጉት። ከትንሽ በኋላ ዓረፉ። በምሥራቁ ተከታያቸው ቫሌንስ የአሪያኒስም ደጋፊ ነው። በምዕራቡ ወንድሙ ፩ ቫሌንቲኒያን የሥላሴ ደጋፊ ናቸው። ቫንዳሎች የተባለው ጀርመናዊ ጎሣ ደግሞ አረመኔነትን ትተው የአሪያኒስም ምዕመናን ሆኑ።
 • 368 ዓም - ጎታውያን እና ጌፒዶች የተባሉት ጀርመናውያን የአሪያኒስም ምዕመናን ሆኑ።
 • 370 ዓም - ቫሌንስ በጦርነት ዓርፎ ተከታዩ በምሥራቁ ፩ ተዎዶስዮስ የሥላሴ ደጋፊ ናቸው።
 • 372 ዓም - የተሰሎንቄ ዐዋጅ የሥላሴ እምነት ወይም ካቶሊክ-ኦርቶዶክስ-ሐዋርያዊ ቤተክርስቲያን በመላው ሮሜ መንግሥት ይፋዊ አደረገው።
 • 373 ዓም - ዮቁስጥንጥንያ ጉባኤ ጸሎተ ሃይማኖት አድሶ ትምህርተ ሥላሴን በይበልጥ ገለጸ።
 • 403 ዓም - ጀርመናዊው የቡርጎኝ መንግሥት የንቅያ ክርስትናን ተቀበለ።
 • 440 ዓም - ጀርመንዊ ስዌቢ ነገድ የንቅያ ክርስትናን ተቀበለ።
 • 442 ዓም - የቡርጎኝ መንግሥት የንቅያ ክርስትናን ትቶ ወደ አሪያኒስም ቀየረ።
 • 443 ዓም - የከልቄዶን ጉባኤ - የሮሜ ቤተክርስትያን ከሐዋርያዊ (ተዋሕዶ) ቤተክርስቲያን ተለያየ።
 • 458 ዓም - ስዌቢ የንቅያ ክርስትናን ትተው ወደ አሪያኒስም ቀየሩ።
 • 508 ዓም - የቡርጎኝ መንግሥት እንደገና ከአሪያኒስም ወደ ካቶሊክ-ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተመለሰ።
 • 526 ዓም - የአሪያን ቫንዳሎች መንግሥት ለቢዛንታይን መንግሥት ወደቀ።
 • 542 ዓም - ስዌቢ እንደገና ከአሪያኒስም ወደ ካቶሊክ-ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተመለሱ።
 • 545 ዓም - የአሪያን ኦስትሮጎታውያን (ምሥራቅ ጎታውያን) መንግሥት ለቢዛንታይን መንግሥት ወደቀ።
 • 559 ዓም - የአሪያን ጌፒዶች መንግሥት ለአቫሮች ወደቀ።
 • 560 ዓም - ከኦስትሮጎታውያንና ከጌፒዶች ቅሬታዎች ጋር ተባብረው ሎምባርዶች የተባሉት ጀርመናውያን ጎሣ የአሪያን ክርስትና ምዕመናን ሆኑ።
 • 581 ዓም - ቪዚጎቶች (ምዕራብ ጎታውያን) አሪያኒስም ትተው ካቶሊክ-ኦርቶዶክስ ሆኑ።
 • 595 ዓም - ሎምባርዶች አሪያኒስም ትተው ካቶሊክ-ኦርቶዶክስ ሆኑ።
 • 619 ዓም - ሎምባርዶች እንደገና ወደ አሪያኒስም ተመለሱ።
 • 645 ዓም - ሎምባርዶች ዳግመኛ አሪያኒስም ትተው ወደ ካቶሊክ-ኦርቶዶክስ ተመለሱ።
 • 653 ዓም - ሎምባርዶች ለ፫ኛው ጊዜ በአሪያን ነገሥታት ተገዙ።
 • 663 ዓም - የሎምባርዶች እንዲሁም የአውሮፓ መጨረሻ አሪያን ንጉሥ ጋሪባልድ አርፎ የአሪያኒስም እምነት ደግሞ ጠፋ።