አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጭ

ከውክፔዲያ
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጭ
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጭ እምዬ ማርያም ተገልጻላቸው

በደብራቸው
ሊቅና ጻድቅ ጊዮርጊስ ሰግላዊ
የተወለዱት በ፲፫፻፶፯ ዓ.ም.
የትውልድ ቦታ  ወሎ ክፍለ ሀገር በቦረና ወረዳ ሸግላ/ሰግላ
የአባት ስም ሕዝበ ጽዮን
የእናት ስም እምነ ጽዮን
ክብረ በዓል ወር በገባ በ፯ኛው ቀን
የሚከበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጭ ገዳም
ዓመታዊ ንግሥ ሐምሌ ፯
ያረፉበት ቀን ሐምሌ ፯ ቀን ፲፬፻፲፯ ዓ.ም.
ታዋቂ ሥራዎቻቸው የሚከተሉት ናቸው
  • ፩ኛ ኆኀተ ብርሃን
  • ፪ኛ መጽሐፈ አርጋኖን
  • ፫ኛ ውዳሴ መስቀል
  • ፬ኛ መጽሐፈ ብርሃን
  • ፭ኛ መጽሐፈ ሰዓታት ዘመዐልት ወሌሊት
  • ፮ኛ የቅዳሴ መጽሐፍ (ማዓዛ ቅዳሴ)
  • ፯ኛ ጸሎተ ፈትቶ
  • ፰ኛ ውዳሴ ሐዋርያትና የሐዋርያት ማኅሌት
  • ፱ኛ መልክዐ ቁርባንና የቁርባን ሥርዓት
  • ፲ኛ ፍካሬ ሃይማኖት
  • ፲፩ኛ መጸሐፈ ሚሥጢር(በጣም ውድ የሆነ መጸሐፍ ኦሪጂናሉ ጀርመን ሀገር የሚገኝ)


ኢትዮጵያዊው ሊቅና ጻድቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጭ የተወለዱት በ፲፫፻፶፯ ዓ.ም. ወሎ ክፍለ ሀገር በቦረና ወረዳ ሸግላ/ሰግላ በተሰኘች ቦታ ነው ። አባታቸው ሕዝበ ጽዮን ከተከበሩ መምህራን ወገን የሆኑ የቤተ መንግሥት ባለሟል ፤ መጽሐፍትን የሚያውቁ ጥበብ የተሞሉ ሲሆን የሰግላ አገረ ገዢም ነበሩ ። እናታቸው እምነጽዮንም ከወለቃ ሹማምንት ወገን የሆኑ ደግ ሰው ነበሩ ።

ሲጀመር እናታቸው ፈሪሃ እግዚአብሔርን እያስተማሩ በጥበብና በዕውቀት አሳደጓቸው ። አባ ጊዮርጊስ የተመረጠ የሆነ ሰማዕቱን ቅዱስ ጊዮርጊስ በመማፀን የተወለዱ ልጃቸው ስለሆኑ እንደሰማዕቱ የእውነት ምስክር እንዲሆኑላቸው በመመኘት ስማቸውን ጊዮርጊስ ብለው ጠርተዋቸዋል ። ከተወለዱበትም ሀገር በመነሳት ጊዮርጊስ ሰግላዊ ተብለው ሲጠሩ በጊዮርጊስ ዘጋስጭና በጊዮርጊስ ሰግላዊ መካከል ምንም ልዩነት የለም ።

ትምህርታቸው[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የአባ ጊዮርጊስ አባት ሕዝበ ጽዮን በቤተ መንግሥት በንጉሡ ስዕል ቤት ከሚያገለግሉት ካህናት ጋር ይሠሩ ስለነበር ልጃቸው በመልካም አስተዳደግና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በማስተማር በዕውቀት አሳድገዋቸዋል ። በድቁናም አሹመዋቸዋል ። ከዚያም በኋላ በንጉሥ ዳዊት ዘመን (፲፫፻፸፮ ፥ ፲፬፻፭) በደብረ ሐይቅ ባሕር ወደምትገኘው የቅዱስ እስጢፋኖስ አባ እየሱስ ሞዐ ገዳምና ታዋቂ ትምህርት ቤት ወስደው ከታላቁ ዓቃቤ ሰዓት አባ ሠረቀ ብርሃን ጉባዔ ተቀላቅለው እንዲማሩ አድርገዋል ። ይሁን እንጂ አባ ጊዮርጊስ በትምህርት ቤቱ የሚሰጡትን የቀለም ትምህርቶች ቶሎ ለማጥናት አልቻሉም ። ወደ ኋላ የመቅረታቸው ዋናው ምክኒያትም አባ ጊዮርጊስ ከመማሩ ይልቅ የማረካቸው በሥራ እየደከሙ የገዳሙን አባቶች መርዳትና የብትህውናው ሕይወት መሆኑ ነው ። ጉዋደኞቻቸው በትምህርት ሲቀድሙአቸው ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ ። በጾምና ጸሎትም ወደ እግዚአብሔር ጮሁ በፍፁም ልባቸውም አምነው ብርቱ ልመናን ከእመቤታችን ሥዕል ፊት ቁሞ በጠለቀ ተመስጦልቦና እንባን በማፍሰስ ወደ እግዚአብሔር " የአባቶቻችን አምላክ የምህረት ጌታ ሁሉን በቃልህ የፈጠርክ ሰውንም በረቂቅ ጥበብህ የፈጠርክ አቤቱ አንተ ከልዑል ጌትነትህ ጥበብን ስጠኝ በእውነትም አትናቀኝ እኔ ባሪያህ ነኝ የባሪያህም ልጅ ነኝና " በማለት ለመኑ ። ከዚህም በኋላ የዓለም ንግሥት የአምላክ እናት ተገለጸችላቸው ። በነሐሴ ፳፩ ቀንም ወደርሳቸው መጣች ፣ በዕውቀትና በትምህርት የሚተጉበትን ኃይል ሰጠቻቸው ። ከዚያም የዜማ የቅኔና የመጽሐፍትን ትርጉዋሜ ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀቁ ብዙ መጽሐፍትንም ደረሱ ።

አተዋጽዎቻቸው[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በዚህም በቀሰሙት ዕውቀታቸው በዜማ በኩል ቅዱስ ያሬድ ቀጥለው የሚጠሩ አባ ጊዮርጊስ ናቸው ። በቤተመቅደስም ዘማሪ ማኅሌታይ ተብለው ይጠራሉ ። በዚያም ዘመን ለነገሥት ፣ ለካህናት ፣ ለመኳንንት ፣ ለንቡራነእድ ፣ ለመሳፍንት ፣ ለሁሉም የቤተመንግሥት ሠራተኞች አስተማሪ ሆኑ ። በአንድ ወቅት ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ በርተሎሜዎስ “ሥላሴን አንድ ገጽ” ብለው ያምናሉ ተብለው በተከሰሱ ጊዜነገሩን እንዲያጣሩ ከተመረጡት ከቄስ ሐፄ ተከሥተ ብርሃንና ከሐይቁ መምህር ከዐቃቤ ሰዓት ዮሴፍ ጋር አብሮ ተልኮ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት አበውጳጳሱን ካነጋገሩ በኋላ ክሱ ውሸት መሆኑን በማረጋገጥ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የሚገልጠውን የጳጳሱን እምነት በጽሑፍ ይዘው መጡ፡፡ ሊቅነታቸውን የተረዱት ዓፄ ዳዊት አባ ጊዮርጊስን ወደ ቤተመንግሥታቸው በማስገባት የስምንቱም ልጆቻቸው መምህር አድርገዋቸው ነበር ። ከእነርሱም ውስጥ ቅዱስ የተባለው ንጉሥ ቴዎድሮስ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜ የነገሡት ንጉሥ እንድርያስዓፄ ይስሐቅንግሥት እሌኒ እና ዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ይገኙበታል።

ዐፄ ዳዊት በጋብቻ እንዲዛመዱዋቸው ጥረው ነበር ነገር ግን አባ ጊዮርጊስ ራሳቸውን የመንግሥተ ሰማያት ጃንደረባ ማድረግን ስለመረጡ በማስተማሩና በብሕትናው ጸንተው የአመክሮ ጊዜያቸውን ሲጨርሱ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ገብተው መንኩሰዋል ።

ተጋድሎዋቸው[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በዘመኑ ለተነሱ ለሁሉም የሃይማኖት ችግሮች አጥጋቢ መልስ በመስጠት የተዋህዶ ጠበቃ ፣ አይሁድን እና ሌሎች መናፍቃንን በጉባዔ ያሳፈሩት ሊቅ ክፉዎችና ምቀኞች በየጊዜው እየተነሱ መከራን ያደርሱባቸውና ይከሱዋቸው ነበር ።

በአንድ ወቅት በሸዋ ይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል ፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን ፣ በቅዱስ ሚካኤል ፣ በአባኖብና በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር ፡፡ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ አሁንም አሉ ፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላውያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር ፡፡ ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ ፡፡ “ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁእኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ” ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው ፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን ፣ ንቡራነእዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውንጥያቄ አቀረበ ፡ “እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ "አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?" ብሎ እንደጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ?” ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር ፡፡ ሊቃውንቱም “እንዲህያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ” ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡በአልጋ ላይ ሆኖም በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት ፡፡ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጥልናል “እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና ፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው ፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን?” በዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝምአለ ፡፡ ንጉሡ ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡

ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ እንደ ሰማዕት ግርፋትንና እሥራትን የተቀበሉ ፣ እንደ ሊቃውንት የመናፍቃንና የከሀድያንን ክርክር የረቱ ፣ እንደ መሐንዲስ ሐናጺ ፣ የሕግና የሥርዐት የሚስጥራትና የትርጉዋሜያት መምህር ፣ የጸሎትና የትምህርት መጻሐፍት ደራሲ ፣ የሥርዓተ ገዳምና ማኅበረ መነኰሳት አባት እንዲሁም ቢያንስ የአንድ ትምህርት መሥራች ሲሆኑ በግዞት በሄዱባቸውና በታሰሩባቸው ቦታዎችም ሆነ በተሾሙባቸው እንደ ደብረዳሞ ገዳም በመሰሉ ቦታዎች ሁሉ ሲያስተምሩና ሲገስጹ ኖረዋል ። በድርሰቱም እስካሁን በሃገራችን ተወዳዳሪ የላቸውም ። እጃቸው ከብዕር ተጨማሪ ከጠንካራ ሥራ ሳይቦዝኑ ዋሻ ሲፈለፍሉ የውሃ ጉድጉዋድ ሲቆፍሩ ድልድይ ሲሠሩ ኖረዋል ። አንደበታቸውና ሕሊናቸው ከምስጋና ሳያቁዋርጡ ለቤተክርስቲያን ጸሎትና ምስጋና ሥርዓት ሲተጉ ኖረው በፅድቅና በቅድስና ሕይወት እንዳጌጡ ለተዋህዶ ኮከብ ሆነው በተወለዱ በ፷ ዓመታቸው በ፲፬፻፲፯ ዓ.ም. ሐምሌ ፯ ቀን አርፈዋል ። ተማሪዎቻቸውም በመረረ ሐዘን ሆነው አፅማቸውን በጋስጫ ራሳቸው ፈልፍለው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በሠሩት ገዳም ውስጥ አስቀምጠውታል ። በትምህርታቸው የተመሰጡት ምዕመናን እና የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በኛ ዘመን የተነሱት አዲሱ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲሏቸው ዓፄ ይስሐቅ ደግሞ መናፍቃንን ሁሉ በማሳፈራቸውና በረቂቅ ድርሰቶቻቸው የኢትዮጵያ ቄርሎስ ብለዋቸዋል ።


በ"Wikimedia Commons"
(የጋራ ፎቶዎች ምንጭ)
ስለ Christianity የሚገኛኙ
ተጨማሪ ፋይሎች አሉ።