አጥናፍሰገድ ኪዳኔ

ከውክፔዲያ
አጥናፍሰገድ ኪዳኔ

አጥናፍሰገድ ኪዳኔ አዲስ አበባ ዑራኤል አካባቢ ኅዳር ፲፮ ቀን ፲፱፻፵፬ ዓ.ም ተወለደ። ዕድሜው ለትምሕርት ሲደርስ ረፒ በልዕልት የሻሸወርቅ አዳሪ ትምሕርት ቤት፤ አዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ እና አስፋ ወሰን ትምሕርት ቤቶች ተምሯል።


ሥራዎች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አጥናፍሰገድ በጋዜጠኝነትና በአሳታሚነት እንድ "ጦቢያ"፣ "ጥቁር ደም" እና "ታይታኒክ" የተባሉ ጋዜጣዎች ላይ የሠራ ሲሆን በመጽሐፍት ረገድ ደግሞ ከዚህ በፊት በትርጉም ሥራ አምስት መጻሕፍቶችን እና አንድ ልብ ወለድ ድርሰቱን ለአንባብያን ያቀረበ ጸሐፊ ነው።

ትርጉም[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • ድንግል ፍቅር፲፱፻፺፬ ዓ/ም "Only Love" በሚል ርዕስ Eric Segal ከጻፈው የተተረጎመ
  • የፍቅር ዕንባ፲፱፻፺፬ ዓ/ም "The Tears of Love" ከተሰኘው የ Barbara Cartland ድርሰት የተተረጎመ
  • እሸት
  • የዕንቁ መዘዝ
  • የሰይጣን ኑዛዜ፲፱፻፺፮ ዓ/ም በRiccardo Orizio ከተጻፈው "Talk of the Devil" የተተረጎመ

ልብ ወለድ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • ሌዮኔ 072392

አጥናፍ ሰገድ ሌዮኔ የተባለውን የመጀመሪያ ልብ ወለድ ድርሰቱን በጥቅምት ፳፻ ዓ.ም. አሳትሞ በሀገር ውስጥ፤ በብሪታኒያ እና በአሜሪካ ገበያ ላይ አውሏል።

ሌዮኔ የተሰኘው ይህ ድርሰቱ በወንጀል፤ በፍቅር፤ በጀብድ፤ በፖለቲካና የሀገር ፍቅር ስሜት የተሞላ ድርሰት ሲሆን፤ ቁም ነገሩ ጥንታዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅርሳ ቅርሶች ቀ.ኃ.ሥ. ከሥልጣን ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ በአንዳንድ ራስ ወዳድ ግለሰቦች እና ባለሥልጣናት እየተሰረቁ በአውሮፓ የጥንታዊ ዕቃዎች ገበያ ላይ እንደዋሉና እየዋሉ መሆኑ ላይ ሲሆን፤ ሴራው ዓፄ ኃይለ ሥላሴቢሮ ጠረጴዛ ላይ ይቀመጥ የነበረው ከወርቅ የተሠራው የአንበሳ ቅርጽ ከፕረዚዳንቱ ቢሮ ተሰርቋል፡ ወደውጭም አውጥቶ ገበያ ላይ ለማዋል እነኛ ራስ ወዳድ ግለሰቦች ከውጭ ዜጎች ጋር ስለሚጎነጉኑት ሴራ እና በዚያውም አኳያ የሀገር ፍቅር ያላቸው አውሮፓ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች ይኼ ትልቅ የሀገር ቅርስ ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ የሚያደርጉትን ጥረት ያካትታል። አጥናፍሰገድ፤ እግረ መንገዱን በደርግ ጊዜ ዋናው ተዋናይ 'አናርኪስት' ተብሎ ከ'አብዮት' ጥበቃ ካድሬዎች ሲሸሽ በዚያ ጊዜ ባገር ላልነበርን እና ለአዲሱ ትውልድ አንባብያን በቃላት የሚቀርጽልን ሁኔታ እውን እዚያው እንደነበርን ያህል ያደርገዋል። እኒያስ ብልሕና ተንኮለኛ ንጉሠ ነገሥት፤ ለካስ የምስጢር የስዊስ ባንክ ቁጥራቸውን የደበቁት እዚያው እተሰረቀው አንበሳ ቅርጽ ላይ ኖሯል! (አያደርጉትም ብለው ነው?)

ደራሲው አንዳንዴ ደግሞ ምርጥ እና አስቂኝ አባባሎችን በመቀላቀል አንባቢውን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ገጽ ድረስ ሳይጨርስ እንዳያስቀምጥ የሚያደርግ የጽሑፍ ባለችሎታ እንደሆነ ሌዮኔ ጥሩ ምስክር ነው። ለምሳሌ፤- "አስፋው ሲጋሩን እያጤሰ ግሩምን ሲያዳምጥ ...የእሥራኤል አገር ጅብ የሰማው ተረት ድንገት ትዝ አለው። 'እሥራኤል አገር ነው አሉ። ሰዎች ሬሳ ተሸክመው ይሄዳሉ። ታዲያ መንገድ ላይ አያ ጅቦ ያገኛቸውና ወዴት እንደሚሄዱ ይጠይቃቸዋል። ሰዎቹም የሞተ ዘመዳቸውን ለመቅበር መሆኑን ይነግሩታል። አያ ጅቦም የሞተ ሰው መቀበሩን እንደማያውቅ ሆኖ በመደንገጥ ራሱን ይይዝና "ልንቀብረው?" ይላቸዋል። ሰዎቹም ግራ ተጋብተው "አዎ ንልቀብረው!" በማለት ይመልሱለታል። በዚህ ጊዜ አያ ጅቦ "ከምትቀብሩት ለምን አትበሉትም?" ይላቸዋል። በጅቡ አነጋገር የተናደዱት ሀዘነተኞች "የሞተ ሰው ሲበላ የት ነው ያየኸው?" ብለው ወደሱ ሲሄዱበት ቆም ይልና "...እሺ እናንተ ካልበላችሁት ለምን ለሚበላ አትሰጡትም?" አላቸው።"[1]

በሌላ ቦታ ደግሞ፤- "...የዘጠኝ ዓመቷ ሠናይት የአስራ ሦስት ዓመቱ አስፋው ቆሎ መያዙን ስታይ ወዲያው ፈገግ ብላ..አቀርቅራ በጥርሷ ጥፍሯን እየነከሰች "አስፊቲ! እስቲ በናትህ ቆሎ ስጠኝ" ትለዋለች። የሠናይት አራዳ መሆን ቢያስገርመውም ጥያቄውን ቸል ብሎ ለመሄድ ግን አላስቻለውም። ከዚያም ቶሎ ብሎ የግራ እጁን ሱሪ ኪሱ ውስጥ ከከተተ በኋላ የተናገርችውን እንዳልሰማ ዓይነት "ቆሎ ስጠኝ?"..አለ። አስፋው ሱሪ ኪሱ ውስጥ ያቆየውን ግራ እጁን ባዶውን ካወጣ በኋላ በኩራት ስሜት "በእጄ መስጠት ትቻለሁ። ከፈለግሽ መጥተሽ ከኪሴ ውሰጂ" አላት። በደስታ የተዋጠችው ሠናይት ወደአስፋው እየሄደች "ምን ቸገረኝ ጠራርጌ ነው የምወስድልህ!" ብላ እጇን ሱሪ ኪሱ ውስጥ ከተተችው። ኪሱ ውስጥ ግን ያገኘችው የጓጓችለትን ቆሎ አልነበረም። የያዘችው ለስላሳና ጠንካራ ነገር ቆሎ ያለመሆኑን ያረጋገጠችው በድንጋጤ በድን ሆኖ የምታየው አስፋው ከት ብሎ በመሳቁ ነበር።"[2]

ዋቢ ማስታወሻዎች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ "ሌዮኔ 072392"፤ አጥናፍሰገድ ኪዳኔ፤ ፳፻ዓ.ም.፤ ገጽ 104/105
  2. ^ "ሌዮኔ 072392"፤ አጥናፍሰገድ ኪዳኔ፤ ፳፻ዓ.ም.፤ ገጽ 47/48