Jump to content

ኤምኔም

ከውክፔዲያ
ኤምኔም
ኤምኔም በእ.ኤ.አ ጁን 2009 በማቀንቀን ላይ
መረጃ
የትውልድ ስም ማርሻል ብሩስ ማዘርስ
የልደት ቀን እ.ኤ.አ ኦክቶበር 17 ቀን 1972

ማርሻል ብሩስ ማዘርስ (የተወለደው ኦክቶበር 17 እ.ኤ.አ 1972)[1] ወይም በመድረክ ስሙ ኤምኔም ወይም ስሊም ሼዲ ታዋቂ የአሜሪካ ራፐር ፣ ሙዚቃ ደራሲ ፣ ሙዚቃ አቀናባሪ እና ተዋናይ ነው። ብቻውን ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ ፣ ዲ12 የተባለ የሙዚቃ ቡድን አባል ነው። በዓለማችን በሙዚቃ ሽያጭ ምርጥ ከሆኑ አርቲስቶች ውስጥም አንዱ ነው። በርካታ መጽሔቶችም የምን ጊዜም ታላቁ አርቲስት በማለት ይገልጹታል። ሮሊንግ ስቶን የተባለው መጽሔት ካወጣው 100 የምን ጊዜም ምርጥ አርቲስቶች መካከል በ83ኛ ደረጃ ላይም ተቀምጧል።[2] ይህም መጽሔት የሂፕ-ሆፕ ንጉሥ በማለት ሰይሞታል።[3] ኤምኔም ፣ ከዲ12 እና ከባድ ሚትስ ኢቭል ጋር የሠራቸውን የሙዚቃ ሥራዎችን ጨምሮ በቢልቦርድ 200 ላይ ዐሥር የሙዚቃ አልበሞቹ የአንደኝነት ደረጃን ለማግኘት በቅተዋል። ኤምኔም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሠማንያ ሚሊየን የሙዚቃ አልበሞችና መቶ ሃያ ሚሊየን ነጠላ ዜማዎችን ሸጧል። እስከ እ.ኤ.አ ጁን 2014 ባለው መረጃ መሠረት ፣ በሙዚቃ ሽያጭ ኤምኔም የኒልሰን ሳውንድስካን ኤራ ሁለተኛ ምርጥ አርቲስት ነው። 45.16 ሚሊዮን የሙዚቃ አልበሞችንም በመሸጥ ከአሜሪካ ስድስተኛው ምርጥ አርቲስት ነው።

ኤምኔም ፣ ኢንፊኒት (Infinite) የተባለውን የመጀመሪያውን የሙዚቃ አልበም እ.ኤ.አ በ1996 ለቀቀ። ከዚያም በኋላ እ.ኤ.አ በ1999 ዘ ስሊም ሼዲ ኤል ፒ የተሠኘውን የሙዚቃ አልበም በመልቀቅ ስመ ጥሩነትን አገኘ። ዘ ስሊም ሼዲ ኤል ፒ ለኤምኔም ታላቅ ስኬት ነበር። ይህም አልበም በምርጥ የራፕ የሙዚቃ አልበም ዘርፍ የመጀመሪያውን የግራሚ ሽልማት እንዲያገኝ አስችሎታል። ዘ ማርሻል ማዘርስ ኤል ፒ (እ.ኤ.አ 2000) እና ዘ ኤምኔም ሾው (እ.ኤ.አ 2002) የተሠኙት አልበሞቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማነትን አግኝተዋል። ሁለቱም አልበሞች በሽያጭ ረገድ የዩ ኤስ ዳይመንድ የምስክር ወረቀት ለማግኘት ችለዋል። በተጨማሪም እነዚህ አልበሞች ምርጥ የራፕ ሙዚቃ አልበሞች በተባለው ዘርፍ የግራሚ ሽልማትን አሸንፈዋል። ይህ ደግሞ የዚህን ዘርፍ የግራሚ ሽልማት ሦስት ጊዜ በተከታታይ በማሸነፍ ኤምኔምን የመጀመሪያው አርቲስት አድርጎታል። ከዚህም በመቀጠል አንኮር (Encore) (እ.ኤ.አ 2004) የተሠኘው የሙዚቃ አልበሙ እንዲሁ ስኬታማ ነበር። ኤምኔም እ.ኤ.አ በ2005 ላይ የሙዚቃ ሥራውን ካቀረበ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ከመድረክ ርቆ ቆይቷል። እ.ኤ.አ በ2009 ሪላፕስ የተሠኘ የሙዚቃ አልበም ለቀቀ። እ.ኤ.አ በ2010 ደግሞ ሪከቨሪ የተሠኘ አልበም በመልቀቅ ከኤምኔም ሾው በመቀጠል ለሁለተኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓመቱ ምርጥ የተሸጠ አልበም ሊሆን ችሏል። ኤምኔም በሪላፕስ እና በሪከቨሪ አልበሞች የግራሚ ሽልማቶችን አግኝቷል። በሥራ ዘመኑ ሁሉ ደግሞ 13 የግራሚ ሽልማቶችን አሸንፏል። ዘ ማርሻል ማዘርስ ኤል ፒ የተሠኘውን ስምንተኛ አልበሙን እ.ኤ.አ በኖቬምበር 2013 ለቅቋል። በዚህም ሁለት የግራሚ ሽልማቶችን አሸንፏል። እ.ኤ.አ በዲሴምበር 15 ቀን 2017 ሪቫይቫል የተሠኘ ዘጠነኛ አልበሙን ለቅቋል።

ኤምኔም ሼዲ ሬከርድስ የተሰኘ የራሱን የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅት እና ሌሎችም የሥራ ድርጅቶችን ከፍቷል። ሼድ 45 የተባለ የራዲዮ ጣብያም አለው። እ.ኤ.አ በ2002 ፣ ኤምኔም 8 ማይል በተባለው የሂፕ ሆፕ ድራማ ፊልም ላይ ተውኗል። በምርጥ ኦሪጂናል ዘፈን ደግሞ "ሉዝ ዩርሰልፍ" (Lose Yourself) የተሰኘው የፊልሙ ዘፈን የአካዳሚ ሽልማትን አሸንፎ ኤምኔም ይህንን ሽልማት በማሸነፍ የመጀመሪያው የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሆኗል። The Wash (2001) ፣ Funny People (2009) እና The Interview (2014) በተባሉት ፊልሞች ላይ እና አንቱራጅ (Entourage) በተባለው የቴሌቪዥን ተከታታይ ፕሮግራም ላይ ብቅ ብሏል።

ሕይወት እና የሥራ ዘመን

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

እ.ኤ.አ 1972-91: የልጅነት ሕይወት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ማርሻል ብሩስ ማዘርስ እ.ኤ.አ በኦክቶበር 17 1972 በሴንት ጆሴፍ ሚዙሪ ተወለደ። የማርሻል ብሩስ ማዘርስ ጁንየር እና የዲቦራ ሬ "ዴቢ" ኔልሰን ብቸኛ ልጅ ነው[4]። ኤምኔም የእንግሊዝ ፣ የጀርመን ፣ የስኮትላንድ እና የስዊስ ዘር አለበት[5]። ዴቢ ከብሩስ ጋር ስትተዋወቅ ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበረች። በ17 ዓመቷ 73 ሠዓታት በፈጀው የልጇ ወሊድ ምክንያት ለሞት ተቃርባ ነበር። በወላጆቹ መሀል ቅራኔ ከመፈጠሩ በፊት ፣ "ዳዲ ዋርባክስ" (Daddy Warbucks) በተባለ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ይጫወቱ ነበር። ብሩስም ቤተሰቡን ትቶ ወደ ካሊፎርኒያ አቀና። ብሩስ ቆይቶም ሁለት ልጆችን ወለደ (ማይክል እና ሣራ)። ዴቢም ናታን "ኔት" ኬን ሳማራ የተባለውን ልጅ ወለደች። በልጅነቱ ፥ ኤምኔም እና ዴቢ አንድ ቤት ውስጥ ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በላይ ሳይቆዩ በሚዙሪ እና በሚሺጋን ይመላለሱ ነበረ። በብዛትም በዘመዶቻቸው ቤት ነበር የሚቆዩት። በሚዙሪ ውስጥ የተለያዩ ከተማዎች ውስጥ ኖረዋል። ኤምኔም ዐሥራ አንድ ዓመት ሲሆነው በዋረን ሚሺጋን መኖር ጀመሩ። በታዳጊነት ዕድሜው ፥ ኤምኔም ለአባቱ ብሩስ ደብዳቤዎችን ጽፎ ነበር። ዴቢ እንደምትለው ከሆነ ፥ ደብዳቤዎቹ "ለላኪው ይመለስ" ተብለው ይመለሱ ነበር። ኤምኔም ደስተኛ ልጅ ግን ደግሞ ትንሽ ብቸኛ እንደነበር በተሰቦቹ እና ጓደኞቹ ይናገራሉ። በጉልበተኛ ልጆችም ጥቃት ይደርስበት ነበር። ዲአንጀሎ ቤይሊ የተባለ አንድ ጥቃት የፈጸመበት ልጅ ፥ ኤምኔምን ክፉኛ ከመደብደቡ የተነሳ ከባድ የጭንቅላት ጉዳት እንዲደርስበት አድርጎ ነበር። በዚህም ምክንያት እናቱ ዴቢ ኔልሰን እ.ኤ.አ በ1982 በትምህርት ቤቱ ላይ ክስ መሥረተች ፤ ነገር ግን ከአንድ ዓመት በኋላ ክሱ ተሰረዘ።[6]

ኤምኔም አብዛኛውን የማደጊያ ዓመቶቹን ያሳለፈው በዝቅተኛ የመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ባለው እና አፍሪካዊ አሜሪካውያን በሚበዙበት በዲትሮይት አካባቢ ነው። ሂፕ ሆፕን ከማግኘቱ በፊት ፥ ኤምኔም ተረት የማውራት ዝንባሌ አድሮበት የኮሚክ መጽሐፍ አርቲስት መሆን ይፈልግ ነበር። ኤምኔም ለመጀመሪያ ጊዜ ያደመጠው የራፕ ሙዚቃ አይስ-ቲ ያቀነቀነበትን ሬክለስ (Reckless) ይባላል። ይህንን ዘፈን እንደ ስጦታ የሠጠው ሮናልድ "ሮኒ" ፖልኪንግሆርን የተባለው የእናቱ የዴቢ ልጅ ነው። ከዐሥር ዓመት በኋላ ሮኒ ራሱን አጠፋ ፤ ይህም ኤምኔምን በጣም ከመጉዳቱ የተነሳ ለቀናት ያህል አይናገርም ነበር። በቀብሩም ላይም አልተገኘም።[7]

የቤት ሕይወቱ ብዙዉን ጊዜ የተደላደለ አልነበረም ፤ ከእንቱም ጋር በተደጋጋሚ ይጣላ ነበር። አንዲት የማኅበራዊ ሠራተኛም ዴቢን "በጣም ተጠራጣሪ ሴት" ብላ ትገልጻታለች። ልጇ ታዋቂ ሲሆን ፥ ጥሩ እናት አይደለችም የተባለውን በመቃወም እንዲያውም ለኤምኔም ስኬት ዋነኛው ምክንያት እንደሆነች ተናግራ ነበር። እ.ኤ.አ በ1987 እናቱ ከቤት የኮበለለችውን ኪምበርሊ አን "ኪም" ስኮት በቤታቸው እንድትቆይ ፈቀደች። ከሆኑ ዓመታት በኋላም ኤምኔም ከኪም ጋር አልፎ አልፎ ግንኙነትን ጀመረ። ከትምህርት በመቅረት እና በደካማ ውጤት ምክንያት ሦስት ዓመታትን በዘጠነኛ ክፍል ካሳለፈ በኋላ በ17 ዓመቱ ከሊንከን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወጣ።[8] ምንም ያህል በእንግሊዝኛ ላይ ጥልቅ የሆነ ፍላጎት ቢኖረውም (የኮሚክ መጽሐፎችን በመምረጥ) ስነ-ጽሑፍን ግን አላጠናም። ሒሳብ እና የኅብረተሰብ ትምህርትንም አይወድም ነበር። እናቱንም ለመርዳት ብዙ ሥራዎችን ይሠራ ነበር ፤ በኋላ ግን ተባረርኹ ማለት ጀመረ። እናቱ ቢንጎ ለመጫወት ከቤት ስትወጣ ፥ ሙዚቃ በኃይል ይከፍትና ግጥም ይጽፍ ነበር።

እ.ኤ.አ 1992-99: የቀድሞ የሥራ ዘመን ፣ ኢንፊኒት እና ዘ ስሊም ሼዲ ኤል ፒ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
ኤምኔም ጀርመን ውስጥ - እ.ኤ.አ 1999

ታዋቂነቱ እየጨመረ በመጣ ጊዜ የተለያዩ የራፕ ቡድኖችን እንዲቀላቀል ተመልምሎ ነበር። ከነዚህም የመጀመሪያው ኒው ጃክስ (New Jacks) ነበር። ይህም ቡድን ከተበታተነ በኋላ ፥ እ.ኤ.አ በ1995 ነጠላ ዜማ የለቀቁትን ሶል ኢንቴንት (Soul Intent) የተባለውን ቡድን ተቀላቀለ። በዚህ ነጠላ ዜማ ላይ ጓደኛው ፕሩፍ አቀንቅኖበት ነበር። እኚህ ሁለት ራፐሮች ተነጥለው በመውጣት ዲ12ን መሠረቱ።

ኤምኔም ከዚያ በኋላ ለኤፍ ቢ ቲ ፕሮዳክሽንስ በመፈረም ኢንፊኒት የተሰኘውን የመጀመሪያው የሙዚቃ አልበሙን ሠራ። በዚህ አልበም ከሸፈናቸው ሃሳቦች አንዱ የተወለደችውን ሴት ልጁን በትንሽ ገቢ ለማሳደግ እንዴት እንደታገለ ነበር። በዚህ ጊዜ ፥ የኤምኔም የግጥም ዘይቤ እንደ ናስ እና ኤዚ የተባሉ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኞች አይነት ዘይቤ ነበር። ሥራዎቹ እንደወደፊቱ ቀልደኛ እና ቁጡ አልነበሩም። ኢንፊኒት በዲትሮይት ዲጄዎች ይህን ያህል ትኩረትን አላገኘም ነበር። ያገኘውም ምላሽ "ለምን ሮክ ኤንድ ሮል አትዘፍንም?" የሚል ነበር። ይህም በንዴት የተሞሉ እና ስሜታዊ የሆኑ ዘፈኖችን እንዲሠራ አደረገው። በዚህ ጊዜ ፥ ኤምኔም እና ኪም ስኮት ወንጀል በሚዘወተርበት ሰፈር ውስጥ አብረው ይኖሩ ነበር። ቤታቸውም በብዛት ዝርፍያ ይደርስበት ነበር። ለሆነ ጊዜም ሴንት ክሌር ሾርስ በሚገኘው ጊልበርትስ ሎጅ በተባለው ሬስቶራንት ውስጥ በወጥ ቤት እና በሳህን ማጠብ ይሠራ ነበር። ልጁ ሄይሊ ጄድ ስኮት ማዘርስ ከተወለደች በኋላ በሣምንት ለስድሳ ሠዓታት ለስድስት ወራት ያህል ሠርቶ ነበር። ለገና በዓል ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ከሚሠራበት ከጊልበርትስ ሎጅ ሬስቶራንት ተባረረ። ስለዚህም ጊዜ ሲናገር እንዲህ ብሏል - "ጊዜው ከገና አምስት ቀናት በፊት ነበር። ይህም የሄይሊ ልደት ቀን ነበር። ለእርሷ የሆነ ነገር ለመግዛት የነበረኝ አርባ ዶላር ብቻ ነበር"። ኢንፊኒት ከተለቀቀ በኋላ የኤምኔም የአደንዛዥ ዕጽ እና የአልኮሆል ከልክ በላይ መጠቀም ወደ አልተሳካ የራሱን የማጥፋት ሙከራ ደረጃ አደረሰው። እ.ኤ.አ በማርች 1997 ከጊልበርትስ ሎጅ ለመጨረሻ ጊዜ ተባረረ። በዚህም ጊዜ ከኪም እና ከሄይሊ ጋር በእናቱ ተንቀሳቃሽ መኖሪያ ቤት ውስጥ ይኖር ነበር።

ኤምኔም ፥ ጨካኝ እና ቁጡ የሆነውን ስሊም ሼዲ የተባለውን ገጸ ባህርይ ከፈጠረ በኋላ ተጨማሪ ትኩረትን ስቦ ነበር። "ስለ ግድያ እና አስገድዶ መድፈር ግጥም የሚገጥመው አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ እና ደም የጠማው ዱርዬ" የሆነው ይህ ገጸ ባህርይ ፥ ንዴቱን እንዲገልጽ አስችሎት ነበር። እ.ኤ.አ 1997 ኤምኔም ዘ ስሊም ሼዲ ኢፒ የተባለውን የሙዚቃ አልበሙን በዌብ ኢንተርቴይንመንት አማካኝነት ለቀቀ። ስለ አደንዛዥ እፅ ፣ ስለ ወሲባዊ ድርጊቶች ፣ ስለ አእምሮ መታወክ እና ስለ ሁከት የሚያወሩ ሐሳቦችን የያዘው ይህ አልበም እንደ ድህነት እና የትዳር እና የቤተሰብ ችግሮችን የመሳሰሉ ቁም ነገር የያዙ ሐሳቦችን አካትቶ ነበር። ዘ ሶርስ የተሰኘው የሂፕ ሆፕ ጋዜጣም ኤምኔምን "አንሳይንድ ሃይፕ (Unsigned Hype)" በሚለው አንቀጹ ስር እ.ኤ.አ ማርች 1998 ላይ አስፍሮት ነበር።

ኤምኔም ከመኖሪያ ቤቱ ከተባረረ በኋላ በእ.ኤ.አ 1997ቱ ራፕ ኦሊምፒክስ (ዓመታዊ የሆነ አገር አቀፍ የራፕ ሙዚቃ ውድድር) ላይ ለመወዳደር ወደ ሎስ አንጀለስ አቀና። በውድድሩም ሁለተኛ ወጣ ፤ በውድድሩ ቦታው የነበሩት የኢንተርስኮፕ ሬከርድስ ሠራተቾች የስሊም ሼዲ ኢፒን ቅጂ ለድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ለሆነው ለጂሚ አዮቪን ላኩለት። አዮቪን የተላከለትን ሙዚቃ ለአፍተርማዝ ኢንተርቴይንመንት ባለቤት ለሆነው ለዶክተር ድሬ አስደመጠው። ጂሚ ሙዚቃውን ካጫወተ በኋላ ፥ ድሬ የሚያስታውሰውን ሲናገር "በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ባሳለፍኩት የሥራ ዘመኔ ለሙከራ ከቀረቡ ሲዲ ወይም ካሴት ምንም አግኝቼ አላውቅም። ጂሚ ይህን ሲያጫውትልኝ 'አሁኑኑ ፈልገው' ነበር ያልኩት"። ነጭ ራፐር በመቅጠሩ በሥራ ባልደረቦቹ ብዙ ቢተችም በውሳኔው ግን ተማምኖ ነበር። "ነጭ አይደለም ወይን ጠጅ ቀለም እንኳን ብትሆን ግድ የለኝም። መሥራት ከቻልክ አብረን እንሠራለን"። ኤምኔም ኤን.ደብል ዩ.ኤን በማድመጥ ከታዳጊነት ዘመኑ ጀምሮ ከሚያደንቀው ከዶክተር ድሬ ጋር አንድ አልበም ላይ መሥራታቸው አስፈርቶት ነበር፦ "በጣም መለማመጥ አልፈለግኹም ነበር...እኔ አንድ ተራ የዲትሮይት ነጭ ልጅ ነኝ። ታዋቂ ሰዎችን አይቼ አላውቅም እንኳን ዶክተር ድሬን ይቅርና"። ከተከታታይ የሙዚቃ ሥራዎች በኋላ ግን መፍራቱን በመተው ከድሬ ጋር መሥራታቸውን ቀጠሉ።

ኤምኔም እ.ኤ.አ ፌብሪዋሪ 1997 ላይ ዘ ስሊም ሼዲ ኤልፒን ለቀቀ። ምንም እንኳን የዓመቱ ታዋቂ አልበም ቢሆንም (በዓመቱ መጨረሻ ላይ የትሪፕል ፕላትነም ምስክር ወረቀት ቢያገኝም) ሁኔታው እና የሥራ አኳዃኑ ኬጅ የተባለውን የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝን ዓይነት ይመስላል የሚሉ ክሶች ቀርበውበት ነበር። በ"97 ቦኒ ኤንድ ክላይድ" ላይ ኤምኔም ከጨቅላ ሴት ልጁ ጋር አብረው ሄደው የሚስቱን ሬሳ ስለሚጥልበት በሚያወራው ግጥም እና በ"ጊልቲ ኮንሸንስ" ላይ ደግሞ ሚስቱን እና ፍቅረኛዋን እንዲገድላቸው ሰውዬውን እያበረታታ የሚናገረው ግጥም ይህንን አልበም ከታዋቂነቱ በተጨማሪ በጣም አነጋጋሪ እንዲሆን አድርጎት ነበር። ጊልቲ ኮንሸንስ በኤምኔም እና በዶክተር ድሬ መካከል ለብዙ ዘመን የሚቆየው ጓደኝነታቸው እና የሙዚቃ ባልደረባነታቸው መጀመሪያ ነበር። እኚህ ሁለቱ ከዚህ በኋላ በተለያዩ ሙዚቃዎች ላይ አብረው ሠርተዋል። ዶክተር ድሬም በእያንዳንዱ የኤምኔም አፍተርማዝ አልበም ላይ ቢያንስ አንድ ጊዜ ያቀነቅን ነበር[9]። ዘ ስሊም ሼዲ ኤል ፒ የኳድሩፕል ፕላትነም ምስክር ወረቀት በአር አይ ኤ ኤ ተሰጥቶታል።

እ.ኤ.አ 2000-2002: ዘ ማርሻል ማዘርስ ኤል ፒ እና ዘ ኤምኔም ሾው

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዘ ማርሻል ማዘርስ ኤል ፒ እ.ኤ.አ በሜይ 2000 ተለቀቀ። በመጀመሪያው ሣምንት 1,760,000 ቅጂዎች ተሽጠው በስኑፕ ዶግ ዶጊስታይል ተይዞ የነበረውን "በፍጥነት-የተሸጠ ሂፕ ሆፕ አልበም" እና በብሪትኒ ስፒርስ ቤቢ ዋን ሞር ታይም ተይዞ የነበረውን "በፍጥነት-የተሸጠ ነጠላ አልበም" ክብረ ወሰኖችን ሰብሯል።[10] ከአልበሙ የመጀመሪያው ዘ ሪል ስሊም ሼዲ የተባለው ነጠላ ዘፈን ምንም እንኳን በኤምኔም ስድቦች ምክንያት አነጋጋሪ ቢሆንም በጣም ስኬታማ ሆኖ ነበር። ዘ ዌይ አይ አም በሚለው ሁለተኛው ነጠላ ዘፈን ላይ እንዴት የሙዚቃ አቀናባሪ ድርጅቱ ማይ ኔም ኢዝን የሚስተካከል ሥራ እንዲሠራ እንዴት ጫና እንዳደረጉበት ይገልጻል። በሦስተኛው ነጠላ ዜማ ስታን ደግሞ ኤምኔም አዲስ ያገኘውን ዝና ለመቆጣጠር ይሞክራል። በዚህም ዘፈን ላይ እራሱን እና ነፍሰ-ጡር እጮኛውን የሚገድል አንድ የእብድ አድናቂን ገጸ ባህርይ ይዞ ይዘፍናል። ኪው መጽሔትም "ስታን" የተባለውን ነጠላ ዜማ ሦስተኛው የምንግዜም ምርጥ የራፕ ሙዚቃ ብሎ ፈርጆታል።[11] ይህም ዘፈን በሮሊንግ ስቶን 500 የምን ጊዜም ምርጥ ዘፈኖች ውስጥ በ296ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።[12][13] እ.ኤ.አ በጁላይ 2000 ፥ ዘ ሶርስ በተሰኘው መጽሔት ላይ በመውጣት ኤምኔም የመጀመሪያው ነጭ አቀንቃኝ ነበር። ዘ ማርሻል ማዘርስ ኤል ፒ የ11×ፕላትነም ምስክር ወረቀትን ከአር አይ ኤ ኤ አግኝቷል።

ዘ ኤምኔም ሾው እ.ኤ.አ በሜይ 2002 ተለቀቀ። ይህም አልበም በመጀመሪያው ሙሉ ሣምንት ከ1.3 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ በመሸጥ በሠንጠረዦች ላይ አንደኛ ደረጃን በማግኘት ስኬታማ ሆኖ ነበር። "ዊዝአውት ሚ" በተሰኘው አንደኛው የአልበሙ ነጠላ ዜማ ላይ ሊምፕ ቢዝኪት ፣ ዲክ እና ላይን ቼኒ ፣ ሞቢ እናም የሌሎችን የተለያዩ የሙዚቃ ባንዶችን ስም አጥፍቷል። ይህም አልበም ኤምኔም ወደ ዝናው በመምጣቱ ስላመጣው ውጤት ፣ ከሚስቱ እና ከሴት ልጁ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ፣ በሂፕ ሆፕ ማህበረሰብ ውስጥ ስለነበረው አቋም እና ሌሎች ሐሳቦችንም አካትቷል። ምንም እንኳን አንዳንድ ዘፈኖቹ በንዴት የተሞሉ ቢሆኑም እንኳን ፥ የኦል ምዩዚኩ ስቴፈን ቶማስ ኧርልዊን ዘ ኤምኔም ሾው ከዘ ማርሻል ማዘርስ ኤል ፒ አንጻር ሲታይ ለዘብተኛ ነው ብሏል። ዘ ኤምኔም ሾው የእ.ኤ.አ 2002 ምርጥ የተሸጠ አልበም ነበር።

እ.ኤ.አ 2003-2007: አንኮር እና ድንገተኛ የሙዚቃ ሥራን ማቆም

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

እ.ኤ.አ በዲሴምበር 8 2003 ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ሲክሬት ሰርቪስ ኤምኔም የዩናይትድ ስቴትስን ፕሬዚደንት ላይ ዝቷል የሚለውን ክስ "በማጣራት ላይ" ነበር። ለዚህም ምክንያት የነበረው በአንኮር በተሰኘው አልበሙ ላይ የሚገኘው "ዊ አዝ አሜሪካንስ" በተባለው ዘፈን ምክንያት ነበር።

በ2004 እ.ኤ.አ የተለቀቀው አንኮር ስኬታማ ሆኖ ነበር። ማይክል ጃክሰንን የሚያንጓጥጥ ስንኞችን የያዘው "ጀስት ሉዝ ኢት" የተባለው የአልበሙ የመጀመሪያ ነጠላ ዜማ ለአልበሙ ሽያጭ ስኬት ከፊል ሚና ተጫውቷል። በእ.ኤ.አ ኦክቶበር 12 2004 ፥ "ጀስት ሉዝ ኢት" ከተለቀቀ ከሣምንት በኋላ ፥ ማይክል ጃክሰን በሎስ አንጀለስ ወደሚገኘው የስቲቭ ሃርቪ የራዲዮ ዝግጅት ላይ በመደወል በቪዲዮው አለመደሰቱን ገለጸ። ቪድዮው በማይክል ጃክሰን ሕጻናትን በማባለግ ክስ ፣ በፕላስቲክ ቀዶ ህክምና እና በእ.ኤ.አ 1984 ላይ ማስታወቂያ ሲሰራ በፀጉሩ ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ ላይ ቀልዷል። ብዙ የማይክል ጃክሰን ጓደኞች ፥ ስቲቪ ዎንደርን ጨምሮ ፥ የሙዚቃ ቪድዮውን ተቃውመዋል። ቪድዮው እነ ፒ-ዊ ኸርመን ፣ ኤም ሲ ሃመር እና ማዶና ላይ ሁሉ ቀልዷል። ምንም እንኳን ብላክ ኢንተርቴይንመንት ቴሌቪዥን ሙዚቃውን ማጫወት ቢያቆምም ኤም ቲቪ ግን ማሠራጨቱን እንደማያቆም ገልጾ ነበር። በእ.ኤ.አ 2007 ማይክል ጃክሰን እና ሶኒ ፥ ፌመስ ምዮዚክን ከቪያኮም ገዙ ፤ ይህም ማይክል ጃክሰንን በኤምኔም ፣ በሻኪራ ፣ በቤክ እና በሌሎች አርቲስቶች ዘፈን ላይ ባለመብት አደረገው።

  1. ^ http://www.imdb.com/name/nm0004896/bio
  2. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2016-03-08. በ2016-03-17 የተወሰደ.
  3. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2015-11-13. በ2016-03-17 የተወሰደ.
  4. ^ United States Public Record Number 1222170896
  5. ^ "Ancestry of Eminem" . Wargs.
  6. ^ "Eminem's dirty secrets". Salon.
  7. ^ The Dark Story of Eminem. Music Sales Group. ገጽ 55 ISBN 9781849384582
  8. ^ "Eminem". Encyclopædia Britannica.
  9. ^ http://www.sptimes.com/2006/01/16/Artsandentertainment/Eminem_and_his_ex_wif.shtml
  10. ^ "Eminem Bounces Britney From Top Spot" ሮሊንግ ስቶን። ከዋናው በእ.ኤ.አ ኤፕሪል 2008 የተወሰደ።
  11. ^ "150 Greatest Rock Lists Ever" Archived ጁላይ 18, 2011 at the Wayback Machine ሮክ ሊስት ምዩዚክ። በእ.ኤ.አ ማርች 17 2016 የተወሰደ።
  12. ^ "The RS 500 Greatest Songs of All Time" ሮሊንግ ስቶን። ከዋናው በእ.ኤ.አ ኤፕሪል 23 2008 የተወሰደ።
  13. ^ Eminem’s Life Story: From Bullied Dropout to Hip Hop Knockout Archived ሜይ 1, 2021 at the Wayback Machine (May 1, 2021)