ካርግ
Appearance
ካርግ (ኮሪይኛ፦ 가륵፤ /ካ - ርግ/፣ በላቲን ፊደል Gareuk) በኮርያ ልማዳዊ አፈ ታሪክ በጥንታዊ ኮርያ (ጎጆሰን) የነገሠ ንጉሥ ወይም «ዳንጉን» ነበር። እርሱ ከአባቱ ዳንጉን ቡሩ መንግሥት ቀጥሎ ገዛ።
በጠቅላላ ለ፵፭ ዓመታት(ምናልባት 1964-1919 ዓክልበ.) እንደ ነገሠ ይጻፋል። ከዚያ በኋላ ልጁ ኦሳጉ ተከተለው።
በ1903 ዓም. በኮሪይኛ የተዘጋጀው ዜና መዋዕል ኋንዳን ጎጊ ስለዚሁ አፈታሪካዊ ዘመን መረጃ ይሰጣል፤ ሆኖም በብዙ የኮርያ መምህሮች ዘንድ ይህ መጽሐፍ እንደ ትክክለኛ ታሪክ አይሆንም። ካርግ ካደረጋቸው ሥራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ እንዲህ ናቸው፦
- በ1964 ዓክልበ. ግድም የፀሐይ ግርዶሽ በኮርያ ታየ (13 ኦገስት 1956 ክ.በ. እ.ኤ.አ.)፤ በዚያም ቀን ቡሩ ዓረፈ፣ ካርግም ተከተለው።
- በ1963 ዓክልበ. ሕገ መንግሥቱን አወጣ
- በ1962 ዓክልበ. ካርግ ሚኒስትሩን «እልቦርግ» አዲስ ፊደል እንዲፈጠር አዘዘ። ከዚህ ቅድም በጠቀማቸው «ኖክዶ» ጽሕፈት እያንዳንዱ ፊደል የአጋዘን ዱካ ይመስል ነበር፣ ለማንበብ ግን ይከብድ ነበር። አዲሱ የተፈጠረው ኮሪይኛ ጽሕፈት «ካሪምቶ» ተባላ።
- በ1961 ዓክልበ ካርግ ሚኒስትሩን «ጎግል» የታሪክ መዝገቦች በአዲሱ ፊደል እንዲጻፉ አዘዘው።
- በ1958 ዓክልበ ካርግ የየውልያንግ (አሁን [[የልያውዶንግ ልሳነ ምድር በቻይና) አገረ ገዥ፣ «ሳክጀውንግ»ን፣ ወደ «ያክሱ» ምድር አጋዘው። በዚያ የሥዮንግ-ኑ ነገድ ወላጅ ሆነ። እሌህ ሥዮንግ-ኑ በኋላ ዘመን (440 ዓ.ም. አካባቢ) «ሁኖች» ተብለው ወደ አውሮፓ የወረሩት ብሄር እንደ ነበሩ ይታሥባል።
- በ1956 ዓክልበ. የካንግገው ሕዝብ አመጹ፣ ካርግም በ«ጂቤትክ ውግያ» አሸነፋቸው። ካርግ ወደ ቡልሃም ተራራ ተነሥቶ ጢስ ከተራ ሰዎች ቤቶች ሲወጣ ተመለከተ፣ ጢሱም ጥቂት በሆነባቸው ቤቶች ግብራቸው እንዲቀነስላቸው አዘዘ።
- በ1954 ዓክልበ. የየ-ዕብ ሕዝብ በዶጂጁ ዙሪያ አመጹ፤ ካርግም ሻለቃውን «የውሹጊ» የየዕብን አለቃ ሶሺሞሪ እንዲገድለው አዘዘው። ከዚህ በኋላ ክፍላገሩ ደግሞ «ሶሺሞሪ» ሕዝቡም «ዉሱ» ይባሉ ጀመር። ይህ አሁን በቻይና የሶንግኋን ወንዝ አገር ነው። ከየ-ዕብ ተወላጆች መካከል አንዱ «ህየውብያኖ» ወደ ባሕር ሸሸ፤ በ«ሦስቱ ደሴቶች»ም ላይ (አሁን ጃፓን) የራሱን ግዛት መሠረተ።
- በ1919 ዓክልበ. ግድም ዳንጉን ካርግ ዓረፈ፤ አልጋ ወራሹም ኦሳጉ ወደ ዙፋኑ ተከተለው።
ቀዳሚው ቡሩ |
የጆሰን ዳንጉን | ተከታይ ኦሳጉ |