Jump to content

ዳንጉን ዋንገም

ከውክፔዲያ

ዳንጉን ዋንገምኮርያ ልማዳዊ አፈ ታሪክ በኮሪያ በጥንት የነገሠ ንጉሥ ነበር። እርሱ ከሺንሺ መንግሥት (ፔዳል) ቀጥሎ የአዲስ መንግሥት መሥራች ሆነ። የዚህ መንግሥት ስም «ጆሰን» ሲሆን፣ በኋላ ዘመን (ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም.) ሌላ «ጆሰን» የተባለ መንግሥት ስለ ኖረ፣ ዳንጉን የመሠረተው መንግሥት አሁን «ጥንታዊ ጆሰን» ወይም «ጎጆሰን» በመባል ይታወቃል። የፔዳል (ጸሐይ) ወገንና የናቱ ወገን «የድብ ጎሣ» በውሕደታቸው የጆሰን ብሔር ሆነው ዳንጉን እንደ ኮርያ መሥራችና አባት ይቆጠራል። ይህ በቻይና (ኋሥያ) ንጉሥ ያው 25ኛው ዓመት እንደ ሆነ ይታመናል።

ዋና ከተማው አሳዳል ምናልባት የአሁኑ ፕዮንግያንግ፥ ወይም ሓርቢንማንቹርያ ነበር። ከዚህ በላይ ዳንጉን የራሱን አምልኮት እንደ ዐዋጀ ይባላል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ዳንጉንን እንደ አምላክ የሚቆጠሩ አንዳንድ ትንንሽ ሃይማኖቶች በኮርያ አገር አሉ።

በጠቅላላ ለ93 ዓመታት (ወይም ለ1500 ዓመታት በአንድ ትውፊት) እንደ ነገሠ ይጻፋል። ከዚያ በኋላ ልጁ ቡሩ ተከተለው።

ኋንዳን ጎጊ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በ1903 ዓም. በኮሪይኛ የተዘጋጀው ዜና መዋዕል ኋንዳን ጎጊ ስለዚሁ አፈታሪካዊ ዘመን መረጃ ይሰጣል፤ ሆኖም በብዙ የኮርያ መምህሮች ዘንድ ይህ መጽሐፍ እንደ ትክክለኛ ታሪክ አይሆንም። ስለ ዳንጉን ዋንገውም ወይም ኢምግም ዘመን እንዲህ ይለናል። ዳንጉን ከአባቱ የሺንሺ ንጉሥና ከእናቱ የዉንግ ንግሥት ከልምጭ ዛፍ በታች ተወለደ (ምናልባት 2145 ዓክልበ. ግድም)። የአምላክ ምግባር ስለነበረው ሰዎች ሁሉ አከበሩት ታዘዙለትም፣ እድሜው 14 ዓመት ሲሆን፣ እናቱ የደዕብ ክፍላገር መስፍን አደረገችው። በ2108 ዓክልበ. ግድም የኮርያ ሰዎች (800 ሰዎች) በልምጭ ቦታ በሥነ ስርዓት ዙፋኑን ለዳንጉን ሰጡት። የሕዝቡ አለባበስ ያንጊዜ ከሣር ተሠራ፣ ጫማ ግን አልለበሱም ነበር ይላል። የዳንጉን ዐዋጅ እንዲህ ነበር፦

«ወደ ገነት (መንግስተ ሰማያት) የሚወስደው በር አንድ ብቻ ነው እንጅ ሁለት በሮች አይደሉም። መንፈስህ በሥራህ ላይ ብታኖረው፣ ያንጊዜ መንፈስህ ወደ ገነት ሊደርስ ይችላል። የገነት ሕግ አንድያ ሕግ ነው፣ እንደ ወትሮ ይቀጥላል፣ የሰውም አዕምሮ እንዲህ የሚቀጥል ነው። እንግዲህ ማንም ሰው የራሱን አዕምሮ ቢመረምር የሰውን አዕምሮ መመልከት ይችላል። ሰውዬው ሌሎቹን ከአምላክ ሕግ ጋር እንዲስማሙ ቢያስተምራቸው፣ ትምህርቱ በዓለሙ የትም ቦታ በትክክል ሊጠቀም ይችላል።
ወላጆቻችሁና አያቶቻችሁ ከገነት (መንግስተ ሰማያት) ተወለዱ፣ እናንተም ያለነርሱ በሕይወት መኖር አትችሉም። ስለዚህ ወላጆቻህን ለማዳገፍና ለማገልገል ግዴታ አለብህ፣ ይህም ገነትን ማክበር ነውና ብሄሩን በሙሉ ይነካል። ወላጆችህንም የምታገልግላቸው ለብሔሩ በመታመንህ ነው። ይህንን ሕግ በመጠብቅ ብቻ ከድንገተኛ አደጋ ወይም ከመዓት ማምለጥ የሚቻል ነው።
እንስሳ ስንኳ የኑሮ ጓደና አለው፣ የተቀደደውም ጫማ ጥንዱን አለው። እንዲህ ወንድና ሴት በሰላም ያለ ጠብ፣ ቅሬታ ወይም መቀኝነት ይኖራሉ። ደግሞ መረንነትና ዝሙት ክልክል መሆን አለባቸው። ጣቶችህን ብትነክስ፣ የትኛው ጣት መጠኑ ምንም ቢሆን ሕመም አያሰኝህም? እያንዳንዳችሁ ከሐሜት ስትቀሩ፣ እርስ በርስ ስትዋደዱ፣ ከጠብ ስትቀሩ፣ ሌሎቹንም ስትረዱአቸው፣ ያንጊዜ መላው ብሐሩና መላው ቤተሠቡ ደህና ይሆናሉ ይበልጸጋሉ። ላሞችና ፈረሶቻቸሁ መኖአቸውን በጋራ ያከፋፍላሉ። ሰውን ከምንም ነገር ካላሳጣችሁ፣ ያለ ሌብነት ከተባበራችሁ፣ አገሩ ሁሉ ይበልጸጋል።... ሁልጊዜ በገነት (መንግሥተ ሰማያት) አክባሪ አዕምሮ ውደዱ። ሰው በአደገኛ ሁኔታ ስታገኘው፣ እሱን መርዳት እንጂ ሌሎችን መሳድብ የለብህም። እኒህን ድንጋጌዎች ካልታዘዝክ፣ ገነት (መንግሥተ ሰማያት) አይረዳህም፣ አንተና ቤተሠብህ እስከሚጠፋ ድረስ። እሳት በሩዝ እርሻ ላይ ብታደርግ፣ የሩዙም ተክል ቢቃጠል፣ ገነት (መንግሥተ ሰማያት) ይቀጣሃል። ጥፋተኛ ብትሰውረውም፣ የወንጀሉ ክርፋት ግን ይወጣል። ሁልጊዜ በጎ ጸባይ በአክባሪ አዕምሮ ትይዛለህ። ክፉ አዕምሮ አይኖርህ፣ ጥፋትን አትደብቅ፣ አደጋንም አትሰውር። አዕምሮህን በማሠልጠን ገነትን (መንግሥተ ሰማያትን) አክበር፤ ለመላውም ሕዝቡ ጓደኛ ሁን። አምስቱ ዋና ሚኒስትሮች እኒህን ድንጋጌዎች መጠብቅ አለባቸው።»

ከዚህ በኋላ ከሚኒስትሮቹ ፐንግ-ዉ ምድረ በዳ እንዲያቀና፣ ሰውንግጁ ቤተ መንግሥት እንዲያሠራ፣ ጎሺ በእርሻ ተግባር ላይ፣ ሺንጂ ምስሎችን እንዲፈጥር፣ ኪሰውንግ በሕክምና ጥናት ላይ፣ ነዑል ቤተሠቦቹን በዝርዝር እንዲዘግብ፣ ኸዊ እድሎችን (በንግር) በመናገር ላይ፣ ዉ በጦር ሠራዊት ላይ ሾማቸው።

በ2059 ዓክልበ. ግድም በታላቅ ጐርፍ ምክንያት የሕዝቡ ምቾት ተበላሸ። ስለዚህ ዳንጉን ሚኒስትሩን ፐንግ-ዉ ወንዞቹን እንዲገድብ አዘዘው። ሐውልት በ«ዉ» መንደር ተሠራ። በ2058 ዓክልበ. ሚኒስትሩን ፐዳል አምባ በሳምላንግ እንሲያሠራ አዘዘው። በ2042 ዓክልበ. ግድም አልጋ ወራሹን ልዑል ቡሩ በተልእኮ ወደ ዩ ላከው፣ ይህ ምናልባት በኋላ ዳ ዩ የተባለው የኋሥያ (ቻይና) አለቃ ይሆናል። በተጨማሪ ዳንጉን የ፭ ንጥረ ነገሮች ትምህርት አስተማረ፣ «ዩጁ» እና «ያንግጁ» ግዛቶችም ወደ ጆሰን ጨመረ። ዳንጉን ደግሞ «ኈዳይ»ን አሸንፎ ተገዥ አደረገው፣ ዩ-ሹን በተገዥነት አስተዳዳሪነቱን ሰጠው ይለናል። «ዩ-ሹን» ማለት የኋሥያ ንጉሥ ሹን ስም ነው፤ «ኈዳይ»ም በሻንዶንግ ልሳነ ምድር እንደ ነበር ይታስባል። በ2016 ዓክልበ. ግድም ለሀብቱ እድገት መስኖ፣ የሐር ትል፣ እና የአሣ ማጥመድ ሥራ ክፍሎች ወደ ጆሰን አስገባ። ዳንጉን ኢንገም በአገሩ ለ93 ዓመታት ነግሦ አረፈ፣ ልጁም ዳንጉን ቡሩ ያንጊዜ የጆሰን ዳንጉን (ንጉሥ) ሆኖ ተከተለው።