1 አመነምሃት

ከውክፔዲያ

ሰኸተፒብሬ 1 አመነምሃት ግብጽን በመካከለኛ መንግሥት (12ኛው ሥርወ መንግሥት) ከ2002 እስከ 1972 ዓክልበ. ግድም ድረስ የገዛ ፈርዖን ነበረ። የ4 መንቱሆተፕ (ነብታዊሬ) ተከታይ ነበር።

አመነምሃት መጀመርያ በነብታዊሬ አጭር ዘመን የነብታዊሬ አለቃ ወይም ሚኒስትር ይመስላል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይህ አመነምሃት እራሱ ፈርዖን ሆነ። ነብታዊሬ ወዴት እንደ ሄደ ወይም እንደ ኖረ እንዳልኖረ አይታወቅም።

አመነምሃት ከ፯ መቶ ያህል ዓመት በፊት ጠፍቶ የነበረውን ጥንታዊ መንግሥት ለማሳደስ ያደረገው ጥረት ሊታወቅ ችሏል። ይህም በጥንታዊ መንግሥት ፈሊጥ የሆነውን ሀረም በማስገንባቱ በኩል ይታያል። እንዲሁም ከአመነምሃት ዘመን በግብጽኛ የተጻፈው ሥነ ጽሁፍ ይህን ሀሣብ ያስረዳል። ከነዚህ መካከል የአመነምሃት ትምህርትየሲኑሄ ታሪክ እና የነፈርቲ ትንቢት ዋናዎቹ ናቸው።

በአመነምሃት ዘመነ መንግሥት በ፳ኛው ዓመት (1982 ዓክልበ. ግድም) ልጁን 1 ሰኑስረትን ከእርሱ ጋር በጋርዮሽ ወደ ዙፋኑ አስነሣው። በዚህ ዓመት ደግሞ የግብጽ ዋና ከተማ ከጤቤስ ወደ አዲስ ከተማ ኢጭታዊ አዛወረው። በ፳፱ኛው ዓመት ዋዋት (ስሜን ኩሽ መንግሥት) እንደ ያዘ ከአንድ ጽላት ታውቋል።[1]

በጽሑፎቹ መሠረት ልጁ ሰኑስረት በሊብያ እየዘመተ አመነምሃት በሤራ እንደ ተገደለ ይታሥባል።

የነፈርቲ ትንቢት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የነፈርቲ ትንቢት በ፩ አመነምሃት ዘመን የተጻፈ ትውፊት ነው። ትውፊቱ በቀድሞ ዘመን በጥንታዊው መንግሥት 4ኛው ሥርወ መንግሥት በነገሰው በስነፈሩ ዘመን ( 2975-2963 ዓክልበ. ግድም) ስለ ኖረ «ነፈርቲ» ስለ ተባለ ቄስ የተመለከተ ነው።

ፈርዖኑ ስነፈሩ ሰልችቶት ነፈርቲ ትንቢት እንዲናገርለት አዘዘውና ንጉሡ የተናገረውን ቃል ጻፈው ይላል። ነቢዩ ለስነፈሩ፦ ወደፊት ሀገሩ አዲስ እንዲመሠረት ያስፈልጋል፤ እስከ መጨረሻውም ጥፍር ድረስ በሙሉ ይጠፋል፤ ማንም የሚጠብቃት አይተርፍምም፤ ሆኖም ወደፊት «አመኒ» የሚባል ንጉሥ ነግሦ መንግሥቱን አዲስ ይሠራዋል ብሎ ነበየለት።

የዚህ ትውፊት መንስዔ በእርግጡ ሊታወቅ ባይቻለንም ፈርዖኑ «አመነምሃት» የሚለውን የዙፋን ስም መውሰዱን ለማጽደቅ እንደ ታሠበ ይሆናል።

ቀዳሚው
4 መንቱሆተፕ
ግብፅ ፈርዖን
2002-1972 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
1 ሰኑስረት

ዋቢ መጻሕፍት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ «የአመነምሃት ትምህርት»፣ ነጥብ ስለ «ኮሩስኮ ጽላት»
  • Wolfgang Kosack: Berliner Hefte zur ägyptischen Literatur 1 - 12: Teil I. 1 - 6/ Teil II. 7 - 12 (2 Bände). Paralleltexte in Hieroglyphen mit Einführungen und Übersetzung. Heft 9: Die Lehre des Königs Amenemhet I. an seinen Sohn. Verlag Christoph Brunner, Basel 2015. ISBN 978-3-906206-11-0.