Jump to content

1 አመንሆተፕ

ከውክፔዲያ

==

አመንሆተፕ ጀሰርካሬ
ከዘመኑ የሆነ የአመንሆተፕ ምስል
ከዘመኑ የሆነ የአመንሆተፕ ምስል
የግብጽ ፈርዖን
ግዛት 1534-1513 ዓክልበ.
ቀዳሚ 1 አሕሞስ
ተከታይ 1 ቱትሞስ
ባለቤት አሕሞስ-መሪታሙን
ሥርወ-መንግሥት 18ኛው ሥርወ መንግሥት
አባት 1 አሕሞስ

==


አመንሆተፕ (ግብጽኛ፦ /የመንኸተፕ/) በጥንታዊ ግብጽግብጽ አዲስ መንግሥትና የ18ኛው ሥርወ መንግሥት ፈርዖን ሲሆን ምናልባት 1534-1513 ዓክልበ. የገዛ ነበረ።

አመንሆተፕ የቀዳሚው የ1 አሕሞስና የንግሥቱ የአሕሞስ-ነፈርታሪ ልጅ ነበር። እንደ አባቱና እንደ አያቱ ሰቀነንሬ ታዖ፣ አመንሆተፕ የገዛ እህቱን አሕሞስ መሪታሙን አገባ። ስለዚህ እነርሱ እንደ ተለመደው ስምንት ቅድማያቶች ሳይኖሯቸው፣ ሁለት ቅድማያቶች ብቻ እነርሱም ሰናኽተንሬ አሕሞስና ንግሥት ተቲሸሪ (1567 ዓክልበ. ገደማ የገዙ) ነበሩ። የአመንሆተፕ ብቸኛ ልጅ ደግሞ በአሥራ ስድስቱ ፈንታዎች እነኚህ ሁለት ብቻ ነበሩት፤ ሆኖም በሕፃንነቱ ዓረፈ።

በአመንሆተፕ ዘመን በ፱ኛው አመት የሥነ ፈለክ ሊቃውንት የውሻ ኮከብ (ሲሪዩስ) የተነሣበት ቀን ስለ ዘገቡ፣ ዘመኑ በ1534 ዓክልበ. እንደ ጀመረ ሊታወቅ ይቻላል።

የጦር አለቆቹ አሕሞስ ወልደ አባና እና አሕሞስ ፐን-ነኽበት ሁለቱ በመቃብር ጽሑፎቻቸው ውስጥ በኩሽ መንግሥት ላይ በጀሰርካሬ (አመነምሃት) ዘመን እንደ ዘመቱ ዘግበዋል። አሕሞስ ፐን-ነኽበት ደግሞ አንድ ዘመቻ በ«ኢሙ-ከኸክ» ላይ ይጠቅሳል። ይህ ሥፍራ በሊብያኖቢያ ወይም ሶርያ ውስጥ ከሆነ አይታወቅም። በተረፈ ግን አመነምሃት በሶርያ ወይም በእስያ እንደ ዘመተ የሚል ዘገባ የለም።

በሌላው ሹም መቃብር ጽሑፍ ዘንድ፣ ፈርዖኑ አመንሆተፕ (ማኔጦን በኋላ እንደ መሠከረ) ለ21 ዓመታት እንደ ነገሠ ያረጋግጣል። ተከታዩ 1 ቱትሞስ አልጋ ወራሽ ተደርጎ ነበር፤ አባቱ ማን እንደ ሆነ እርግጥኛ አይደለም። የቱትሞስ እናት ተራ ሴት ሰንሰነብ መሆኗ ይታወቃል።

በአመንሆተፕ ዕረፍት እስከ አዲሱ መንግሥት መጨረሻ ድረስ (1513-1077 ዓክልበ.) አመንሆተፕና እናቱ አሕሞስ-ነፈርታሪ እንደ አማልክት ተቆጠሩ። በተለይ የአምልኮቱ ማዕከል እሱ በመሠረተው ጣኦት ፋብሪካ መንደር በሰት መዓት (አሁን ደይር ኤል-መዲና ተብሎ) ይገኝ ነበር። ከዚህ የተነሣ ከዘመኑ በኋላ የተሠሩ አመንሆተፕን የሚያሳዩ በርካታ ሐውልቶችና ሥነ ጥበብ ታውቀዋል። ከራሱ ጊዜ የሚያሳዩት ምስሎች ግን ጥቂት ናቸው።

ቀዳሚው
1 አሕሞስ
ግብፅ ፈርዖን
1534-1513 ዓክልበ.
ተከታይ
1 ቱትሞስ