ጨረቃ
ጨረቃ (ምልክት፦) የመሬት ብቸኛዋ ሳተላይት ስትሆን በሥርዓተ-ፀሐይ ውስጥ አምስተኛ ትልቅ ሳተላይት ናት። ከመሬት መሀል እስከ ጨረቃ መሀል ድረስ ያለው አማካይ ርቀት 384,403 ኪ.ሜ. (238,857 ማይል) ያህል ነው። ይህ ርቀት ከመሬት አንድ ጫፍ እስከ ሌላኛው ተቃራኒ ጫፍ (diameter) ያለውን ርቀት ሰላሳ (30X) ይበልጣል። ሁለቱ አካላት ሥርዓታቸውን የሚጠብቁበት ማዕከላዊ ነጥብ 1,700 ኪ.ሜ. (1,100 ማይል) ማለትም የመሬትን ራዲየስ አንድ አራተኛ (1/4) ከመሬት ጠለል ዝቅ ብሎ ይገኛል። ጨረቃ በመሬት ዙሪያ በየ27.3 ቀናት አንድ ሙሉ ዙር ታጠናቅቃለች። ይህም መዞር ለጨረቃ በየ29.5 ቀናት የሞላና የጎደለ መመልክ መያዝ ዋና ምክንያት ነው። የጨረቃ ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላኛው ተቃራኒ ጫፍ (diameter) ያለው ርቀት 3,474 ኪሜ (2,159 ማይል) ሲሆን ከመሬት ተመሳሳይ አንድ አራተኛ (1/4 X የመሬት ዲያሜትር) በትንሽ ይበልጣል። የመሬትን አንድ አራተኛ ስፋት ሲኖራት ይዘቷ (volume) ግን የመሬትን ሁለት በመቶ (2%) ብቻ ነው። የጨረቃ ስበት የመሬት ስበትን አስራ ሰባት በመቶ (17%) ጋር ይነጻፀራል። ጨረቃ የሰው ልጅ ያረፈባት ብቸኛዋ የጠፈር አካል ናት።
በ2011 የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ ሳይንቲስቶች ሮቦቶችን ወደ ጨረቃ ልከው የጎመንዘር አይነት (Brassica napus)፣ የድንችና የጥጥ ዘሮችን በጨረቃ ላይ በመያያዣ ውስጥ ማብቀል እንደተቻለ አስረዱ። ወደፊት ሰዎች ወደ ጨረቃ ቢመልሱ ኖሮ፣ በነዚህ ሦስት ምርቶች፦ ጎመንዘር ለዘይት፣ ድንች ለምግብ፣ ጥጥም ለልብስ፦ እንደሚረዷቸው አሉ። እንዲሁም የድንጋይ ፌጦ (Arabidopsus spp)፣ እርሾና የፍራፍሬ ዝንብ በሙከራው ውስጥ እየታደጉ ነበር። ሆኖም ከ፫ ቀን በኋላ ናሙናዎቹ ሁሉ ከጨረቃ አየር ሙቀት የተነሣ በርደው አርፈው ነበር።
ይህች የመሬት ብቸኛ ሳተላይት በአማርኛ ጨረቃ ስትሆን በእንግሊዝኛው ደግሞ the Moon ትባላላለች። Moon የጀርመንኛ ቃል ሲሆን ከላቲን mensis እና ከጥንታዊ ግሪክ μήνας ተመሳሳይ የሆነ ወር የሚል ትርጉም አላቸው። ለቃሉ መፈጠር ከወር በተጨማሪ እንደ ሰኞ እና የወር አበባ የመሰሉ ቃላት አንድም በእንግሊዝኛው ትርጉማቸው ከቃሉ ጋር ተመሳሳይ አጀማመር በመኖሩ አልያም በሂደታቸው ርዝማኔ ከጨረቃ ጋር ስለሚገናኙ አስተዋጽዖ አላቸው።
ጨረቃ ከመሬት አንፃር ስትትታይ ግዙፍ አካል ናት። ይህም ከላይ ለማነፃፅእር እንደተሞከረው የመሬትን አንድ አራተኛ ዲያሜትር መኖሯ እና የመሬትን አንድ ሰማኒያኛ (1/80 X የመሬት ክብደት) መመዘኗ ያረጋግጣል። እህ እንግዲህ ሳተላይቷ ከባለቤት ፕላኔቷ ጋር ምን ያህል የመጠን ቅርርብ እንዳላት ያሳያል (ምንም እንኳን ቻሮን የተባለችው የፕሉቶ ሳተላይት በንፅፅር ግዙፍ ብትሆንም)።
ከላይ እንደተገለፅእው ጨረቃ በመሬት ዙሪያ አንድ ሙሉ ዙር ለመዞር 27.3 ቀናት ይፈጅባታል። ነገር ግንመሬትም ከፀሐይ አንፃር በራሷ ምህዋር በተመሳሳይ ጊዜ ስለምትጓዝ የጨረቃን ገጽታ በየ29.5 ቀናት ሲቀያየር እናየዋለን። ጨረቃ በመሬት ዙሪያ እንድትሽከረከር የሚያደርጋትን ኃይል የምታገኘው ከመሬት ስበት እና ከፀሐያዊ የስበት ሥርዓት ነው።
በጨረቃ ገፅ ላይ የወቅቶች መፈራረቅ በጥቂቱም ቢሆን ይከሰታል። ይህም ለመለየት በሚያስቸግር መልኩ የተከፋፈሉ የበጋ እና የክረምት ወቅቶችን መታዘብ ተችሏል። ለዚህም ምክንያቱ በጨረቃ እና በፀሐይ መካከል ያለው የመፋጠጫ አንግል ትንሽ ስለሆነ (1.54 ዲግሪ) ነው።
ግርዶሽ የሚፈጠረው ፀሐይ፣ መሬት እና ጨረቃ በአንድ መስመር ላይ ሲሆኑ ነው። በተለይም የጨረቃ ግርዶሽ የሚባለው የሚከሰተው ጨረቃ በመሬት እና በፀሐይ መካከል እትሆን ብቻ ነው። በተቃራኒው የመሬት ግርዶሽ የሚፈጠረው መረት በፀሐይ እና በጨረቃ መካከል ስትሆን ነው።