Jump to content

ሐለብ

ከውክፔዲያ
(ከሃላብ የተዛወረ)
ሐለብ
ﺣﻠﺐ
ክፍላገር ሐለብ ጠቅላይ ግዛት
ከፍታ 379 ሜ
የሕዝብ ብዛት
   • አጠቃላይ 1,800,000
ሐለብ is located in Syria
{{{alt}}}
ሐለብ

36°13′ ሰሜን ኬክሮስ እና 37°10′ ምሥራቅ ኬንትሮስ

ሐለብሶርያ ጥንታዊ ከተማ ነው። በብዙ አውሮፓዊ ቋንቋዎች ሐለብ «አሌፖ» በመባል ይታወቃል።

ሐለብ መጀመርያ የሚጠቀሰው በኤብላ ጽላቶች (2127-2074 ዓክልበ. ግ.) «ሐለም» ተብሎ ሲሆን ነው። በብዙ ሊቃውንት ዘንድ ለኤብላ መንግሥት ጥገኛ የሆነው የአርሚ መንግሥት መቀመጫ ነበር። የአካድ ንጉሥ ናራም-ሲን ደግሞ ኤብላ ሲያጠፋ (2038 ዓክልበ. ግድም) አርማኑምን የተባለ ሀገር ደግሞ እንዳጠፋ ዘገበ፤ የአርማኑም መታወቂያ ከአርሚም ሆነ ከሐለብ ጋራ አጠያያቂ ሆኗል።

ባቢሎን መጀመርያ መንግሥት ዘመን (ከ1807-1507 ዓክልበ.) ጀምሮ የከተማ መጠሪያ እንደ ዛሬ «ሐለብ» በመባል ታወቀ። የያምኻድ አሞራዊ መንግሥት ዋና ከተማ ሆነ፤ ይህም የኬጥያውያን መንግሥት ንጉስ 1 ሙርሲሊ በ1507 ዓክልበ ያሕል ያምኻድን እስካሸነፈው ድረስ ቀረ። ሆኖም ከያምኻድ መንግሥት ውድቀት ቀጥሎ ሐለብ እንደ ነጻ ከተማ-አገር እስከ 1480 ዓክልበ. ያህል የሚታኒ መንግሥት እስከ ያዘው ድረስ ቆየ።

በኋላ ከተማው እንደገና ለኬጥያውያን (1350 ዓክልበ. ግ.)፣ ለአሦር መንግሥት (1186 ዓክልበ) ተገዥነት ወደቀ። ምናልባት 1050-900 ዓክልበ. «ዋሊስቲን» ወይም «ፓለስቲን»፣ ከ900-750 ዓክልበ. «ቢት አጉሢ» የተባለ ነጻ መንግሥት ውስጥ ነበር። በ748 ዓክልበ. የአሦር ንጉሥ 3 ቴልጌልቴልፌልሶር ዳግመኛ ያዘው።

ከአሦር አልፎ ከተማው ለባቢሎኒያ (620 ዓክልበ.)፣ ለፋርስ አኻይመኒድ መንሥት (547 ዓክልበ.)፣ እና ለታላቁ እስክንድር (341 ዓክልበ.) ተዛወረ። ግሪኮችም የከተማውን ስም በሮያ አሉት። እስከ 96 ዓክልበ. ድረስ የሴሌውቅያ መንግሥት፣ ከዚያ እስከ 72 ዓክልበ. ድረስ የአርሜኒያ፣ ከዚያም እስከ 604 ዓም ድረስ በሮያ የሮሜ መንግሥት በኋላም የቢዛንታይን መንግሥት ከተማ ሆነ።

በ604 ዓም የፋርሳውያን ሳሳኒድ መንግሥት ለአጭር ጊዜ ከተማውን በጦርነት ያዘ። በ629 ዓም ለአረብ እስላም ኃይላት ራሺዱን ኻሊፋት ተጨመረ። በ938 ዓም ሐለብ ነጻ ኤሚራት ሆነ፣ ሆኖም ከአረቦችና ከቢዛንታይኖች መካከል እስከ 1056 ዓም ድረስ ብዙ ጊዜ ይፈራረቅ ነበር፣ ከዚያም ቢዛንታይኖችና ሠልጁክ ቱርኮች ይታግሉበት ነበር። በ1120 ዓም ሐለብ የቱርኮች ዘንጊድ ሥርወ መንግሥት ዋና ከተማ ሆነ።

ሞንጎሎች ሐለብን ለአጭር ጊዜ በ1252፣ በ1273 እና በ1392 ዓም ይዘው እያንዳንዱ ጊዜ ብዙ ኗሪዎችን በእልቂጥ ገደሉ። በ1508 ዓም ሐለብ የኦቶማን መንግሥት ክፍል ሆነ፣ አንደኛው የአለም ጦርነት እስከ ጨረሰ እስከ 1912 ዓም ድረስ የኦቶማን ከተማ ሲሆን ከዚያ ወደ ፈረንሳይ ሶርያ አስተዳደር ተጨመረ። በ1938 ዓም ከተለያዩ ፈረንሳያዊ አስተዳደሮች በኋላ የነጻ ሶርያ መንግሥት ከተማ ሆነ።

2004 እስከ 2009 ዓም ድረስ በሶርያ እርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ብዙ ጥፋት በሐለብ ላይ ተደርጎ ነበር። ሐለብ አሁን እየታደሰ ነው።