Jump to content

ሌዊ

ከውክፔዲያ
ሌዊ (ከሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምስል፣ ምናልባት 1700 ዓ.ም. አካባቢ ተሳለ።)

ሌዊ (ዕብራይስጥ፦ לֵּוִי‎ /ለዊ/) በብሉይ ኪዳን ዘንድ ከያዕቆብ ፲፪ ወንድ ልጆች አንዱ ሲሆን ከእስራኤል ፲፪ ነገዶችም የሌዋውያን አባት ነበረ።

ሌዊ ከሮቤልና ከስምዖን በኋላ የያዕቆብና የልያ ፫ኛው ልጅ ነበር፤ በፓዳን-አራም ተወለደ። በኦሪት ዘፍጥረት ፴፬፡፳፭፣ ቤተሠቡ በከነዓን ሲኖር ስምዖንና ሌዊ ስለ እኅታቸው ዲናሴኬም ባላባት ኤዊያዊው ኤሞርን አሸነፉ፣ የሴኬምን ሠፈር አጠፉ። ስለዚህ አባታቸው ያዕቆብ ገሰጻቸው (፴፬፤፴)።

የሌዊ ወንድ ልጆች ጌድሶንቀዓትሜራሪ ተባሉ፤ እነዚህ ሁሉ ወደ ጌሤም ፈለሱ። በኦሪት ዘኊልቊ ፳፮፡፶፱ ሴት ልጁን ዮካብድን ይጠቅሳል፤ እርስዋም የቀዓት ልጅ እንበረም አግብታ አሮንን፣ ማርያምንና ሙሴን ወለደች።

በያዕቆብ በረከት ኑዛዜ (ኦሪት ዘፍጥረት ፵፱፡፭-፯) ሌዊ ግን ከወንድሙ ስምዖን ጋር ይረገማል፦

«ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። በምክራቸው፣ ነፍሴ፣ አትግባ፤ ከጉባኤአቸውም ጋር፣ ክብሬ፣ አትተባበር፤ በቊጣቸው ሰውን ገድለዋልና፣ በገዛ ፈቃዳቸውም በሬን አስነክሰዋልና። ቊጣቸው ርጉም ይሁን፣ ጽኑ ነበርና፤ ኲርፍታቸውም፣ ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ አከፋፍላቸዋለሁ፣ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ።»

ኦሪት ዘጸአት ፮፡፲፮ የሌዊ ሕይወት ዘመን ፻፴፯ ዓመታት እንደ ነበር ይነግረናል። በኋላ ዘሮቹ ሌዋውያን ከከነዓን የራሳቸውን ርስት አልተቀበሉም፣ ነገር ግን የካህናት መደብ ሆነው በነገዶቹ መካከል ተበተኑ።

ሌዊ በሆላንድ በ1580 ዓ.ም. ግድም እንደ ተሳለ

በሙሴም በረከት ኑዛዜ (ኦሪት ዘዳግም ፴፫፡፰-፲፩)፣ ሙሴ ስለ ነገደ ሌዊ እንዲህ ይላል፦

«ቱሚምህና ኡሪምህ ለቅዱስህ ሰው ነው፣ በማሳህ ለፈተንኸው፣ በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፣ ስለ አባቱና ስለ እናቱ፦ አላየሁም ላለ፣ ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፣ ልጆቹንም ላላወቀ፤ ቃልህን አደረጉ፣ ቃል ኪዳንህንም ጠበቁ። ፍርድህን ለያዕቆብ፣ ሕግህንም ለእስራእል ያስተምራሉ፤ በፊትህ ዕጣንን፣ በመሥዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ይሠዋሉ። አቤቱ፣ ሀብቱን ባርክ፣ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ የሚነሣበትን ወገብ ውጋው፣ የሚጠሉትም አይነሡ።»

ትንቢተ ሚልክያስ ፪፡፬-፮፣ እግዚአብሔር ካህናቱ (ሌዋውያን) ስለ ሌዊ ጽድቅ እንደ ተመረጡ ይገልጻል፦ «ቃል ኪዳኔ ከሌዊ ጋር ይሆን ዘንድ ይህን ትእዛዝ እንደ ሰደድሁላችሁ ታውቃላችሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ቃል ኪዳኔ ከእርሱ ጋር የሕይወትና ሰላም ቃል ኪዳን ነበረ፤ ይፈራ ዘንድም እነርሱን ሰጠሁት፣ እርሱም ፈራኝ፣ ከስሜም የተነሣ ደነገጠ። የእውነት ሕግ በአፉ ውስጥ ነበረች፣ በከንፈሩም ውስጥ በደል አልተገኘበትም፣ ከእኔም ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፣ብዙ ሰዎችንም ከኃጢአት መለሰ።»

መጽሐፈ ኩፋሌ መሠረት፣ ሌዊ በ2127 ዓ.ዓ. ተወለደ። ኩፋሌ ፳፩፡፲፱ እንዲህ ይላል፦

«እነርሱም በእውነተኛነት እንደ ተቈጠሩ የሌዊም ልጅ ለክህነት እንደ ተመረጠ፣ እኛ (መላዕክት) በዘመኑ ሁሉ እንዳገለገልን፣ ሌዋውያንም በእግዚአብሔር ፊት ያገለግሉ ዘንድ እንደ ተመረጡ እይ። እውነት ነገር ይሠራ ዘንድ ፍርድንም ይፈርድ ዘንድ በእስራኤል ላይ በጠላትነት ከሚነሡ ብድራትን ይመልስ ዘንድ ቀንቶአልና ሌዊ ይክበር ልጆቹም ለዘላለም ይክበሩ።»

በዚህ መጽሐፍ ፳፪፡፲፪-፲፮፣ ያዕቆብ ሌዊን ባረከው እንጂ አልረገመውም። በ፳፪፡፴፬፣ «ሌዊም እንደ ሾሙት፣ ለልዑል አምላክም እርሱን አገልጋይ እንዳደረጉት፣ ልጆቹንም እስከ ዘላለም ድረስ አገልጋይ እንዳደረጉአቸው ሕልም አየ።» ያንጊዜ አባቱ ያዕቆብ ሌዊን ቄስ አደረገው። በኩፋሌ ፳፬፡፳፮ የሌዊ ሚስት ስም ሜልካ ተባለ፣ «ከቃራ (ወይም በሌሎቹ ቅጂዎች ታራ) ልጆች ወገን ከሚሆን ከአራም ልጆች የተወለደች»።

በኋላ ዘመን ያዕቆብ በጌሤም በምድረ ግብፅ ባረፈው ወቅት፣ የአባቶቹን መጻሕፍት ሁሉ የወረሰው ሌዊ ሆነ (ኩፍ. ፴፪፡፱)።

የሌዊ ምስክር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

«የሌዊ ምስክር» በተባለው ጽሑፍ ዘንድ፣ ሌዊ ሳይሞት የህይወቱን ታሪክ ያወራል። በዚህ መሠረት፣ ሌዊ በካራን ተወልዶ የስምንት ዓመት ልጅ ሲሆን ወደ ከነዓን ፈለሰ፤ ስለ እህቱም ዲና ሴኬምን ያጠፋው እድሜው ፲፰ ወይም ፳ ነበር፤ በ፲፱ኛው ዓመት ቄስ ተደረገ፤ በ፳፰ኛው ዓመት ሚስቱን ሜልካን አገባት፤ ጌድሶንን ወለደችለት። በሌዊ ፴፭ኛው ዓመት ቀዓትን ፤ በ፵ኛውም ዓመት ሜራሪን ወለደችለት፤ ዮካብድም በግብጽ በ፷፬ኛው ዓመት ተወለደችለት። እንበረምም ዮካብድ በተወለደች ቀን ተወለደና በሌዊ ፺፬ኛው ዓመት የእንበረም ሚስት ሆነች። በሌዊ ፻፲፰ኛው ዓመት ዮሴፍ አረፈ።

በተጨማሪ ሌዊ በዚህ መጽሐፍ ብዙ ምሳሌዎች፣ ምክሮች፣ ትንቢቶችና ራዕዮች ለልጆቹ ያስተምራቸዋል።[1]

ዮሴፍና አሰናት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

«ዮሴፍና አሰናት» የሚባል ታሪክ ስለ ዮሴፍና ግብጻዊት ሚስቱ አሰናት አንዳንድ ትውፊት አለው። በዚህም ሌዊ እንደ ነቢይና ተዋጊ ይታያል። በዚህ አፈ ታሪክ፣ የያዕቆብ ልጆች ወደ ግብጽ ገብተው ወንድማቸው ብንያም የፈርዖንን አልጋ ወራሽ ገደለው፤ ፈርዖንም ዕድሜው ፻፱ ዓመት ሲሆን አረፈና ዮሴፍ እራሱ ለ፵፰ ዓመታት የግብጽ ንጉሥ ሆነ። ያንጊዜ ዮሴፍ ዘውዱን ለፈርዖኑ ልጅ ልጅ ሰጥቶ ለእርሱ እንደ አባት ሆነ።[2] ይህ ጽሑፍ በሶርያኛስላቮንኛአርሜንኛና በሮማይስጥ ይታወቃል፤ መቼ እንደ ተቀናበረ ግን ተከራካሪ ነው።

  1. ^ http://www.newadvent.org/fathers/0801.htm
  2. ^ http://www.markgoodacre.org/aseneth/translat.htm