Jump to content

እንበረም

ከውክፔዲያ

እንበረም (ዕብራይስጥ፦ ዐምራም፣ አረብኛ፦ ዒምራን) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሙሴ፣ የአሮንና የማርያም አባት ነበረ። ኦሪት ዘጸአት ስለ እንበረም ጥቂት መረጃ ቢገኝም፣ በመጽሐፈ ኩፋሌ፣ በቁራንና እንዲሁም በሌሎች ምንጮች ተጨማሪ ልማዶች አሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ኦሪት ዘጸአትና ኦሪት ዘኊልቊ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በኦሪት ዘጸአት ፪፡፩፣ የእንበረም ስም ሳይጠቅስ እንዲህ ይለናል፦

«ሌዊ ወገን አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ። ሴቲቱም ፀነሰች፣ ወንድ ልጅም ወለደች፣ መልካምም እንደ ሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው።»

ከዚህ በኋላ ህጻኑ የግብጽኛ ስሙን «ሙሴ» ተቀበለ (ዘጸ ፪፡፲)። በኋላም በምዕራፍ ፮፡፲፮-፳፣ እንዲህ እንረዳለን፦

«የሌዊ ልጆች ስሞች ጌድሶንቀዓትሜራሪ ናቸው።... የቀዓትም ልጆች እንበረምይስዓርኬብሮንዑዝኤል ናቸው... እንበረም የእጎቱን ልጅ ዮካብድን አገባ፣ አሮንንና ሙሴንም ወለደችለት፤ የእንበረምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው።»

በዚህ የአማርኛው ትርጉም እንደ ግሪክኛው ይከተላል፤ የዕብራይስጥ ትርጉም ግን «እንበረም የአባቱን እህት ዮካብድን አገባ» ይለናል። በሳምራዊ ኦሪት ቅጂ ደግሞ «አሮንን፣ ሙሴንምና እኅታቸውን ማርያምን ወለደችለት» ይላል።

እንደገና በኦሪት ዘኊልቊ ፳፮፡፶፰-፶፱ እንዲህ እናነባለን፦ «ቀዓትም እንበረምን ወለደ። የእንበረም ሚስት ስም ዮካብድ ነበረ። እርስዋ በግብጽ ከሌዊ የተወለደች የሌዊ ልጅ ነበረች፤ ለእንበረምም አሮንንና ሙሴን እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት።»

በተለይ በዚህ ጥቅስ ዮካብድ የሌዊ ሴት ልጅ መሆንዋ ይገለጻል፤ ስለዚህ ዕብራይስጡ ትርጉም እንዳለው እንበረም አክስቱን አገባ። (ይህ አይነት ትዳር በእግዚአብሔር ትዕዛዝ የተከለከለው ከዚያ በኋላ ሙሴ ሕጉን በደብረ ሲና ሲቀበለው ነበር።[1])

መጽሐፈ ኩፋሌ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

መጽሐፈ ኩፋሌ ፴፪፡፲፯-፳፪ ስለ ሙሴ አባት እንበረም ወይም «ዕብራን» እንዲህ ይጨምራል፦

«የእስራኤል ልጆች ከዮሴፍ አፅም በቀር የያዕቆብን ልጆች አፅም ሁሉ አውጥተው በምድረ በዳ በተራራ ላይ ባለች እጥፍነት ባላት ዋሻ ቀበሩ። ብዙ ሰዎች ወደ ግብጽ ተመለሱ፣ ከእነርሱ ጥቂት ሰዎች በኬብሮን ቀሩ፤ አባትህ ዕብራንም ከእነርሱ ጋር ቀረ። ... በአርባ ሰባተኛው ኢዮቤልዩ በሰባተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት (2303 ዓ.ዓ. ወይም 1768 ዓክልበ. ግ.) አባትህ ከከነዓን መጣ፣ በአርባ ስምንተኛው ኢዮቤልዩ በአራተኛው ሱባኤ በስድስተኛው ዓመት (2330 ዓ.ዓ. ወይም 1741 ዓክልበ. ግ.) ተወለድህ፤ ይከውም በእስራኤል ልጆች ላይ መከራ የጸናበት ወራት ነው።»

ሙሴም ከተወለደ በኋላ፣ የፈርዖንን ግቢ ምንም ቢገባም፣ መጽሐፍን ያስተማረው ዕውነተኛ አባቱ ዕብራን መሆኑን ይገልጻል (፴፫፡፫)።

እስልምና[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የእስላም መምኅሮች ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለቅመው የሙሴ (ወይም ሙሳ)፣ የአሮን (ወይም ሃሩን) እና የማርያም (ሜሪያም) አባት ስም እንበራም (ኢምራን) ይሉታል። ነገር ግን በቁርዓን ምዕራፍ ሱራ ፫ «የኢምራን ቤተሠብ ሱራ» መሠረት፣ የድንግል ማርያም (ወይም መርየም) አባት ደግሞ «ዒምራን» ተባለ። (በክርስትና ልማድ የድንግል ማርያም አባት ኢያቄም ተባለ፤ አዲስ ኪዳን ግን ስለ ስሙ ዝም ይላል።)

አይሁድና[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አይሁድ ረቢዎች መጻሕፍት ስለ እንበረም (ዐምራም) ተጨማሪ ትውፊቶች አሉባቸው። «የጸአት ራባህ» በሚባለው ዘንድ፣ ፈርዖን የዕብራውያን ወንድ ሕጻናት እንዲገደሉ ባዘዘው ጊዜ፣ ዮካብድ በሙሴ ፫ ወር እርጉዝ ሁና፣ ዐምራም ሚስቱን ከትዳር ፈታት፤ ልጆቼስ ቢገደሉ አባት መሆን ምንም አይረባም ብሎ። ሴት ልጁ ማርያም ግን ወቀሰችውና ዳግመኛ እናቷን እንዲያግባት አሳመነችው ይባላል።

ተልሙድ ዘንድ ደግሞ፣ ዐምራም በረጅም እድሜው ላይ የትዳርና የመፍታት ሕግጋት በእብራውያን መካከል በግብጽ ምድር አሳወቃቸው። በዕድሜው ልክ መቸም ሀጢአት ስላልሠራ፣ ባረፈው ጊዜ ሬሳው ምንም አልበሰበሰም ይላሉ ረቢዎቹም፤ ከዐምራምም በስተቀር ብንያምእሤይዶሎሕያ ብቻ ያለ ሀጢአት እንደ ሞቱ ይላሉ።

ሌላ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

«የ፲፪ አበው ምስክሮች» ከሚባሉት መጻሕፍት መካከል አንዱ «የሌዊ ምስክር» ይባላል። በዚህ የያዕቆብ ልጅ ሌዊ የሕይወቱን ታሪክ ሲያወራ እንዲህ ተጽፏል፦

«ዮካብድም በኔ ፷፬ኛው ዓመት በግብጽ ተወለደች፣ ... በኔም ፺፬ናው ዓመት አምብራም (እንበረም) ልጄን ዮካብድን እንደ ሚስቱ ወሰዳት፣ እነርሱም በአንድ ቀን ተወለዱ፣ እርሱና ሴት ልጄ።»[2]

ቁምራን ጥቅል ብራናዎች መካከል አንዱ (4Q535B) በእንበረም እራሱ እንደ ተጻፈ ስለሚለን «የእንበረም ምስክር» ተብሏል። በዚህ መሠረት እንበረም የሚካኤልና የቤሊያል (የዲያብሎስ) ራዕይ አለመ፤ እነዚህ ሁለት «ትጉሃን» መናፍስት፣ አንዱ መልካም ሌላውም ክፉ፣ በሰው ልጆች ላይ ይገዛሉ በሕልሙ ተባለ። በዚሁ ብራና መግቢያ ዘንድ፣ የእንበረም ዕድሜ እስከ 166 ዓመታት ደረሰ፣ ይህም ወደ ግብጽ ከገቡ 152 ዓመታት ነበር ይላል።

  1. ^ ዘሌዋውያን ፲፰፡፩፪።
  2. ^ http://www.newadvent.org/fathers/0801.htm