Jump to content

ናጋር

ከውክፔዲያ

ናጋር (አካድኛ፤ በኋላ ሁርኛ ናዋር፣ አሁንም አረብኛ ተል ብራክ) በጥንት ከቅድመ-ታሪክ ጀምሮ በስሜን መስጴጦምያ (አሁን ሶርያ) የተገኘ ከተማ ነበር።

በብዙ ሥነ ቅርስ ሊቃውንት ዘንድ የቦታው ቅድመ-ታሪክ እስከ 5000 ዓክልበ. ድረስ ይዘረጋል። መመሠረቱ ከተጻፉ መዝገቦች አስቀድሞ ስለ ሆነ ይህን ያህል ዘመን ሁሉ ማረጋገጥ አጠያያቂ ነው። የጽሕፈት (ኩነይፎርም) ጥቅም በዙሪያው የገባው ምናልባት 2150 ዓክልበ. (ኡልትራ አጭር አቆጣጠር) በመሆኑ፣ ይህ ቅድመ-ታሪካዊ ዘመን ከ2500 እስከ 2150 ዓክልበ. ድረስ መቆየቱ ይቻላል።

የቅድመ-ታሪካዊ ዘመን ቤተ መቅደስ ጣኦታት

የሠፈሩ መጀምርያ ኗሪዎች «ሃላፍ ባሕል» ተብለዋል፤ ይህም በሸክላ የተሠሩት የዕቃዎች አይነት ይወስናል። ከዚያ ባኋላ «ኡባይድ ባህል» የሚሉት፣ ይህም ከደቡቡ ከኤሪዱ የተስፋፋ የተጌጠ ሸክላ ዕቃ አይነት ቄንጥ ነበር።

የጽሕፈት ጥቅም ሲገባ፣ የከተማው ስም «ናጋር» ነው፤ ቦታው ከጎረቤቶቹ ከኤብላና ከማሪ ጽላቶች ይጠቀሳል። የናጋር ንጉሦች ብዙ ጊዜ በማዕረጋቸው «ኤን» (ገዥ) ብቻ ይታወቃሉ። የአንዱ የናጋር ንጉሥ ስም «አማር-አን» በማሪ ጽላቶች ተገነ፣ ይህም ምናልባት በኤብላ ጽላቶች የተገኘው ስም የናጋር ንጉስ «ማራ-ኢል» አንድላይ ነው።

የናጋር ግዛት ከኤብላና ከማሪ መካከል፤ 2109 ዓክልበ. ግድም

በ2100 ዓክልበ. ግድም በኤብላ ሚኒስትር እብሪዩም ፯ኛው ዓመት ማሪ ናጋርን ያዘ። በኋላ የኤብላ ንጉሥ ኢሻር-ዳሙ ከናጋርና ከኪሽ ጋራ በማሪ ላይ ተባበረ፤ በ2077 ዓክልበ. ግድም እነርሱ ማሪን በተርቃ ውግያ አሸነፉት። ከዚያ በኋላ ከኤብላ ያመጸውን ከተማ አርሚን መቱ። በ2074 ዓክልበ. ግን የአካድ ንጉሥ ታላቁ ሳርጎን እብላንም ናጋርንም አጠፋቸው።

«የናራም-ሲን (የአካዳውያን) ቤተ መንግሥት»

አካዳውያን ናጋርን ዳግመኛ ሠርተውት ያንጊዜ ሑራውያን ኗሪዎች ከኡርከሽ ይገቡ ጀመር። እነርሱ የከተማውን ስም ናዋር አሉት። የኡርከሽ ንጉሥ አታል-ሸን ደግሞ እራሱን «የናዋር» ንጉሥ ይል ጀመር። አካዳውያን ግን በናራም-ሲን ዘመን ናጋርን ሁለተኛ ያዙት። «የናራም-ሲን ቤተ መንግሥት» የሚባል ፍርስራሽ ከዚህ ዘመን የተገነባ ነበር። ከሻርካሊሻሪ ዘመን መጨረሻ (2013 ዓክልበ. ግ.) የአካድ መንግሥት ደክሞ ናዋር እንደገና ኗሪ ሑራዊ ንጉሥ ታልፑስ-አቲሊ ነበረው። ይህ የሑራውያን ግዛት እስከ ማሪ ንጉሥ ያኽዱን-ሊም ዘመን (1720 ዓክልበ. ግድም) ቆየ፣ ከዚያው ናዋር ወደ ማሪና በታራ ከማሪ ወደ አሦር (የ1 ሻምሺ-አዳድ) መንግሥት ተሳለፈ።

የሚታኒ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ

ናዋር በኋላ በሚታኒ መንግሥት ዘመን የሚታኒ ከተማ ሆነ። ከዚህ ዘመን ደግሞ የሚታኒ ቤተ መንግሥት ተገኝቷል። አሦራውያን በ1275 ዓክልበ. ናዋርን አጥፈው ከዚያ በኋላ አልተሠራም፣ እስካሁንም ድረስ ፍርስራሽ አለ።