Jump to content

ውክፔዲያ:ከቁርሾ ወደ ሥርየት

ከውክፔዲያ


ሰሞኑን በሀገራችን ታሪክ እምብዛም ከማይዘወተሩ ነገሮች አንዱ ተፈጽሟል። በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ከእርሱ በፊት ለነበረ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ምሕረት አድርጓል።

ሆ ብዬ እመጣለሁ ሆ ብዬ በድል መግደል ያባቴ ነው ጠላቴን ማደን

እያለ ባደገ ማኅበረሰብ ውስጥ ጠላትን ገድሎ በመቃብሩ ላይ ቤተ መንግሥት መሥራት አስደናቂ አይደለም። ዝሆን መግደል፣ አንበሳ መግደል፣ ነብር መግደል እንጂ አንበሳ ማርባት፣ ዝሆን ማርባት እና ነብር ማርባት እንዲህ ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ አልተለመዱም። እናም ነገ ልጆቻችን አንበሳ እና ነበር ለማየት ወደ አውሮፓ ፓርኮች መጓዝ ሳይኖርባቸው አይቀርም።

ልጅ ኢያሱዐፄ ምኒሊክን ቀብር በድብቅ ይሁን አሉ። ፍትሐት እንዳይደረግ ዐወጁ። በይፋ እንዳይለቀስ ከለከሉ። ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ኢያሱን ገድለው የት እንዳደረጓቸው ሳይታወቅ ቀረ። ባለወልድ ቤተ ክርሰቲያን ቆመው ማንንም ሳይፈሩ ይናገሩ የነበሩት አባ ጉኒና «ኢያሱን እንደጣልክ አንተም ትጣላለህ» እንዳሏቸው ዐፄ ኃይለ ሥላሴም በሰው እጅ ታንቀው እንደ ውሻ ተጥለው ቀሩ።

ደርግም በተራው በዐፄ ኃይለ ሥላሴ መቃብር ላይ ቤተ መንግሥት ገንብቶ ተቀመጠ። አሥራ ሰባቱ ዓመት ሲያልፍ ደግሞ ኢሕአዴግ ገባና የደርግ ባለ ሥልጣናት ወደ ከርቸሌ ወርደው እነሆ ሃያኛ ዓመታቸውን ሊደፍኑ ነው።

ማንበርከክ፣ መማረክ፣ መግደል፣ መምታት፣ መረሸን፣ ማሠር፣ መቅበር በታሪካችን ውስጥ ጉልሕ ሥፍራ ይዘው የኖሩ ናቸው። እንኳን ያለፉትን መንግሥታት ቀርቶ ከወንድሞቹ መካከል አንዱ ሲነግሥ ሌሎቹን ወኅኒ አስገብቶ መቆለፍ በየዜና መዋዕሎቻችን ሞልቶ የተረፈ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ከመንግሥታት ወደ መንግሥታት የሚደረገው የታሪክ ሽግግራችን ድልድዩ ያላማረ ከመሆኑ የተነሣ በወግ ለመተረክ እንኳን የሚከብድበት ጊዜ አለ። እንኳን በዓለማዊው ታሪካችን ቀርቶ በመንፈሳዊው ታሪካችን እንኳን በግልጽ የማናውቃቸው የመሻገርያ ዘመናት አሉ። ከአቡነ ቴዎፍሎስ ወደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሽግግር የተደረገው እንዴት ነበር? ከአቡነ መርቆሬዎስ ወደ አቡነ ጳውሎስስ? ድንብዝብዝ ያለ ድልድይ ነው የሚታየው።

ትልቁ ራስ ዓሊ በጎንደር ሲገዙ። ከትግራዩ ደጃች ውቤ ጋር ይቀናቀኑ ነበር ይባላል። ታድያ አንድ ጊዜ ደጃዝማች ክተት ሠራዊት ብለው ወደ ደብረ ታቦር ይመጣሉ። በውጊያ ላይ የራስ ዓሊ ጦር እንደ መሸነፍ ሲል ጊዜ ራስ ዓሊ ጠፍተው ወሎ ገብተው ይደበቃሉ። ደጃች ውቤም ደብረ ታቦር ገብተው አዳራሽ ውስጥ ድግስ እያበሉ እያለ አንድ የተናደደ የራስ ዓሊ የጦር ሰው ያለውን ጦር አስተባብሮ አዳራሹን ይከብና ደጃች ውቤን ይማርካቸዋል።

ታድያ በኋላ ያ የራስ ዓ ባለሟል ግዳይ ሊጥል ጌታውን ቢፈልግ ቢፈልግ ያጣቸዋል። በመጨረሻ ራስ ዓሊ ከወሎ ተፈልገው ይመጣሉ። ነገሩም በዕርቅ ያልቃል።

ሰንበትበት ብሎ አንድ የደብረ ታቦር ሰውና አንድ የጎጃም ሰው መንገድ ላይ ይገናኙና ይህንኑ ጉዳይ ያነሣሉ። ጎጃሜው ጎንደሬውን

«አንተ የራስ ዓሊና የደጃች ውቤ ነገር እንዴት ሆነ» ይለዋል፡፡

«ራስ ዓሊም ተሸንፈው ሸሹ፤ ደጃች ውቤም ተማረኩ» ይለዋል ጎንደሬው፡፡

ጎጃሜውም ይገረምና «ኧረ እባክህ እስኪ በወግ በወግ አድርገህ ንገረኝ» ይለዋል፡፡

«ሆ፣ እነርሱ ራሳቸው በወግ በወግ ያልሆኑትን እኔ እንዴት አድርጌ በወግ ልንገርህ» አለው ይባላል፡፡ ሲል የዐፄ ቴዎድሮስ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ይተርካል፡፡

እንዲህ እንደ ራስ ዓሊ እና እንደ ደጃች ውቤ ጦርነት በወግ በወጉ ሆነው ያላለቁ፤ ለተራኪም ወግ የሌላቸው አያሌ የዘመን ምዕራፎች አሉን፡፡ ምን ተደርጎ ነበር? ማን ምን አደረገ? ለምን እንደዚያ ተደረገ? ጥፋተኛው ማን ነበር? ከዚያስ ምን እንማራለን? እንዳይደገም ምን እናድርግ? ሳንባባል ምዕራፎቹ ስለሚዘጉ በተመሳሳይ የስሕተት አዙሪት ውስጥ ደጋግመን እንወድቃለን፡፡ የምኒሊክን ዘመን ብንወቅስም የምኒሊክን ስሕተት እንደግማለን፡፡ የዐፄ ኃይለ ሥላሴን ጥፋት ብናማርርም የዐፄ ኃይለ ሥላሴን ጥፋት በእጥፍ እንደግማለን፡፡ የደርግን ወንጀል ብንኮንንም የደርግን ወንጀል እንደግመዋለንለን፡፡ ለምን? ያለፈውን አጥርቶ በማየት፤ በመፈተሽ እና በማረም ለአሁኑ ስለማንነሳ፡፡ ማዳፈን እንጂ መተንተን፤ መቅበር እንጂ መግለጥ፤ ማሠር እና መግደል እንጂ ማረም ስለማንችልበት፡፡

ለቀድሞ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ምሕረት መደረግ ያለበት ንጹሐን ስለሆኑ አይደለም፡፡ በዚያ ዘመን የተሠራው ጥፋትም ለሀገሪቱ የሚጠቅማት ስለሆነም አይደለም፡፡ በወቅቱ የመከራው ገፈት ቀማሽ የሆኑት ወገኖቻችን ቁስላቸው ቁስላችን፤ ሕመማቸውም ሕመማችን ስላልሆነም አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቱ የወሰነው ውሳኔ ትክክል ስላልሆነም አይደለም፡፡ የነዚያ መከራው የተፈጸመባቸውን ወገኖች ዕንባ፣ ኡኡታ እና ሰቆቃ ከንቱ ለማድረግም አይደለም፡፡ ፈጽሞ፤ ኧረ ፈጽሞ፡፡ ነገሩ ሌላ ነው፡፡

ይህቺ ሀገር አዲስ የታሪክ መዝጊያ ያስፈልጋታል፡፡ እስካሁን ታሪኳን በማሠር፣ በመግደል እና በማሰደድ ዘግታለች፡፡ የዚህ ውጤቱ ደግሞ ቁርሾ እና ቂም መሆኑን እኛው ለእኛው ምስክር ነን፡፡ አሁን ግን አዲስ የታሪክ መዝጊያ ገጽ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ይቅርታ፡፡ ከስድሳ ስድስት በኋላ የተፈጠረው ታሪካችን መገዳደል፣ መተላለቅ፣ መረሻሸን፣ ቀይ እና ነጭ ሽብር፣ ስደት እና እንግልት፤ እሥር እና ግርፋት የሞላው ነው፡፡ የዚያ ታሪክ አንዱ ምእራፍ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ ተጠናቀቀ፡፡ ነገር ግን የታሪኩ መጽሐፍ የመጨረሻ ገጹን አላገኘም፡፡ የዚያ ታሪክ የመጨረሻ ገጽ ሦስት አማራጮች ነበሩት፡፡ በመግደል፣ በማሠር፣ በይቅርታ፡፡

ኢሕአዴግ የደርግን ባለ ሥልጣናት ሰብስቦ ደርግ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ እና በባለ ሥልጣናቱ ላይ የወሰደውን ርምጃ አልወሰደባቸውም፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም ይህ ያስመሰግናል፡፡ የፍርዱ ሂደት ቢረዝምም ቢያንስ ፍርድ ቤት የሚባለውን ወግ እንዲያዩ አድርጓል፡፡ የፍርዱ ውሳኔም እሥር እና ሞትን አምጥቷል፡፡

በዚህም ምክንያት የተወሰኑት እድሜ ልክ፣ ሌሎች የተወሰኑ ዓመታት፣ ጥቂቶቹ ደግሞ ሞት ተፈረደባቸው፡፡ ይህ ሁኔታ የዚያ ዘመን ታሪክ በእሥር እና በሞት እንዲጠናቀቅ ሊያደርግ ነበር፡፡ የታሪኩ የመጨረሻ ገጽ ከቀድሞ ታሪካችን የተለየ አልነበረም፡፡ ምንም ፍርድ እና ውሳኔ ቢኖረው ፍጻሜው ግን ሞት ሆነ፡፡ «አዘለም አንጠለጠለ ያው ተሸከመ ነው» አይደል የሚባለው፡፡

ይህ ሁኔታ ሰዎቹን ያሸንፍ ይሆናል፤ ለዘመናት የተቆራኘንን አስተሳሰብ ግን አላሸነፈም፡፡ አሁንም ከመግደል እና ከማሠር አልወጣንምና፡፡ እነዚህ ሰዎች የሞት ቅጣቱ ተፈጽሞባቸው ይቀበራሉ፤ ወይንም የእሥር ጊዜያቸውን ጨርሰው ይወጣሉ፡፡ የሄድንበት የአስተሳሰብ ቁራኝነት ግን ከእኛው ጋር ይኖራል፡፡

አሁን ግን መንግሥት ምሕረት አደረገ፡፡ እናም ያ አሳዛኝ ታሪካችን አስደሳች አፈጻጸም ገጠመው፡፡ የዚያ ታሪክ የመጨረሻው ገጽ ተቀየረ፡፡ ያቺ ገጽ «ምሕረት» ትላለች፡፡ ለትውልዱ አስደናቂ የሚሆነውም መጽሐፉ በዚህ መልኩ ሲጠናቀቅ ነበር፡፡ የነገው ትውልድ ያንን የሰቆቃ እና የመከራ ታሪክ ሲያነብብ ቆይቶ በመጽሐፉ የመጨረሻ ገጽ ሲደርስ «ይህ ትውልድ ግን ከእነርሱ የበለጠ የሞራል እና የአስተሳሰብ ልዕልና ስላለው ይቅርታ አደረገላቸው» ከሚለው ላይ ይደርሳል፡፡ ያን ጊዜ ልቡ በሐሴት ይሞላል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ድል ምንድን ነው? ብለን እንድንጠይቅም ያደርገናል፡፡ እውነተኛ ድል ችግሩን ያመነጨውን ሥር መንቀል እንጂ ጉቶውን እየተው ቅርንጫፎቹን መመልመል አይደለም፡፡ ያ ሁሉ መጨፋጨፍ እና መገዳደል ለምን መጣ? ለምን አንድ ትውልድ አለቀ? ለምንስ የሀገሪቱ ልጆች እርስ በእርሳቸው ተገዳደሉ? በዓለም ላይ ከታዩት የሰቆቃ ዓይነቶች ሁሉም ለምን እኛ ሀገር ተፈጸሙ? ምክንያቱ አንድ ነው፡፡ ከጭካኔ ያለፈ የችግር መፍቻ መንገድ በማይታያቸው አካላት ምክንያት፡፡ ከመግደል ከማሠር እና ከማሰቃየት ውጭ ምንም ዓይነት የብርሃን መንገድ በማይታያቸው ሰዎች የተነሣ፡፡

እነዚህ አካላት ምን ያውቃሉ? መግደል፡፡ ምን ይረዳሉ? ማሠር፡፡ ምን ሠልጥነዋል? ሰቆቃ፡፡ ምን ተክነዋል? ግርፋት፡፡ ምን ዜማ ይወድዳሉ? ግደል ግደል አለኝ፡፡ ታድያ እነርሱ የሚያውቁትን እና የሠለጠኑበትን ነገር መልሶ በእነርሱው ላይ መፈጸም እንዴት ድል ሊሆን ይችላል? ሽንፈት እንጂ፡፡ ንፉግን በመንፈግ ሥጋውን እንጂ ኅሊናውን አናሸንፈውም፡፡ ገዳይን በመግደል ሥጋውን እንጂ ኅሊናውን አናሸንፈውም፡፡ ንፉግን በመለገሥ፣ ገዳይንም በማኖር ግን ኅሊናውን መርታት ይቻላል፡፡

በዘመነ መሳፍንት ጎንደር ጭልጋ ውስጥ ሁለት ባላባቶች ይጋጫሉ፡፡ አንደኛው በንዴት የአንደኛውን ልጅ ይገድልና ይሸፍታል፡፡ ያኛውም ዘመድ ወዳጁን አሰልፎ በረሃ ለበረሃ ሽፍታውን ያድናል፡፡ በመጨረሻ አንዲት ወዳጁ ቤት ማታ ማታ ብቅ እንደሚል ይደረስበትና እዚያው ከወዳጁ ጋር እንደ ተኛ ሽፍታው ይያዛል፡፡

ልጁ የተገደለበት ባላባት ገበያ መሐል ያመጣውና ገዳዩን በሰባት ጥይት ደብድቦ ይገድለዋል፡፡

ታድያ ይህንን ያየ ጎንደሬ እንዲህ ብሎ ዘፈነ ይባላል

ጌቶችን ከጌቶች ያስበልጧል ወይ ይህም ነፍሰ ገዳይ ያም ነፍሰ ገዳይ

ከማንኛውም ዓይነት ልዕልና የመንፈስ ልዕልና ይበልጣል፡፡ የመንፈስ ልዕልና ላቅ ያለ ልዕልና ነው፡፡ ይህ ልዕልና ደግሞ ጠላትን በማያውቀው ስልት በማሸነፍ የሚገኝ ልዕልና ነው፡፡ ሌባን በመስጠት፤ ለፍላፊን በዝምታ፤ ንፉግን በልግሥና፤ ክፉን በደግ፤ ጨለማን በብርሃን፤ ጭካኔን በርኅራኄ፤ ክፋትን በደግነት፡፡ አምባገነንነትን በዴሞክራሲ፤ ፍርደ ገምድልነትን በፍትሕ፤ ንቀትን በክብር ማሸነፍ ማለት ነው፡፡

በእኛው ታሪክ ውስጥ በዚያ ዘመን ተጠያቂ የነበሩት ሰዎች እነርሱ ያለ ፍርድ ቢገድሉም እነርሱ ግን ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ይህ ድል ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ እነርሱ ሰዎችን ያለ ኃጢአታቸው ቢረሽኑም ለእነርሱ ግን ምሕረት ተደርጎላቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የማያውቁት አዲስ ትምህርት ነው፡፡ ምናልባት ይህ ምሕረት አካላቸውን ከወኅኒ ነጻ ያደርገው ይሆናል፡፡ ኅሊናቸውን ግን ከባድ ቅጣት ይቀጣዋል፡፡ ይቅርታ ምሕረት ብቻ አይደለም ቅጣትም ነው፡፡

ሟቹ የሮም ፖፕ ዳግማዊ ጆን ፖል የመግደል ሙከራ ያደረገባቸውን ሰው እሥር ቤት ድረስ ሄደው «ይቅር ብዬሃለሁ» ሲሉት

«አሁን ገና ቀጡኝ» ነበር ያላቸው፡፡ የእርሳቸው ደግነት ኃጢአቱን ይበልጥ አጎላበት፡፡ የርሳቸው ብርሃንነት ጨለማነቱን አጋለጠው፡፡ የርሳቸው ደግነት ጭካኔውን ዕርቃኑን አስቀረበት፡፡

ይቅር ማለታችን ከእነርሱ በላይ የሚጠቅመው እኛን ነው፡፡ በየትኛውም እምነት ከይቅርታ ጠያቂ ይልቅ ይቅር ባይ ሰማያዊ ዋጋ አለው፡፡ በድሎ ይቅርታ ከመጠየቅ በላይ ተበድሎ ይቅር ማለት ፈጣሪን መምሰል ነው፡፡

ይቅር ባዮች ለዚህች ሀገር ታሪክ ሥርየት እየሰጡት ነው፡፡ በዚህች ሀገር ታሪክ ውስጥ ሥርየት የሚያስፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡

«ለዘኃለፈ ሥርየት ወለዘይመጽእ ዕቅበት» ይላሉ ካህናቱ፡፡ ላለፈው ሥርየት ለሚመጣው መጠበቅ ማለት ነው፡፡ ለሚመጣው መጠበቅ የሚቻለው ግን አስቀድሞ ላለፈው ሥርየት ሲኖር ነው፡፡ እናም እናንተ ይቅር ባይ ቤተሰቦች ሆይ፤ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ ለዚህች ሀገር የቁርሾ ታሪክ ሥርየት አስገኝታችኋልና፡፡ እናንተ ይቅር ባይ ቤተሰቦች ሆይ ጀግኖች ናችሁ፤ የዚህችን አገር የደም ታሪክ በይቅርታ አድሳችሁላታልና፡፡ ክብር ለእናንተ ይሁን፡፡

ለእሥረኞቹ እኮ ኢትዮጵያ ተለውጣለች፡፡ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ቀበሌ ነበረ አሁን የለም፡፡ ቀጣና ነበረ፡፡ አሁን የለም፡፡ ኢሠፓ ነበረ፡፡ አሁን የለም፡፡ አራት ኪሎ ተቀይሯል፡፡ ልደታ ተቀይሯል፡፡ መንገዶቹ ተቀይረዋል፡፡ ልጆቻቸው ወይ አድገዋል፤ ወይ አርጅተዋል፡፡ ትዳራቸው ተናግቷል፡፡ የመኖርያ ዐቅማቸው ተዳክሟል፡፡ እድሜያቸው አርጅቷል፡፡

ኮንዶሚኒየም፡፡ ቀለበት መንገድ፡፡ ፎረም፡፡ አነስተኛ እና ጥቃቅን፡፡ ሞባይል፡፡ ዲኤስ ቲቪ፤ ዓረብ ሳት፤ ክልል፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ የግል ጋዜጣ፤ ኤፍ ኤም ሬዲዮ፤ የዘጠና ብር ሥጋ፤ የሰባ ብር ዘይት፤ የሃያ ብር ሽንኩርት፤ የስምንት ብር ለስላሳ፤ የአሥራ ሁለት ብር ቢራ፤ ኢሕአዴግ እና ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ይህ ሁሉ እነርሱ ከታሠሩ በኋላ የመጣ ነው፡፡

የእሥር ቤቱን ኑሮማ ቢያንስ ላለፉት ሃያ ዓመታት ስለኖሩበት ለምደውት ይሆናል፡፡ ለእነርሱ እንግዳ የሚሆነውኮ የውጭው ዓለም ነው፡፡ እናም እኛ ይቅር በማለታችን የምናገኘውን ርካታ እና የሞራል ልዕልና ያህል እነርሱ አያገኙም፡፡ እኛ ይቅር በማለታችን ለትውልድ የምናተርፈውን የሞቀ የሥርየት ታሪክ ያህል እነርሱ ከእሥር ሲወጡ የሞቀ ኑሮ አያገኙም፡፡

ይልቅስ እነዚህ ሰዎች በቀረችው እድሜያቸው ቢነግሩን፤ ቢያስተምሩን፡፡ ለምን እንደዚያ ተደረገ? ዛሬ ሲያስቡት ምን ይሰማቸዋል? ያልሰማናቸው እና የማናውቃቸው ምሥጢሮች አሉ፡፡ ቢነግሩን፡፡ እንደ በዓሉ ግርማ ያሉ ሰዎች ጠፍተው ቀርተዋል፡፡ መረጃ ቢሰጡን፡፡ ይኼው ትልቁን መረጃ የያዙት ሰው ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ምንም ሳይነግሩን ሞት ቀደማቸው፡፡ ስንት ነገር እንፈልግ ነበር ከእርሳቸው፡፡

እስኪ አንድ ዕድል እንስጣቸው፡፡ ታሪካቸውን እንዲነግሩን ወይንም እንዲጽፉት፡፡ እስኪ ነጻነት እንስጣቸውና ያልሰማናቸውን ያሰሙን፡፡ ምናልባት እነርሱ ሲለዩን ቆፍረን የማናወጣቸው አያሌ የዚህች ሀገር ምሥጢሮች ሊጠፉ ይችላሉ፡፡ የዘመናት ክፍተት ይፈጠራል፡፡ ከራሱ ከፈረሱ አፍ መስማትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ አሁን ለማውጣት ቢከብዳቸው እንኳን ጽፈው ይተውልን፤ ወይንም ቀድተው ያቆዩልን፡፡ ሙት አይወቀስ በምንልበት ጊዜ ያን ጊዜ እናገኘዋለን፡፡

እነዚህ ሰዎች ከእሥር ወጥተው በአዳዲሶቹ ጎዳናዎች ያለ ሥጋት ሲሄዱ ካየን እውነትም የኢትዮጵያ ታሪክ ተቀይሯል እንላለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ሳይሞቱ ካልዲስ ሻሂ ሲጠጡ፤ ቤሎስ ኬክ ሲበሉ፡፡ ገደል ግቡ ጠጅ ቤት ብርሌ ሲይዙ፤ ባምቢስ ዕቃ ሲገዙ፤ ፒያሳ ሲዝናኑ፤ በግል ሆስፒታል ካርድ አውጥተው ሲታከሙ፤ ልቅሶ ሲደርሱ እና ሠርግ ሲታደሙ ካየን እውነትም ይህቺ ሀገር አዲስ ምእራፍ ጀምራለች እንላለን፡፡

ያም ምእራፍ እንዲህ ይላል «ከቁርሾ ወደ ሥርየት፤ ከመግደል ወደ ይቅርታ»

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ነገር መጽሔት ላይ የወጣ ነው