የብርሃን ልጆች ጦርነት በጨለማ ልጆች ላይ
Appearance
«የብርሃን ልጆች ጦርነት በጨለማ ልጆች ላይ» በቁምራን ዋሻ ከተገኙት ከሙት ባሕር ብራናዎች አንዱ ነው።
ምናልባት ከ165 ዓክልበ እና 40 ዓ.ም. መካከል ጽሕፈቱን የጻፈው ንቅናቄ አባላት ስለ መጨረሻው ዘመን ጦርነት የሠልፍ ትዕዛዙን እንደሚስጥ ያምኑ ነበር።
በመጀመርያ ክፍል፣ የብርሃን ልጆች ከነ ሌዊ፣ ይሁዳና ብንያም ወገኖች በኤዶም፣ ሞዓብ፣ አሞንና በአሦር ኪቲም ላይ ጦርነት ያደርጋሉ። ከዚያ በኋላ በግብጽ ኪቲም ላይ ጦርነት ያደርጋሉ።
በዚህ ጽሑፍ ጦርነቱ ፴፭ ዓመታት እንደሚፈጅ ይነበያል። መጀመርያ ፮ ዓመታት መሠለፍ ነው። በተረፉት ፳፱ ዓመታት የውግያ ተራ እንዲህ ይገለጻል፦
- ፩ኛው ዓመት - መስጴጦምያ
- ፪ኛው - ልድያ
- ፫ኛው - ሶርያ ወይም ዑፅ፣ ሁል፣ ጌቴርና ሞሶሕ
- ፬ኛው-፭ኛው - አርፋክስድ
- ፮ኛው-፯ኛው - አሦር፣ ፋርስ፣ ምሥራቅ ሁሉ እስከ ታላቅ በረሃ ድረስ
- ፰ኛው - ኤላም
- ፱ኛው - የእስማኤል የኬጡራ ልጆች
- ፲ኛው-፲፱ኛው - የካም ልጆች
- ፳ኛው-፳፱ኛው - የ[...] ልጆች (ያፌት?)
ከዚያ በኋላ በብርሃን ልጆች ጦርነት ዕቃ ላይ የሚጻፉት መፋክሮች ይዘረዝራል፦
- በመላው ማህበር መለከቶች ላይ፦ «የእግዚአብሔር ተባባሪዎች» ይጽፉ።
- በመኳንንት ማህበር መለከቶች ላይ፦ «የእግዚአብሔር መሳፍንት»
- በመጠሪያ መለከቶች ላይ፦ «የእግዚአብሔር ማዕረግ»
- በሹማምንት መለከቶች ላይ፦ «የማህበር ቤተሠብ አለቆች»
- በጠቅላላ ጉባኤ ሲሰበሰቡ፦ «የእግዚአብሔር ድንጋጌዎች ለተቀደሰው ጉባኤ» ይጽፉ።
- በሠፈሮቹ መለከቶች ላይ፦ «የእግዚአብሔር ሰላም በቅዱሳኑ ሠፈሮች ይሁን።»
- በግስጋሴ መለከቶች ላይ፦ «የእግዚአብሔር ኃይል ጠላቱን ሊበትነውና ጽድቅን የጠሉትን ሁሉ ሊያባርራቸው ይችላል። እግዚአብሔርም የወዳጆቹን ታማኝነት ይሸልማል፣ የጠላቶቹን ቂም ግን ይመልሳል።»
- በውግያ ሠልፍ መለከቶች ላይ፦ «የተሠለፉት የእግዚአብሔር ጭፍሮች የመዓቱን ቂም በጨለማ ልጆች ላይ መብቀል ይችላሉ።»
- በእግረኞች መለከቶች ላይ፣ ወደ ጠላቶች ሠልፍ እንዲሄዱ የጦርነት በሮች ሲከፈቱ፦ «በእግዚአብሔር ዘመን ስለሚበቀለው ቂም ማስታወሻ ነው።»
- በግድያ መለከቶች ላይ፦ «በውግያ የእግዚአብሔር ከሃሊነት ጉልበት ከሀዲዎቹን ሁሉ እንደ ሙታን ሊያዋርዳቸው ይችላል።»
- በደፈጣ መለከቶች ላይ፦ «የእግዚአብሔር ድብቅ ምስጢራት ክፋትን ለማጥፋት ይችላሉ።»
- በፍለጋ መከታተል መለከቶች ላይ፦ «እግዚአብሔር የጨለማ ልጆችን ሁሉ መቷል። እስከሚፈጃቸው ድረስ መዓቱን አይመልስም።»
- ከውግያው ወደ ሠልፉ ሲመለሱ በመመለስ መለከቶች ላይ፦ «እግዚአብሔር አሰብስቧል።»
- ከጦርነቱም ወደ ኢየሩሳሌም ማኅበር ሲመለሱ በሚነፉ መለከቶች ላይ፦ «በሰላም መመልስ የእግዚአብሔር ደስታ»
ከዚህ በኋላ በዓላማዎቹ ላይ የሚጻፉት ቃላት ትዕዛዝ ይሰጣል። ለምሳለ፦
- በሺህ ዓለቃ ዓላማ ላይ፦ «የእግዚአብሔር ቁጣ በቤሊያልና ከርሱ ጋር ድርሻ ባላቸው ሁሉ ላይ ምንም ቅሬታ እንዳይኖራቸው በመዓት ይበቀላል።»
- በመቶ ዓለቃ ዓላማ ላይ፦ «የውግያ ኃይል በኃጥአን ሥጋ ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ይመጣል።»
- በሀምሳ ዓለቃ ዓላማ ላይ፦ «በእግዚአብሔር ታላቅ ሥራዎች በኩል የእኩያን ትግል የተጨረሰ ነው።»
በተጨማሪ ብዙ ሌሎች ትዕዛዛት በዚህ ጥንታዊ ብራና ጽሑፍ ተገኙ።