Jump to content

የኢትዮጵያ ሙዚቃ

ከውክፔዲያ
በገና መደበኛ የጣት አቀማመጥ

በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ጊዜ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የመጀመሪያውን ግራማፎን ወይም የሸክላ ማጫወቻ በ፲፰፻፹፱ ዓ.ም. ሄንሪ ደ አርሊንስ እና ኒኮላስ ሊዋንቲቭዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ አመጡላቸው። ይኸውም ማጫወት ብቻ እንጂ ድምጽ አይቀዳም ነበር። በኋላ ግን በዓመቱ በ፲፱፻፺ ዓ.ም. ከንግሥት ቪክቶሪያ የተላኩ የእንግሊዝ መልዕክተኞች በመጡ ጊዜ ግራማፎኑንና ድምፅ መቅጃውን ይዘውላቸው መጡ።[1]

ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፃቸው በዲስክ የተቀረፁት ዓፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ናቸው። ዛሬ በእንግሊዝ አገር በለንደን ከተማ ብሪቲሽ ኢንስቲቲውት ኦፍ ሪኮርድ ሳውንድ በተባለው ሙዚየም ውስጥ ይገኛል።[1]

በሸክላ ቀረፃ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ በሸክላ የተቀረፀው የመጀመሪያው ዜማ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ስራዎች ሲሆኑ ዘመኑም በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነበር። ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በጀርመን ቆይታቸው ወቅት የጀርመን የሙዚቃ ድርጅት ጠይቋቸው የኢትዮጵያ መዲናና ዘለሰኛ ዜማዎች በ፲፯ አይነት ስልት እየተጫወቱ ተቀርፀዋል። ኩባንያው የተሰማ እሸቴን ዜማዎች በ፲፯ ሸክላዎች የቀረፀው ሲሆን ለዜማው ባለቤት የድካም ዋጋ እንዲሆን በወቅቱ ፲፯ ሺህ የጀርመን ማርክ ከፍሏቸዋል። በዘመኑ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያም አሁንም እነዚህ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ብርቅዬ ሸክላዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ተሰብስበው ይገኛሉ።[2]

እነዚህ በተቋሙ እጅ ያሉት ፲፮ ሸክላዎች እያንዳንዳቸው ሁለት ዜማዎችን የያዙ ሲሆኑ ባጠቃላይ ፴፪ ዜማዎች ተቀርፀውባቸዋል። እያንዳንዱ የሸክላው ገፅ ላይ A ወይም B ተብሎ ተሰይሟል፣ የዜማው ስም ተፅፎበታል፣ የዜማው ባለቤት ተሰማ እሸቴ ስም አለ፣ ሸክላው ጀርመን ሀገር መሰራቱ እንዲሁም የሸክላው ቁጥር ተጠቅሷል።[2]

በ፲፱፻፳፭-፳፮ ዓ.ም. አካባቢ የእነ ፈረደ ጎላንጋቷ ከልካይተሻለ መንግሥቱ የዜማ ሸክላዎች ብቅ እስከሚሉ ድረስ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሸክላዎች ከ፳ ዓመታት በላይ አቅም ባላቸው ቤተሰቦች ዘንድ በብቸኝነት በግራማፎን ሲደመጡ ቆይተዋል።[2]

በቀ.ኃ.ሥ. ጊዜ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ግርማዊ ጃንሆይ በአልጋ ወራሽነታቸው በ፲፱፻፲፮ ዓ.ም. አውሮፓን ጎብኝተው ሲመለሱ አርባ የአርመን ተወላጆች በበጎ አድራጎት ለመርዳት ካስመጧቸው የመንፈስ ማነቃቂያና የሞራል መጠበቂያ እንዲሁም ለሀገሪቱ የሥልጣኔ እርምጃ ይጠቅማል በማለት የሙዚቃ ትምህርት ቤት አቋቋሙ። ከዚህ በኋላ በዚሁ ዓመተ ምሕረት ከወለጋ ጠቅላይ ግዛት ከሾጎሌ ፻፳ የሚሆኑ ወጣቶች መጥተው በሙዚቃ ትምህርት እንዲሰለጥኑ ተደርጎ በ፲፱፻፳፫ ዓ.ም. የግርማዊ ጃንሆይ ንግሥ በዓል በነዚሁ ሙዚቀኞች ተከብሮ ውሏል። እነዚህ የመጀመሪያው ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች በጣሊያን ወረራ ጊዜ ግማሾቹ ሲገደሉ የቀሩትም ተበታትነዋል።[3]

የኢትዮጵያ ነፃነት እንደተመለሰ ይኸው የሙዚቃ ክፍል ድርጅት አስፈላጊ በመሆኑ ከመስከረም ፳፩ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ.ም. ጀምሮ እንደገና እንዲቋቋም በግርማዊ ጃንሆይ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ከጣሊያን ወረራ በፊት በቦይስካውትና በየትምህርት ቤቱ የሙዚቃ ትምህርት የጀመሩ ስለነበሩ ተመርጠው በካፒቴን ኬቮርክ ናልባንዲያን አስተማሪነት ሥራው በክቡር ዘበኛ ድርጅት ውስጥ ተጀመረ።[3]

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ሥልጣኔ የተስፋፋውና የተጀመረው ከውጭ ሀገር የሙዚቃ መምህራንን በማስመጣት በክቡር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ሲሆን ለዚሁ ክፍል ከሰለጠኑት ብዙዎቹ በልዩ ልዩ ድርጅቶች ውስጥ በመሰማራት የሀገራቸውን ወጣቶች በሙዚቃ ጥበብ በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ። ከዚህም በተረፈ ድርጅቱ ያሰለጠናቸውን የሙዚቃ አዋቂዎች በ፲፱፻፴፭ ዓ.ም. ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል እየላከ እንዲያስተምሩ አድርጓል።[3]

በ፲፱፻፴፯ ዓ.ም. የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አሁን የቀ.ኃ.ሥ. ቲያትር ክፍል የተባለው ተቋቁሞ ቲያትር በሚታይበት ጊዜ የክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ረድቷል።[3]

የክብር ዘበኛ ሙዚቀኛ ክፍል በግርማዊ ቀ.ኃ.ሥ. መልካም አሳቢነት ከ፲፱፻፲፮ ዓ.ም. ሥራውን ከወጠነበት ቀን ጀምሮ የተጣለበትን አደራ በሚገባ ያከናወነ ለመሆኑ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ክፍሎች የረዳ ከመሆኑም በላይ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የአማርኛ ሙዚቃን አራቆ በመቀመር ለሌሎች ሁሉ መልካም አርአያ ሆኖ የኢትዮጵያ ዜማ ከሀገሩ አልፎ በሌላው ዓለም እንዲታወቅ አድርጓል። በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. በቀ.ኃ.ሥ. ቲያትር ቤት በተደረገው የሙዚቃ ውድድር የክ/ዘ ሙዚቃና ቲያትር ክፍል ፩ኛ ሆኖ የተሸለመ ከመሆኑም በላይ እስከ ዛሬ ድረስ ሌላ ውድድር ስላልተደረገ የከፍተኛነቱን ደረጃ አሁንም እንደያዘ ነው።[3]

ተዛማጅ መጣጥፎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
  1. ^ የአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ የሕይወት ታሪክ፣ ገጽ 5
  2. ^ የአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ የሕይወት ታሪክ፣ ገጽ 6 Cite error: Invalid <ref> tag; name "natbio6" defined multiple times with different content
  3. ^ የአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ የሕይወት ታሪክ፣ ገጽ 4