ዳኛቸው ወርቁ

ከውክፔዲያ

ዳኛቸው ወርቁ በዛብህ «አደፍርስ» (፲፱፻፷፪ ዓ.ም.) በተሰኘ ልብ ወለድ ድርሰቱ ባነሳቸው ጭብጦች እና የተራቀቀ የአጻጻፍ ስልቱ የአማርኛን ዘመናዊ ልብ ወለድ ወደ ድንቅ ከፍ ካለ እርከን ያወጣ፥ «እምቧ በሉ ሰዎች» በሚለው የግጥም መድብሉ (፲፱፻፷፯ ዓ.ም.) ውስጥ በተካተቱ ግጥሞቹ ስለሀገሩ ልማትና ዕድገት ተቆርቋሪነቱን የገለጠ ዕውቅ የሥነ ጽሑፍ ምሁር፥ ሐያሲና ተርጓሚ የነበረ ሲሆን በልሳነ እንግልጣር (እንግሊዝኛ) በመጻፍም «The Thirteenth Sun» የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ በዓለም አቀፉ መድረክ ካስተዋወቁ በጣት ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጸሓፍት አንዱ ነበር።

'የ ፊውዳል ኢትዮጵያን ሶሲዮሎጂና የታሪክ ጥራዞች ከማንበብ፥ «አደፍርስ» ድርሰቱን ማንበብ ይቀላል’ የተባለለት ዳኛቸው ወርቁ የካቲት ፲፮ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. በሰሜን ሸዋይፋትጥሙጋደብረ ሲና ከተማ አቅራቢያ ከአቶ ወርቁ በዛብህና ከወይዘሮ አሰገደች ሀብተወልድ ተወለደ። ከቤተ ሰቡ አምሥት ልጆች ዳኛቸው በኩር ነበር።

ዳኛቸው ከ፲፱፻፴፮ ዓ.ም. እስከ ፲፱፻፵፪ ዓ.ም. ድረስ በተወለደበት አካባቢ በደብረ ሲናው አብዬ ትምሕርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምሕርቱን ተከታተለ። እዚያ ሳለ ገና በ አሥራ ሦስት ዓመቱ፥ «ያላቻ ጋብቻ ትርፉ ሐዘን ብቻ» የተሰኘች ተውኔት ደርሶ በመተወን ታዋቂነት ያተረፈ ወጣት ነበር።

፲፱፻፵፫ ዓ.ም. አዲስ አበባ መጥቶ መጀመሪያ ሊሴ ገብረማርያም ኋላ ግን በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሁለተኛ ደረጃ ትም?ህርቱን የተከታተለ ሲሆን በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምሕርት ቤት ይሰጥ የነበረውን የመምሕርነት ኮርስ ለአንድ ዓመት ተከታትሎ በመምሕርነት ተመርቋል። ከምረቃ በኋላ በሐረር መድኃኔዓለም ለሁለት ዓመታት፥ በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ለሁለት ዓመታት ግዕዝአማርኛ ያስተማረ ሲሆን፣ «ሰቀቀንሽ እሳት» የተሰኘ ተውኔቱን በመድረስ ተሰጥዖውን የገለጸ፥ «ሰው አለ ብዬ» የተውኔት ድርሰቱን በማሳተም ያበረከተ የፈጠራ ሰው ነበር።

ዳኛቸው በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምሕርቱን እየተከታተለ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ በረዳት መምሕርነት ጭምር በዩኒቨርሲቲው ያገለገለ ሲሆን ተመርቆ እስከወጣበት ጊዜም ድረስ በወቅቱ የተማሪው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ከዘመነኞቹ የኮሌጅ ገጣሚዎች ከነታምሩ ፈይሳዮሐንስ አድማሱአበበ ወርቄይልማ ከበደኢብሳ ጉተማኃይሉ ገብረዮሐንስመስፍን ሀብተማርያም፥ ወዘተ ጋር እነ «ወጣቱ ፈላስማ» በመሳሰሉ ግጥሞቹ የለውጥ ሐሳቡን ሲያስተጋባ የነበረ ገጣሚም ነበር።

፲፱፻፶፮ ዓ.ም ተመርቆ፣ ከ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. እስከ ፲፱፻፷፩ ዓ.ም. ድረስ እዚያው ዩኒቨርሲቲው በመምሕርነት ያገለገለ ሲሆን «ትበልጭ» የተሰኘ ተውኔቱን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ለመድረክ ያበቃ «ጸሐፌ-ተውኔት» ነበር። በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. በአሜሪካ ኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ሥነ ጽሑፍ አጥንቶ በመመረቅ ‘የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ’ የሚል ማዕረግ ያገኘ፥ የመጀመሪያዎቹንም አጫጭር ልብ ወለዶች ደርሶ የታተሙለት ብርቅ ሰው ነበር።

ወደሀገሩ ተመልሶ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ መምሕርነት እስከ ፲፱፻፷፭ ዓ.ም. ያገለገለው ዳኛቸው የ”ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል”ን ከነ ጌታቸው ኃይሌ፥ ከነአብርሃም ደሞዝዮሐንስ አድማሱኃይሉ ፉላስ.. ወዘተ ጋር ያደራጀ፣ ወጣት የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን በማደራጀት አስተዋጽዖ ያደረገ ምሁር ሲሆን፥ ባነሳቸው በሳል የለውጥ ሐሳቦችና የተራቀቀ ሥነ ጽሑፋዊ የአቀራረብ ስልቱ የተደነቀውን የኢትዮጵያን የዘመናዊ ልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ ልዩ ልዩ በእድገት ምዕራፍ ያሸጋገረውን «አደፍርስ» ልብ ወለዱን በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. በማሳተም ታላቅ ጠቢብነቱን ማስመስከሩ ብቻ ሳይሆን፤ በወቅቱ ይታተሙ በነበሩ የዛሬይቱ ኢትዮጵያየኢትዮጵያ ድምጽ እና አዲስ ዘመን ጋዜጦችም የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ የተመለከቱና የወጣት ደራሲያንን ሥራዎችን በመሔስ ለሀገሪቱ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ምሁራዊ ተልዕኮውን የተወጣበት ወቅት ነበር።

«አደፍርስ» ልብ ወለዱ ከዩኒቨርሲቲው አካዴሚ ጋር ግንኙነቱን ያደፈረሰበት ዳኛቸው - በዚሁም ሳቢያ ዩኒቨርሲቲውን ለቆ መጀመሪያ በጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ኋላ ደግሞ በፈረንሳይ ኮሌጅ እስከ ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. የአማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ አስተማረ። ኋላም «በኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ድርጅት» በትርጉም አዋቂነት፥ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነትና በኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት ሹምነት ለአሥራ አምሥት ዓመታት አገልግሎ፣ በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ጡረታ ወጣ።

የዛሬዎቹን ወጣት ኢትዮጵያውያን በጥበቡ ዘርፍ የሚታደጉ የሥነ ጽሑፍ ጥበብ መመሪያ፣ የአማርኛ ፈሊጦች መጽሐፍት ያሳተመ ምሁር ሲሆን አንድም ለሀገሪቱ ቋንቋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያላቸውን «የማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት» እና «የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት» የመሳሰሉ ጥልቅ እና ምጡቅ ሥራዎች ዝግጅት ላይ በመሳተፍ ምሁራዊ ግዴታውን የተወጣ ኢትዮጵያዊ ነበር።

የሀገሩን እምነትና ባህል ጠንቅቆ የሚያውቅ፥ ለሥራ ነገን የማያውቅ፥ ለውጥ ፈላጊ፥ አገር ወዳድ፥ ስለሀገር ኋላ ቀርነት ሁሌ የሚቆረቆር ፥ ማጎብደድና ማቆሻበድ የማይወድ፥ ፊት ለፊት ተናጋሪ ባጠቃላይ በ«አደፍርስ» ልብ ወለድ ድርሰቱ ጠጣርና ምጡቅ ሐሳቦች በድንቅና ውብ የአጻጻፍ ስልት፥ ልዩ በሆነ የቋንቋ ኃይል የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ልዕልና ያሳየ - ዳኛቸው ወርቁ - በዚሁ ድርሰቱ የፈጠራ መጽሐፍ የሚነበብ ብቻ ሳይሆን ተደጋግሞ የሚነበብና የሚያወያይ መሆኑን - አዲስ ባህል የተከለ ብርቅ የጥበብ ሰው ነበር።

ዳኛቸው ወርቁ ኅዳር ፳፪ ቀን ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. በድንገት ታሞ አርፎ በተወለደበት ደብረ ሲና ከተማ ቀብሩ ተፈጸመ። በሥራዎቹ ዛሬም ከእኛው ጋር ነው።

ዋቢ መጻሕፍትና ምንጮች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • ብርሃነ መስቀል ደጀኔ እና ጌታሁን ሽብሩ ፤ «ያሠርቱ ምእት ፥ የብርዕ ምርት - ክፍል ፩» ፤ ጳጉሜን ፫ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.፤ ገጽ ፵፭ - ፵፮
  • http://www.adefris.info/index.html