Jump to content

ወጋየሁ ደግነቱ

ከውክፔዲያ
የ07:08, 9 ጁን 2023 ዕትም (ከWikiBayer (ውይይት | አስተዋጽኦ) ተዘጋጅቶ)
(ለውጡ) ← የፊተኛው እትም | «የአሁኑን እትም ለመመልከት» (ለውጡ) | የሚከተለው እትም → (ለውጡ)

አርቲስት ሻለቃ ወጋየሁ ደግነቱ ከአባቱ ከአቶ ደግነቱ ጅማ ከእናቱ ከወ/ሮ አበራሽ ወዳጆ ጥር 12 ቀን 1940 ዓ/ም. በሀረርጌ ክ/ሀገር በወበራ አውራጃ በጎሮ ጉቱ ወረዳ ልዩ ስሙ መካኒሳ በተባለው ስፍራ ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሐረር ልዑል ራስ መኮንን አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትሏል። በነበረው ልዩ የሙዚቃ ፍቅር የተነሳ መጋቢት 1 ቀን 1955 ዓ.ም. በሐረርጌ ክ/ሀገር ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል በታዳጊነት ዕድሜው ተቀጠረ። ከ1957 ዓ/ም ጀምሮ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅና ተፈቃሪ ድምፃዊ ለመሆን የበቃው ሻለቃ ወጋየሁ ደግነቱ በ1959 ዓ/ም ከድምፃዊነቱ በተጨማሪ የሐረር ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል የተወዛዋዥ ቡድን አሰልጣኝ የዜማ እና የግጥም ደራሲ ሆኗል።

ይኸው ለኪነ-ጥበብ ያለው ፍቅር እየጎለበተ እያበበና እየጎመራ በመሄዱ ወጋየሁ በቀድሞ ፖሊስ ሠራዊት ውስጥ በ1960ዎቹ የተውኔት ባለሞያና አዘጋጅ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች የሙዚቃ መሣሪያዎች ቴክኒሻን ጭምር በመሆን የዘርፈ ብዙ ባለሞያዎች ባለቤት መሆኑን ለባልደረቦቹ እና ለአለቆቹ ለማሳየት ችሏል። ከሙዚቃ ስራው በተጓዳኝ የአቋረጠውን ትምህርት በማታው የትምህርት ክፍል በመከታተል ለተጨማሪ እውቀት የነበረውን ትጋትም አሳይቷል። በ1964 ዓ/ም የሙሉ 10 አለቅነት ማዕረግ ያገኘው ወጋየሁ ቀጥሎም የመኮንንነትን ኮርስ በሰንዳፋ ፖሊስ ኮሌጅ በመውሰድ ሚያዚያ 14 ቀን 1968 ዓ/ም በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ ተመርቋል። በፖሊስ ሠራዊት ባልደረባነቱ ወቅት በቀድሞ ኤርትራ ክ/ሀገርና በመላው ሀገሪቱ ተዘዋውሮ በሙያው ሀገሩን ያገለገለው ወጋየሁ ኤርትራ ውስጥ በነበረው በ5ኛ ሻለቃ ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ውስጥ የመቶ መሪ በመሆን ወቅቱ የጠየቀውን ሐገራዊ ግዳጅ ተወጥቷል። ሀገሩ እና ወገኖቹ ሁሉ ሊዘነጉት የማይቻላቸውን የጀግንነት ተግባርም በመወጣት በመኮንንነቱ የተዋጊ አዋጊነት ዘመን ፈጽሟል። ስለ እናት ኢትዮጵያ ክብር «የደስታሽ ሕይወት ተካፋይ ለችግርሽ ሆኜ ተወካይ መቆሜን አውቃለሁ ጠንቅቄ ታሪክሽን ለማኖር ጠብቄ…» ብሎ ያዜመው ስለ ወላጅ እናት ፍፁምነት እና መተኪያ አልባነት «የሰው የእንስሣት የአራዊት… እናት እኮነች መድኃኒት” በማለት ያንጎራጎረው እና “አርኬ የሁማ…» በተሰኘው ማሕበረሰባዊ ተወዳጅ የኦሮምኛ ዜማው የሚታወቀው ሻለቃ ወጋየሁ ደግነቱ ከጦር ግንባር ግዳጅ መልስ በመስከረም ወር 1969 ዓ.ም. የኤርትራ ክ/ሀገር ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል አዛዥ ሆኖ አገልግሏል። በ1978 ዓ.ም. የሻለቅነት ማዕረግ እስካገኘበት ጊዜ ድረስ እና ከዚያም በኋላ በኪነ-ጥበብና በፖሊሳዊ ሙያው ከሀረርጌ ጫፍ እስከ አሰብና የቀድሞይቱ ኢትዮጵያ ደሴቶች ድረስ በመነቃነቅ ከእሱ ይጠበቅ የነበረውን የዜግነት ድርሻ ተወጥቷል። አርቲስት ሻለቃ ወጋየሁ ደግነቱ፤ በቀድሞ የኢትዮጵያ ፊናንስ ፖሊስ፣ የፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃና የቴአትር እንደሁም በአዲስ አበባ ፖሊስ መምሪያ የ6ኛ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ሆኖ ሰርቷል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም የህግ ፋኩልቲ በማታው የትምህርት ክፍል የህግ ሙያን በመከታተል በ1984 ዓ/ም ወርሀ ታህሣስ የህግ ዲፕሎማውን የተቀበለው አርቲስት ወጋየሁ ደግነቱ ጅማ በጥብቅናና በህግ አማካሪነት ሙያ ሕብረተሰቡን በቅንነት ሲያገለግል የቆየ ስሙ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ነበረ። በሳቂታነቱ፣ የተጣሉትን በማስታረቅ ተግባሩ፣ በተግባቢነቱና በጨዋታ አዋቂነቱ፣ በሥራ እና በወገን ወዳድነቱ በኢትዮጵያዊን ዘንድ ልዩ አክብሮትን ያገኘ ሰው ነበረ። ሻለቃ ወጋየሁ ባለትዳር እና የአንድ ሴት ልጅ አባት እንደዚሁም የአንድ ወንድ ልጅ አያት ሲሆን፤ ከወራት በፊት በአጋጠመው የጤና መታወክ ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በ61 ዓመቱ አርብ ሐምሌ 10 ቀን 2001 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶናል ። የቀብሩ ስነ-ሥርዓትም ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 2001 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ በቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ወዳጅ ዘመዶቹ እና በርካታ አድናቂዎቹ በተገኙበት ከቀኑ በ10 ሰዓት ተፈጽሟል።

ቤተሰቦቹ ታሞ ህክምና እየተከታተለ በነበረበት ሰዓትም ሆነ በሐዘናቸው ጊዜ ከጎናቸው ላልተለዩ የአርቲስቱ ልባዊ ወዳጆች እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የከበረ ምስጋና ያቀርባሉ።