Jump to content

ራስታፋራይ እንቅስቃሴ

ከውክፔዲያ
(ከራስ ተፈሪያን የተዛወረ)
አንድ ራስታ በጃማይካ

ራስታፋራይ በመጀመርያ በ1930ዎቹ እ.ኤ.አ.ጃማይካ የተነሣ እንቅስቃሴና እምነትና አኗርኗር ነው። ዛሬ በአለም ዙሪያ ምናልባት 1 ሚሊዮን ራስታዎች አሉ።

የራስታፋራይ እንቅስቃሴ የጀመረው አፄ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ1930 እ.ኤ.አ. (1923 ዓም.) የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዘውድ ከመጫናቸው ቀጥሎ ዜናውስ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ቅኝ ግዛት ደሴት በካሪቢያን ባህር ውስጥ ወደ ጃማይካ በደረሰበት ወቅት ያሕል ነበር። ስያሜው «ራስታፋራይ» የመጣው ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ቀድሞ አርእስት ከራስ ተፈሪ በማክበርም ነው።

ከዚህ በፊት የጃማይካ ሕዝቦች ታሪክ በቅኝ ግዛትነት ሥር በመከራዎች ይሞላ ነበር። የሕዝቡ ብዛት ከአፍሪካዊ ዘር ሲሆን፣ አያቶቻቸው በባርነት ዘመን (ከ1800ዎቹ አስቀድሞ) ከአፍሪካ ተወስደው በሸንኮራ ኣገዳ እርሻ በስኳር ግብርና እንዲሠሩ ወደ ጃማይካ ደርሰው ነበር። አንዳንዶቹ ወደ ተራሮቹ አምልጠው ማሩን የተባሉት አመጸኞች ሆኑ። ባርነት ከተከለከለ በኋላም ቅኝ አገሪቱ የብሪታንያ ስኳር እርሻ መሆንዋ አልተቋረጠም ነበር። የጃማይካ ሕዝብም ጥልቅና ጽኑ መንፈሳዊነት ያላቸውና የመጽሐፍ ቅዱስ አንባብያን ስለ ሆኑ በነርሱ በኩል በርካታ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተነሥተው ነበር። የጃማይካ ሕዝብ ዘር ብዙ ክፍል ደግሞ ከአሻንቲ መንግሥት በመድረሱ፣ ከምዕራብ አፍሪካ የተዘረጉ ልማዶች፣ እምነቶች ወይም ተጽእኖች ሊገኙ ተችሏል። ከነዚህ ቅድመኞች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካከል፦

እንግዲህ ራስታፋራይ በዚህ አይነት ሁኔታና ትርምስ ተወለደ ማለት ሰባኪው አቶ ሌናርድ ፕ ሃወል በብዕር ስሙ «ጋንጉሩ ማራግ» ሥር በጽሑፉ የተስፋ ቁልፍ ያሳተማቸው ጽንሰ ሀሣቦች ልደት ነበር። የተስፋ ቁልፍ በተለይ ከፊጽ ባልንታይን ፐተስቡርግ ጽሑፍ ንጉሣዊ ጥቅል ብራና ብዙ መፈክሮች ከመበደሩ በላይ፣ ሃወል ባስተማረው ትምህርት ዘንድ የ«ንጉሥ አልፋ» ትርጉም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ የ«ንግሥት ኦሜጋ»ም መታወቂያ እቴጌ መነን ነበሩ። ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊነትና ክርስትና እና ስለ ጃንሆይ ሥራተ ነግሥም ይገልጻል። ጃንሆይ በራሳቸው እግዚአብሔር ወልድ (መሢኅ) ተመልሰው ስለ ሆኑ፣ አዲስ ሃይማኖት መመሥረት እንደሚገባ የሚል ጽሑፍ ነው። እነዚህም ሀሣቦች እስካሁን ድረስ በራስታፋራይ አማኞች (ራስተፈሪያውያን) በኩል ተቀብለዋል። (በሃወል ጽሑፍ ደግሞ ጥቁሮች ከሌሎች ዘሮች ብልጫ አንዳላቸው ይላልና ስለ ነጮች በተለይም ስለ እንግሊዝ ዘር ብዙ ስድቦች ሲኖሩበት፣ በአሁን ዘመን ግን ብዙ ራስታዎች ስለ ጃንሆይ እራሳቸው ቃላት በደንብ በማጥናት፡ ብዙዎቹ በዘሮች ሁሉ እኩልነት የሚያምኑ ሆነዋል። )

የጃማይካ ባለሥልጣናት በመጀመርያው በአዲሱ እንቅስቃሴ ደስ አላላቸውም ነበርና ራስታዎቹ ከነርሱ ዘንድ መሳደድን ያገኙ ነበር። አሁን ዝነኛ የሆነው የራስታዎች «ድረድሎክ» (ጉንጉን) ጽጉር አሠራር መጀመርያው የታየው በ1941 ዓም በኪንግስተን «ወጣቶች ጥቁር እምነት» በተባለው ንዑስ-ክፍል አባላት መካከል ነበር። ሆኖም «ባለ ድረድሎክ ሁሉ ራስታ አይደለም፣ ራስታ ሁሉ ባለ ድረድሎክ አይደለም» በማለት የመንፈስና የልቡና ፍቅር ከጽጉሩ ይልቅ በአይነተኛነት እንደሚበልጥ ይናገራሉ።

የራስታዎች አምላክና ንጉሥ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ

ጃንሆይ የእምነት አባት በመሆናቸው መጠን፣ ራስታዎች ባብዛኛው ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ወይም ጳጳሳት አይኖራቸውም። እንዲህ ያሉት መዋቅሮች በአለም ታሪክ ሲገኙ በጠላቶችም ሲበረዙ ታይተዋልና ይላሉ። በዚያው ፈንታ ሰዎች ሁሉ ቢያውቁትም ባያውቁትም የሰማዩ አባትና የምድራዊት እማማ ልጆች ሆነው እንደ ወንድማማችና እኅትማማች በመከባበር መኖር ይገባቸዋል ባዮች ናቸው። እያንዳንዱ ወንድም «ንጉሥ» ተብሎ በመንፈሱ ውስጥ ከአምላክ (ሥላሴ) ጸባይ ጋር መዋኸድ ስለሚገባ፣ በቃላቸው ራስታዎች «I & I» (እኔ እና እኔ) ሲሉ፣ የተናጋሪውና የአምላኩ ውኅደት በራስታፋራይ መንፈስ ውስጥ ያመልከታሉ። እንዲሁም እያንዳንዱ ራስታ እኅት ወይም «ንግሥት» ደግሞ «I & I» ትላለች።

እቴጌ መነን - ንግሥት ኦሜጋ ለራስታፋራይ እንቅስቃሴ

1953 ዓም አንዳንድ የራስታ ሽማግሌዎች ወደ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ተጉዘው ከጃንሆይ ጋራ ተገናኙ። ከ1958 ዓም ጀምሮ አንዳንድ ራስታዎች በሻሸመኔ ደርሰው አነስተኛ ርስት ተሰጥተዋል። በዚያም ዓመት ጃንሆይ እራሳቸው ወደ ጃማይካ ጉብኝት ሲያድርጉ፣ አንድ መቶ ሺህ ራስታዎች በአውሮፕላን ማረፊያው ለአምላካቸው የጋለ ሰላምታ ሰጡዋቸው። የዚሁም ጉብኝት መታሠቢያ ቀን እንደ በዓል ይከበራል።

የራስታዎች አምልኮት ከብዙ ከበሮ፣ መዝሙር፣ የኢትዮጵያ ቀለማት (አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ) በማሳየት፣ እና ካያን (እጸ ፋርስን) በፒፓዎች በማጨስ ይደረጋል። ከ1960 ዓም ጀምሮ ብዙ ራስታ ሙዚቀኞች አዲሱን «ሬጌ» ቄንጥ ወይም ዘርፍ አሰምተዋል፤ ከሁሉ ዝነኛ የሆነው ቦብ ማርሊ ሆኖዋል።

ከጃንሆይ በቀር ምንም የተወሰነ ትምህርት መሪነት ባይኖራቸውም፣ ራስታዎች ባጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስን ይቀበላሉ፤ ይህም በኢትዮጵያ ከሚከበረው አዋልድ መጻሕፍት ክፍል ጭምር ይከበራል። በተጨማሪ ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ እና ክብረ ነገሰት እንደ ቅዱሳን መጻሕፍት የሚያጥኑ ራስታዎች አሉ።

በሰፊው በራስታፋራይ እምነቶች ዘንድ፣ ለወደፊት የተነበየው የእግዚአብሐር መንግሥት ከዋና ከተማው በኢትዮጵያ በመሲሃቸው ሥር ለዘላለም ይገዛል፤ የዓለሙም መደበኛ ቋንቋ ያንጊዜ አማርኛ ይሆናል። ባብዛኛው አጼ ኃይለ ሥላሴ እንደ ሞቱ አይቀበሉም፤ እግዚአብሔር አይሞትምና አሁን መሢህ በስውር ለባቢሎን ውድቀት ሰዓት እየጠበቁ ነው ይላሉ። ይህም ውድቀት ከብዙ አመታት በላይ ስለማይቀር፣ ባጠቃላይ እንደ ክርስትና ወይም እንደ ሌሎች ሃይማኖቶች ጽኑ መዋቅርና አስተዳደር ለመመሥረት ጊዜው አይገባም ይላሉ። ጃንሆይ እንዳስረዱትም የኅሊና ነጻነት እጅግ ይከበራል። እስከዚያው ድረስ የአሁኑ ባቢሎን መከራ ዘመን «አማጊዴዎን» (ቃሉ ከአርማ ጌዶን ተወስዶ) ይሉታል። የራስታፋራይ ወንድም ወይም እኅት ለመሆን መጀመርያው እርምጃ ባቢሎንን መተዉ ነው ብለው ያስተምራሉ።

ራስታዎች ሁሉ ባይሆኑም ብዙዎቹ በምግብነት ሥጋ አይበሉም፣ የአትክልትን ምግብ ይመርጣሉ። ሌሎችም በሕገ ሙሴ ከተከለከሉት ሥጋዎች (በተለይም ከአሳማ) ቀርተዋል። ወደ ቤተ መቅደስ መሄዱ ሳይሆን ሰውነት እራሱ ቤተ መቅደስህ መቆጠር ይገባልና ይላሉ። የአመጋገብ ጉዳዮች እንደገና ከፍቅርና ሰላም ቁም ነገሮች ግን አይበልጡም። እንቅስቃሴው በጃማይካ እንደ ተደረጀ ቋንቋቸው ከእንግሊዝኛ የተለወጠ ቀበሌኛ ሊመስል ይችላል፤ ከ«I & I» በቀር አያሌ «I-» ያለባቸውን አዳዲስ ቃላት ፈጥረዋል።

ኦሪት እንደሚገለጽና እንደ ሶምሶንናዝራዊ ሥርዓት ለመፈጽም የሚምሉ አጥብቀው ከሥጋ፣ ከአረቄ ወይም ትምባሆ፣ ከመቀስ ወይም ሚዶ የሚርቁ ናቸው። ከተፈጥሮአዊ ካያ በቀር ሌላ አደንዛዥ አይነኩም።

በራስተፋራይ እንቅስቃሴ ውስጥ በዓመታት ላይ አንዳንድ ተቃራኒ ክፍልፋዮች ወይም «ቤተሠቦች» ተነሥተዋል፤ ዋናዎቹም፦

  • ናያቢንጊ - ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ውጭ ካለው ሁሉ አጥብቀው የሚጠብቁ ናቸው።
  • ቦቦ አሻንቲ - በትምህርታቸው የ«ሥላሴ» ትርጉም ጃንሆይ፣ ማርከስ ጋርቪ እና ሦስተኛው መሪያቸው ቻርልስ ኤድዋርድስ ሲሆን በሦስት መሲሆች አንድላይ የሚያምኑ ናቸው።
  • አሥራ ሁለቱ ነገዶች - ከእስያ ሃይማኖቶች የተመላሽ-ትስብዕት (ሰምሳረ) ጽንሰ ሃሣብ ተቀብለው እራሳቸው ከጥንቱ እስራኤል ነገዶች ነፍሶች እንደ ተመለሱ ይላሉ። የ12 ነገዶቹም አከፋፈል በየፈረንጅ ወሩ በልደታቸው ወር ነው።

ዛሬም ከጃማይካ ወይም ካካሪቢያን ውጭ ራስታዎች በመላው ዓለም አገራት በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካም ሆነ በእስያ በአውስትራሊያም ይገኛሉ።