ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር

ከውክፔዲያ

ስብሐት (ስብሐት ለአብ) ገብረ እግዚአብሔር (ሚያዝያ 27 [1928]ዓ.ም. - ሰኞ፣ ቀን

[ትግራይ] ጠቅላይ ግዛት፣ አድዋ አውራጃ፣ እርባ ገረድ በተባለች መንደር ከአባቱ ከቄስ ገብረ እግዚአብሔር ዮሐንስ እና ከወይዘሮ መአዛ ወልደ መድኅን  ተወለደ። ትምህርቱን በስዊድን ሚሲዮን፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተከታትሎ በትምህርት አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል። በአስፋ ወሰን ትምህርት ቤት በእንግሊዝኛ መምህርነት ለ2 ዓመት አገልግሏል። በመቀጠልም ከየተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ ሳየንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ባገኘው የትምህርት እድል አማካይነት ወደ ፈረንሳይ (ኤክስ አን ፕሮቫንስ) በመሄድ ከ1962-1964 ቆይቷል። የሄደበትን ትምህርት አጠናቆ ምስክር ወረቀት ባይቀበልም ቆይታው ከአውሮፓ ባህል እና ስነ-ጽሁፍ እንዲተዋወቅ በጣም እንደረዳው ይናገራል። ወደ ፈረንሳይኛ «Les Nuits d'Addis-Abeba» ተብሎ በፍራንሲስ ፋልሴቶ የተተረጎመውን የልብ-ወለድ ድርስቱን «ሌቱም አይነጋልኝ»ን ብዙውን ለመጻፍ የበቃው እዚያው በፈረንሳይ እንደሆነም ይናገራል። ይኸው ድርሰቱም ወደ ፈረንሳይኛ ቋንቋ የተተረጎመ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ልብ-ወለድ ነው።

ስብሐት ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ በመነን መጽሄት የዝግጅት ክፍል ውስጥ ሰርቷል። በ1966 ዓ.ም. ወታደራዊው ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲቋቋም በአርታኢነት ተቀጥሮ ሰርቷል። በመንግሥት ትእዛዝም ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን የካርል ማርክስ ሥራ የሆነውን ካፒታልን (Das Capital) ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ በመመለስ ሥራ ላይ ተሳትፏል።

ብዙዎቹ የስብሐት ሥራዎች በተጻፉበት ጊዜ ለመታተም ባይታደሉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የህትመትን ብርሃን ለማየት በቅተዋል። ጽሁፎቹ ረዘም ላለ ጊዜ ሳይታተሙ ለመቆየታቸው ዋነኛው ምክንያቱ ስብሐት በመጽሐፉ የሚጠቀማቸው ቃላት ብዙዎቹ በኢትዮጵያ ባህል ያደገ አንባቢን አይን የሚያስፈጥጡ፣ ጆሮ የሚያስይዙ በመሆናቸው ነው። በገበያ ላይ በቅርብ የወጡት ድርሰቶቹ ከመጀመሪያ ቅጂያቸው ብዙ ለውጥ እና የአርትኦት ሥራ የተደረገባቸው እንደሆኑ ይነገራል። ስለዚሁ ጉዳይ ለአዲስ ላይቭ በሰጠው ቃለመጠይቅ ላይ ሲናገር «በጨለማ ያልተደረገውን ነገር አንድም የጻፍኩት የለም... ያለውን እንዳለ ነው የምጽፈው» ብሏል። ይህንኑም ከኤሚል ዞላ የአጻጻፍ ዘይቤ የወሰደው እንደሆነ ይናገራል።

ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ደራሲ፣ አርታኢ፣ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም - የልብ-ወለድ ድርሰት ገጸባህርይም ነው። ደራሲው የተሰኘው የበአሉ ግርማ ልብ-ወለድ በስብሐት ህይወት ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ነው። ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር የ2 ወንዶች እና የ3 ሴቶች አባት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነው።

ድርሰቶች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አምስት ስድስት ሰባት እና ሌሎችም ታሪኰች
ትኩሳት
7ኛው መልአክ
ሌቱም አይነጋልኝ
የፍቅር ሻማዎች
ስምንተኛው ጋጋታ
እነሆ ጀግና
ዛዙ(ትርጉም)
እግረ-መንገድ (1፣2)
የትረካ ጥበብ

መጣጥፎቹ የታተሙባቸው ጋዜጦች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አዲስ ዘመን
የኢትዮጵያ ሄራልድ
መነን መጽሔት
ቁም ነገር
ለዛ
ምእራፍ
እፎይታ
አዲስ አድማስ

ዋቢ ምንጭ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]