ሽመና

ከውክፔዲያ

የሽመና ጥበብ አጀማመር ታሪክ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በአዲስ አበባ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አዲስ አበባ ሸማኔ፣ በ፲፰፻፺ ዎቹ

(በአምሳሉ መላከ ብርሃን)

ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው በርካታ ባህላዊ አና ታሪካዊ እሴቶች መካከል የሕዝቦች ባህላዊ አለባበስ አንዱ ነው። ይህ ባህላዊ አለባበስ ደግሞ በአመዛኙ የሽመና ሥራ ውጤት ነው። የሽመና ሥራ በሀገራችን መቼና እንዴት እንደተጀመረ በትክክል የሚገልጽ የጽሑፍ መረጃ ባይኖርም ከሺ ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳለው አንዳንድ ጽሑፎች ይጠቁማሉ።

በሀገራችን የሺ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የሽመና ሥራ በአዲስ አበባ በስፋት የተዋወቀው ከጋሞ ተራራማ ቦታዎች ወደ አዲስ አበባ በተለያዩ ምክንያቶች በመጡ የጋሞ ማሕበረሰብ አባላት አማካይነት ከ፲፰፻፺፰ ዓ.ም. ጀምሮ ነው። በዚህ ዓመተ ምሕረት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ጋሞ ጎፋን የግዛታቸው አካል ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞ ንጉሡ ከማሕበረሰቡ አባላት መካከል ወታደሮችን እና አገልጋዮችን መልምለው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ውስጥ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተስፋፉ መምጣታቸው ከርዕሰ ከተማዋ የገበያ ፍላጎት ጋር ተዳምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የጉልበት ሠራተኞች ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል። ከእነዚህም መካከል የጋሞ ተወላጆች ይገኙበታል።

ሦስተኛው ምክንያት የጋሞ ተወላጆች ለዓፄ ምኒልክ ግብር ለማስገባትና አቤቱታቸውን ለማቅረብ ወደ መዲናዋ በብዛት መምጣት ነበር። በሌላ በኩል በቀለ ዘለቀ (፲፱፻፸፫ ዓ/ም) እንዳስገነዘቡት ከሰላሳ እስከ ሃምሳ ሺህ የሚሆኑ የጋሞ ተወላጆች በ፲፱፻ ዓ/ም. ጋሞጎፋን የጎበኙትን የዳግማዊ ምኒልክን እንደራሴ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲናግዴን አጅበው ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል። ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ወደ አዲስ አበባ የመጡ የጋሞ ማሕበረሰብ አባላት የሽመና ሥራን ከጀመሩባቸው ምክንያቶች መካከል በመሠረተ ልማት ግንባታው የሚከፈላቸው ገንዘብ በቂ አለመሆኑ እና ይዘው የመጡትን ግብርና አቤቱታ የሚያስተናግድ የቤተ-መንግሥት ባለሙያ ማጣታቸው ይጠቀሳሉ።

በዚህም ምክንያት ለብዙ ጊዜ በቤተ-መንግሥት አካባቢ በዛፍ ሥርና በሜዳ ላይ በመቀመጥ በደጅ ጥናት ጊዜያቸውን ያሳልፉ ነበር። በኋላም ችግሩ ሲጠናባቸው ከትውልድ ቀያቸው ይዘውት በመጡት የሽመና መሣሪያ አማካይነት የሽመና ሥራ መስራት ጀመሩ። /ጋሞዎች ከትውልድ ቀያቸው ለቀው ወደ ተለያየ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የሽመና መሣሪያቸውን ይዘው መሄድ የለመዱት ባህል ነው። በዚህ ወቅት ጋሞዎች የሽመና ሥራን በሁለት መንገድ ያከናውኑ ነበር። አንደኛ ሸማ ማሠራት በሚፈልጉ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት አጥር / በረንዳ ውስጥ መሣሪያቸውን በመትከል ይሰሩ ነበር። ለሥራቸውም የሚከፈላቸው የዕለት ምግብ ነበር። ከሥራቸውም በኋላ አመሻሽ ላይ አሁን የአሜሪካ ኤምባሲ በሚገኝበት አካባቢ በመሄድ ያድሩ ነበር።

ሁለተኛው ለቤተ-መንግሥት ባለሟሎች ተቀጥረው የሚሠሩ ናቸው። የሥራቸውንም ውጤት ለቤተ-መንግሥት ባለሟሎች ያቀርባሉ። ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከልም አምሳ /፶/ የሚሆኑት ወደ አንኮበር ተልከው የሸዋን የአሸማመን ጥበብ ተምረው እንደመጡ ጋሪሰን (፲፱፻፸፬ ዓ/ም) ያስረዳሉ። በዚህ ሁኔታ የሽመና ሥራቸውን በአዲስ አበባ የጀመሩ ጋሞዎች ታዋቂ የሆኑት ከ፲፰፻፺፰ ዓ.ም. እስከ በ፲፱፻ ዓ/ም. ባለው የጊዜ ክልል ውስጥ በአዲስ አበባ በተከሰተው ማሕበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ክስተቶች ምክንያት ነው።

በዚህ ወቅት ጋሞዎች እና ከጋሞ ውጭ የሆኑ የሽመና ባለሙያዎች በሌሎች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ የሚሰጣቸው ማሕበራዊ ደረጃ ዝቅተኛ ነበር። ሙያውም የተናቀ ነበር። በመሆኑም በወቅቱ ከከተማ ዕድገት ጋር በተፈጠረው የሥራ ዕድል በመጠቀም ከጋሞ ማሕበረሰብ ውጭ የሆኑ ብዛት ያላቸው ሸማኔዎች ሽመናን ሥራ በመተው ወደ ሌላ ሥራ ተሰማርተዋል። አንዳንድ የጋሞ ማሕበረሰብ አባላትም «በቂ» ነው ብለው የሚያስቡትን ገንዘብ ከአጠራቀሙ በኋላ ወደ ትውልድ ቀያቸው ይመለሳሉ። ምክንያቱም በጋሞ ተራራማ ቦታዎች የሽመና ሥራ እና ባለሙያው ከፍተኛ ማሕበራዊ ከበሬታ የተሰጠው ነበርና።

በተጨማሪም በዚህ የጊዜ ክልል ውስጥ ከውጭ ሀገር በተለይም ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገባ የጥጥ ምርት የአዲስ አበባን ገበያ ተቆጣጥሮት ነበር። የከተማዋ ነዋሪም ፊቱን ወደ ዘመን አመጣሾቹ የፋብሪካ ምርቶች አዙሯል። በዚህም ሰበብ በሽመና ሥራ የሚተዳደሩ ባለሙያዎች ገቢ አሽቆልቁሏል። ለችግርም ተጋልጠዋል። በመሆኑም ከጋሞ ውጭ የሆኑ ሌሎች የሽመና ባለሙያዎች በተፈጠረው የምጣኔ ሀብት ቀውስ ምክንያት ወደ ሌላ ሥራ ተሰማርተዋል። የጋሞ ማሕበረሰብ አባላት ግን የተፈጠረውን ማሕበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግር በጽናት በመቋቋም የአዲስ አበባ ምርጥ የሽመና ባለሙያዎች የሚያስብል ደረጀ ላይ መድረሳቸውን የተለያዩ ምሁራን መስክረውላቸው።

፲፱፻፭ ዓ/ም ጀምሮ የሸማ ተፈላጊነት የገነነበት ወቅት ነው። የቤተ-መንግሥት ባለሙያዎች እና ፊቱን ወደ ዘመን አመጣሹ የፋብሪካ ምርት አዙሮ የነበረው የአዲስ አበባ ነዋሪ ለተለያዩ ክብረ በዓላት / ለፋሲካ፣ ለጥምቀት፣ ለገና፣/ የማንነቱ መግለጫ አድርጎ በማሰቡ «የአበሻ ልብስ» የሚል ስያሜ ሰጥቷቸዋል። እንዲሁም ሸማዎች በሚለበሱበት የተለያዩ አጋጣሚዎች እና ዓውዶች ላይ የተጠቃሚዎችን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዋ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ደረጃ ማሳየት የጀመሩበት ወቅት ነው። የሸማ ሥራ በአዲስ አበባ በስፋት ከተዋወቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ፲፱፻፹፭ ዓ/ም አካባቢ ድረስ በብዛት የሚመረቱ ምርቶች ጋቢነጠላቀሚስጥበብ ልብስ፣ ሙሉ ልብስ ፣ ቡልኮ፣ መጠምጠሚያ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በዝማሬ የሚለብሱት ጥንግ ድርብ ነበሩ። ለሽመናም የሚጠቀሙበት ጥሬ ዕቃ ድርማግ እና ጥለት ነበር።እንደ አካባቢው ባህል ይለያይ እንጅ(ስሙ) ድግር መወርወሪያ እና የመሳሰሉትም የሽመና እቃ ውጤቶች ናቸው። የሽያጭ አገልግሎቱሎም በሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ ነበር ማለት ይቻላል። በእርግጥ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የሽመና ውጤቶችን ወደ ውጭ ሀገር ይዘው ይሄዱ ነበር።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በሽመና ዙሪያ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለእደ ጥበብ ባለሞያዎች ያለን ምልከታ ትንሽ መስተካከል ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም እንደተናቀ ስራ የመቁጠር አባዜ ስላለብን ነው። ይሄ ደግሞ አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ይሆናል። ነጮች ከብረት ቅጥቀጣ ተነስተው ወደ አውሮፕላን ሲያድጉ እኛ ግን....ነጮች ከሽመና ተነስተው ወደ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሲያድጉ እኛ ግን...."ብቻ ብዙ የቤት ስራ አለብን።

ሸማና ሥልጣኔ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

፲፱፻፹፭ ዓ.ም. በኋላ ለአዲስ የአሸማመን ስልት፣ ጥሬ ዕቃ፣ አልባሳት እና ጌጣጌጦች መታየት ጀምረዋል። በተለይም በውጭ ሀገር (በአውሮፓና በአሜሪካ) ባሉ «የፋሽን»፣ «የዲዛይን» እና «የስታይል» ማሠልጠኛ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በሽመና ሥራ ውጤቶች ላይ መሳተፋቸው አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር ለሽመና ባለሙያዎች የተለያዩ ተከታታይ ሥልጠናዎች መስጠታቸው እና የመንግስት አካላት የሸማ ባለሙያዎችን በማህበር እንዲደራጁ ማድረጋቸው ለለውጡ የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው። እንዲሁም የባህል ልብስ ዓውደ ርዕይ /ፋሽን ሾው/ አዘጋጆች፣ የግል እና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አዳዲስ የሽመና ሥራዎችን በማስተዋወቅ በተጠቃሚዎችና በአምራቾች መካከል የመገናኛ ድልድይ ፈጥረዋል። በዚህ ሁኔታ የተለያዩ የለውጥ አሻራ የታተመባቸው የሽመና ውጤቶች የዘመኑን ወጣት ቀልብ ለመሳብ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ወጣቱም ከዘመኑ ፋሽን እና ከፍላጎቱ ጋር የሚሄዱ አልባሳት፡- ሸሚዝ፣ ቀሚስ፣ ጉርድ ቀሚስ፣ ሚኒ ፓሪ፣ የአንገት ልብስ፣ ቦርሳ፣ የተለያዩ ጌጣጌጦች… ወዘተ በሽመና ሥራ መመረታቸው ፊቱን ወደ ሽመና ሥራ ውጤቶች እንዲመለስ ጋብዞታል። ይህም ሁኔታ ሰዎች የሀገራቸውን ምርት እንዲጠቀሙ እና በሀገራቸው ምርት እንዲኮሩ መንገድ ከፍቷል። በባዕድ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና አፍቃሪ ኢትዮጵያ የሽመና ውጤቶችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ሕዝቦች ባህላዊ አለባበስ ለሌላው ዓለም ሕዝብ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ለውጭ ንግድ በር ከፍተዋል። ያም ሆኖ ሀገራችን ወደ ውጭ ከሚላኩ አልባሳት በቀጥታ ተጠቃሚ አይደለችም። አልባሳቱ ወደ ውጭ የሚወጡት በመደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ ሳይሆን በግለሰቦች አማካይነት በሻንጣ ተይዘው ነው። በመሆኑም ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳት እና የዘመኑን የሽመና ውጤቶች የሚያሳይና የሚያስተዋውቅ ዓውደ ርዕይ / ፋሽን ሾው/ በማዘጋጀት ረገድ የበለጠ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

ሆኖም የዘመናዊው ትውልድ ጥንት ኢትዮጵያ ጥጡን አብቅላ፣ ፈልቅቃ ነድፋ፣ ፈትላ፣ ሸምና በመልበስ ራሷን በራሷ የምታለብስ እንደነበረና ሠለጠኑ የሚባሉት አገሮች እንኳን በዚህ ረገድ ችሎታ ቢስ እንደነበሩ በመዘንጋት ባህሉ ሲጠፋ፣ ዕውቀቱ ሲያወድም፣ ያችውም በስንት መባተል መድከም የምትገኘው የውጭ ምንዛሪ ለጨርቃ ጨርቅ መግዣ ወደ ሕንድ እና ቻይና ስትገበር እያየ ዝም ብቻ ነው ስሜቱ።

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ከብዙ ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደአገራቸው ሲመለሱ የገጠማቸውንና የተሰማቸውን «የሕይወቴ ታሪክ» በተባል መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ይሉናል፦

«አዲስ አበባ የገባሁ ዕለት ያገሬን ልብስ ለብሼ ነበር። በማግሥቱ ዘመዶቼ አስለወጡኝ። የፈረንጅ ልብስ ያስከብርሃል፤ ያማራው ያዋርድሃል እያሉ መከሩኝ። ስለዚህ ሐዘን ተሰማኝ፤ የተወልዶየን መምሰል አምሮኝ ነበር፤ ተሣቀቅሁ።.....በማግሥቱ ወደ ግቢ ሄድኩ፤ እንደአውሮፓውያን ለብሻለሁ፤ ልብሴ ሁሉ ፓሪስ የተሰፋ ዘመናይ ነው። ወደ ግቢ ስገባ እስከ ውስጠኛው በር ድረስ ከበቅሎ እንዳልወርድ ዘመዶቼ አስጠንቅቀውኛል። ገና ወደ በሩ ቀረብ ስል በረኛው ጮኸ። ዞር በሉ እያለ መንገዱን አስለቀቀልኝ። (እንደአማራ ለብሼ ቢሆን መመታት አይቀርልኝም ነበር)፤ በገዛ አገሬ ውስጥ ለመከበሪያየ የሰው ልብስ መከታ ስለሆነኝ ልቤ ተቃጠለ።» [1]

ዛሬስ ምን ለውጥ አለ?

ማገናዘቢያ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም፤ (፲፱፻፺፰ ዓ/ም)፣ ገጽ ፻፵፮ - ፻፵፯

ዋቢ ምንጭ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • ባህል፣ ቋንቋና ጥበብ ፦ አዲስ አበባ ባለፈውና በአዲሱ ሚሌኒየም

http://www.addismillennium.org/Addis%20In%20the%20Past%20Millennium%20&%20its%20Prospects%20in%20the%20the%20new%20Millennium(Amharic).pdf