Jump to content

አለቃ ታየ

ከውክፔዲያ
አለቃ ታዬ

አለቃ ታየ ገብረማርያም ልደት በዘመነ ወንጌላዊ ሉቃስ፣ ኅዳር ፳፩ ቀን ፲፰፻፶፫ ዓ/ም። ይህም አፄ ቴዎድሮስ በነገሡ በሰባተኛው ዓመት መሆኑ ነው።

ጣና ሐይቅ በስተምስራቅ በምትገኘው ልዩ ስሟ ይፋግ ተብላ በምትታወቀው መንደር የተወለዱት አለቃ ታየ በልጅነታቸው ወራት ወላጆቻቸውን በማጣታቸው፣ የእናታቸው ወንድም ትግራይ ይኖሩ ስለነበር አጎታቸውን ፍለጋ ወደ ትግራይ ያመራሉ። እዚያም እንደደረሱ አጎታቸውን ስላጡዋቸው ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ አቅደው ምፅዋ ደረሱ። ምፅዋ ይገኝ በነበረው የስዊድናውያን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመሩትም ያኔ ነበር።

በዚያው ትምህርት ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኦሮምኛ የተረጎሙት ኦኔሲሞስም ይማሩ ነበር። እምኩሉ በተባለው በዚህ ትምህርት ቤት ለብዙ ዓመታት የወንጌልን ቃል ከተማሩ በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ጎጃም ተመለሱና የግዕዝ ቅኔ ትምህርት ቤት ገቡ። ቅኔውን ከሙሉ አገባቡ ጋር አሳምረው ከዘረፉ በኋላ አለቃ የሚለውን ከፍተኛ ማዕረግ አግኝተው እንደገና ምፅዋ በመመለስ በተማሩበት እምኩሉ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገለገሉ ።

በዚህ ጊዜም "መጽሐፈ ሰዋሰው " የተሰኘውን የመጀመርያ መፅሐፋቸውን ፅፈዋል። አለቃ በሕይወት ዘመናቸው ከደረሷቸው መፅሐፍቶቻቸው ዋና ዋናዎቹ እስካሁን ድረስ የሚገኘው በስዊድንኛ ቋንቋ የጻፉት en Teologisk strid infor Ras Mengescha" ( A theological debate before Ras Mengesha....ወይም ነገረ መለኮታዊ ክርክር በራስ መንገሻ ችሎት ) እና በእጅ ፅሑፋቸው የተዘጋጀውና አብዛኛው ማጣቀሻው በግዕዝ የሆነው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ወይም የፅንሰ-ሐሣብ መዝገብ ናቸው ።

እንደገና ወደ ትውልድ መንደራቸው የተመለሱት አለቃ ታዬ በወቅቱ ቤጌምድርን ይገዙ በነበሩት በራስ መንገሻ አቲከም ዘንድ ሞገስ በማግኘታቸው በ፲፰፻፺፩ ዓ/ም ወደ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ላኩዋቸው ። ለንጉሠ ነገሥቱም የበኩር ሥራቸው የሆነውን መፅሐፈ ሰዋሰውን በገጠ በረከትነት ሰጡ። ንጉሠ ነገሥቱም የግል ፀሐፌያቸውን ፀሐፌ-ትዕዛዝ ገብረሥላሴን ባልደረባ አድርገው ሰጡዋቸው። በንጉሠ ነገሥቱ እና በመኳንንቱ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ በማግኘታቸው የቀኑ አንዳንድ የቤተ ክህነት ሰዎች «አለቃ ታዬ ትምህርቱን የቀሰመው ከሚስዮናውያን ነው» በሚል ሰበብ ብቻ ክስ ያበዙባቸው ስለነበር ይህኑኑ ጉዳይ ለአፄ ምኒልክ አመልክተው የሚከተለውን ደብዳቤ ተቀበሉ፦

«ሞዐ አንበሳ ዘዕምነገደ ይሁዳ፣ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ። አለቃ ታየ ገብረማርያም የሚባል ምጥዋ የነበረ ሀይማኖቱን እኛ መርምረነዋልና ማንም አንዳች አይበለው በሀይማኖት ነገር ። በኅዳር ወር በስድስተኛው ቀን ፲፰፻፺፩ ዓ/ም በወረኢሉ ከተማ ተፃፈ ።»

ከዚህ በኋላ ወደ ቤጌምድር ተመልሰው ሥራቸውን ቀጠሉ። ዳሩ ግን አሁንም «የታዬ ሀይማኖት የፈረንጅ ነው። ንጉሡ ሳያውቁ ነው ማህተም የሰጡት።» የሚሉ ከሳሾች በመነሳታቸው እንደገና ተከሰው ግብፃዊው ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ፊት ቀረቡ። አቡነ ማቴዎስም ጉባዔ ከተው አለቃ ታዬን ካስጠሩ በኋላ «አንት አህያ ! ሀይማኖትህ ምንድነው?» በማለት ሲጠየቁዋቸው፤ አለቃም «እኛን አህያ የሚያስብለን እናንተን በመሾማችን ነው።» ብለው ስለመለሱ፣ ነገሩ እየከረረ መጥቶ ንጉሠ ነገሥቱ ፊት ድረስ ደረሰ። ዳግማዊ ምኒልክም አለቃንም ሊቀ-ጳጳሱንም ገስጸው ነገሩን ካበረዱት በኋላ ወደ ቤጌምድር መልሰው ላኩዋቸው። ወድያውኑም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ደረሳቸው፦

«ሞዐ አንበሳ ዘዕምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ። ይድረስ ከአለቃ ታዬ፣ እንደምን ሰንብተሀል? ከንምሳ መንግሥት ተልከው የመጡ ሰዎች ወደ ሀገራቸው ለመሄድ በጎጃም በኩል ወጥተዋል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ቋንቋ የተፃፉ የጥንት መፅሐፍት በአገራችን አሉ ያንን የሚያውቅ ብልህ ሰው ይሂድና እንዲመለከት ይሁን ብለውኛል። አንተ የዚያን ሀገር ባህል ለምደኸዋልና እናንተ ዘንድ በደረሱ ጊዜ አንተም ከነሱ ጋር አብረህ ሂድ። መጋቢት ፱ ቀን ፲፰፻፺፯ ዓ/ም አዲስ አበባ ከተማ ተፃፈ።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ 'የሕይወት ታሪኬ' በሚለው መፅሐፋቸው ይህኑኑ ሁኔታ እንዲህ ገልጠውታል፦ «የጀርመን መንግሥት የግዕዝ ቋንቋ የሚያስተምር አንድ ሊቅ ይሰጠኝ ብሎ ዓፄ ምኒልክን በለመነ ጊዜ ስመ-ጥሩውን ሊቅ አለቃ ታዬን መርጠው ሰደዱዋቸው። በጀርመን መንግሥት ሦስት ዓመት ሙሉ የግዕዝ ቋንቋ አስተምረው ኒሻን ተሸልመው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ፣ ዓፄ ምኒልክም ኒሻን ሸልመው የአባታቸውን አገር ሰጥተው ወደ ቤጌምድር ሰደዱዋቸው።

አለቃ ታዬ በአውሮፓ አኅጉር በቆዩበት ጊዜ ብዙ ሀገራትን ጎብኝተዋል። የሚከተለው ከግል ማስታዋሻ ደብተራቸው የተገኘ ነው።


ማክሰኞ ግንቦት ፳፪ ቀን ፲፰፻፺፯ ዓ/ም

በዚህ ቀን ሌሊቱን ስንሄድ አድረን ማለዳ ሲቂልያ በ፮ ሰዓት ደረስን። ስንሄድ ውለን ማታ በ፯ ሰዓት ኒያፓል ገብተን አደርን። ሲቂልያ የኢጣልያ ክፍል ናት እርስዋም ቃሮዳን የምታህል ታላቅ ደሴት ናት። ከተሞቿም በባሕር ዳር ተሠርተው እጅግ የሚያምሩ ናቸው። ኒያፓልም በባሕር ዳር የተሠራ የጥንት የጣልያን ነገሥታት ከተማ ነው። ዛሬ ግን ራሱ ከተማው ሮማ ነው።


ቅዳሜ ግንቦት ፳፮ ቀን ፲፰፻፺፯ ዓ/ም

በዚህ ቀን በማርሴል ዋልን። ባቡሪቱ ዕቃ ስታወርድ ዕቃ ስትቀበል ዋለች። እኔና ዮሴፍ ሱማሊ በ፰ ሰዓት ከባቡር ወጥተን በሰረገላ ከተማ ለከተማ እኩል ሰዓት ሄድነ። ወርደን በእግራችን ደግሞ እየዞርን ብዙ ነገር አየነ። በዚያም እጅግ ሀፍረት የሌላቸው ደፋሮች ጋለሞቶች አየነ። በ፭ ሰዓት ወደ ማታ ባቡራችን ገብተን አደርነ።

አለቃ በጀርመን ቆይታቸው ከዓፄ ምኒልክ ጋር እየተፃፃፉ በግዕዝ የተፃፉትን መፅሐፍት ከመሰብሰብና ከመመርመር በተጨማሪ አማርኛንና ግዕዝን በበርሊን ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል።


ጳጉሜ ፫ ቀን ፲፰፻፺፰ ዓ/ም ለንጉሠ ነገሥቱ የፃፉት ደብዳቤ እንዲህ ይነበባል፦

«.....እኔ ያስተማርኩዋቸው አማርኛና ግዕዝ ያነባሉ ይፅፋሉ። ...ደህና ሰዎች ናቸው ....የጃንሆይ መልክተኛ ብለው አክብረውና አፍቅረው ይዘውኛል ...ከአገር ናፍቆት በቀር የጎደለብኝ ነገር የለም ......ለጥበባቸው ፍፃሜ የለውም ....በየዕለቱ አዲስ ነገር አያለሁ .....አዲስ ነገር እሰማለሁ።»

«ጃንሆይ ከአገርዎ ልጆች ወደ አውሮፓ ሰደው ቢያስተምሩ መልካም በሆነ ....የያጆንና የሞሮኮ መንግሥት ሰው እየሰደዱ አስተማሩ ....ይህን አይቼ ለአገሬ መንግሥት ቅንአት እንደ እሳት በላኝ ....ምንኮ አደርጋለሁ ? አዝኘ ወደ መቃብር እወርዳለሁ .....የጃንሆይ ብር እንዲሰለጥን (እንዲለመድ ማለታቸው ነው) የፊተኛውን ብርና አሞሌ ያጥፉ .....»

በማከታተልም በግንቦት ወር ፲፰፻፺፱ ዓ/ም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለንጉሠ ነገሥቱ ፃፉ፦

«...እኛ ሀበሾች በመንፈሳዊና በሥጋዊ ጥበብ ወደፊት የማንገፋበት ምክንያት ምን ይሆን? ብሎ ለሚጠይቅ ሕዝቡ ሁሉ ባይማርና የወንጌልን ስብከት በብዙው ባይሰማ እውነተኛ እውቀትና አፍቅሮ-ቢጽ፣ ትህትና ቢጠፋ ነው .....ባገራችን ጥቂት ዕውቀት ያላቸው ሰዎች በመከበር ፈንታ ስለሚሰደቡና ስለሚዋረዱ ስለሚጠቁም የሚያውቁትን ጠቃሚ የጥበብ ሥራ ትተው በቦዘን መኖርን መረጡ።»

«የአዳምን ልጆች ሁሉ የፈጠረ አድልዎ የሌለበት አንድ ልዑል እግዚአብሔር ነው። ላንዱ ወገን ሕዝብ ሙሉ ላንዱ ጎደሎ ልብ አልፈጠረም .....እንዲህ ከሆነ ስለምን ያውሮፓና የእስያ ልጆች ካፍሪካ ክፍልም ጥቂቶች ብልሀተኞች ሲሆኑ ....እኛ ሀበሾች መፅሐፍ ቢማሩ፣ 'ኮቸሮ ለቃሚ'፤ ብር እና ወርቅ ቢሠሩ፣ 'ቀጥቃጭ፣ ቡዳ'፤ እንጨት ቢሠራ፣ 'አናጢ፣ እንጨት ቆርቋሪ'፤ ቆዳ ቢፍቅ 'ጥንበ-በላ፣ ፋቂ' እየተባለ ስም እየተሰጠው ስለሚሰደብ የጥበብ ሥራ ጠፋ። ስለዚህ ጉዳይ ጃንሆይ አስበው እንዲህ ያለው ነገር በአዋጅ እንዲከለከል፣ ሰዎች እንዲከበሩ ቢያደርጉ በሌላ መንግሥት ስምና መልክ በተቀረጸ ገንዘብ (የማሪያ ተሬዛ ብር ማለታቸው ነው) ከመገበያየት በጃንሆይ መልክና ስም ገንዘብ እንዲወጣ ቢያደርጉ ነፃ መንግሥትም ራሱን የቻለና የተምዋላም ይሆናል።»

ይህ ደብዳቤ ከተፃፈ ከአራት ወር በኋላ ጥር ፲፯ ቀን ፲፱፻ ዓ/ም ዓፄ ምኒልክ የትምህርትን አስፈላጊነትና የሥራን ክቡርነት ያካተተውን፤ «ሠራተኛን በሥራው የምትሰድብ ተወኝ» የሚለውን አስደንጋጭና ብርቱ አዋጅ አወጁ። [1]

ከጀርመን አገር ሲመለሱ የኢትዮጵያን ሦስተኛ ደረጃ የክብር ኮኮብ ኒሻን የተሸለሙት አለቃ ታዬ፣ በቤጌምድር እንደገና ታላቅ ተቃውሞ ተነሳባቸው። የአገሩ ገዢ የነበሩት ራስ ወልደጊዮርጊስ አቦዬም (በኋላ ንጉሥ) የሚከተለውን ደብዳቤ ሰደዱላቸው፦

«የተላከ ከራስ ወልደጊዮርጊስ፤ ይድረስ ከአለቃ ታዬ እንዴት ሰንብተሀል? እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። ዝም ብለህ ተቀመጥ ስንልህ እንደዚህ ያል ትምህርት ከየት ነው ያመጣኸው? በምን ተጣላኝ እንዳትል! በ ፲፱፻፫ ዓ/ም ኅዳር ፳፬ ቀን ተፃፈ።»

አለቃም ሀይማኖታቸው ተዋሕዶ መሆኑንና የተፈጠመባቸውም ግፍ መሆኑን በመግለፅ ደብዳቤ ፅፈው ላጼ ምኒልክ መልስ ላኩ። ንጉሠ ነገሥቱም የተወሰደባቸው መሬት እንዲመለስላቸው ትዕዛዝ ሰጡ። ሁኔታው ያልተዋጠላቸው የቤተ ክህነት ሰዎች ታዬ ፀረ ማርያም ነውና አገር መግዛት አይገባውም የሚል ሌላ ክስ አመጡ። ነገሩ የሀይማኖት ጉዳይ በመሆኑ ወደ ግብፃዊው ሊቀ-ጳጳስ ዘንድ ነገር ተመራና ጥር ፳፬ ቀን ፲፱፻፫ ዓ/ም በዋለው ጉባዔ አለቃ ፈለቀ የተባሉ የቤተ-ክህነት ወኪል ከሳሽ ሆነው በመቅረብ፣ «አለቃ ታዬ ለስዕልና ለመስቀል አይሰግድም፤ በሞቱ ቅዱሳን አማላጅነት አያምንም፤ ዝክርና ምፅዋት የሞተ ሰውን ሊያፀድቅ እንደማይችል ይናገራል፤ የልማድ ፆም ዋጋ እንደሌለው ይናገራል፤ ቀናትን አያከብርም» ሲሉ የክሱን ጭብጥ አስረዱ።

በቀረቡት ክሶች ላይ ከፍተኛ ክርክር ተደርጎ ሊቀ-ጳጳሱ ከመሳፍንቱና ከባልደረቦቻቸው ጋርዔ በመሆን አለቃ ታዬን ከገሰፁ በኋላ በነፃ ቢለቁዋቸውም፤ በነፃ መለቀቃቸው ያበሳጫቸው ካህናት የንጉሠ ነገሥቱ ባለ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ለነበሩት ለራስ ተሰማ ናደው አቤት በማለታቸው ያለ ሕግ ወደ ታላቁ ወህኒ ቤት እንዲገቡ ተደረገ።

ከጥቂት ጊዜ እሥራት በኃላ ተፈተው በቁም እሥር እንዲቆዩ ተደርገው፣ በ፲፱፻፲፪ ዓ/ም ለመንግሥት አማካሪነት ተመርጠው መሥራት ጀምረው ነበር። ምሁሩ አለቃ ታዬ ነሐሴ ፲፭ ቀን ፲፱፻፲፮ ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

በቀብራቸው ወቅት እህታቸው ወይዘሮ ላቀች አምነህ እንዲህ ሲሉ ተቀኙላቸው

ከወህኒ ቤት አስረው የዘጉበት ሳንቃ

ብሎ ተናግሮ ነው የወንጌል ቃል ይብቃ

የወንጌልን ስራት ተማሩ ቢላቸው

ትልቁም ትንሹም ሁሉም ደደብ ናቸው

አሉት ጸረ ማርያም መልስ ቢሳናቸው

እውቀትና ምግባር ጉድጓድ ተከተተ

አራት ነው እንጂ መች አንድ ሰው ሞተ

ወዝውዘው ወዝውዘው ጣሉት እንደ ዝሆን

ያው ወደቀላቸው ይበሉት እንደሆን

ከጨለማ መሀል ቢወጣ ብርሀን

ኣጥፉት አጥፉት አሉ እንዳይታየን


የግርጌ ማስታወሻ

[2]

  1. ^ ጳውሎስ ኞኞአጤ ምኒልክ (፲፱፻፹፬ ዓ/ም)፣ ገጽ ፪፻፴፰ - ፪፻፴፱
  2. ^ ኃይሉ ከበደ የአለቃ ታዬ ገብረማርያም የሕይወት ታሪክ ቀ .ኃ . ሥ . ዩኒቨርሲቲ 1963 ኅሩይ ወልደሥላሴ (ብላቴን ጌታ) የሕይወት ታሪኬ አ .አ . 1951 ገብረሕይወት ባይከዳኝ ...አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ ብርሀን ይሁን ማተሚያ ቤት አስመራ 1912 ባህሩ ዘውዴ pioneers of change in Ethiopa....the reformist intellectualls at the early twentineeth century,Oxford 2002 Getachew Hayle......Aasulv Land, Samuel Robinson (eds-) the missionary factor in ethiopia........Lund university August 1996 Prouty,Chris..... Empress Taytu and Minilik 2nd Ethiopia....1883-1910 London