ወርቃማው ሕግ

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

ወርቃማው ሕግክርስትና አለም ማለት በተለይ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ያስተማረው ቃል ነው፦

«እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፣ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።» (የማቴዎስ ወንጌል 7:12)

ጽንሰ ሀሣቡ ከብሉይ ኪዳንሕገ ሙሴ ዘመን ጀምሮ ይገኛል፣ ከዚያም በኋላ ተመሳሳይ መርኆች በሌሎች እምነቶች ወይም ፍልስፍኖች በጽሑፎቻቸው ታይተዋል። በጊዜ ላይ ተመሳሳይ ሀሳቦች በመላው ዓለም በመስፋፋት፣ እንዲህ ያለ መርኅ የብዙ ባህሎች ስነልቡናዊ እና ኅብረተሠባዊ መሠረት ሆንዋል። በተለይም፦

 • አይሁድና፦ «ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ...» - ኦሪት ዘሌላውያን 19:18 (ምናልባት 1660 ዓክልበ. ግድም)
 • ሂንዱኢዝም፦ «ዳርማን (ምግባርን) ዋና ትክተትህን በማድረግ፣ ራስህን እንደምታድርግ ሌሎችንም አድርግ።» - መሃበራተ ሻንቲ ፐርቨ 167:9 (ምናልባት 950 ዓክልበ. ግድም)
 • ግሪክ ፈላስፋ፦ «ሌሎች ቢያደርጉት የምትወቅሰውን ነገር አንተም ከማድረጉ ይቅርብህ።» - ጣሌስ (600 ዓክልበ. ግድም)
 • ቡዲስም፦«ራስህን የሚጎዳ ቢመስልህ፣ ሌሎችን እንደዚያ እንዳትጎዳቸው።» - ጎታማ ቡዳ ኡዳነቨርገ 5:18 (500 ዓክልበ. ግድም)
 • ጃይኒስም፦ «ሰው ሲመላለስ እሱ ሊደረግለት እንደሚወድደው ለፍጥረቶች ሁሉ ማድረግ ይገባዋል።» - ሱትረክርታንጋ 1:11:33 (500 ዓክልበ. ግድም)
 • ኮንግ-ፉጸ ፍልስፍና፦ «ሰውን በሕይወት የሚመራው አንድያ ቃል አለ? ሲጠየቅ "በራስህ ላይ የማትወድደውን በሌሎች ላይ አታድርግ" ብሎ መለሰ።» - አናሌክትስ 15:24 (480 ዓክልበ. ግድም)
 • ግሪክ ፈላስፋ፦ «ሌሎች ቢያድርጉብህ የሚያስቆጣህን ሥራ በነርሱ ላይ አታድርግ።» - ኢሶክራቴስ (400 ዓክልበ. ግድም)
 • የግብጽ ጽሑፍ፦ «ባንተ ላይ ቢደረግ የጠላኸውን በሌላው ላይ አታድርግ።» - ፓፒሩስ Brooklyn 47:218:135 (350 ዓክልበ. ግድም)
 • ግሪክ ፈላስፋ፦ «ባንተ ላይ ቢደርስብህ የማትወድደውን አንተም ራስህ አታድርግ።» - ሴክቲዩስ (50 ዓክልበ. ግድም)
 • ታሚልኛ ሂንዱ ጽሁፍ፦ «ራስህን የሚጎዳ መሆኑ ቢታወቅልህ፣ በሌሎች ላይ አታድርገው። » ቲሩኩራል (1 ዓም ግድም?)
 • አይሁድና፦ «አንተን የሚያስከፋ ነገር በባልንጀራህ ላይ አታድርግ፤ ይህም መላው ኦሪት ነው፤ የተረፈውም ዝርዝር ነው።» - የባቢሎን ተልሙድ ሻባጥ 30:a (400 ዓም ግድም)
 • እስልምና፦ «ለራሱ እንደሚወድድ ለባልንጀራውም እስከሚወድድ ድረስ፣ ከናንተ ማንም ሰው እምነት የለውም።» - ነቢዩ ሙሐመድ፣ የተለያዩ ሀዲስ (600 ዓም ግድም)
 • ዞራስተር እምነት ጽሑፍ፦ «ለራስህ የማይስማማ ነገር በሌሎች ላይ አታድርግ።» - ሻየስት ኔ ሻየስት 13:29 (800 ዓም ግድም)
 • ዳዊስም፦ «የባልንጀራህን ጥቅም እንደ ራስህ ጥቅም፣ የባልንጀራህን ጉዳት እንደ ራስህ ጉዳት አስብ።» - ድርሰት ስለ ዳው መልስ (1200 ዓም ግድም)
 • ሂንዱኢዝም፦ «መላው ዳርማ በጥቂት ቃላት ቢነገር፣ ይህ ነው፤ ለኛ የማይስማማው ነገር በሌሎች ላይ አታድርግ።» - ፓድመ ፑረና 19:357 (1400 ዓም ግድም)
 • ባኃኢ እምነት፦ «ዓይኖችህ ወደ ፍትሕ ቢዞሩ፣ ለራስህ የመረጥኸውን ለባልንጀራህም ምረጥ።» (1850 ዓም ግድም)