Jump to content

ጌዴኦ

ከውክፔዲያ
ጌዴኦ
አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት
986,977
በስፋት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች
 ኢትዮጵያ
ቋንቋዎች

ጌዴኦኛአማርኛ

ሀይማኖት

በአብዛኛው ፕሮቴስታንት ክርስትና፣ ባህላዊ እምነት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና

ተዛማጅ ብሔሮች

ጉጂ ኦሮሞሲዳማወላይታ

ጌዴኦ በደቡብ ማእከላዊ ኢትዮጵያ የሚነገረው የአፍሮ እስያ ቤተሰብ ሃይላንድ ምስራቅ ኩሺቲክ ቋንቋ ነው። የቋንቋው ተለዋጭ ስሞች ዴራሳ ፣ ዴሬሳ ፣ ዳራሳ ፣ ጌዴኦ ፣ ዴራሳንያ ፣ ዳራሳ ያካትታሉ። ከዲላ ደቡብ ምዕራብ እና ከአባያ ሀይቅ በስተምስራቅ በሃይላንድ አካባቢ በሚኖሩ የጌዴኦ ሰዎች ይነገራል።[1]

ጌዴኦኢትዮጵያ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኝ ብሔር ነው። የጌዴኦ ብሔረሰብ በዋናነት በጌዴኦ ዞን ውስጥ ባሉ ስድስት ወረዳዎች በስፋት የሚኖር ሲሆን ከዞኑ ውጪም በሲዳማ ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል በቦረና እና በጉጂ ዞኖች በሚገኙ አጎራባች አካባቢዎች ወይንም ወረዳዎች በብዛት እንደሚገኙ ይገመታል። የጌዴኦ ብሔረሰብ በዋናነት በሚገኝባቸው የከተማና የገጠር አካባቢዎች ሌሎች የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የሲዳማ፣ የወላይታ በተለይም ደግሞ በከተሞች የጉራጌ እና የስልጤ ብሔረሰብ አባላት ከብሔረሰቡ ጋር በስብጥር ይኖራሉ። በሰሜን ከሲዳማ በደቡብ በምስራቅ እና በምዕራብ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ጋር ይወሰናል። በ፲፱፻፺፱ ዓ/ም በተደረገው የቤቶችና ሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሠረት የብሔረሰቡ ሕዝብ ብዛት በግልፅ አይታወቅም ይሁን ግን የተለያዩ ጥናት እንደ ምያሳዩ 3.4.ሚሊዮን ህዝብ ይሆናል ተብለው ይገመታል።

መልከዓ ምድር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የጌዴኦ ብሔረሰቡ በስፋት የሚገኝበት አካባቢ በአብዛኛው ተራራማና ወጣ ገባ፣ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ሜዳማ የሆነ መልክዕ ምድራዊ ገጽታ ያለው ነው። ብሔረሰቡ ከሚገኝበት ወረዳዎች መካከል ቡሌ፣ ይርጋጨፌ፣ ኮቸሬ እና ገደብ ወረዳዎች ደጋና ወይና ደጋ የሆነ የአየር ንብረት ሲኖራቸው የተቀሩት የወናጐ እና ዲላ ዙሪያ ወረዳዎች ደጋ፣ ወይናደጋ እና ቆላማ የአየር ንብረትን ያካተቱ ናቸው።

የጌዴኦ ብሔረሰብ ኢኮኖሚ የተመሠረተው በእርሻና በከብት እርባታ ሲሆን ከእርሻ ምርቶቹ መካከል ቡና እና እንሰት ከፍጆታ አልፈው ለገበያ የሚውሉ ዋና ዋና ምርቶች ናቸው። በተለይ በተለይ በይርጋጨፌ እና አጎራባች ወረዳዎች የሚመረተው የቡና ምርት ለአለም አቀፍ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ የሚቀርብ በመሆኑ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ያስገኛል።ከዚሁ ጋር ተያይዞ የእንሰት ምርት ውጤት የሆነው «ቆÝ» ከሕዝቡ የእለት የምግብ ፍጆታ አልፎ በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ለገበያ ይቀርባል። ከነዚህ ዐበይት የእርሻ ምርቶች በተጨማሪ ከእህል ሰብሎች ገብስ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ባቄላ፤ ከፍራፍሬ ምርቶች ሙዝ፣ አቦካዶ፣ማንጐ፣ ጊሽጣ እና አናናስ ፣ከስራስር ምርቶች ስኳር ድንች፣ጐደሬና ቦይና እንዲሁም ከቅመማ ቅመም ኮረሪማ እና ዝንጅብል ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በብሔረሰቡ ውስጥ የሚገኙ የእደ ጥበብ ባለሙያዎች በአካባቢያቸው ከሚያገኙዋቸው ጥሬ እቃዎች ለማህበረሰቡ አገልግሎት የሚውሉ የእደ ጥበብ ውጤቶችን በማምረት ከእርሻና ከከብት እርባታ በተጓዳኝ ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ኑሮአቸውን ይደጉማሉ።

ዋና መጣጥፍ፦ ጌዴኦኛ

የጌዴኦ ብሔረሰብ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ጌዴኦኛ ሲሆን በብሔረሰቡ አባላት ጌዴኡፋ በመባል ይጠራል። በኩታ ገጠም ወይም አጎራባች ሥፍራዎች ያሉ የብሔረሰቡ አባላት ከጌዴኦኛ በተጨማሪ ሲዳምኛን እና ኦሮሚኛን እንዲሁም በከተሞች ያሉ ደግሞ አማርኛን በሁለተኛ ደረጃ ይጠቀማሉ።

ታሪካዊ አመጣጥ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የቀድሞዎቹ የጌዴኦ ብሔረሰብ አባላት/ ሕዝቦች/ ታሪካዊ አመጣጥ በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኘው እና ልዩ ስሙ «ሐርሱ» ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ተነስተው የሐዋጣን ወንዝ ተሻግረው «ሐሮ ወላቦ» በዛሬው" ቡሌ ወረዳ" አካባቢ እንደሰፈሩ የብሔረሰቡ የእድሜ ባለ ፀጋ አዛውንቶች ከአያት ቅደመ አያቶታቸው የተላለፈላቸውን ትውፊት መሠረት አድርገው ይናገራሉ። አያይዘውም እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የጌዴኦ አባቶች እና እናቶች በ«ሐሮ ወላቦ» አካባቢ ከሰፈሩና ከተባዙ በኋላ «አዳ ያኣ» በሚባለው የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ የሚመሩበትንና የሚተዳደሩበትን ባህላዊና መንፈሣዊ ሥርዓትና ደንብ ማደራጀታቸው ታሪኩን የሚያውቁ የሀገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ። በእነዚህ ሰዎች አገላለጽ «ደረሶ» የብሔረሰቡ መጠሪያ እንደሆነ ፤ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የነበሩት የገዢ መደቦች የብሔረሰቡን ማንነት ዝቅ ለማድረግ ሲሉ «ደረሶ» የሚለውን በማዛባት «ደራሣ» በማለት ይጠሩት እንደነበር ይነገራል። ስያሜው በብሔረሰቡ አባላት እያሣደረ የመጣውን መጥፎ ጠባሣ ለመፋቅ ሲባል በፊውዳሉ ሥርዓት ወቅት የተሰጠውን ስያሜ በ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. «ጌዴኦ» በሚል ስያሜ እንዲተካ በብሔረሰቡ አባላት ጥያቄ ቀርቦ ውሣኔ አግኝቷል።

የጌኤኦዎች አባት የነበረው ደረሶ ከሁለት ሚስቶች የወለዳቸው ሰባት ልጆች እንደነበሩትና እነዚህም ዳራሻ ፣ ጐርጐርሻ፣ ደቦኣ፣ ሀኑማ፣ ጤምባኣ፣ ሎጐዳ እና በካሮ በመባል እንደሚጠሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። እነዚህ ከ"ደረሶ" ሁለት ሚስቶች የተወለዱት ልጆች በሙሉ ከጥንት ጀምሮ ሁሉም ጌዴኦዎች እንደሚባሉና የብሔረሰቡ የጐሣ መሠረቶች እንደሆኑ ታሪኩን የሚያውቁ አዛውንቶች ይናገራሉ። እነዚህ ሰባቱ የጐሣ መሰረቶች በውስጣቸው ሌሎች ንዑሣን ጐሣዎች አካተው ይዘዋል።

ባህላዊ አስተዳደር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የጌዴኦ ብሔረሰብ አባላት ባህላዊውን የገዳ ስርዓት ከመመስረታቸው በፊት በእማዊ ዘመን ይተዳደር እንደነበር ይነገራል። ይህ ዘመን የሴቶች ፈላጭ ቆራጭነት የነገሠበት፣ በወንዶች ላይ የሴቶች የበላይነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ "የአኮማኖዬ" ዘመን ተብሎ ይጠራ ነበር። «አኮማኖዬ» የቤተ መንግስት የማዕረግ ስም ሲሆን በዚህ ሥርዓት አንድ ንግስት ስትሞት ሌላኛዋ ሥርወ መንግስቱን እየተካች ለረጅም ዓመታት ሕዝቡን እንዳስተዳደሩ በአፈ ታሪክ ይነገርላቸዋል። በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበረው ይኽው የአኮማኖዬ የአስተዳደር ስርዓት በነበረው አምባገነናዊ ባህርይ በወንዶች ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደሩ እና ሊከናወን የማይቻል ትዕዛዝ በመስጠቱ በአመጽ ከስልጣን እንደተወገደ አባቶች ያስረዳሉ። በአኮማኖዬ እግር የተተካው ባህላዊ አስተዳደር «የጐሣሎ» አስተዳደር እንደነበር ተያይዞ ይነገራል።

ይህ የጐሣሎ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት በባህሪይው አሀዳዊና አምባገነናዊ በመሆኑ እንደቀድሞው የአንድ ሰው ፊላጭ ቆራጭነት የነገሰበት ነበር። በዚህ የተነሣ የአንድ ጐሣሎ አስተዳደር የሥልጣን መቆያ ጊዜው የተወሰነ ስላልነበር በዕድሜ መግፋት ወይንም በጤና መታወክ ምክንያት ለሚቀጥለው እስከሚያስተላልፍ ድረስ ሕዝቡን በፈላጭ ቆራጭነት ይመራ እንደነበር የብሔረሰቡ የሀገር ሽማግሌዎችና ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። በጐሣሎው አምባገነናዊ አስተዳደር እጅግ የተማረሩ የብሔረሰቡ አባላት የጎሣሎን መሪ በሀይል በማስወገድ የጌዴኦ ባህላዊ የገዳ አስተዳደር ሥርዓት ለመመስረት በቅተዋል።

በወቅቱ በአዲስ መልኩ የተመሠረተው የገዳ ሥርዓት የተለያየ የስልጣን እርከን ባላቸው ክፍሎች የተደለደለ፣ ሁሉም የየራሳቸውን የሥራ ድርሻ ሊያከናውኑ በሚችሉበት መልክ የተዋቀረ በመሆኑ ሥርዓቱ በባህሪው በጣም ዲሞክራሲያዊ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይነገራል። ይህ የጌዴኦ የገዳ ሥርዓት ዘጠኝ አባላት የሚገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ያለው ሲሆን አመራር የሚሰጠው በጠቅላላ ጉባኤው በብሔረሰቡ ቋንቋ በ«ያኣው» ነው። የያኣው አባላት ልዩ ልዩ የስልጣን ደረጃዎች ያሏቸው ሲሆን እነዚህ የስልጣን እርከኖች በተዋረድ "አባ ገዳ" ፣ “ጃላባ”፣ “ሮጋ”፣ “ጃልቃባ”፣ እና "ሀይቻ" በመባል ይታወቃሉ። የሁሉም የበላይ የሆነው አባ ገዳ የሥርዓቱ የበላይ መሪ እና ለሕዝቡ ስላምን፣ ብልጽግናን፣ ፍቅርን ጤናን የሚለምን በመሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ከማንኛውም ሀጢያትና መጥፎ ሥራ የነፃ ነው ተብሎ ይታመናል። ሁለተኛው የስልጣን እርከን "ጃላባ" የሚባለው የአባ ገዳው ምክትል ሲሆን ዋና ተግባሩ ከአባ ገዳው መልዕክት እየተቀበለ ለ"ሮጋ"ዎች የሚያቀብልና ከሌሎችም አካላት መልዕክት በመቀበል ለአባ ገዳው የማድረስ ስልጣን የተሰጠው ነው። ሌሎች እርከኖች እንደዚሁ የየራሣቸው ሀላፊነትና የሥራ ድርሻ ያላቸው ሲሆን በዚህ መልኩ የተዋቀረው የጌዴኦ የገዳ ሥርዓት በየስምንት ዓመቱ የስልጣን ርክክብ እንዲደረግ ያዛል። ወቅቱ ሲደርስ ይህን የስልጣን ርክክብ የሚያከናውኑ "ራባ" ዎች ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ስልጣን ተረካቢው "ሉባ"፣ ስልጣን አስረካቢው ደግሞ "ዮባ" በመባል ይታወቃሉ።

የጌዴኦ ብሔረሰብ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ "ማገኖ" ብሎ በሚጠራው አንድ አምላክ እንደሚያምን ፤ ይኽው የሰማይ አምላክ ርህሩህ ከሁሉ የበላይ በተለይም የሁሉ ነገር ፊጣሪ በመሆኑ ሕዝቡ ተገቢ የሆነ ክብርና መስዋዕትን ያቀርባል። በጌዴኦ ባህላዊ እምነት " ወዮ" የሚባሉና ስርዓተ መስዋዕቱን የሚፈፅሙ ከሰባቱም የጌዴኦ ጎሣዎች የተወጣጡ የሀይማኖት መሪዎች አሉ። እያንዳንዳቸው የተለያዩ መንፈሣዊ ተግባራትን የመፈፀም፣ በእምነቱ መሠረት የመመረቅ እና የመርገም የሥራ ድርሻ ሲኖራቸው ከማገኖ ዘንድ ለዝናብ ለመብረቅ ለውሃ ሙላት ...ወዘተ የተሰጣቸው የተለያየ "ቃሮ" ወይንም መንፈሣዊ ኃይል እንዳላቸው ይታመናል።

ባህላዊ እሴቶች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የጌድኦ የጋብቻ ሥርዓት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በጌዴኦ ብሔረሰቡ ዘንድ ተግባራዊ የሚደረጉ የተለያዩ የጋብቻ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን እነዚህም "ካጃ"/ ህጋዊ ወይንም የስምምነት ጋብቻ/ ፣ ቡታ" /የጠለፋ ጋብቻ/፣ጃላ፣ ኪንቾ፣" አደባና" ፣ ሀዋዴ፣ ዋራዬ ኦልታ፣ "ሰባ" እና "ጊንባላ" በመባል ይታወቃሉ። ከነዚህ መካከል “ካጃ” እና "ሀዋዴ" የተሰኙት የጋብቻ ዓይነቶች በብሔረሰቡ ውስጥ በስፋት ተቀባይነት ያላቸው ሲሆን "ቡታ" እና "ዋራዬ ኦልታ" የተሰኙት በአፈፃፀማቸው በህገ ወጥነት ይፈረጃሉ። እንደነዚህ ያሉ የጋብቻ ዓይነቶች ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ ቢፈፀሙም በመጨረሻ ውስጥ ለውስጥ በሚደረግ ስምምነት እና ባህላዊ አስተዳደርና እምነት ፍራቻ ሕጋዊነታቸው ይፀድቃል። "ሰባ" የሚባለው ጋብቻ በወንዱና በሴቷ ወላጆች ይሁንታ ወይንም መፈቃቀድ የሚከናወን ሲሆን "ሀዋዴ" የሚባለው ደግሞ በሌላ ሶስተኛ ሰው አግባቢነት ወንዱና ሴቷ ስምምነት ላይ የሚደርሱበት ከዚህም በኋላ ወደ ሴቷ ቤተሰቦች ሽማግሌ በመላክ የሚፈፀም የጋብቻ ዓይነት ነው።

ብሔረሰቡ በሕጋዊነት የተቀበላቸው የጋብቻ ዓይነቶች ከመፈፀማቸው በፊት ከጥንት ጀምሮ በዓይነት የሚተገበር የጥሎሽ ሥርዓት ይኖራል። በጥንታዊ የጋብቻ ሥርዓት ጥሎሽ ይሰጥ የነበረው ለአባትና እናት ሲሆን ከሚቀርቡ ስጦታዎች መካከል ለአባት ጠገራ፣ ድርብ ቡልኮ፣ ሂቶ/መቀነት/ በዋናነት የሚሰጡ ሲሆን ለእናት ደግሞ ነጠላ ቡልኮ/ ዱዳ/ይሰጣል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባህላዊ የጥሎሽ ስጦታ ወደ ገንዘብ ተለውጦ ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። የጥሎሽ ገንዘብ ከፍ ማለት በብሔረሰቡ ዘንድ ሕጋዊ ጋብቻን እያመነመነ በመምጣቱ በገዳ ሥርዓት ጠቅላላ ጉባኤው/ያኣ/ ለአባት ቡልኮ መግዣ ስድሣ ብር፣ ለእናት ደግሞ ሃያ ብር በድምሩ ብር ሰማኒያ እንዲሰጥ ቢወሰንም አንዳንድ የብሔረሰቡ አባላት በገዳ ስርዓቱ የተወሰነውን የጥሎሽ መጠን በመተላለፍ ከብር 1ሺህ እስከ ፲፭፻ የሚደርስ የጥሎሽ ገንዘብ ሲሰጡ ይስተዋላሉ።

በቤተሰብ ስምምነት በሚፈፀመው ሕጋዊ ጋብቻ ወቅት ተጋቢዎች በተጋቡ በሶስተኛው ቀን የሙሽራው ወላጆችና ቤተዘመድ በወንዱ ቤት ተሰባስበው የጉርሻ /ጊጫ/ ሥነ ሥርዓት በማከናወን ለሙሽሪት የተለያዩ ስጦታዎችን የሚሰጥበት ሥርዓት አለ። በዚህን ዕለት የሙሽራው ዘመድ አዝማድ በተገኘበት ሙሽራዎች /ወንዱ በስተቀኝ ሴቷ በስተግራ በመሆን/ ከተሰብሳቢዎች ፊት ለፊት ቁጢጥ ብለው የሚከናወነውን የጉርሻ /የስጦታ/ ሥነ ሥርዓት ለመፈፀም ይጠባበቃሉ። ጉርሻው /ስጦታው/ የሚጀመረው ከሙሽራው አባት ወይንም አባት ከሌለ ከተሰብሳቢዎች መካከል አንጋፋ ከሆነው ሰው ስለሆነ ሙሽሪት ቀደም ብላ በተዘጋጀችበት መሠረት ጉርሻውን /ስጦታውን/ ለመቀበል ወደ አባት ወይንም አንጋፋው ሰው ተጠርታ ትሄዳለች። በዚህ ሥነ ሥርዓት ወቅት ሙሽሪት ከወንዱ ቤተሰብ የምትፈልገውንና የምትጠብቀውን ስጦታ እስከምታገኝ ድረስ የሚሰጣትን ጉርሻ አትቀበልም። ስለዚህ በጥሪው መሠረት የልጁ አባት ወይንም አንጋፋው ቤተዘመድ አጉራሽ " ይህን ያህል ብር ሰጠሁሽ ይላታል። " እሷም " አይበቃኝም" ትላለች። በመቀጠል " ይህን ያህል መሬት ሰጠሁሽ" ይላል። አሁንም መልሳ “አይበቃኝም” ትላለች። ከዚያም "ይህንን ያህል ከብት ሰጠሁሽ" ሲላት አይበቃኝም አይበቃኝም " እያለች ከቆየች በኋላ ከአጉራሹ /ከስጦታ ሰጪ/ ዘንድ የምትፈልገውን ያህል ስጦታ ስታገኝ ጉርሻውን ትቀበላለች። በዚህ መልኩ የተሰበሰበውን ቤተ ዘመድ በሙሉ በማዳረስ ለጎጆ መውጫ የሚሆናትን በቂ ሀብትና ንብረት ታገኛለች።

የቤት አሠራር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በጌዴኦ ብሔረሰብ ቤት የአንድን ግለሰብ ወይም ቤተሰብ ማህበራዊ ደረጃ መገለጫ ስለሆነ ትልቅ ግምትና ክብር አለው። በብሔረሰቡ ባህል መሠረት አንድ ልጅ ካገባ በኋላ እስከ አንድ ዓመት ድረስ በአባቱ ወይም ወላጆቹ ቤት መቆየት ይችላል። ከአንድ አመት በኋላ ግን ደረጃውን የሚያስጠብቅ ቤት ሠርቶ መውጣት የግድ ነው። ጌዴኦዎች ቤት የሚሠሩት በአንድ አካባቢ ተሰባስቦ በመንደር መልክ ነው። በጌዴአዎች የተለያዩ የቤት ዓይነቶች ያሉ ሲሆን ዓይነታቸው የሚወሰነው ፡- በቅርፅ፣ በግንባታ፣ ቁሳቁስ፣ በክዳን ዓይነትና በሚሰጠው አገልግሎት ነው።

ዶጐዶ ለአጭር ጊዜ ለሚቆይ ዝግጅት የሚሆን ጊዜያዊ ቤት ነው። አገልግሉቱ ለጫጉላ ቤት፣ እህል ለመጠበቅ ባህላዊ በዓላት ለማክበር እና እንሰት ለመፋቅ ነው። ቅርፁ ክብ ሆኖ ከ4 ካሬ ሜትር የማይበልጥ ስፋትና ከ2 ሜትር የማይበልጥ ቁመት ያለው ነው። ከቀጫጭን ጭራሮ እንጨት፣ ከወፊቾ ገመድና በእንሰት ቅጠል ሊሠራ ይችላል።

የዚህን ዓይነት ቤት የሚሠሩት ሰዎች በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ፣ አዲስ ጐጆ ወጪዎች እና ከዋናው ቤት በተጨማሪ ለከብት ማደሪያነት የሚጠቀሙ ናቸው። ቤቱ ከቀርቀሃ፣ ከሸምበቆ ከወፎፊቾና ከሰምበሌጥ ሊሠራ ይችላል። የቤቱ የውስጥ አደረጃጀት በአብዛኛው ሁለት ክፍል ያለው ሲሆን በር ኖሮት መስኮት አይኖረውም።

አዲቻሞ (መደበኛ ቤት)

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የዚህ ቤት ዓይነት ረጅም ጊዜ ዝግጅት የሚጠይቅ ነው። ዝግጅቱ የመሥሪያ ቁሣቁስ በጥንቃቄ ይዘጋጃል፣ ለቤት ሠሪዎች ምግብ፣ እና በተለይ ከቁሳቁስ የምሰሶ መረጣ ትልቁን ጊዜ የሚወስዱ ተግባራት ናቸው። የዚህ ቤት የውስጥ አደረጃጀት ሲታይ ከሁለት በላይ ክፍሎች ሊኖሩት ይችላሉ፣ መስኮትና የጓሮ በር ይኖረዋል። የአዲች ሚኔ ቤት ሥራ ልዩ ባለሙያ ለምሰሶ መረጣ፣ ለሣር ክዳን ሥራ፣ የመሥሪያ ቦታ ማዘጋጀትና የምሰሶ ቅርፅ ማውጣት እንዲሁም ጣራ ማዋቀር የተለየ ባለሙያ ይፈልጋል።

ሌላው አራተኛ ዓይነት ቤት ሸካ (የቀርከሃ ቤት) ነው። የቤቱ ዓይነትና አሠራር ከዲቻ ማኔ ሆኖ ልዩነቱ ከቀርቀሃ ልባስ (ጳሻ) እና ከቀርከሃ የሚሠራ በመሆኑ ብቻ ነው። ቤቱ የሚታወቀው የደገኞች ቤት በመባል ነው። የቤቱ መዝጊያም ጭምር ቀርከሃ ሲሆን ከፍተኛ የቀርከሃ ጥበብ የሚታይበት ነው።

ባህላዊ ምግብና የአሠራር ሥርዓት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የብሔረሰቡ ዋነኛ ባህላዊ ምግብ «ቆÝ» ወይንም በብሔረሰቡ አጠራር «ዋሳ» ሲሆን ከዕለታዊ ምግብነቱ በተጨማሪ ለደስታም ሆነ ለሀዘን በተለያየ ዓይነት እየተዘጋጀ ከሌሎች የማባያ ዓይነቶች ጋር ይበላል። በስምንት የተለያዩ ባህላዊ አዘገጃጀት የሚዘጋጀው ቆÝ ከሚቆይበት ጊዜ አንፃር ፣ ከማበያው ዓይነት፣ እና ከሚጠቀመው ሰው አኳያ እንደሁኔታው እየታየ ይዘጋጃል። ከባህላዊ የቆÝ ምግብ ዓይነቶች አንዱ «ወእረሞ» የሚባል ሲሆን ብዙውን ጊዜ በኳስ ቅርጽ ተድበልብሎ ከገብስ ወይም ከበቆሎ ዱቄት ጋር በመደባለቅ የሚዘጋጅ፣ ለማንኛውም ዓይነት ዝግጅት የሚውል ከጐመን ወይንም ከስጋ ጋር የሚበላ ጣፋጭ ምግብ ነው።

ሌላው ተወዳጅ ምግብ «ኮፎ» በመባል የሚታወቅ ሲሆን አዘገጃጀቱ እንደ ዱቄት ሆኖ የተዘጋጀ ቆÝ ከገብስ ዱቄት ጋር በመደባለቅ የሚነኮር፣ በቅቤ እና ሌሎች ቅባት ነክ ነገሮች እንዲለሰልስ ተደርጐ የሚዘጋጅና፣ የተለየ ክብር ለሚሰጠው እንግዳ ወይንም ትላልቅ ሰዎች የሚቀርብ ነው። አንዳንዴም ይህን ምግብ ከአደንጓሬ ጋርም በመደባለቅ አዘጋጀተው ይጠቀሙታል። «ጣልታ» እና «ኬቦ» የተሰኙት የቆÝ ምግብ ዓይነቶች የመጠን ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ጠፍጠፍ ወይንም ሞልሞል ተደርገው በቀላሉ በአምባሻ መልክ የሚዘጋጁ ናቸው። «ሆጨቆ» ቆÝ ብቻውን በማድበልበል በመጠን አነስ ተደርጐ የሚዘጋጅ ከጐመን ጋር የሚቀቀል ጣፋጭ ምግብ ነው። «ቁንጭሣ» ደግሞ የቆÝ ዱቄት በምጣድ ላይ ተደርጐ ሲበስል እንደእንጀራ እየተቆረሰ የሚበላ ብዙ ማገዶ የማይፈጅ የዘወትር ባህላዊ ምግብ ነው። ኦጣ ርሞጦ የሚባለው ደግሞ ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ እንዲያገለግል በተለይም ለረጅም ጉዞና በጦርነት ወቅት ስንቅ እንዲሆን ታስቦ የሚዘጋጅ እንደ ድፎ ዳቦ ዓይነት ነው። ኮሣ /ጉንጃ/ በማድበልበል ጠቅለል ተደርጎ በእሣት ፍም ወይንም ትኩስ ረመጥ ላይ ተደርጎ ሲበስል የሚበላ ተዘውታሪ ምግብ ነው። በአጠቃላይ የቆÝ ምግብ በዓይነቱና በአቀራረቡ የተለያየ ቢሆንም ማባያዎቹም በዋናነት ጎመን፣ ወተትና ሥጋ ናቸው።

ባህላዊ የለቅሶ ሥርዓት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በጌዴኦ ብሔረሰብ ሰው ሲሞት ለየት ያለ ባህላዊ የለቅሶ ሥርዓት ይካሄዳል። በተለይ በተለይ ወጣት ወይንም አዛውንት የሆነ ሰው ሲሞት «ዘመድ አዝማድ ሣይሰበሰብ ከተቀበረ ጥሩ አይደለም» ተብሎ ስለሚታመን እስከ ሁለት ሶስት ቀናት ድረስ አስከሬን ሣይቀበር ሊቆይ ይችላል። ሕፃናት ሲሞቱ ግን አስከሬን በዕለቱ ይቀበራል፤ ሀዘኑም የዚያኑ ዕለት እንዲያበቃ ሽማግሌዎች ቤተሰቡን ይመክራሉ፤ የሐዘን ዳርቻ እንዲያደርግላቸውም ይመርቃሉ። የዕድሜ ባለፀጋ የሆነ ሰው ሲሞት የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ከተፈፀመበት እለት ጀምሮ የሚፈፀሙ የተለያዩ ባህላዊ የለቅሶ ሥርዓቶች አሉ። ሁሉም የየራሳቸው የአከባበር ሥርዓት አላቸው። ከነዚህ መካከል አንዱና የመጀመሪያው በብሔረሰቡ ቋንቋ «ዊልኢሻ» ይባላል። በዚህ የሐዘን መግለጫ ሥርዓት ሟች ከተቀበረበት ዕለት ከሰዓት በኋላ ጀምሮ የሟች ማንነትና ያከናወናቸው ሥራዎች፣ ለሕዝቡ የፈፀመው መልካም ተግባር፣ ለጋሽነቱ፣ ሀብቱ፣ የልጆች አባትነቱ፣ ርህሩህነቱ፣ ጀግና ከሆነ ጀግንነቱ እየተገለፀ፣ በግጥም እየተገጠመ፣ እየተጨፈረ ይለቀሳል። ዊልኢሻ ከአራት እስከ ስምንት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ማታ ማታ «ጋዳ» የተባለ የሀዘን ማስረሻ ዘፈን እና ጭፈራ ሐዘንተኞች ወይንም የሟች ቤተሰቦች እንዲሁም የአካባቢው ሕብረተሰብ ተሰባስበው ይጨፍራሉ። ጋዳ በሀዘን የተቆራመዱትን የሟች ዘመዶችና ቤተሰቦችን ከሀዘን ድባብ ለማውጣትና ለማጽናናት ማታ ማታ የሚከናወን ድራማዊ ጭፈራ ነው።

ከዚህም "በዊልኢሻ" የመጨረሻ ቀን ማታ ጀምሮ ልዩ ልዩ የተዝካር ዓይነቶች ይፈፀማሉ። የመጀመሪያው ተዝካር በብሔረሰቡ ቋንቋ /ሬንሽማ/ ሲከናወን የሚደረግ ዝግጅት ሲሆን «ሁጐ» የሚባለው ደግሞ የሟች ቤተሰብ ሙታንን የሚዘክሩበት፣ የሚያናግሩበት፣ የሟች እህት በባህል መሠረት የ«ኡማቶ» ሥርዓት በቀዳሚነት የምትፈፅምበት እንደሆነ ይነገራል። የመጀመሪያው የተዝካር ሥርዓት በተከናወነ ማግስት የቤትና የግቢ ፅዳት የሚደረግ ሲሆን ይህም «በዳኣ» ተብሎ ይጠራል። የመጨረሻው የተዝካር ዓይነት «አዋላ» በመባል የሚታወቅ ሲሆን በዚህን ዕለት ከብት ታርዶ ከሟች የሥጋ ዘመድ በስተቀር ሌሎች የታረደውን ከብት ሥጋ በአካባቢው «ሀይቻ» አማካይነት የሚከፋፈሉበት ነው።

ከዊልኢሻ ቀጥሎ ያለው የለቅሶ ሥርዓት «ቡቺሣ» የሚባል ሲሆን በዚህ የለቅሶ ዓይነት ፆታን በመለየት የማስለቀስ ተግባር ይከናወናል። ሟች ሴት ከሆነች ውበቷን፣ የዋህነቷን፣ ለጋሽነቷን፣ ሙያዋን፣ እንግዳ ተቀባይነቷን ...ወዘተ እየጠቃቀሱ የለቅሶ ጭፈራ ይከናወናል። እንደዚሁም ሟች ወንድ ከሆነ ጀግንነቱን፣ ቤተሰባዊ አመጣጡን፣ ያከናወናቸውን ተግባራት /ክንውኖች/ ...ወዘተ የሚገልፁ ግጥሞችን በመደርደር ይለቀሣል፣ ይጨፈራል። ሟች ጀግና ከሆነ ለጀግንነቱ መለያ እንዲሆን «ዱፈኣ» ከተባለ ጥቁር እንጨት የሚዘጋጅ ረጅም ጊዜያዊ ሀውልት በመቃብሩ ላይ ተተክሎ በዊልአሻ ጊዜ ለጀግንነቱ መገለጫ ማቶት ተዘጋጅቶ የሰጎን ላባ ተሰክቶበት በመቃብሩ ላይ በተደረገው ጊዜያዊ ሀውልት ላይ ይንጠለጠላል። የሟችን «ሞቴ» የሚባል መቀመጫ እና «በራቴ» የሚባል የእንጨት ትራስ በመሰባበር እዚያው ሀውልት ስር በመታሰቢያነት በማስቀመጥ የሀዘን ፍፃሜ እንዲሆን ይደረጋል።

በጌዲኦ ብሔረሰብ ባህላዊ የለቅሶ ሥርዓት ደንብ መሠረት ለቅሶ የሚጠናቀቀው በአራተኛ ቀን ሲሆን ይህም ቀን ከሀጢያት የሚነፃበት ቀን ነው ተብሎ ይታመናል። በዚህን ዕለት የቤት ጠረጋ ሥርዓት ይከናወናል። በቤት ጠረጋው ቀን ከባልዋ ተጣልታ ወደ ወላጆቿ የመጣች ሴት ያለማንም አስታራቂ ከባሏ ጋር ተያይዛ ወደ ቤቷ ትሄዳለች። ከዚህ በተጨማሪ ዕለቱ የሟች ኑዛዜ ካለ በሕዝቡ ፊት ከተሰማ በኋላ ቤተሰቦቹ ተስማምተው እንዲኖሩ የሚመከሩበት የተጣላ ካለ የሚታረቅበት ዕለት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል።

  1. ^ ጌዴኦ በደቡብ ማእከላዊ ኢትዮጵያ የሚነገረው የአፍሮ እስያ ቤተሰብ ሃይላንድ ምስራቅ ኩሺቲክ ቋንቋ ነው። የቋንቋው ተለዋጭ ስሞች ዴራሳ ፣ ዴሬሳ ፣ ዳራሳ ፣ ጌዴኦ ፣ ዴራሳንያ ፣ ዳራሳ ያካትታሉ። ከዲላ ደቡብ ምዕራብ እና ከአባያ ሀይቅ በስተምስራቅ በሃይላንድ አካባቢ በሚኖሩ የጌዴኦ ሰዎች ይነገራል። [1] ጌዴኦ