Jump to content

የማርቆስ ወንጌል

ከውክፔዲያ
ቅ.ማርቆስ ወንጌላዊው
አንበሳው ማርቆስ
አንበሳው ማርቆስ
የቅዱስ ማርቆስ ወንጌል
የፀሐፊው ስም ዮሐንስ በኋላ ማርቆስ
የተወለደበት ቀን ጥቅምት ፴ በ፩ኛው ክፍለዘመን
የተወለደበት ቦታ ሲሬን (ሰሜን አፍሪካ)
የእናት ስም ማርያም ብሉይ ኪዳንን ማለት የሃይማኖት ትምህርት በዕውቅ ት/ቤት እንዲማር ምክኒያት የሆነች ትልቅ ሴት ናት ዕብራዪስጥና ዮናይስጥ ይጽፋል ይናገራል
የአባት ስም አሪስቶፑለስ
በዓለንግሥ ሚያዝያ ፴
ምልክት
ሥራው ፀሐፊ ሰባኪም
የሚከበረው በዓለም ክርስቲያን ሕዝብ [1]
የጻፈው ወንጌል ፲፮ ምዕራፍ
ያረፈበት ቀን ሚያዝያ ፴[2]


የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ቅዱስ ማርቆስ እንደ ጻፈው። ቅዱስ ማርቆስ ወንግልን ለመስበክ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ወደ ሮም ተጉዞ ቀዳሚ የወንጌል ፀሐፊ ሆነ ። (፩ኛ ጴጥ ም፡፭ ቁ፡፲፪- ፲፫) ከጌታ የሰማውንና የተማረውን ጽፎአል። ወንጌልንም የጻፈበት ዘመን ጌታ ከዐረገ አሥራ አንደኛው ተፈፅሞ አሥራ ሁለተኛው ሲጀምር፣ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በአራተኛው ዓመት ሲሆን ወንጌል ተብሎ ይፋ የወጣበት ቋንቋ ሮማይስጥ ነው ማለት ቅዱስ ጴጥሮስ በሮማይስጥ አስተርጉሞ የሮማ ሰዎችን ለማስተማር ተጠቅሞበታል ። ወንጌሉም ቅዱስ ማርቆስ ካለፈ በኋላ በስሙ ተጠርቷል።

ቀጥሎም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በግብፅ አገር ተልኮውን ማኪያሄድ እንዳለበት ተረድቶ እዚሁ አገር ላይ የአንበሳ ጣዖቶችን በማጥፋት የነገደ ይሁዳ የሆነውን አንበሳ ክርስቶስን በመስበክ ከዚያም የመጀመሪያው ጳጳስ ሆኖ በመናፍቃን ተገድሎ በሰማዕትነት ያለፈ ቅዱስ ነው። ይህ ክርስቲያናዊ ተጋድሎ ነው የአንበሳ ምልክት እንዲሰጠው ዋና ምክኒያት የሆነው። በተጨማሪ በራዕዪ ዮሐንስ (፭፡፭) ጌታች መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ አሸናፊ የይሁዳ አንበሳ ተብሎ ተሰይሟል ፣ በነብዩ በሆሴዕ (፲፫፡፯) አንበሳ ተብሎ መጠራቱን እናያለን [3]

አንበሳው፡ማርቆስ



የማርቆስ ወንጌል

1፤የእግዚአብሔር፡ልጅ፡የኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ወንጌል፡መዠመሪያ። 2-3፤እንሆ፥መንገድኽን፡የሚጠርግ፡መልክተኛዬን፡በፊትኽ፡እልካለኹ፡የጌታን፡መንገድ፡ አዘጋጁ፡ጥርጊያውንም፡አቅኑ፡እያለ፡በምድረ፡በዳ፡የሚጮኽ፡ሰው፡ድምፅ፡ተብሎ፡ በነቢዩ፡በኢሳይያስ፡እንደ፡ተጻፈ፥ 4፤ዮሐንስ፡በምድረ፡በዳ፡እያጠመቀ፡የንስሓንም፡ጥምቀት፡ለኀጢአት፡ ስርየት፡እየሰበከ፡መጣ። 5፤የይሁዳም፡አገር፡ዅሉ፡የኢየሩሳሌምም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ወደ፡ ርሱ፡ይወጡ፡ነበር፥ ኀጢአታቸውንም፡እየተናዘዙ፡በዮርዳኖስ፡ወንዝ፡ከርሱ፡ይጠመቁ፡ነበር። 6፤ዮሐንስም፡የግመል፡ጠጕር፡ለብሶ፡በወገቡ፡ጠፍር፡ይታጠቅ፡አንበጣና፡የበረሓ፡ ማርም፡ይበላ፡ነበር። 7፤ተጐንብሼ፡የጫማውን፡ጠፍር፡መፍታት፡የማይገ፟ባ፟ኝ፡ ከእኔ፡የሚበረታ፡በዃላዬ፡ይመጣል። 8፤እኔ፡በውሃ፡አጠመቅዃችኹ፡ርሱ፡ግን፡በመንፈስ፡ቅዱስ፡ያጠምቃችዃል፡እያለ፡ ይሰብክ፡ነበር። 9፤በዚያ፡ወራትም፡ኢየሱስ፡ከገሊላ፡ናዝሬት፡መጥቶ፡ከዮሐንስ፡በዮርዳኖስ፡ወንዝ፡ተጠመቀ። 10፤ወዲያውም፡ከውሃው፡በወጣ፡ጊዜ፡ሰማያት፡ሲቀደዱ፡መንፈስም፡እንደ፡ርግብ፡ሲወርድበት፡ አየና፦የምወድኽ፡ልጄ፡አንተ፡ነኽ፥ 11፤ባንተ፡ደስ፡ይለኛል፡የሚል፡ድምፅ፡ከሰማያት፡መጣ። 12፤ወዲያውም፡መንፈስ፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡አወጣው። 13፤በምድረ፡በዳም፡ከሰይጣን፡እየተፈተነ፡

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ
ክርስቶስ ሲጠመቅ

አርባ፡ቀን፡ሰነበተ፡ከአራዊትም፡ጋራ፡ነበረ፥ መላእክቱም፡አገለገሉት። 14-15፤ዮሐንስም፡ዐልፎ፡ከተሰጠ፡በዃላ፡ኢየሱስ፡የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡ወንጌል፡ እየሰበከና፦ዘመኑ፡ተፈጸመ፡የእግዚአብሔርም፡መንግሥት፡ቀርባለች፡ንስሓ፡ግቡ፡ በወንጌልም፡እመኑ፡እያለ፡ወደ፡ገሊላ፡መጣ። 16፤በገሊላ፡ባሕርም፡አጠገብ፡ሲያልፍ፡ስምዖንን፡ወንድሙንም፡እንድርያስን፡መረባቸውን፡ ወደ፡ባሕር፡ሲጥሉ፡አየ፥ዓሣ፡አጥማጆች፡ነበሩና። 17፤ኢየሱስም፦በዃላዬ፡ኑና፡ሰዎችን፡አጥማጆች፡እንድትኾኑ፡አደርጋችዃለኹ፡አላቸው። 18፤ወዲያውም፡መረባቸውን፡ትተው፡ተከተሉት። 19፤ከዚያም፡ጥቂት፡እልፍ፡ብሎ፡የዘብዴዎስን፡ልጅ፡ያዕቆብን፡ወንድሙንም፡ዮሐንስን፡ደግሞ፡በታንኳ፡ ላይ፡መረባቸውን፡ሲያበጁ፡አየ። 20፤ወዲያውም፡ጠራቸው፡አባታቸውንም፡ዘብዴዎስን፡ከሞያተኛዎቹ፡ጋራ፡በታንኳ፡ላይ፡ ትተው፡ተከትለውት፡ኼዱ። 21፤ወደ፡ቅፍርናሖምም፡ገቡ፤ወዲያውም፡በሰንበት፡ወደ፡ምኵራብ፡ገብቶ፡አስተማረ። 22፤እንደ፡ባለሥልጣን፡ያስተምራቸው፡ነበር፡እንጂ፡እንደ፡ጻፊዎች፡አይደለምና፡በትምህርቱ፡ ተገረሙ። 23፤በዚያን፡ጊዜም፡በምኵራባቸው፡ርኩስ፡መንፈስ፡ያለው፡ሰው፡ነበረ፤ 24፤ርሱም፦የናዝሬቱ፡ኢየሱስ፡ሆይ፥ከአንተ፡ጋራ፡ምን፡አለን፧ልታጠፋን፡መጣኽን፧ማን፡እንደ፡ ኾንኽ፡ዐውቄያለኹ፥የእግዚአብሔር፡ቅዱሱ፡ብሎ፡ጮኸ። 25፤ኢየሱስም፦ዝም፡በል፡ከርሱም፡ውጣ፡ብሎ፡ገሠጸው። 26፤ርኩሱም፡መንፈስ፡አንፈራገጠውና፡በታላቅ፡ድምፅ፡ጮኾ፡ከርሱ፡ወጣ። 27፤ዅሉም፦ይህ፡ምንድር፡ነው፧በሥልጣን፡ርኩሳን፡መናፍስትን፡ያዛ፟ል፤እነርሱም፡ ይታዘዙለታልና፥ይህ፡ዐዲስ፡ትምህርት፡ምንድር፡ነው፧ብለው፡እስኪጠያየቁ፡ድረስ፡አደነቁ። 28፤ዝናውም፡ወዲያው፡በየስፍራው፡ወደገሊላ፡ዙሪያ፡ዅሉ፡ወጣ። 29፤ወዲያውም፡ከምኵራብ፡ወጥቶ፡ከያዕቆብና፡ከዮሐንስ፡ጋራ፡ወደስምዖንና፡ወደእንድርያስ፡ቤት፡ገባ። 30፤የስምዖንም፡ዐማት፡በንዳድ፡ታማ፡ተኝታ፡ነበር፥ስለ፡ርሷም፡ወዲያው፡ነገሩት። 31፤ቀርቦም፡እጇን፡ይዞ፡አስነሣት፡ንዳዱም፡ወዲያው፡ለቀቃትና፡አገለገለቻቸው። 32፤ፀሓይም፡ገብቶ፡በመሸ፡ጊዜ፥የታመሙትንና፡አጋንንት፡ያደረባቸውን፡ዅሉ፡ወደ፡ርሱ፡አመጡ፤ 33፤ከተማዪቱም፡ዅላ፡በደጅ፡ተሰብስባ፡ነበር። 34፤በልዩ፡ልዩ፡ደዌም፡የታመሙትን፡ብዙዎችን፡ፈወሰ፥ብዙዎችንም፡አጋንንት፡አወጣ፥ አጋንንትም፡ክርስቶስ፡መኾኑን፡ዐውቀው፡ነበርና፥ሊናገሩ፡አልፈቀደላቸውም። 35፤ማለዳም፡ተነሥቶ፡ገና፡ሌሊት፡ሳለ፡ወጣ፡ወደ፡ምድረ፡በዳም፡ኼዶ፡በዚያ፡ጸለየ። 36፤ስምዖንና፡ከርሱ፡ጋራ፡የነበሩትም፡ገሥግሠው፡ተከተሉት፥ 37፤ባገኙትም፡ጊዜ፦ዅሉ፡ይፈልጉኻል፡አሉት። 38፤ርሱም፦በዚያ፡ደግሞ፡ልሰብክ፡ወደ፡ሌላ፡ስፍራ፡በቅርብ፡ወዳሉ፡መንደሮች፡እንኺድ፡ስለዚህ፡ወጥቻለኹና፡አላቸው። 39፤በምኵራባቸውም፡እየሰበከ፡አጋንንትንም፡እያወጣ፡ወደ፡ገሊላ፡ዅሉ፡መጣ። 40፤ለምጻምም፡ወደ፡ርሱ፡መጥቶ፡ተንበረከከና፦ብትወድስ፡ልታነጻኝ፡ትችላለኽ፡ብሎ፡ለመነው። 41፤ኢየሱስም፡ዐዘነለት፡እጁንም፡ዘርግቶ፡ዳሰሰውና፦እወዳ፟ለኹ፤ንጻ፡አለው። 42፤በተናገረም፡ጊዜ፡ለምጹ፡ወዲያው፡ለቀቀውና፡ነጻ። 43፤በብርቱም፡ተናግሮ፡ወዲያው፡አወጣው፤ 44፤ለማንም፡አንዳች፡እንዳትናገር፡ተጠንቀቅ፥ነገር፡ግን፥ኼደኽ፡ራስኽን፡ለካህን፡አሳይ፡ለእነርሱም፡ምስክር፡እንዲኾን፡ ስለ፡መንጻትኽ፡ሙሴ፡ያዘዘውን፡አቅርብ፡አለው። 45፤ርሱ፡ግን፡ሲወጣ፡ብዙ፡ሊሰብክና፡ነገሩን፡ሊያወራ፡ዠመረ፥ስለዚህም፡ኢየሱስ፡ተገልጦ፡ወደ፡ከተማ፡መግባት፡ወደ፡ ፊት፡ተሳነው፥ነገር፡ግን፥በውጭ፡በምድረ፡በዳ፡ይኖር፡ነበር፤ከየስፍራውም፡ወደ፡ርሱ፡ይመጡ፡ነበር።

1፤ከጥቂት፡ቀን፡በዃላ፡ወደ፡ቅፍርናሖም፡ደግሞ፡ገብቶ፡በቤት፡እንደ፡ኾነ፡ተሰማ። 2፤በደጅ፡ያለው፡ስፍራም፡እስኪጠባ፟ቸው፡ድረስ፡ብዙ፡ሰዎች፡ተሰበሰቡ፤ቃሉንም፡ይነግራቸው፡ነበር። 3፤አራት፡ሰዎችም፡የተሸከሙትን፡ሽባ፡አመጡለት። 4፤ስለሕዝቡም፡ብዛት፡ወደ፡ርሱ፡ማቅረብ፡ቢያቅታቸው፡ርሱ፡ያለበትን፡የቤቱን፡ጣራ፡አነሡ፥ነድለውም፡ ሽባው፡የተኛበትን፡ዐልጋ፡አወረዱ።5፤ኢየሱስም፡እምነታቸውን፡አይቶ፡ሽባውን፦አንተ፡ልጅ፥ኀጢአትኽ፡ተሰረየችልኽ፡አለው። 6፤ከጻፊዎችም፡አንዳንዶቹ፡በዚያ፡ተቀምጠው፡ነበር፡በልባቸውም፦ይህ፡ሰው፡ስለ፡ምን፡እንደዚህ፡ያለ፡ ስድብ፡ይናገራል፧ 7፤ከአንዱ፡ከእግዚአብሔር፡በቀር፡ኀጢአት፡ሊያስተሰርይ፡ማን፡ይችላል፧ብለው፡ዐሰቡ። 8፤ወዲያውም፡ኢየሱስ፡በልባቸው፡እንዲህ፡እንዳሰቡ፡በመንፈስ፡ዐውቆ፡እንዲህ፡አላቸው፦በልባችኹ፡ይህን፡ ስለ፡ምን፡ታስባላችኹ፧ 9፤ሽባውን፦ኀጢአትኽ፡ተሰረየችልኽ፡ከማለት፡ወይስ 1 ተነሣ፡ዐልጋኽንም፡ተሸከምና፡ኺድ፡ከማለት፡ ማናቸው፡ይቀላል፧ 10፤ነገር፡ግን፥ለሰው፡ልጅ፡በምድር፡ላይ፡ኀጢአትን፡ሊያስተሰርይ፡ሥልጣን፡እንዳለው፡እንድታውቁ፤ 11፤ሽባውን፦አንተን፡እልኻለኹ፥ተነሣ፥ዐልጋኽን፡ተሸከምና፡ወደ፡ቤትኽ፡ኺድ፡አለው። 12፤ተነሥቶም፡ወዲያው፡ዐልጋውን፡ተሸክሞ፡በዅሉ፡ፊት፡ወጣ፥ስለዚህም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ ተገረሙና፦እንዲህ፡ያለ፡ከቶ፡አላየንም፡ብለው፡እግዚአብሔርን፡አከበሩ። 13፤ደግሞም፡በባሕር፡አጠገብ፡ወጣ፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡ወደ፡ርሱ፡መጡና፡አስተማራቸው። 14፤ሲያልፍም፡በመቅረጫው፡ተቀምጦ፡የነበረውን፡የእልፍዮስን፡ልጅ፡ሌዊን፡አየና፦ተከተለኝ፡ አለው።ተነሥቶም፡ተከተለው። 15፤በቤቱም፡በማእዱ፡ተቀምጦ፡ሳለ፥ብዙ፡ቀራጮችና፡ኀጢአተኛዎች፡ከኢየሱስና፡ከደቀ፡መዛሙርቱ፡ጋራ፡ ተቀመጡ፤ብዙ፡ነበሩ፡ይከተሉትም፡ነበር። 16፤ጻፊዎችና፡ፈሪሳውያንም፥ከቀራጮችና፡ከኀጢአተኛዎች፡ጋራ፡ሲበላ፡አይተው፡ለደቀ፡ መዛሙርቱ፦ከቀራጮችና፡ከኀጢአተኛዎች፡ጋራ፡የሚበላና፡የሚጠጣ፡ስለ፡ምንድር፡ነው፧አሉ። 17፤ኢየሱስም፡ሰምቶ፦ሕመምተኛዎች፡እንጂ፡ብርቱዎች፡ባለመድኀኒት፡አያስፈልጋቸውም፤ኀጢአተኛዎችን፡ እንጂ፡ጻድቃንን፡ልጠራ፡አልመጣኹም፡አላቸው። 18፤የዮሐንስ፡ደቀ፡መዛሙርትና፡ፈሪሳውያን፡ይጦሙ፡ነበር።መጥተውም፦የዮሐንስና፡የፈሪሳውያን፡ደቀ፡ መዛሙርት፡የሚጦሙት፡የአንተ፡ደቀ፡መዛሙርት፡ግን፡የማይጦሙት፡ስለ፡ምንድር፡ነው፧አሉት። 19፤ኢየሱስም፡አላቸው፦ሙሽራው፡ከነርሱ፡ጋራ፡ሳለ፡ሚዜዎች፡ሊጦሙ፡ይችላሉን፧ሙሽራው፡ከነርሱ፡ ጋራ፡ሳለ፡ሊጦሙ፡አይችሉም። 20፤ነገር፡ግን፥ሙሽራው፡ከነርሱ፡የሚወሰድበት፡ወራት፡ይመጣል፥በዚያ፡ወራትም፡ይጦማሉ። 21፤በአረጀ፡ልብስ፡ዐዲስ፡ዕራፊ፡የሚጥፍ፡የለም፤ቢደረግ፡ግን፥ዐዲሱ፡መጣፊያ፡አሮጌውን፡ ይቦጭቀዋል፥መቀደዱም፡የባሰ፡ይኾናል። 22፤በአረጀ፡አቍማዳም፡ዐዲስ፡የወይን፡ጠጅ፡የሚያኖር፡የለም፤ቢደረግ፡ግን፥የወይን፡ጠጁ፡አቍማዳውን፡ ያፈነዳል፡የወይኑም፡ጠጅ፡ይፈሳል፡አቍማዳውም፡ይጠፋል፡ዐዲሱን፡የወይን፡ጠጅ፡ግን፡በዐዲስ፡አቍማዳ፡ ያኖራሉ። 23፤በሰንበትም፡በዕርሻ፡መካከል፡ሲያልፍ፡ደቀ፡መዛሙርቱ፡እየኼዱ፡እሸት፡ይቀጥፉ፡ዠመር። 24፤ፈሪሳውያንም፦እንሆ፥በሰንበት፡ያልተፈቀደውን፡ስለ፡ምን፡ያደርጋሉ፧አሉት። 25፤ርሱም፦ዳዊት፡ባስፈለገውና፡በተራበ፡ጊዜ፥ርሱ፡ዐብረውት፡ከነበሩት፡ጋራ፡ያደረገውን፥ 26፤አብያተር፡ሊቀ፡ካህናት፡በነበረ፡ጊዜ፡ወደእግዚአብሔር፡ቤት፡እንደ፡ገባ፥ከካህናት፡በቀር፡መብላት፡ ያልተፈቀደውን፡የመሥዋዕትን፡እንጀራ፡እንደ፡በላ፥ከርሱም፡ጋራ፡ለነበሩት፡እንደ፡ሰጣቸው፡ከቶ፡ አላነበባችኹምን፧አላቸው። 27፤ደግሞ፦ሰንበት፡ስለ፡ሰው፡ተፈጥሯል፡እንጂ፡ሰው፡ስለ፡ሰንበት፡አልተፈጠረም፤ 28፤እንዲሁም፡የሰው፡ልጅ፡ለሰንበት፡እንኳ፡ጌታዋ፡ነው፡አላቸው።

1፤ደግሞም፡ወደ፡ምኵራብ፡ገባ፥በዚያም፡እጁ፡የሰለለች፡ሰው፡ነበር፤ 2፤ሊከሱትም፥በሰንበት፡ይፈውሰው፡እንደ፡ኾነ፡ይጠባበቁት፡ነበር። 3፤እጁ፡የሰለለችውንም፡ሰው፦ተነሥተኽ፡ወደ፡መካከል፡ና፡አለው። 4፤በሰንበት፡በጎ፡ማድረግ፡ተፈቅዷልን፧ወይስ፡ክፉ፧ነፍስ፡ማዳን፡ወይስ፡መግደል፧አላቸው፤እነርሱም፡ ዝም፡አሉ። 5፤ስለልባቸውም፡ድንዛዜ፡ዐዝኖ፡ዙሪያውን፡እየተመለከተ፡በቍጣ፡አያቸው፥ሰውየውንም፦እጅኽን፡ዘርጋ፡ አለው። 6፤ዘረጋትም፥እጁም፡ዳነች።ፈሪሳውያንም፡ወጥተው፡ወዲያው፡እንዴት፡አድርገው፡እንዲያጠፉት፡ከሄሮድስ፡ ወገን፡ጋራ፡ተማከሩበት። 7፤ኢየሱስም፡ከደቀ፡መዛሙርቱ፡ጋራ፡ወደ፡ባሕር፡ፈቀቅ፡አለ፤ከገሊላ፡የመጡም፡ብዙ፡ሰዎች፡ተከተሉት፤ 8፤እንዴት፡ትልቅ፡ነገርም፡እንዳደረገው፡ሰምተው፡ብዙ፡ሰዎች፡ከይሁዳ፡ከኢየሩሳሌምም፡ከኤዶምያስም፡ ከዮርዳኖስ፡ማዶም፡ከጢሮስና፡ከሲዶና፡ምድርም፡ወደ፡ርሱ፡መጡ። 9፤ሰዎቹም፡እንዳያጋፉት፡ታንኳን፡ያቈዩለት፡ዘንድ፡ደቀ፡መዛሙርቱን፡አዘዛቸው፤ 10፤ብዙ፡ሰዎችን፡አድኖ፡ነበርና፥ስለዚህም፡ሥቃይ፡ያለባቸው፡ዅሉ፡እንዲዳስሱት፡ይወድቁበት፡ነበር። 11፤ርኩሳን፡መናፍስትም፡ባዩት፡ጊዜ፡በፊቱ፡ተደፍተው፦አንተ፡የእግዚአብሔር፡ልጅ፡ነኽ፡እያሉ፡ጮኹ። 12፤እንዳይገልጡትም፡በጣም፡አዘዛቸው። 13፤ወደ፡ተራራም፡ወጣ፥ራሱም፡የወደዳቸውን፡ወደ፡ርሱ፡ጠራ፥ወደ፡ርሱም፡ኼዱ። 14፤ከርሱም፡ጋራ፡እንዲኖሩና፡ለመስበክ፡እንዲልካቸው፥ 15፤ድውዮችንም፡ሊፈውሱ፡አጋንንትንም፡ሊያወጡ፡ሥልጣን፡ይኾንላቸው፡ዘንድ፡ዐሥራ፡ኹለት፡አደረገ፤

እየሱስ ከደቀመዝሙሮቹ ጋር

16፤ስምዖንንም፡ጴጥሮስ፡ብሎ፡ሰየመው፤ 17፤የዘብዴዎስንም፡ልጅ፡ያዕቆብን፡የያዕቆብንም፡ወንድም፡ዮሐንስን፡ቦአኔርጌስ፡ብሎ፡ሰየማቸው፥
የነጐድጓድ፡ ልጆች፡ማለት፡ነው፤ 18፤እንድርያስንም፡ፊልጶስንም፡በርተሎሜውስንም፡ማቴዎስንም፡ቶማስንም፡የእልፍዮስን፡ልጅ፡
ያዕቆብንም፡ ታዴዎስንም፡ቀነናዊውንም፡ስምዖንን፥ 19፤አሳልፎ፡የሰጠውንም፡የአስቆሮቱን፡ይሁዳን። 20፤ወደ፡ቤትም፡መጡ፤እንጀራም፡መብላት፡ስንኳ፡እስኪሳናቸው፡ድረስ፡እንደ፡ገና፡ብዙ፡ሰዎች፡
ተሰበሰቡ። 21፤ዘመዶቹም፡ሰምተው፦አበደ፡ብለዋልና፥ሊይዙት፡ወጡ። 22፤ከኢየሩሳሌም፡የወረዱ፡ጻፊዎችም፦ብዔል፡ዜቡል፡አለበት፤ደግሞ፦በአጋንንት፡አለቃ፡አጋንንትን፡
ያወጣል፡ብለው፡ተናገሩ።
23፤እነርሱንም፡ወደ፡ርሱ፡ጠርቶ፡በምሳሌ፡አላቸው፦ሰይጣን፡ሰይጣንን፡ሊያወጣው፡እንዴት፡ይችላል፧ 24፤መንግሥትም፡ርስ፡በርሷ፡ከተለያየች፡ያች፡መንግሥት፡ልትቆም፡አትችልም፤ 25፤ቤትም፡ርስ፡በርሱ፡ከተለያየ፡ያ፡ቤት፡ሊቆም፡አይችልም። 26፤ሰይጣንም፡ራሱን፡ተቃውሞ፡ከተለያየ፥መጨረሻ፡ይኾንበታል፡እንጂ፡ሊቆም፡አይችልም። 27፤ነገር፡ግን፥አስቀድሞ፡ኀይለኛውን፡ሳያስር፡ወደኀይለኛው፡ቤት፡ገብቶ፡ዕቃውን፡ሊበዘብዝ፡የሚችል፡ የለም፥ከዚያም፡ወዲያ፡ቤቱን፡ይበዘብዛል። 28፤እውነት፡እላችዃለኹ፥ለሰው፡ልጆች፡ኀጢአት፡ዅሉ፡የሚሳደቡትም፡ስድብ፡ዅሉ፡ይሰረይላቸዋል፤ 29፤በመንፈስ፡ቅዱስ፡ላይ፡የሚሳደብ፡ዅሉ፡ግን፡የዘለዓለም፡ኀጢአት፡ዕዳ፡ይኾንበታል፡እንጂ፡ለዘለዓለም፡ አይሰረይለትም። 30፤ርኩስ፡መንፈስ፡አለበት፡ይሉ፡ነበርና። 31፤እናቱና፡ወንድሞቹም፡መጡ፥በውጭም፡ቆመው፡ወደ፡ርሱ፡ልከው፡አስጠሩት። 32፤ብዙ፡ሰዎችም፡በዙሪያው፡ተቀምጠው፡ነበሩና፦እንሆ፥እናትኽ፡ወንድሞችኽም፡በውጭ፡ቆመው፡ ይፈልጉኻል፡አሉት። 33፤መልሶም፦እናቴ፡ማን፡ናት፧ወንድሞቼስ፡እነ፡ማን፡ናቸው፧አላቸው። 34፤በዙሪያው፡ተቀምጠው፡ወደነበሩትም፡ተመለከተና፦እንሆ፥እናቴ፡ወንድሞቼም። 35፤የእግዚአብሔርን፡ፈቃድ፡የሚያደርግ፡ዅሉ፥ርሱ፡ወንድሜ፡ነው፡እኅቴም፡እናቴም፡አለ።

1፤ደግሞም፡በባሕር፡ዳር፡ሊያስተምር፡ዠመረ።እጅግ፡ብዙ፡ሰዎችም፡ወደ፡ርሱ፡ስለ፡ተሰበሰቡ፡ርሱ፡ በታንኳ፡ገብቶ፡በባሕር፡ላይ፡ተቀመጠ፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡በባሕር፡ዳር፡በምድር፡ላይ፡ነበሩ። 2፤በምሳሌም፡ብዙ፡ያስተምራቸው፡ነበር፥በትምህርቱም፡አላቸው፦ስሙ፤ 3-4፤እንሆ፥ዘሪ፡ሊዘራ፡ወጣ።ሲዘራም፡አንዳንዱ፡በመንገድ፡ዳር፡ወደቀና፡ወፎች፡መጥተው፡በሉት።

ክርስቶስ ሲያስተምር ፣ ሊዘራ የወጣው ገበሬ ምሳሌ

5፤ሌላውም፡ብዙ፡መሬት፡በሌለበት፡በጭንጫ፡ላይ፡ወደቀና፡ጥልቅ፡መሬት፡ስላልነበረው፡ ወዲያው፡በቀለ፤ 6፤ፀሓይም፡ሲወጣ፡ጠወለገ፥ሥርም፡ስላልነበረው፡ደረቀ። 7፤ሌላውም፡በሾኽ፡መካከል፡ ወደቀ፥ሾኽም፡ ወጣና፡ዐነቀው፥ፍሬም፡አልሰጠም። 8፤ሌላውም፡በመልካም፡መሬት፡ላይ፡ወደቀና፡ወጥቶ፡አድጎ፡ፍሬ፡ ሰጠ፥አንዱም፡ሠላሳ፡ አንዱም፡ስድሳ፡ አንዱም፡መቶ፡አፈራ። 9፤የሚሰማ፡ዦሮ፡ያለው፡ይስማ፡አለ። 10፤ብቻውንም፡በኾነ፡ጊዜ፥በዙሪያው፡የነበሩት፡ከዐሥራ፡ ኹለቱ፡ጋራ፡ስለ፡ምሳሌው፡ጠየቁት። 11-12፤እንዲህም፡አላቸው፦ለእናንተ፡የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡ምስጢር፡ማወቅ፡ተሰጥቷችዃል፤ በውጭ፡ላሉት፡ግን፥አይተው፡እንዲያዩ፡እንዳይመለከቱም፥ሰምተውም፡እንዲሰሙ፡ እንዳያስተውሉም፥እንዳይመለሱ፡ኀጢአታቸውም፡እንዳይሰረይላቸው፡ነገር፡ዅሉ፡በምሳሌ፡
ይኾንባቸዋል። 13፤አላቸውም፦ይህን፡ምሳሌ፡አታውቁምን፧እንዴትስ፡ምሳሌዎቹን፡ዅሉ፡ታውቃላችኹ፧ 14፤ዘሪው፡ቃሉን፡ይዘራል።ቃልም፡በተዘራበት፡በመንገድ፡ዳር፡የኾኑት፡እነዚህ፡ናቸው፥ 15፤በሰሙት፡ጊዜም፡ሰይጣን፡ወዲያው፡መጥቶ፡በልባቸው፡የተዘራውን፡ቃል፡ይወስዳል። 16፤እንዲሁም፡በጭንጫ፡ላይ፡የተዘሩት፡እነዚህ፡ናቸው፥ቃሉንም፡ሰምተው፡ወዲያው፡በደስታ፡ ይቀበሉታል፥ 17፤ለጊዜውም፡ነው፡እንጂ፡በእነርሱ፡ሥር፡የላቸውም፥ዃላም፡በቃሉ፡ምክንያት፡መከራ፡ወይም፡ስደት፡ በኾነ፡ጊዜ፡ወዲያው፡ይሰናከላሉ። 18፤በሾኽም፡የተዘሩት፡ሌላዎች፡ናቸው፥ቃሉን፡የሰሙት፡ እነዚህ፡ናቸው፥ 19፤የዚህም፡ዓለም፡ዐሳብና፡የባለጠግነት፡ማታለል፡የሌላውም፡ነገር፡ምኞት፡ገብተው፡ቃሉን፡ ያንቃሉ፥የማያፈራም፡ይኾናል። 20፤በመልካምም፡መሬት፡የተዘሩት፡ቃሉን፡ሰምተው፡የሚቀበሉት፡ አንዱም፡ሠላሳ፡አንዱም፡ስድሳ፡አንዱም፡መቶ፡ፍሬ፡የሚያፈሩት፡እነዚህ፡ናቸው። 21፤እንዲህም፡አላቸው፦መብራትን፡ከእንቅብ፡ወይስ፡ከዐልጋ፡በታች፡ሊያኖሩት፡ያመጡታልን፧በመቅረዝ፡ ላይ፡ሊያኖሩት፡አይደለምን፧ 22፤እንዲገለጥ፡ባይኾን፡የተሰወረ፡የለምና፤ወደ፡ግልጥ፡እንዲመጣ፡እንጂ፡ የተሸሸገ፡የለም። 23፤የሚሰማ፡ዦሮ፡ያለው፡ቢኖር፡ይስማ። 24፤አላቸውም፦ምን፡እንድትሰሙ፡ተጠበቁ።በምትሰፍሩበት፡መስፈሪያ፡ይሰፈርላችዃል፡ለእናንተም፡ ይጨመርላችዃል። 25፤ላለው፡ይሰጠዋልና፤ከሌለውም፡ያው፡ያለው፡እንኳ፡ይወሰድበታል። 26፤ርሱም፡አለ፦በምድር፡ዘርን፡እንደሚዘራ፡ሰው፡የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡እንደዚህ፡ናት፡ሌሊትና፡ ቀን፡ይተኛልም፡ይነሣልም፥ 27፤ርሱም፡እንዴት፡እንደሚኾን፡ሳያውቅ፡ዘሩ፡ይበቅላል፡ያድግማል። 28፤ምድሪቱም፡ዐውቃ፡በመዠመሪያ፡ቡቃያ፡ዃላም፡ዛላ፡ዃላም፡በዛላው፡ፍጹም፡ሰብል፡ታፈራለች። 29፤ፍሬ፡ግን፡ሲበስል፡መከር፡ደርሷልና፥ወዲያው፡ማጭድ፡ይልካል። 30፤ርሱም፡አለ፦የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡በምን፡እናስመስላታለን፧ወይስ፡በምን፡ምሳሌ፡እንመስላታለን፧ 31፤እንደ፡ሰናፍጭ፡ቅንጣት፡ናት፥ርሷም፡በምድር፡በተዘራች፡ጊዜ፡በምድር፡ካለ፡ዘር፡ዅሉ፡ ታንሳለች፤በተዘራችም፡ጊዜ፡ትወጣለች፡ከአትክልትም፡ዅሉ፡የምትበልጥ፡ትኾናለች፥ 32፤የሰማይ፡ወፎችም፡በጥላዋ፡ሊሰፍሩ፡እስኪችሉ፡ታላላቅ፡ቅርንጫፎች፡ታደርጋለች። 33፤መስማትም፡በሚችሉበት፡መጠን፡እነዚህን፡በሚመስል፡በብዙ፡ምሳሌ፡ቃሉን፡ይነግራቸው፡ ነበር፤ያለምሳሌ፡
ግን፡አልነገራቸውም፥
34፤ለብቻቸውም፡ሲኾኑ፡ነገሩን፡ዅሉ፡ለገዛ፡ደቀ፡መዛሙርቱ፡ ይፈታላቸው፡ነበር።
35፤በዚያም፡ቀን፡በመሸ፡
ጊዜ፦ወደ፡ማዶ፡እንሻገር፡አላቸው።
36፤ሕዝቡንም፡ትተው፡በታንኳ፡እንዲያው፡ወሰዱት፥ሌላዎች፡ታንኳዎችም፡ከርሱ፡ጋራ፡ነበሩ። 37፤ብርቱ፡ዐውሎ፡ነፋስም፡ተነሣና፡ውሃ፡በታንኳዪቱ፡እስኪሞላ፡ድረስ፡ማዕበሉ፡በታንኳዪቱ፡ይገባ፡ነበር።

ክርስቶስ በመዐበሉ መሐል ተኝቶ
38፤ርሱም፡በስተዃላዋ፡ትራስ፡ተንተርሶ፡ተኝቶነበር፤አንቅተውም፣ መምህርሆይ፥ስንጠፋ አይገድኽምን፡አሉት።

39፤ነቅቶም፡ነፋሱን፡ገሠጸው፡ባሕሩንም፦ዝም፡በል፥ጸጥ፡በል፡አለው።ነፋሱም፡ተወ፥ታላቅ፡ጸጥታምኾነ። 40፤እንዲህ፡የምትፈሩ፡ስለ፡ምን፡ነው፧እንዴትስ፡እምነት፡የላችኹም፧አላቸው። 41፤ እጅግም ፈሩና፡እንግዲህ፡ነፋስም፡ባሕርም፡የሚታዘዙለት፡ይህ፡ማን፡ነው፧ተባባሉ።

1፤ወደባሕር፡ማዶም፡ወደጌርጌሴኖን፡አገር፡መጡ። 2፤ከታንኳዪቱም፡በወጣ፡ጊዜ፥ርኩስ፡መንፈስ፡የያዘው፡ሰው፡ከመቃብር፡ወጥቶ፡ወዲያው፡ተገናኘው፤ 3፤ርሱም፡በመቃብር፡ይኖር፡ነበር፥በሰንሰለትም፡ስንኳ፡ማንም፡ሊያስረው፡በዚያን፡ጊዜ፡አይችልም፡ነበር፤ 4፤ብዙ፡ጊዜ፡በእግር፡ብረትና፡በሰንሰለት፡ይታሰር፡ነበርና፥ዳሩ፡ግን፡ሰንሰለቱን፡ይበጣጥስ፡እግር፡ብረቱንም፡ ይሰባብር፡ነበር፥ሊያሸንፈውም፡የሚችል፡አልነበረም፤ 5፤ዅልጊዜም፡ሌሊትና፡ቀን፡በመቃብርና፡በተራራ፡ኾኖ፡ይጮኽ፡ነበር፡ሰውነቱንም፡በድንጋይ፡ይቧጭር፡ ነበር። 6፤ኢየሱስንም፡ከሩቅ፡ባየ፡ጊዜ፡ሮጦ፡ሰገደለት፥ 7፤በታላቅ፡ድምፅም፡እየጮኸ፦የልዑል፡እግዚአብሔር፡ልጅ፡ኢየሱስ፡ሆይ፥ከአንተ፡ጋራ፡ምን፡ አለኝ፧እንዳታሠቃየኝ፡በእግዚአብሔር፡አምልኻለኹ፡አለ፤ 8፤አንተ፡ርኩስ፡መንፈስ፥ከዚህ፡ሰው፡ውጣ፡ብሎት፡ነበርና፦ 9፤ስምኽ፡ማን፡ነው፧ብሎ፡ጠየቀው፦ብዙዎች፡ነንና፡ስሜ፡ሌጌዎን278፡ነው፡አለው፥ 10፤ከአገርም፡ውጭ፡እንዳይሰዳቸው፡አጥብቆ፡ለመነው። 11፤በዚያም፡በተራራ፡ጥግ፡ብዙ፡የዕሪያ፡መንጋ፡ይሰማራ፡ነበርና፦ 12፤ወደ፡ዕሪያዎቹ፡እንድንገባ፡ስደደን፡ብለው፡ለመኑት። 13፤ኢየሱስም፡ፈቀደላቸው።ርኩሳን፡መናፍስቱም፡ወጥተው፡ወደ፡ዕሪያዎቹ፡ገቡ፥ኹለት፡ሺሕም፡የሚያኽል፡ መንጋ፡ከአፋፉ፡ወደ፡ባሕር፡ተጣደፉና፡በባሕር፡ሰጠሙ። 14፤እረኛዎቹም፡ሸሽተው፡በከተማውና፡በአገሩ፡አወሩ፤ነገሩም፡ምን፡እንደ፡ኾነ፡ለማየት፡መጡ። 15፤ወደ፡ኢየሱስም፡መጡ፥አጋንንትም፡ያደሩበትን፡ሌጌዎንም፡የነበረበትን፡ሰው፡ተቀምጦ፡ለብሶም፡ልቡም፡ ተመልሶ፡አዩና፡ፈሩ። 16፤ያዩት፡ሰዎችም፡አጋንንት፡ላደሩበት፡ሰው፡የኾነውንና፡ስለ፡ዕሪያዎቹ፡ተረኩላቸው። 17፤ከአገራቸውም፡እንዲኼድላቸው፡ይለምኑት፡ዠመር። 18፤ወደ፡ታንኳዪቱም፡በገባ፡ጊዜ፡አጋንንት፡ዐድረውበት፡የነበረው፡ሰው፡ከርሱ፡ጋራ፡እንዲኖር፡ለመነው። 19፤ኢየሱስም፡አልፈቀደለትም፥ነገር፡ግን፦ወደ፡ቤትኽ፡በቤተ፡ሰዎችኽ፡ዘንድ፡ኼደኽ፡ጌታ፡እንዴት፡ያለ፡ ታላቅ፡ነገር፡እንዳደረገልኽ፡እንዴትስ፡እንደ፡ማረኽ፡አውራላቸው፡አለው። 20፤ኼዶም፡ኢየሱስ፡እንዴት፡ያለ፡ታላቅ፡ነገር፡እንዳደረገለት፡ዐሥር፡ከተማ፡በሚባል፡አገር፡ይሰብክ፡ ዠመር፤ዅሉም፡ተደነቁ። 21፤ኢየሱስም፡ደግሞ፡በታንኳዪቱ፡ወደ፡ማዶ፡ከተሻገረ፡በዃላ፥ብዙ፡ሰዎች፡ወደ፡ርሱ፡ ተሰበሰቡ፥በባሕርም፡አጠገብ፡ነበረ። 22፤ኢያኢሮስ፡የተባለ፡ከምኵራብ፡አለቃዎች፡አንዱ፡መጣ፤ባየውም፡ጊዜ፡በእግሩ፡ላይ፡ወደቀና፦ 23፤ታናሺቱ፡ልጄ፡ልትሞት፡ቀርባለችና፡እንድትድንና፡በሕይወት፡እንድትኖር፡መጥተኽ፡እጅኽን፡ጫንባት፡ ብሎ፡አጥብቆ፡ለመነው። 24፤ከርሱም፡ጋራ፡ኼደ።ብዙ፡ሕዝብም፡ተከተሉት፡አጋፉትም። 25፤ከዐሥራ፡ኹለት፡ዓመትም፡ዠምሮ፡ደም፡የሚፈሳ፟ት፡ሴት፡ነበረች፥ 26፤ከብዙ፡ባለመድኀኒቶችም፡ብዙ፡ተሠቃየች፤ገንዘቧንም፡ዅሉ፡ከስራ፡ባሰባት፡እንጂ፡ምንም፡ አልተጠቀመችም፤ 27፤የኢየሱስንም፡ወሬ፡ሰምታ፡በስተዃላው፡በሰዎች፡መካከል፡መጥታ፡ልብሱን፡ዳሰሰች። 28፤ልብሱን፡ብቻ፡የዳሰስኹ፡እንደ፡ኾነ፡እድናለኹ፡ብላለችና። 29፤ወዲያውም፡የደሟ፡ምንጭ፡ደረቀ፡ከሥቃይዋም፡እንደ፡ዳነች፡በሰውነቷ፡ዐወቀች። 30፤ወዲያውም፡ኢየሱስ፡ከርሱ፡ኀይል፡እንደ፡ወጣ፡በገዛ፡ራሱ፡ዐውቆ፡በሕዝቡ፡መካከል፡ዘወር፡ ብሎ፦ልብሴን፡የዳሰሰ፡ማን፡ነው፧አለ። 31፤ደቀ፡መዛሙርቱም፦ሕዝቡ፡ሲያጋፉኽ፡እያየኽ፦ማን፡ዳሰሰኝ፡ትላለኽን፧አሉት። 32፤ይህንም፡ያደረገችውን፡ለማየት፡ዘወር፡ብሎ፡ይመለከት፡ነበር። 33፤ሴቲቱ፡ግን፡የተደረገላትን፡ስላወቀች፥እየፈራች፡እየተንቀጠቀጠችም፥መጥታ፡በፊቱ፡ተደፋች፡ እውነቱንም፡ዅሉ፡ነገረችው። 34፤ርሱም፦ልጄ፡ሆይ፥እምነትሽ፡አድኖሻል፤በሰላም፡ኺጂ፡ከሥቃይሽም፡ተፈወሽ፡አላት። 35፤ርሱም፡ገና፡ሲናገር፡ከምኵራብ፡አለቃው፡ቤት፡ዘንድ፡የመጡት፦ልጅኽ፡ሞታለች፤ስለ፡ምን፡ መምህሩን፡አኹን፡ታደክመዋለኽ፧አሉት። 36፤ኢየሱስ፡ግን፡የተናገሩትን፡ቃል፡አድምጦ፡ለምኵራቡ፡አለቃ፦እመን፡ብቻ፡እንጂ፡አትፍራ፡አለው። 37፤ከጴጥሮስም፡ከያዕቆብም፡ከያዕቆብም፡ወንድም፡ከዮሐንስ፡በቀር፡ማንም፡እንዲከተለው፡አልፈቀደም። 38፤ወደምኵራቡ፡አለቃ፡ቤትም፡መጥቶ፡ሰዎች፡ሲንጫጩና፡ሲያለቅሱ፡ዋይታም፡ሲያበዙ፡አየ፤ 39፤ገብቶም፦ስለ፡ምን፡ትንጫጫላችኹ፥ታለቅሳላችኹም፧ብላቴናዪቱ፡ተኝታለች፡እንጂ፡አልሞተችም፡ አላቸው። 40፤በጣምም፡ሣቁበት።ርሱ፡ግን፡ዅሉን፡አስወጥቶ፡የብላቴናዪቱን፡አባትና፡እናትም፡ከርሱ፡ጋራ፡ የነበሩትንም፡ይዞ፡ብላቴናዪቱ፡ወዳለችበት፡ገባ። 41፤የብላቴናዪቱንም፡እጅ፡ይዞ፦ጣሊታ279፡ቁሚ፡አላት፤ፍችውም፡አንቺ፡ብላቴና፡ተነሽ፡እልሻለኹ፡ነው። 42፤ብላቴናዪቱም፡የዐሥራ፡ኹለት፡ዓመት፡ልጅ፡ነበረችና፡ወዲያው፡ቆማ፡ተመላለሰች።ወዲያውም፡ታላቅ፡ መገረም፡ተገረሙ። 43፤ይህንም፡ማንም፡እንዳያውቅ፡አጥብቆ፡አዟቸው።የምትበላውን፡ስጧት፡አላቸው።

  • ሮማ.፥ሌጌዎን፡(ሰራዊት፥ጭፍራ፤6000፡ጭፍራ፡ከናለቃው፡አንድ፡ሌጌዎን፡ይባላል።ኪ.ወ.ክ.፥ገ.558)።

1፤ከዚያም፡ወጥቶ፡ወደገዛ፡አገሩ፡መጣ፡ደቀ፡መዛሙርቱም፡ተከተሉት። 2፤ሰንበትም፡በኾነ፡ጊዜ፡በምኵራብ፡ያስተምር፡ዠመር፤ብዙዎችም፡ሰምተው፡ተገረሙና፦እነዚህን፡ነገሮች፡ ይህ፡ከወዴት፡አገኛቸው፧ለዚህ፡የተሰጠችው፡ጥበብ፡ምንድር፡ናት፧በእጁም፡የሚደረጉ፡እንደነዚህ፡ያሉ፡ ተኣምራት፡ምንድር፡ናቸው፧ 3፤ይህስ፡ጸራቢው፡የማርያም፡ልጅ፡የያዕቆብም፡የዮሳም፡የይሁዳም፡የስምዖንም፡ወንድም፡ አይደለምን፧እኅቶቹስ፡በዚህ፡በእኛ፡ዘንድ፡አይደሉምን፧አሉ፤ይሰናከሉበትም፡ነበር። 4፤ኢየሱስም፦ነቢይ፡ከገዛ፡አገሩና፡ከገዛ፡ዘመዶቹ፡ከገዛ፡ቤቱም፡በቀር፡ሳይከበር፡አይቀርም፡አላቸው። 5፤በዚያም፡በጥቂቶች፡ድውዮች፡ላይ፡እጁን፡ጭኖ፡ከመፈወስ፡በቀር፥ተኣምር፡ሊያደርግ፡ምንም፡አልቻለም። 6፤ስላለማመናቸውም፡ተደነቀ።በመንደሮችም፡እያስተማረ፡ይዞር፡ነበር። 7፤አስራ፡ኹለቱንም፡ወደ፡ርሱ፡ጠራ፥ኹለት፡ኹለቱንም፡ይልካቸው፡ዠመር፥በርኩሳን፡መናፍስትም፡ላይ፡ ሥልጣን፡ሰጣቸው፥ 8፤ለመንገድም፡ከበትር፡በቀር፡እንጀራም፡ቢኾን፡ከረጢትም፡ቢኾን፡መሐለቅም፡በመቀነታቸው፡ቢኾን፡ እንዳይዙ፡አዘዛቸው።

ክርስቶስ ደቀመዝሙሮቹን በርኩሳን መንፈስ ላይ ስልጣን ሰጥቶ ሁለት ሁለት አርጎ ሲልካቸው

9፤በእግራችኹ፡ጫማ፡አድርጉ፡እንጂ፡ኹለት፡እጀ፡ጠባብ፡አትልበሱ፡አለ። 10፤በማናቸውም፡ስፍራ፡ወደ፡ቤት፡ብትገቡ፡ከዚያ፡እስክትወጡ፡ድረስ፡በዚያው፡ተቀመጡ። 11፤ከማይቀበሏችኹና፡ከማይሰሟችኹ፡ስፍራ፡ዅሉ፥ከዚያ፡ወጥታችኹ፡ምስክር፡ይኾንባቸው፡ዘንድ፡ ከእግራችኹ፡በታች፡ያለውን፡ትቢያ፡አራግፉ።እውነት፡እላችዃለኹ፥ከዚያች፡ከተማ፡ይልቅ፡ለሰዶምና፡ ለገሞራ፡በፍርድ፡ቀን፡ይቀልላቸዋል፡አላቸው። 12፤ወጥተውም፡ንስሓ፡እንዲገቡ፡ሰበኩ፥ብዙ፡አጋንንትንም፡አወጡ፥ 13፤ብዙ፡ድውዮችንም፡ዘይት፡እየቀቡ፡ፈወሷቸው። 14፤ስሙም፡ተገልጧልና፥ንጉሡ፡ሄሮድስ፡በሰማ፡ጊዜ፦መጥምቁ፡ዮሐንስ፡ከሙታን፡ተነሥቷል፡
ስለዚህም፡ኀይል፡በርሱ፡ይደረጋል፡አለ። 15፤ሌላዎችም፦ኤልያስ፡ነው፡አሉ፤ሌላዎችም፦ከነቢያት፡እንደ፡አንዱ፡ነቢይ፡ነው፡አሉ። 16፤ሄሮድስ፡ግን፡ሰምቶ፦እኔ፡ራሱን፡ያስቈረጥኹት፡ዮሐንስ፡ይህ፡ነው፡ርሱ፡ከሙታን፡ተነሥቷል፡አለ። 17፤ሄሮድስ፡የወንድሙን፡የፊልጶስን፡ሚስት፡ሄሮድያዳን፡አግብቶ፡ነበርና፥በርሷ፡ምክንያት፡ራሱ፡ልኮ፡
ዮሐንስን፡አስይዞ፡በወህኒ፡አሳስሮት፡ነበር፤ 18፤ዮሐንስ፡ሄሮድስን፦የወንድምኽ፡ሚስት፡ለአንተ፡ልትኾን፡አልተፈቀደም፡ይለው፡ነበርና። 19፤ሄሮድያዳ፡ግን፡ተቃውማው፡ልትገድለው፡ትፈልግ፡ነበር፡አልቻለችም፤ 20፤ሄሮድስ፡ዮሐንስ፡ጻድቅና፡ቅዱስ፡ሰው፡እንደ፡ኾነ፡ዐውቆ፡ይፈራውና፡ይጠባበቀው፡ነበር፤ርሱንም፡ ሰምቶ፡በብዙ፡ነገር፡ያመነታ፡ነበር፤ 21፤በደስታም፡ይሰማው፡ነበር።ሄሮድስም፡በተወለደበት፡ቀን፡ለመኳንንቱና፡ለሻለቃዎቹ፡ለገሊላም፡ሹማምንት፡ ግብር፡ባደረገ፡ጊዜ፡ምቹ፡ቀን፡ኾነላትና፡ 22፤የሄሮድያዳ፡ልጅ፡ገብታ፡ስትዘፍን፡ሄሮድስንና፡ከርሱ፡ጋራ፡የተቀመጡትን፡ደስ፡አሠኘቻቸው።ንጉሡም፡ ብላቴናዪቱን፦የምትወጂውን፡ዅሉ፡ለምኚኝ፡እሰጥሽማለኹ፡አላት፤ 23፤የመንግሥቴ፡እኩሌታ፡ስንኳ፡ቢኾን፡የምትለምኚውን፡ዅሉ፡እሰጥሻለኹ፡ብሎ፡ማለላት። 24፤ወጥታም፡ለእናቷ፦ምን፡ልለምነው፧አለች።ርሷም፦የመጥምቁን፡የዮሐንስን፡ራስ፡አለች። 25፤ወዲያውም፡ፈጥና፡ወደ፡ንጉሡ፡ገብታ፦የመጥምቁን፡የዮሐንስን፡ራስ፡በወጭት፡አኹን፡ልትሰጠኝ፡ እወዳለኹ፡ብላ፡ለመነችው። 26፤ንጉሡም፡እጅግ፡ዐዝኖ፡ስለ፡መሐላው፡ከርሱም፡ጋራ፡ስለተቀመጡት፡ሊነሣት፡አልወደደም። 27፤ወዲያውም፡ንጉሡ፡ባለወግ፡ልኮ፡ራሱን፡እንዲያመጣ፡አዘዘው።ኼዶም፡በወህኒ፡ራሱን፡ቈረጠ፥ 28፤ራሱንም፡በወጭት፡አምጥቶ፡ለብላቴናዪቱ፡ሰጣት፥ብላቴናዪቱም፡ለእናቷ፡ሰጠች። 29፤ደቀ፡መዛሙርቱም፡ሰምተው፡መጡ፡በድኑንም፡ወስደው፡ቀበሩት። 30፤ሐዋርያትም፡ወደ፡ኢየሱስ፡ተሰብስበው፡ያደረጉትንና፡ያስተማሩትን፡ዅሉ፡ነገሩት። 31፤እናንት፡ራሳችኹ፡ብቻችኹን፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ኑና፡ጥቂት፡ዕረፉ፡አላቸው፤የሚመጡና፡የሚኼዱ፡ ብዙዎች፡ነበሩና፥ለመብላት፡እንኳ፡ጊዜ፡ዐጡ። 32፤በታንኳውም፡ብቻቸውን፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ኼዱ። 33፤ሰዎችም፡ሲኼዱ፡አይዋቸው፡ብዙዎችም፡ዐወቋቸውና፡ከከተማዎች፡ዅሉ፡በእግር፡እየሮጡ፡ወዲያ፡ ቀደሟቸው፡ወደ፡ርሱም፡ተሰበሰቡ። 34፤ኢየሱስም፡ወጥቶ፡ብዙ፡ሕዝብ፡አየና፡እረኛ፡እንደሌላቸው፡በጎች፡ስለ፡ነበሩ፡ዐዘነላቸው፥ብዙም፡ ነገር፡ያስተምራቸው፡ዠመር። 35፤በዚያን፡ጊዜም፡ብዙ፡ሰዓት፡ካለፈ፡በዃላ፡ደቀ፡መዛሙርቱ፡ወደ፡ርሱ፡ቀርበው፦ቦታው፡ምድረ፡በዳ፡ ነው፡አኹንም፡መሽቷል፤ 36፤የሚበሉት፡የላቸውምና፡በዙሪያ፡ወዳሉ፡ገጠሮችና፡መንደሮች፡ኼደው፡እንጀራ፡ለራሳቸው፡እንዲገዙ፡ አሰናብታቸው፡አሉት። 37፤ርሱ፡ግን፡መልሶ፦እናንተ፡የሚበሉትን፡ስጧቸው፡አላቸው፦ኼደን፡እንጀራ፡በኹለት፡መቶ፡ዲናር፡ እንግዛላቸውን፧እንዲበሉም፡እንስጣቸውን፧አሉት። 38፤ርሱም፦ስንት፡እንጀራ፡አላችኹ፧ኺዱና፡እዩ፡አላቸው።ባወቁም፡ጊዜ፦ዐምስት፥ኹለትም፡ዓሣ፡ አሉት። 39፤ዅሉንም፡በየክፍሉ፡በለመለመ፡ሣር፡ላይ፡እንዲያስቀምጧቸው፡አዘዛቸው። 40፤መቶ፡መቶውና፡ዐምሳ፡ዐምሳው፡እየኾኑ፡በተራ፡በተራ፡ተቀመጡ። 41፤ዐምስቱንም፡እንጀራ፡ኹለቱንም፡ዓሣ፡ይዞ፡ወደ፡ሰማይ፡አሻቅቦ፡አየና፡ባረከ፥እንጀራውንም፡ቈርሶ፡ እንዲያቀርቡላቸው፡ለደቀ፡መዛሙርቱ፡ሰጠ፥ 42፤ኹለቱን፡ዓሣ፡ደግሞ፡ለዅሉ፡ከፈለ።ዅሉም፡በልተው፡ጠገቡ፤ 43፤ከቍርስራሹም፡ዐሥራ፡ኹለት፡መሶብ፡የሞላ፡አነሡ፥ከዓሣውም፡ደግሞ።

እየሱስ ከዐምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ ፭ሺውን ሲመግብ

44፤እንጀራውንም፡የበሉት፡ወንዶቹ፡ዐምስት፡ሺሕ፡ነበሩ። 45፤ወዲያውም፡ሕዝቡን፡ሲያሰናብት፡ሳለ፡ደቀ፡መዛሙርቱ፡በታንኳ፡ገብተው፡ወደ፡ማዶ፡
ወደ፡ቤተ፡ ሳይዳ፡እንዲቀድሙት፡ግድ፡አላቸው።
46፤ካሰናበታቸውም፡በዃላ፡ሊጸልይ፡ወደ፡ተራራ፡ወጣ።
47፤በመሸም፡ጊዜ፡ታንኳዪቱ፡በባሕር፡መካከል፡ሳለች፡ርሱ፡ብቻውን፡በምድር፡ላይ፡ነበረ። 48፤ነፋስ፡ወደ፡ፊታቸው፡ነበረና፡እየቀዘፉ፡ሲጨነቁ፡አይቶ፥ከሌሊቱ፡በአራተኛው፡ክፍል፡
በባሕር፡ላይ፡ እየኼደ፡ወደ፡እነርሱ፡መጣ፤ሊያልፋቸውም፡ይወድ፡ነበር።

እየሱስ ክርስቶስ በባሕር ላይ ሲራመድ

49፤እነርሱ፡ግን፡በባሕር፡ላይ፡ሲኼድ፡ባዩት፡ጊዜ፡ምትሀት፡መሰላቸውና፡ጮኹ፥ 50፤ዅሉ፡አይተውታልና፥ታወኩም።ወዲያውም፡ተናገራቸውና፦አይዟችኹ፤እኔ፡ነኝ፥አትፍሩ፡
አላቸው። 51፤ወደ፡እነርሱም፡ወደ፡ታንኳዪቱ፡ገባ፥ነፋሱም፡ተወ፤በራሳቸውም፡ያለመጠን፡እጅግ፡ተገረሙ፤ 52፤ስለ፡እንጀራው፡አላስተዋሉምና፤ነገር፡ግን፥ልባቸው፡ደንዝዞ፡ነበር። 53፤ተሻግረውም፡ወደ፡ምድር፡ወደ፡ጌንሴሬጥ፡ደረሱ፡ታንኳዪቱንም፡አስጠጉ። 54፤ከታንኳዪቱም፡ሲወጡ፡ወዲያው፡ዐውቀውት፡ 55፤በዚያች፡አገር፡ዅሉ፡ዙሪያ፡ሮጡና፡ርሱ፡እንዳለ፡ወደሰሙበት፡ስፍራ፡ሕመምተኛዎችን፡በዐልጋ፡ላይ፡ ያመጡ፡ዠመር። 56፤በገባበትም፡ስፍራ፡ዅሉ፥መንደርም፡ከተማም፡ገጠርም፡ቢኾን፥በገበያ፡ድውዮችን፡ያኖሩ፡ ነበር፤የልብሱንም፡ጫፍ፡እንኳ፡ሊዳስሱ፡ይለምኑት፡ነበር፡የዳሰሱትም፡ዅሉ፡ዳኑ።
(ጣልያታ፡ወይም፡ጣሊታ፡ማለት=ሴት፡ልጅ፥ቈንዦ፥ገና፡አካለ፡መጠን፡ያልሞላች)።

1፤ፈሪሳውያንና፡ከጻፊዎች፡ወገን፡ከኢየሩሳሌም፡የመጡትም፡ወደ፡ርሱ፡ተሰበሰቡ። 2፤ከደቀ፡መዛሙርቱም፡አንዳንድ፡በርኩስ፡ማለት፡ባልታጠበ፡እጅ፡እንጀራ፡ሲበሉ፡አዩ። 3፤ፈሪሳውያንና፡አይሁድም፡ዅሉ፡የሽማግሌዎችን፡ወግ፡ሲጠብቁ፡እጃቸውን፡ደኅና፡አድርገው፡ሳይታጠቡ፡ አይበሉምና፥ 4፤ከገበያም፡ተመልሰው፡ካልታጠቡ፡አይበሉም፥ጽዋንም፡ማድጋንም፡የናስ፡ዕቃንም፡ዐልጋንም፡እንደ፡ ማጠብ፡ሌላ፡ነገር፡ሊጠብቁት፡የተቀበሉት፡ብዙ፡አለ። 5፤ፈሪሳውያንም፡ጻፊዎችም፦ደቀ፡መዛሙርትኽ፡እንደ፡ሽማግሌዎች፡ወግ፡ስለ፡ምን፡አይኼዱም፧ነገር፡ ግን፡እጃቸውን፡ሳይታጠቡ፡እንጀራ፡ይበላሉ፡ብለው፡ጠየቁት። 6፤ርሱ፡ግን፡እንዲህ፡አላቸው፦ኢሳይያስ፡ስለ፡እናንተ፡ስለ፡ግብዞች፦ይህ፡ሕዝብ፡በከንፈሩ፡ያከብረኛል፡ ልቡ፡ግን፡ከእኔ፡በጣም፡የራቀ፡ነው፤ 7፤የሰውም፡ሥርዐት፡የኾነ፡ትምህርት፡እያስተማሩ፡በከንቱ፡ያመልኩኛል፡ተብሎ፡እንደ፡ተጻፈ፡በእውነት፡ ትንቢት፡ተናገረ። 8፤የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡ትታችኹ፡ጽዋን፡ማድጋንም፡እንደ፡ማጠብ፡የሰውን፡ወግ፡ ትጠብቃላችኹ፥ይህንም፡የመሰለ፡ብዙ፡ሌላ፡ነገር፡ታደርጋላችኹ። 9፤እንዲህም፡አላቸው፦ወጋችኹን፡ትጠብቁ፡ዘንድ፡የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡እጅግ፡ንቃችዃል። 10፤ሙሴ፦አባትኽንና፡እናትኽን፡አክብር፤ደግሞ፦አባቱን፡ወይም፡እናቱን፡የሰደበ፡ፈጽሞ፡ይሙት፡ ብሏልና። 11፤እናንተ፡ግን፡ትላላችኹ፦ሰው፡አባቱን፡ወይም፡እናቱን፦ከእኔ፡የምትጠቀምበት፡ነገር፡ዅሉ፡ቍርባን፡ ማለት፡መባ፡ነው፡ቢል፥ 12፤ለአባቱና፡ለእናቱ፡ምንም፡እንኳ፡ሊያደርግ፡ወደ፡ፊት፡አትፈቅዱለትም፤ 13፤ባስተላለፋችኹትም፡ወግ፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ትሽራላችኹ፤እንደዚሁም፡ይህን፡የሚመስል፡ብዙ፡ነገር፡ ታደርጋላችኹ። 14፤ደግሞም፡ሕዝቡን፡ጠርቶ፦ዅላችኹ፡እኔን፡ስሙ፥አስተውሉም። 15፤ከሰው፡የሚወጡት፡ሰውን፡የሚያረክሱ፡ናቸው፡እንጂ፥ከሰው፡ውጭ፡የሚገባውስ፡ሊያረክሰው፡የሚችል፡ ምንም፡የለም። 16፤የሚሰማ፡ዦሮ፡ያለው፡ቢኖር፡ይስማ፡አላቸው። 17፤ከሕዝቡ፡ዘንድ፡ወደ፡ቤት፡ከገባ፡በዃላ፡ደቀ፡መዛሙርቱ፡ምሳሌውን፡ጠየቁት። 18፤ርሱም፦እናንተ፡ደግሞ፡እንደዚህ፡የማታስተውሉ፡ናችኹን፧ከውጭ፡ወደ፡ሰው፡የሚገባ፡ሊያረክሰው፡ ምንም፡እንዳይችል፡አትመለከቱምን፧ 19፤ወደ፡ሆድ፡ገብቶ፡ወደ፡እዳሪ፡ይወጣል፡እንጂ፡ወደ፡ልብ፡አይገባምና፤መብልን፡ዅሉ፡እያጠራ፡ አላቸው። 20፤ርሱም፡አለ፦ከሰው፡የሚወጣው፡ሰውን፡የሚያረክስ፡ያ፡ነው።21፤ከውስጥ፡ከሰው፡ልብ፡የሚወጣ፡ክፉ፡ዐሳብ፥ 22፤ዝሙት፥መስረቅ፥መግደል፥ምንዝርነት፥መጐምዠት፥ክፋት፥ተንኰል፥መዳራት፥ምቀኝነት፥ስድብ፥ት ዕቢት፥ስንፍና፡ናቸውና፤ 23፤ይህ፡ክፉው፡ዅሉ፡ከውስጥ፡ይወጣል፡ሰውን፡ያረክሰዋል። 24፤ከዚያም፡ተነሥቶ፡ወደ፡ጢሮስና፡ወደሲዶና፡አገር፡ኼደ።ወደ፡ቤትም፡ገብቶ፡ማንም፡እንዳያውቅበት፡ ወደደ፡ሊሰወርም፡አልተቻለውም፤ 25፤ወዲያው፡ግን፡ታናሺቱ፡ልጇ፡ርኩስ፡መንፈስ፡ያደረባት፡አንዲት፡ሴት፡ስለ፡ርሱ፡ሰምታ፡መጣችና፡ በእግሩ፡ላይ፡ተደፋች፡ 26፤ሴቲቱም፡ግሪክ፥ትውልዷም፡ሲሮፊኒቃዊት፡ነበረች፤ከልጇ፡ጋኔን፡ያወጣላት፡ዘንድ፡ለመነችው። 27፤ኢየሱስ፡ግን፦ልጆቹ፡በፊት፡ይጠግቡ፡ዘንድ፡ተዪ፡የልጆቹን፡እንጀራ፡ይዞ፡ለቡችሎች፡መጣል፡ አይገ፟ባ፟ምና፥አላት። 28፤ርሷም፡መልሳ፦አዎን፥ጌታ፡ሆይ፥ቡችሎች፡እንኳ፡ከማእዱ፡በታች፡ኾነው፡የልጆችን፡ፍርፋሪ፡ ይበላሉ፡አለችው። 29፤ርሱም፦ስለዚህ፡ቃልሽ፡ኺጂ፡ጋኔኑ፡ከልጅሽ፡ወጥቷል፡አላት። 30፤ወደ፡ቤቷም፡ኼዳ፡ጋኔኑ፡ወጥቶ፡ልጇም፡በዐልጋ፡ላይ፡ተኝታ፡አገኘች። 31፤ደግሞም፡ከጢሮስ፡አገር፡ወጥቶ፡በሲዶና፡ዐልፎ፡ዐሥር፡ከተማ፡በሚባል፡አገር፡መካከል፡ወደገሊላ፡ ባሕር፡መጣ። 32፤ደንቈሮና፡ኰልታፋም፡የኾነ፡ሰው፡ወደ፡ርሱ፡አመጡ፥ 33፤እጁንም፡ይጭንበት፡ዘንድ፡ለመኑት።ከሕዝቡም፡ለይቶ፡ለብቻው፡ወሰደው፥ጣቶቹንም፡በዦሮዎቹ፡አገባ፡ እንትፍም፡ብሎ፡ምላሱን፡ዳሰሰ፤ 34፤ወደ፡ሰማይም፡አሻቅቦ፡አይቶ፡ቃተተና፦ኤፍታሕ፡አለው፥ርሱም፡ተከፈት፡ማለት፡ነው። 35፤ወዲያውም፡ዦሮዎቹ፡ተከፈቱ፡የምላሱም፡እስራት፡ተፈታ፡አጥርቶም፡ተናገረ። 36፤ለማንም፡አትንገሩ፡ብሎ፡አዘዛቸው፡እነርሱ፡ግን፡ባዘዛቸውም፡መጠን፡ይልቅ፡እጅግ፡አወሩት። 37፤ያለመጠንም፡ተገረሙና፦ዅሉን፡ደኅና፡አድርጓል፤ደንቈሮዎችም፡እንዲሰሙ፡ዲዳዎችም፡እንዲናገሩ፡ ያደርጋል፡አሉ።

1፤በዚያ፡ወራት፡ደግሞ፡ብዙ፡ሕዝብ፡ነበረ፡የሚበሉትም፡ስለሌላቸው፡ደቀ፡መዛሙርቱን፡ጠርቶ፦ 2፤ሕዝቡ፡ከእኔ፡ጋራ፡እስካኹን፡ሦስት፡ቀን፡ውለዋልና፥የሚበሉት፡ስለሌላቸው፡አዝንላቸዋለኹ፤ 3፤ከነርሱም፡አንዳንዶቹ፡ከሩቅ፡መጥተዋልና፥ጦማቸውን፡ወደ፡ቤታቸው፡ባሰናብታቸው፡በመንገድ፡ይዝላሉ፡ አላቸው። 4፤ደቀ፡መዛሙርቱም፦በዚህ፡በምድረ፡በዳ፡እንጀራ፡ከየት፡አግኝቶ፡ሰው፡እነዚህን፡ማጥገብ፡ ይችላል፧ብለው፡መለሱለት። 5፤ርሱም፦ስንት፡እንጀራ፡አላችኹ፧ብሎ፡ጠየቃቸው፥እነርሱም፦ሰባት፡አሉት። 6፤ሕዝቡም፡በምድር፡እንዲቀመጡ፡አዘዘ።ሰባቱንም፡እንጀራ፡ይዞ፡አመሰገነ፥ቈርሶም፡እንዲያቀርቡላቸው፡ ለደቀ፡መዛሙርቱ፡ሰጠ፥ለሕዝቡም፡አቀረቡ። 7፤ጥቂትም፡ትንሽ፡ዓሣ፡ነበራቸው፤ባረከውም፡ይህንም፡ደግሞ፡እንዲያቀርቡላቸው፡አዘዘ። 8፤በሉም፡ጠገቡም፥የተረፈውንም፡ቍርስራሽ፡ሰባት፡ቅርጫት፡አነሡ። 9፤የበሉትም፡አራት፡ሺሕ፡ያኽል፡ነበሩ። 10፤አሰናበታቸውም።ወዲያውም፡ከደቀ፡መዛሙርቱ፡ጋራ፡ወደ፡ታንኳዪቱ፡ገብቶ፡ወደዳልማኑታ፡አገር፡ መጣ። 11፤ፈሪሳውያንም፡ወጡና፡ሊፈትኑት፡ከሰማይ፡ምልክት፡ከርሱ፡ፈልገው፡ከርሱ፡ጋራ፡ይከራከሩ፡ዠመር። 12፤በመንፈሱም፡እጅግ፡ቃተተና፦ይህ፡ትውልድ፡ስለ፡ምን፡ምልክት፡ይፈልጋል፧እውነት፡ እላችዃለኹ፥ለዚህ፡ትውልድ፡ምልክት፡አይሰጠውም፡አለ። 13፤ትቷቸውም፡እንደ፡ገና፡ወደ፡ታንኳዪቱ፡ገብቶ፡ወደ፡ማዶ፡ኼደ። 14፤እንጀራ፡መያዝም፡ረሱ፥ለእነርሱም፡ካንድ፡እንጀራ፡በቀር፡በታንኳዪቱ፡አልነበራቸውም። 15፤ርሱም፦ተጠንቀቁ፤ከፈሪሳውያንና፡ከሄሮድስ፡ርሾ፡ተጠበቁ፡ብሎ፡አዘዛቸው። 16፤ርስ፡በርሳቸውም፦እንጀራ፡ስለሌለን፡ይኾናል፡ብለው፡ተነጋገሩ። 17፤ኢየሱስም፡ዐውቆ፡እንዲህ፡አላቸው፦እንጀራ፡ስለሌላችኹ፡ስለ፡ምን፡ትነጋገራላችኹ፧ገና፡ አልተመለከታችኹምን፧አላስተዋላችኹምን፧ 18፤ልባችኹስ፡ደንዝዟልን፧ዐይን፡ሳላችኹ፡አታዩምን፧ዦሮስ፡ሳላችኹ፡አትሰሙምን፧ትዝስ፡አይላችኹምን፧ 19፤ዐምስቱን፡እንጀራ፡ለዐምስት፡ሺሕ፡በቈረስኹ፡ጊዜ፥ቍርስራሹ፡የሞላ፡ስንት፡መሶብ፡ አነሣችኹ፧እነርሱም፦ዐሥራ፡ኹለት፡አሉት። 20፤ሰባቱን፡እንጀራስ፡ለአራት፡ሺሕ፡በቈረስኹ፡ጊዜ፥ቍርስራሹ፡የሞላ፡ስንት፡ቅርጫት፡ አነሣችኹ፧እነርሱም፦ሰባት፡አሉት። 21፤ገና፡አላስተዋላችኹምን፧አላቸው። 22፤ወደ፡ቤተ፡ሳይዳም፡መጡ።ዕውርም፡አመጡለት፥እንዲዳስሰውም፡ለመኑት። 23፤ዕውሩንም፡እጁን፡ይዞ፡ከመንደር፡ውጭ፡አወጣው፥በዐይኑም፡ተፍቶበት፡እጁንም፡ጭኖበት።አንዳች፡ ታያለኽን፡ብሎ፡ጠየቀው። 24፤አሻቅቦም፦ሰዎች፡እንደ፡ዛፍ፡ሲመላለሱ፡አያለኹ፡አለ።

ክርስቶስ ዕውሩን ሲፈውስ

25፤ከዚህም፡በዃላ፡ደግሞ፡እጁን፡በዐይኑ፡ላይ፡ጫነበት፡አጥርቶም፡አየና፡ዳነም፡ከሩቅም፡ሳይቀር፡ዅሉን፡ ተመለከተ። 26፤ወደ፡ቤቱም፡ሰደደውና፦ወደ፡መንደሩ፡አትግባ፡በመንደሩም፡ለማንም፡አንዳች፡አትናገር፡አለው። 27፤ኢየሱስና፡ደቀ፡መዛሙርቱም፡በፊልጶስ፡ቂሳርያ፡ወዳሉ፡መንደሮች፡ወጡ፡በመንገድም፦ሰዎች፡እኔ፡ ማን፡እንደ፡ኾንኹ፡ይላሉ፧ብሎ፡ደቀ፡መዛሙርቱን፡ጠየቃቸው። 28፤እነርሱም፦መጥምቁ፡ዮሐንስ፥ሌላዎችም፡ኤልያስ፥ሌላዎችም፡ከነቢያት፡አንዱ፡ብለው፡ነገሩት። 29፤እናንተስ፡እኔ፡ማን፡እንደ፡ኾንኹ፡ትላላችኹ፧ብሎ፡ጠየቃቸው።ጴጥሮስም፦አንተ፡ክርስቶስ፡ነኽ፡ ብሎ፡መለሰለት። 30፤ስለ፡ርሱም፡ለማንም፡እንዳይናገሩ፡አዘዛቸው። 31፤የሰው፡ልጅ፡ብዙ፡መከራ፡ሊቀበል፥ከሽማግሌዎችም፡ከካህናት፡አለቃዎችም፡ከጻፊዎችም፡ ሊጣል፥ሊገደልም፡ከሦስት፡ቀንም፡በዃላ፡ሊነሣ፡እንዲገባው፡ያስተምራቸው፡ዠመር፤ቃሉንም፡ገልጦ፡ ይናገር፡ነበር። 32፤ጴጥሮስም፡ወደ፡ርሱ፡ወስዶ፡ይገሥጸው፡ዠመር። 33፤ርሱ፡ግን፡ዘወር፡አለ፡ደቀ፡መዛሙርቱንም፡አይቶ፡ጴጥሮስን፡ገሠጸውና፦ወደ፡ዃላዬ፡ኺድ፥አንተ፡ ሰይጣን፤የሰውን፡እንጂ፡የእግዚአብሔርን፡ነገር፡አታስብምና፡አለው። 34፤ሕዝቡንም፡ከደቀ፡መዛሙርቱ፡ጋራ፡ጠርቶ፡እንዲህ፡አላቸው፦በዃላዬ፡ሊመጣ፡የሚወድ፡ ቢኖር፥ራሱን፡ይካድ፡መስቀሉንም፡ተሸክሞ፡ይከተለኝ። 35፤ነፍሱን፡ሊያድን፡የሚወድ፡ዅሉ፡ያጠፋታልና፥ስለ፡እኔና፡ስለ፡ወንጌል፡ነፍሱን፡የሚያጠፋ፡ዅሉ፡ግን፡ ያድናታል። 36፤ሰው፡ዓለምን፡ዅሉ፡ቢያተርፍ፡ነፍሱንም፡ቢያጐድል፡ምን፡ይጠቅመዋል፧ 37፤ሰውስ፡ስለነፍሱ፡ቤዛ፡ምን፡ይሰጣል፧ 38፤በዚህም፡በዘማዊና፡በኀጢአተኛ፡ትውልድ፡መካከል፡በእኔና፡በቃሌ፡የሚያፍር፡ዅሉ፥የሰው፡ልጅ፡ ደግሞ፡በአባቱ፡ክብር፡ከቅዱሳን፡መላእክት፡ጋራ፡በመጣ፡ጊዜ፡በርሱ፡ያፍርበታል።

1፤እውነት፡እላችዃለኹ፥በዚህ፡ከቆሙት፡ሰዎች፡የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡በኀይል፡ስትመጣ፡እስኪያዩ፡ ድረስ፥ሞትን፡የማይቀምሱ፡አንዳንዶች፡አሉ፡አላቸው። 2፤ከስድስት፡ቀንም፡በዃላ፡ኢየሱስ፡ጴጥሮስንና፡ያዕቆብን፡ዮሐንስንም፡ይዞ፡ወደ፡ረዥም፡ተራራ፡ብቻቸውን፡ አወጣቸው።በፊታቸውም፡ተለወጠ፥ልብሱም፡አንጸባረቀ፤ 3፤ዐጣቢም፡በምድር፡ላይ፡እንደዚያ፡ሊያነጣው፡እስከማይችል፡በጣም፡ነጭ፡ኾነ። 4፤ኤልያስና፡ሙሴም፡ታዩዋቸው፥ከኢየሱስም፡ጋራ፡ይነጋገሩ፡ነበር። 5፤ጴጥሮስም፡መልሶ፡ኢየሱስን፦መምህር፡ሆይ፥በዚህ፡መኾን፡ለእኛ፡መልካም፡ነውና፥አንድ፡ለአንተ፡ አንድም፡ለሙሴ፡አንድም፡ለኤልያስ፡ሦስት፡ዳሶች፡እንሥራ፡አለው። 6፤እጅግ፡ስለ፡ፈሩ፡የሚለውን፡አያውቅም፡ነበር። 7፤ደመናም፡መጥቶ፡ጋረዳቸው፥ከደመናውም፦የምወደ፟ው፡ልጄ፡ይህ፡ነው፥ርሱን፡ስሙት፡የሚል፡ድምፅ፡ መጣ።8፤ድንገትም፡ዞረው፡ሲመለከቱ፡ከነርሱ፡ጋራ፡ከኢየሱስ፡ብቻ፡በቀር፡ማንንም፡አላዩም። 9፤ከተራራውም፡ሲወርዱ፡የሰው፡ልጅ፡ከሙታን፡እስኪነሣ፡ድረስ፡ያዩትን፡ለማንም፡እንዳይነግሩ፡አዘዛቸው። 10፤ቃሉንም፡ይዘው፦ከሙታን፡መነሣት፡ምንድር፡ነው፧እያሉ፡ርስ፡በርሳቸው፡ተጠያየቁ። 11፤እነርሱም፦ኤልያስ፡አስቀድሞ፡ሊመጣ፡እንዲገባው፡ጻፊዎች፡ስለ፡ምን፡ይላሉ፧ብለው፡ጠየቁት። 12፤ርሱም፡መልሶ፦ኤልያስማ፡አስቀድሞ፡ይመጣል፥ዅሉንም፡ያቀናናል፤ስለ፡ሰው፡ልጅም፡እንዴት፡ ተብሎ፡ተጽፏል፧ብዙ፡መከራ፡እንዲቀበል፡እንዲናቅም። 13፤ነገር፡ግን፥እላችዃለኹ፥ኤልያስ፡ደግሞ፡መጥቷል፥ስለ፡ርሱም፡እንደ፡ተጸፈ፡የወደዱትን፡ዅሉ፡ አደረጉበት፡አላቸው። 14፤ወደ፡ደቀ፡መዛሙርቱም፡በመጣ፡ጊዜ፥ብዙ፡ሕዝብ፡ሲከቧ፟ቸው፥ጻፊዎችም፡ከነርሱ፡ጋራ፡ሲከራከሩ፡ አየ። 15፤ወዲያውም፡ሕዝቡ፡ዅሉ፡ባዩት፡ጊዜ፡ደነገጡ፥ወደ፡ርሱም፡ሮጠው፡እጅ፡ነሡት። 16፤ጻፊዎችንም፦ስለ፡ምን፡ከነርሱ፡ጋራ፡ትከራከራላችኹ፧ብሎ፡ጠየቃቸው። 17፤ከሕዝቡ፡አንዱ፡መልሶ፦መምህር፡ሆይ፥ዲዳ፡መንፈስ፡ያደረበትን፡ልጄን፡ወዳንተ፡አምጥቻለኹ፤ 18፤በያዘውም፡ስፍራ፡ዅሉ፡ይጥለዋል፤ዐረፋም፡ይደፍቃል፥ጥርሱንም፡ያፋጫል፡ ይደርቃልም፤እንዲያወጡለትም፡ለደቀ፡መዛሙርትኽ፡ነገርዃቸው፥አልቻሉምም፡አለው። 19፤ርሱም፡መልሶ፦የማታምን፡ትውልድ፡ሆይ፥እስከ፡መቼ፡ከእናንተ፡ጋራ፡እኖራለኹ፧እስከ፡መቼስ፡ እታገሣችዃለኹ፧ወደ፡እኔ፡አምጡት፡አላቸው። 20፤ወደ፡ርሱም፡አመጡት።ርሱንም፡ባየ፡ጊዜ፡ያ፡መንፈስ፡ወዲያው፡አንፈራገጠው፤ወደ፡ምድርም፡ ወድቆ፡ዐረፋ፡እየደፈቀ፡ተንፈራፈረ። 21፤አባቱንም፦ይህ፡ከያዘው፡ስንት፡ዘመን፡ነው፧ብሎ፡ጠየቀው።ርሱም፦ከሕፃንነቱ፡ዠምሮ፡ነው፤ 22፤ብዙ፡ጊዜም፡ሊያጠፋው፡ወደ፡እሳትም፡ወደ፡ውሃም፡ጣለው፤ቢቻልኽ፡ግን፡ዕዘንልን፥ርዳንም፡አለው። 23፤ኢየሱስም፦ቢቻልኽ፡ትላለኽ፤ለሚያምን፡ዅሉ፡ይቻላል፡አለው። 24፤ወዲያውም፡የብላቴናው፡አባት፡ጮኾ፦አምናለኹ፤አለማመኔን፡ርዳው፡አለ። 25፤ኢየሱስም፡ሕዝቡ፡እንደ፡ገና፡ሲራወጥ፡አይቶ፡ርኩሱን፡መንፈስ፡ገሠጸና፦አንተ፡ዲዳ፡ደንቈሮም፡ መንፈስ፥እኔ፡አዝኻለኹ፥ከርሱ፡ውጣ፡እንግዲህም፡አትግባበት፡አለው። 26፤ጮኾም፡እጅግም፡አንፈራግጦት፡ወጣ፤ብዙዎችም፦ሞተ፡እስኪሉ፡ድረስ፡እንደ፡ሙት፡ኾነ። 27፤ኢየሱስ፡ግን፡እጁን፡ይዞ፡አስነሣው፡ቆመም። 28፤ወደ፡ቤትም፡ከገባ፡በዃላ፡ደቀ፡መዛሙርቱ፦እኛ፡ልናወጣው፡ያልቻልን፡ስለ፡ምንድር፡ነው፧ብለው፡ ብቻውን፡ጠየቁት። 29፤ይህ፡ወገን፡በጸሎትና፡በጦም፡ካልኾነ፡በምንም፡ሊወጣ፡አይችልም፡አላቸው። 30-31፤ከዚያም፡ወጥተው፡በገሊላ፡በኩል፡ዐለፉ፤ደቀ፡መዛሙርቱንም፡ያስተምር፡ስለ፡ነበር፡ማንም፡ያውቅ፡ ዘንድ፡አልወደደም፤ለእነርሱም፦የሰው፡ልጅ፡በሰዎች፡እጅ፡ዐልፎ፡ይሰጣል፥ይገድሉትማል፥ተገድሎም፡ በሦስተኛው፡ቀን፡ይነሣል፡ይላቸው፡ነበር። 32፤እነርሱም፡ነገሩን፡አላስተዋሉም፥እንዳይጠይቁትም፡ፈሩ። 33፤ወደ፡ቅፍርናሖምም፡መጣ።በቤትም፡ኾኖ፦በመንገድ፡ርስ፡በርሳችኹ፡ምን፡ተነጋገራችኹ፧ብሎ፡ ጠየቃቸው። 34፤እነርሱ፡ግን፡በመንገድ፦ከዅሉ፡የሚበልጥ፡ማን፡ይኾን፧ተባብለው፡ነበርና፥ዝም፡አሉ። 35፤ተቀምጦም፡ዐሥራ፡ኹለቱን፡ጠርቶ፦ሰው፡ፊተኛ፡ሊኾን፡ቢወድ፡ከዅሉ፡በዃላ፡የዅሉም፡አገልጋይ፡ ይኹን፡አላቸው። 36፤ሕፃንም፡ይዞ፡በመካከላቸው፡አቆመው፡ዐቅፎም። 37፤እንደዚህ፡ካሉ፡ሕፃናት፡አንዱን፡በስሜ፡የሚቀበል፡ዅሉ፡እኔን፡ይቀበላል፤የሚቀበለኝም፡ዅሉ፡የላከኝን፡ እንጂ፡እኔን፡አይቀበልም፡አላቸው። 38፤ዮሐንስ፡መልሶ፦መምህር፡ሆይ፥አንድ፡ሰው፡በስምኽ፡አጋንንትን፡ሲያወጣ፡አየነው፥ 39፤ስለማይከተለንም፡ከለከልነው፡አለው።ኢየሱስ፡ግን፡አለ፦በስሜ፡ተኣምር፡ሠርቶ፡በቶሎ፡በእኔ፡ላይ፡ ክፉ፡መናገር፡የሚችል፡ማንም፡የለምና፡አትከልክሉት፤ 40፤የማይቃወመን፡ርሱ፡ከእኛ፡ጋራ፡ነውና። 41፤የክርስቶስ፡ስለ፡ኾናችኹ፡በስሜ፡ጽዋ፡ውሃ፡የሚያጠጣችኹ፡ዅሉ፥ዋጋው፡እንዳይጠፋበት፡እውነት፡ እላችዃለኹ። 42፤በእኔም፡ከሚያምኑት፡ከነዚህ፡ከታናናሾቹ፡አንዱን፡የሚያሰናክል፡ዅሉ፡ትልቅ፡የወፍጮ፡ድንጋይ፡ በዐንገቱ፡ታስሮ፡ወደ፡ባሕር፡ቢጣል፡ይሻለው፡ነበር። 43-44፤እጅኽ፡ብታሰናክልኽ፡ቍረጣት፤ኹለት፡እጅ፡ኖሮኽ፡ትላቸው፡ወደማይሞትበት፡እሳቱም፡ ወደማይጠፋበት፡ወደ፡ገሃነም፡ወደማይጠፋ፡እሳት፡ከመኼድ፡ጕንድሽ፡ኾነኽ፡ወደ፡ሕይወት፡መግባት፡ ይሻላል። 45-46፤እግርኽ፡ብታሰናክልኽ፡ቍረጣት፤ኹለት፡እግር፡ኖሮኽ፡ትላቸው፡ወደማይሞትበት፡እሳቱም፡ ወደማይጠፋበት፡ወደ፡ገሃነም፡ወደማይጠፋ፡እሳት፡ከመጣል፡ዐንካሳ፡ኾነኽ፡ወደ፡ሕይወት፡መግባት፡ ይሻልኻል። 47-48፤ዐይንኽ፡ብታሰናክልኽ፡አውጣት፤ኹለት፡ዐይን፡ኖሮኽ፡ትላቸው፡ወደማይሞትበት፡እሳቱም፡ ወደማይጠፋበት፡ወደ፡ገሃነመ፡እሳት፡ከመጣል፡አንዲት፡ዐይን፡ኖራኽ፡ወደእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ መግባት፡ይሻልኻል። 49፤ሰው፡ዅሉ፡በእሳት፡ይቀመማልና፥መሥዋዕትም፡ዅሉ፡በጨው፡ይቀመማል። 50፤ጨው፡መልካም፡ነው፤ጨው፡ግን፡ዐልጫ፡ቢኾን፡በምን፡ታጣፍጡታላችኹ፧በነፍሳችኹ፡ጨው፡ ይኑርባችኹ፥ርስ፡በርሳችኹም፡ተስማሙ።

1፤ከዚያም፡ተነሥቶ፡በዮርዳኖስ፡ማዶ፡ወደይሁዳ፡አገር፡መጣ፥ደግሞም፡ብዙ፡ሰዎች፡ወደ፡ርሱ፡ተሰበሰቡ፡ እንደ፡ልማዱም፡ደግሞ፡ያስተምራቸው፡ነበር። 2፤ፈሪሳውያንም፡ቀርበው፦ሰው፡ሚስቱን፡ሊፈታ፡ተፈቅዶለታልን፧ብለው፡ሊፈትኑት፡ጠየቁት። 3፤ርሱ፡ግን፡መልሶ፦ሙሴ፡ምን፡አዘዛችኹ፧አላቸው። 4፤እነርሱም፦ሙሴስ፡የፍቿን፡ጽሕፈት፡ጽፎ፡እንዲፈታት፡ፈቀደ፡አሉ። 5፤ኢየሱስም፡መልሶ፡እንዲህ፡አላቸው፦ስለልባችኹ፡ጥንካሬ፡ይህችን፡ትእዛዝ፡ጻፈላችኹ። 6፤ከፍጥረት፡መዠመሪያ፡ግን፡እግዚአብሔር፡ወንድና፡ሴት፡አደረጋቸው፤ 7፤ስለዚህ፥ሰው፡አባቱንና፡እናቱን፡ይተዋል፥ከሚስቱም፡ጋራ፡ይተባበራል፥ 8፤ኹለቱም፡አንድ፡ሥጋ፡ይኾናሉ፤ስለዚህ፥አንድ፡ሥጋ፡ናቸው፡እንጂ፡ወደ፡ፊት፡ኹለት፡አይደሉም። 9፤እግዚአብሔር፡ያጣመረውን፡እንግዲህ፡ሰው፡አይለየው። 10፤በቤትም፡ደግሞ፡ደቀ፡መዛሙርቱ፡ስለዚህ፡ነገር፡ጠየቁት። 11፤ርሱም፦ሚስቱን፡ፈቶ፟፡ሌላ፡የሚያገባ፡ዅሉ፡በርሷ፡ላይ፡ያመነዝራል፤ 12፤ርሷም፡ባሏን፡ፈታ፟፡ሌላ፡ብታገባ፡ታመነዝራለች፡አላቸው። 13፤እንዲዳስሳቸውም፡ሕፃናትን፡ወደ፡ርሱ፡አመጡ፤ደቀ፡መዛሙርቱም፡ያመጧቸውን፡ገሠጿቸው። 14፤ኢየሱስ፡ግን፡አይቶ፡ተቈጣና፦ሕፃናትን፡ወደ፡እኔ፡ይመጡ፡ዘንድ፡ ተዉ፥አትከልክሏቸው፤የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡እንደነዚህ፡ላሉት፡ናትና። 15፤እውነት፡እላችዃለኹ፤የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡እንደ፡ሕፃን፡የማይቀበላት፡ዅሉ፡ከቶ፡አይገባባትም፡ አላቸው። 16፤ዐቀፋቸውም፡እጁንም፡ጭኖ፡ባረካቸው። 17፤ርሱም፡በመንገድ፡ሲወጣ፡አንድ፡ሰው፡ወደ፡ርሱ፡ሮጦ፡ተንበረከከለትና፦ቸር፡መምህር፡ሆይ፥የዘለዓለም፡ሕይወትን፡እወርስ፡ዘንድ፡ምን፡ላድርግ፧ብሎ፡ጠየቀው። 18፤ኢየሱስም፦ስለ፡ምን፡ቸር፡ትለኛለኽ፧ከአንዱ፡ከእግዚአብሔር፡በቀር፡ቸር፡ማንም፡የለም። 19፤ትእዛዛትን፡ታውቃለኽ፤አታመንዝር፥አትግደል፥አትስረቅ፥በሐሰት፡አትመስክር፥አታታል፟፥አባትኽንና፡ እናትኽን፡አክብር፡አለው። 20፤ርሱም፡መልሶ፦መምህር፡ሆይ፥ይህን፡ዅሉ፡ከሕፃንነቴ፡ዠምሬ፡ጠብቄያለኹ፡አለው። 21፤ኢየሱስም፡ወደ፡ርሱ፡ተመልክቶ፡ወደደውና፦አንድ፡ነገር፡ጐደለኽ፤ኺድ፥ያለኽን፡ዅሉ፡ሽጠኽ፡ ለድኻዎች፡ስጥ፥በሰማይም፡መዝገብ፡ታገኛለኽ፥መስቀሉንም፡ተሸክመኽ፡ና፥ተከተለኝ፡አለው። 22፤ነገር፡ግን፥ስለዚህ፡ነገር፡ፊቱ፡ጠቈረ፥ብዙ፡ንብረት፡ነበረውና፡እያዘነም፡ኼደ። 23፤ኢየሱስም፡ዘወር፡ብሎ፡አይቶ፡ደቀ፡መዛሙርቱን፦ገንዘብ፡ላላቸው፡ወደእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ መግባት፡እንዴት፡ጭንቅ፡ይኾናል፡አላቸው። 24፤ደቀ፡መዛሙርቱም፡እነዚህን፡ቃሎች፡አደነቁ።ኢየሱስም፡ደግሞ፡መልሶ፦ልጆች፡ሆይ፥በገንዘብ፡ ለሚታመኑ፡ወደእግዚአብሔር፡መንግሥት፡መግባት፡እንዴት፡ጭንቅ፡ነው። 25፤ባለጠጋ፡ወደእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ከሚገባ፡ግመል፡በመርፌ፡ቀዳዳ፡ቢያልፍ፡ይቀላል፡አላቸው። 26፤እነርሱም፡ያለመጠን፡ተገረሙና፡ርስ፡በርሳቸው፦እንግዲያ፡ማን፡ሊድን፡ይችላል፧ተባባሉ። 27፤ኢየሱስም፡ተመለከታቸውና፦ይህ፡በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡እንጂ፡በሰው፡ዘንድ፡ አይቻልም፤በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ዅሉ፡ይቻላልና፥አለ። 28፤ጴጥሮስም፦እንሆ፥እኛ፡ዅሉን፡ትተን፡ተከተልንኽ፡ይለው፡ዠመር። 29፤ኢየሱስም፡መልሶ፡እንዲህ፡አለ፦እውነት፡እላችዃለኹ፥ስለ፡እኔና፡ስለ፡ወንጌል፡ቤትን፡ወይም፡ ወንድሞችን፡ወይም፡እኅቶችን፡ወይም፡አባትን፡ወይም፡እናትን፡ወይም፡ሚስትን፡ወይም፡ልጆችን፡ወይም፡ ዕርሻን፡የተወ፥ 30፤አኹን፡በዚህ፡ዘመን፡ከስደት፡ጋራ፡ቤቶችን፡ወንድሞችንና፡እኅቶችንም፡እናቶችንም፡ልጆችንም፡ ዕርሻንም፡መቶ፡ዕጥፍ፥በሚመጣውም፡ዓለም፡የዘለዓለም፡ሕይወት፡የማይቀበል፡ማንም፡የለም። 31፤ግን፡ብዙ፡ፊተኛዎች፡ዃለኛዎች፡ዃለኛዎችም፡ፊተኛዎች፡ይኾናሉ። 32፤ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡ሊወጡ፡በመንገድ፡ነበሩ፥ኢየሱስም፡ይቀድማቸው፡ነበርና፥ተደነቁ፤የተከተሉትም፡ ይፈሩ፡ነበር።ደግሞም፡ዐሥራ፡ኹለቱን፡ወደ፡ርሱ፡አቅርቦ፡ይደርስበት፡ዘንድ፡ያለውን፡ይነግራቸው፡ዠመር። 33፤እንሆ፥ወደ፡ኢየሩሳሌም፡እንወጣለን፥የሰው፡ልጅም፡ለካህናት፡አለቃዎችና፡ለጻፊዎች፡ዐልፎ፡ ይሰጣል፥የሞት፡ፍርድም፡ይፈርዱበታል፥ለአሕዛብም፡አሳልፈው፡ይሰጡታል፥ 34፤ይዘብቱበትማል፡ይተፉበትማል፡ይገርፉትማል፡ይገድሉትማል፥በሦስተኛውም፡ቀን፡ይነሣል፡አላቸው። 35፤የዘብዴዎስ፡ልጆች፡ያዕቆብና፡ዮሐንስም፡ወደ፡ርሱ፡ቀርበው፦መምህር፡ሆይ፥የምንለምንኽን፡ዅሉ፡ እንድታደርግልን፡እንወዳለን፡አሉት። 36፤ርሱም፦ምን፡ላደርግላችኹ፡ትወዳላችኹ፧አላቸው። 37፤እነርሱም፦በክብርኽ፡ጊዜ፡አንዳችን፡በቀኝ፡አንዳችንም፡በግራኽ፡መቀመጥን፡ስጠን፡አሉት። 38፤ኢየሱስ፡ግን፦የምትለምኑትን፡አታውቁም።እኔ፡የምጠጣውን፡ጽዋ፡ልትጠጡ፥እኔ፡የምጠመቀውንስ፡ ጥምቀት፡ልትጠመቁ፡ትችላላችኹን፧አላቸው። 39፤እነርሱም፦እንችላለን፡አሉት።ኢየሱስም፦እኔ፡የምጠጣውን፡ጽዋ፡ትጠጣላችኹ፥እኔ፡የምጠመቀውንም፡ ጥምቀት፡ትጠመቃላችኹ፤ 40፤በቀኝና፡በግራ፡መቀመጥ፡ግን፡ለተዘጋጀላቸው፡ነው፡እንጂ፡የምሰጥ፡እኔ፡አይደለኹም፡አላቸው። 41፤ዐሥሩም፡ሰምተው፡በያዕቆብና፡በዮሐንስ፡ይቈጡ፡ዠመር። 42፤ኢየሱስም፡ወደ፡ርሱ፡ጠርቶ፡እንዲህ፡አላቸው፦የአሕዛብ፡አለቃዎች፡ተብሎ፡የምታስቡት፡ እንዲገዟቸው፡ታላላቆቻቸውም፡በላያቸው፡እንዲሠለጥኑ፡ታውቃላችኹ። 43፤በእናንተስ፡እንዲህ፡አይደለም፤ነገር፡ግን፥ማንም፡ከእናንተ፡ታላቅ፡ሊኾን፡የሚወድ፡የእናንተ፡አገልጋይ፡ ይኹን፥ 44፤ከእናንተም፡ማንም፡ፊተኛ፡ሊኾን፡የሚወድ፡የዅሉ፡ባሪያ፡ይኹን፤ 45፤እንዲሁ፡የሰው፡ልጅም፡ሊያገለግልና፡ነፍሱን፡ለብዙዎች፡ቤዛ፡ሊሰጥ፡እንጂ፡እንዲያገለግሉት፡አልመጣም። 46፤ወደ፡ኢያሪኮም፡መጡ።ከደቀ፡መዛሙርቱና፡ከብዙ፡ሕዝብ፡ጋራ፡ከኢያሪኮ፡ሲወጣ፡የጤሜዎስ፡ልጅ፡ ዕውሩ፡በርጤሜዎስ፡እየለመነ፡በመንገድ፡ዳር፡ተቀምጦ፡ነበር። 47፤የናዝሬቱ፡ኢየሱስም፡እንደ፡ኾነ፡በሰማ፡ጊዜ፦የዳዊት፡ልጅ፡ኢየሱስ፡ሆይ፥ማረኝ፡እያለ፡ይጮኽ፡ ዠመር። 48፤ብዙዎችም፡ዝም፡እንዲል፡ገሠጹት፤ርሱ፡ግን፦የዳዊት፡ልጅ፡ሆይ፥ማረኝ፡እያለ፡አብዝቶ፡ጮኸ። 49፤ኢየሱስም፡ቆመና፦ጥሩት፡አለ።ዕውሩንም፦አይዞኽ፥ተነሣ፥ይጠራኻል፡ብለው፡ጠሩት። 50፤ርሱም፡እየዘለለ፡ተነሣና፡ልብሱን፡ጥሎ፡ወደ፡ኢየሱስ፡መጣ። 51፤ኢየሱስም፡መልሶ፦ምን፡ላደርግልኽ፡ትወዳለኽ፧አለው።ዕውሩም፦መምህር፡ሆይ፥አይ፡ዘንድ፡ አለው። 52፤ኢየሱስም፦ኺድ፤እምነትኽ፡አድኖኻል፡አለው።ወዲያውም፡አየ፡በመንገድም፡ተከተለው።

1፤ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡ከደብረ፡ዘይት፡አጠገብ፡ወዳሉቱ፡ወደ፡ቤተ፡ፋጌና፡ወደ፡ቢታንያ፡በቀረቡ፡ ጊዜ፥ከደቀ፡መዛሙርቱ፡ኹለቱን፡ልኮ። 2፤በፊታችኹ፡ወዳለችው፡መንደር፡ኺዱ፥ወዲያውም፡ወደ፡ርሷ፡ገብታችኹ፡ከሰው፡ማንም፡ገና፡ ያልተቀመጠበት፡ውርንጫ፡ታስሮ፡ታገኛላችኹ፤ፈታ፟ችኹ፡አምጡልኝ። 3፤ማንም፦ስለ፡ምን፡እንዲህ፡ታደርጋላችኹ፧ቢላችኹ።ለጌታ፡ያስፈልገዋል፡በሉት፥ወዲያውም፡ደግሞ፡ ወደዚህ፡ይሰደዋል፡አላቸው። 4፤ኼዱም፡ውርንጫውንም፡በመንገድ፡መተላለፊያ፡በደጅ፡ውጭ፡ታስሮ፡አገኙት፥ፈቱትም፦ 5፤በዚያም፡ከቆሙት፡አንዳንዶቹ፦ውርንጫውን፡የምትፈቱት፡ምን፡ልታደርጉት፡ነው፡አሏቸው። 6፤እነርሱም፡ኢየሱስ፡እንዳዘዘ፡አሏቸው፤ተዉአቸውም፦ 7፤ውርንጫውንም፡ወደ፡ኢየሱስ፡አመጡት፥ልብሳቸውንም፡በላዩ፡ጣሉ፥ተቀመጠበትም። 8፤ብዙ፡ሰዎችም፡ልብሳቸውን፡በመንገድ፡ላይ፡አነጠፉ፥ሌላዎችም፡ከዛፍ፡ቅጠሎችን፡እየቈረጡ፡ያነጥፉ፡ ነበር። 9፤የሚቀድሙትም፡የሚከተሉትም፦ሆሣዕና፤በጌታ፡ስም፡የሚመጣ፡የተባረከ፡ነው፤ 10፤በጌታ፡ስም፡የምትመጣ፡የአባታችን፡የዳዊት፡መንግሥት፡የተባረከች፡ናት፤ሆሣዕና፡በአርያም፡እያሉ፡ ይጮኹ፡ነበር። 11፤ኢየሱስም፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ወደ፡መቅደስ፡ገባ፤ዘወር፡ብሎም፡ዅሉን፡ከተመለከተ፡በዃላ፥ጊዜው፡መሽቶ፡ስለ፡ነበር፥ከዐሥራ፡ኹለቱ፡ጋራ፡ወደ፡ቢታንያ፡ወጣ። 12፤በማግስቱም፡ከቢታንያ፡ሲወጡ፡ተራበ። 13፤ቅጠልም፡ያላት፡በለስ፡ከሩቅ፡አይቶ፡ምናልባት፡አንዳች፡ይገኝባት፡እንደ፡ኾነ፡ብሎ፡መጣ፥ነገር፡ ግን፥የበለስ፡ወራት፡አልነበረምና፡መጥቶ፡ከቅጠል፡በቀር፡ምንም፡አላገኘባትም። 14፤መልሶም፦ካኹን፡ዠምሮ፡ለዘለዓለም፡ማንም፡ከአንቺ፡ፍሬ፡አይብላ፡አላት።ደቀ፡መዛሙርቱም፡ሰሙ። 15፤ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡መጡ።ወደ፡መቅደስም፡ገብቶ፡በመቅደስ፡የሚሸጡትንና፡የሚገዙትን፡ያወጣ፡ ዠመር፥የገንዘብ፡ለዋጮችንም፡ገበታዎች፡የርግብ፡ሻጪዎችንም፡ወንበሮች፡ገለበጠ፤ 16፤ዕቃም፡ተሸክሞ፡ማንም፡በመቅደስ፡ሊያልፍ፡አልፈቀደም። 17፤አስተማራቸውም፦ቤቴ፡ለአሕዛብ፡ዅሉ፡የጸሎት፡ቤት፡ትባላለች፡ተብሎ፡የተጻፈ፡አይደለምን፧እናንተ፡ ግን፡የወንበዴዎች፡ዋሻ፡አደረጋችዃት፡አላቸው። 18፤የካህናት፡አለቃዎችም፡ጻፊዎችም፡ሰምተው፥ሕዝቡ፡ዅሉ፡በትምህርቱ፡ይገረሙ፡ስለ፡ነበር፡ይፈሩት፡ነበርና፥እንዴት፡አድርገው፡እንዲያጠፉት፡ፈለጉ። 19፤ማታ፡ማታም፡ከከተማ፡ወደ፡ውጭ፡ይወጣ፡ነበር። 20፤ማለዳም፡ሲያልፉ፡በለሲቱን፡ከሥሯ፡ደርቃ፡አይዋት። 21፤ጴጥሮስም፡ትዝ፡ብሎት።መምህር፡ሆይ፥እንሆ፥የረገምኻት፡በለስ፡ደርቃለች፡አለው። 22፤ኢየሱስም፡መልሶ፡እንዲህ፡አላቸው፦በእግዚአብሔር፡እመኑ። 23፤እውነት፡እላችዃለኹ፥ማንም፡ያለው፡ነገር፡እንዲደረግለት፡ቢያምን፡በልቡ፡ሳይጠራጠር፥ይህን፡ ተራራ፦ተነቅለኽ፡ወደ፡ባሕር፡ተወርወር፡ቢል፡ይኾንለታል። 24፤ስለዚህ፥እላችዃለኹ፥የጸለያችኹትን፡የለመናችኹትንም፡ዅሉ፡እንዳገኛችኹት፡እመኑ፥ይኾንላችኹማል። 25፤ለጸሎትም፡በቆማችኹ፡ጊዜ፥በሰማያት፡ያለው፡አባታችኹ፡ደግሞ፡ኀጢአታችኹን፡ይቅር፡ እንዲላችኹ፥በማንም፡ላይ፡አንዳች፡ቢኖርባችኹ፡ይቅር፡በሉት። 26፤እናንተ፡ግን፡ይቅር፡ባትሉ፡በሰማያት፡ያለው፡አባታችኹም፡ኀጢአታችኹን፡ይቅር፡አይላችኹም። 27፤ደግሞም፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡መጡ።ርሱም፡በመቅደስ፡ሲመላለስ፥የካህናት፡አለቃዎችና፡ጻፊዎች፡ ሽማግሌዎችም፡ወደ፡ርሱ፡መጥተው፦ 28፤እነዚህን፡በምን፡ሥልጣን፡ታደርጋለኽ፧ወይስ፡እነዚህን፡ለማድረግ፡ይህን፡ሥልጣን፡ማን፡ ሰጠኽ፧አሉት። 29፤ኢየሱስም፦እኔም፡አንዲት፡ነገር፡እጠይቃችዃለኹ፥እናንተም፡መልሱልኝ፥እኔም፡በምን፡ሥልጣን፡ እነዚህን፡እንዳደርግ፡እነግራችዃለኹ። 30፤የዮሐንስ፡ጥምቀት፡ከሰማይ፡ነበረችን፡ወይስ፡ከሰው፧መልሱልኝ፡አላቸው። 31፤ርስ፡በርሳቸውም፡ሲነጋገሩ፦ከሰማይ፡ነው፡ብንል፦እንግዲያውስ፡ስለ፡ምን፡ አላመናችኹበትም፧ይለናል፤ 32፤ነገር፡ግን፦ከሰው፡ነው፡እንበልን፧አሉ፤ዅሉ፡ዮሐንስን፡በእውነት፡እንደ፡ነቢይ፡ያዩት፡ ነበርና፥ሕዝቡን፡ፈሩ። 33፤ለኢየሱስም፡መልሰው፦አናውቅም፡አሉት፡ኢየሱስም፦እኔም፡በምን፡ሥልጣን፡እነዚህን፡እንዳደርግ፡ አልነግራችኹም፡አላቸው።

1፤በምሳሌም ይነግራቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፥ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።

2፤በጊዜውም ከወይን አትክልት ፍሬ ከገበሬዎቹ እንዲቀበል አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤

3፤ይዘውም ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት።

4፤ዳግመኛም ሌላውን ባሪያ ወደ እነርሱ ላከ እርሱንም ወግረው ራሱን አቈሰሉት አዋርደውም ሰደዱት።

5፤ሌላውንም ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፥ ከሌሎችም ከብዙዎች አንዳንዱን ደበደቡ አንዳንዱንም ገደሉ።

6፤የሚወደው አንድ ልጅ ገና ነበረው፤ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ እርሱን ከሁሉ በኋላ ወደ እነርሱ ላከ።

7፤እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው፦ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለው፥ ርስቱም ለኛ ይሆናል ተባባሉ።

8፤ይዘውም ገደሉት፥ ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ ጣሉት።

9፤እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋል? ይመጣል ገበሬዎቹንም ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል።

10-11፤ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው። የሚለውን ይህን መጽሐፍ አላነበባችሁምን?

12፤ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፥ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ።

13፤በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ።

14፤መጥተውም፦ መምህር ሆይ፥ የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ? አሉት።

15፤እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ፦ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ አላቸው።

16፤እነርሱም አመጡለት። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው፤ እነርሱም፦ የቄሣር ናት አሉት።

17፤ኢየሱስም መልሶ፦ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በእርሱም ተደነቁ።

18፤ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም አሉት፦

19፤መምህር ሆይ፥ ሙሴ፦ የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን።

20፤ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ዘር ሳያስቀር ሞተ፤

21፤ሁለተኛውም አገባት፥ ዘርም ሳይተው ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤

22ሰባቱም አገቡአት፥ ዘርም አላስቀሩም። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች።

23፤ሰባቱ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀን ሲነሡ ከእነርሱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?

24፤ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን?

25፤ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፥ አይጋቡምም።

26፤ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር፦ እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን?

27፤የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ።

28፤ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ፦ ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው።

29፤ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥

30፤አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

31፤ሁለተኛይቱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።

32፤ጻፊውም፦ መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤

33፤በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው አለው።

34፤ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ፦ አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።

35፤ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ፦ ጻፎች ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?

36፤ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ።

37፤ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር።

38-39፤ሲያስተምርም እንዲህ አለ፦ ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን፥ በገበያም ሰላምታን፥ በምኵራብም የከበሬታን ወንበር፥ በግብርም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤

40፤የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።

41፤ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤

42፤አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች።

43፤ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤

44፤ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው።

1 እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ አለው።

2 ኢየሱስም መልሶ፦ እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አለው።3 በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም፦

4 ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት።

5 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።

6 ብዙዎች፦ እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ።

7 ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው።

8 ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።

9 እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ።

10 አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል።

11 ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።

12 ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤

13 በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።

14 ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥

15 በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥

16 በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።

17 በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው።

18 ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤

19 በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና።

20 ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።

21 በዚያን ጊዜም ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም፦ እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤

22 ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ።

23 እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ።

24 በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ 25 ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ።

26 በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።

27 በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።

28 ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤

29 እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ።

30 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 31 ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።

32 ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም።

33 ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም።

34 ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፥ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ።

35 እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና

36 ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ።

37 ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።

1 ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር።

2 የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን ይሉ ነበርና።

3 እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው።

4 አንዳንዶችም፦ ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው?

5 ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት።

6 ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች።

7 ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። 8 የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው።

9 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል።

10 ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ።

11 ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር።

12 ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ፦ ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት።

13 ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው፦ ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤

14 ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ፦ መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት።

15 እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤

16 በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ።

17 በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ።

18 ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ።

19 እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም፦ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር።

20 እርሱም መልሶ፦ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው።

21 የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው።

22 ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ።

23 ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ።

24 እርሱም፦ ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው።

25 እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው።

26 መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።

27 ኢየሱስም፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና።

28 ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው።

29 ጴጥሮስም፦ ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው።

30 ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው።

31 እርሱም ቃሉን አበርትቶ፦ ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ።

32 ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም፦ ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ አላቸው።

33 ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና።

34 ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው።

35 ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና፦

36 አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ።

37 መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም፦ ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን?

38 ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።

39 ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ።

40 ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም።

41 ሦስተኛም መጥቶ፦ እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል።

42 ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው።

43 ወዲያውም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ። በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። 44 አሳልፎ የሚሰጠውም፦ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።

45 መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና፦ መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤

46 እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት።

47 በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ።

48 ኢየሱስም መልሶ፦ ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን?

49 በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው።

50 ሁሉም ትተውት ሸሹ።

51 ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥

52 ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።

53 ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ።

54 ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር።

55 የካህናት አለቆችም ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤

56 ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም።

57-58 ሰዎችም ተነሥተው፦ እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው ብለው በሐሰት መሰከሩበት።

59 ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም።

60 ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ፦ አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው።

61 እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና፦ የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው።

62 ኢየሱስም፦ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ።

63 ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፦ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል?

64 ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ፦ ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት።

65 አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና፦ ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።

66 ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥

67 ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና፦ አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው።

68 እርሱ ግን፦ የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ።

69 ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት፦ ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር።

70 እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን፦ የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት። 71 እርሱ ግን፦ ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ።

72 ጴጥሮስንም ኢየሱስ፦ ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።

1፤ወዲያውም፡ማለዳ፡የካህናት፡አለቃዎች፡ከሽማግሌዎችና፡ከጻፊዎች፡ከሸንጎውም፡ዅሉ፡ጋራ፡ከተማከሩ፡ በዃላ፥ኢየሱስን፡አሳስረው፡ወሰዱትና፡ለጲላጦስ፡አሳልፈው፡ሰጡት። 2፤ጲላጦስም፦አንተ፡የአይሁድ፡ንጉሥ፡ነኽን፧ብሎ፡ጠየቀው።ርሱም፦አንተ፡አልኽ፡ብሎ፡መለሰለት። 3፤የካህናት፡አለቃዎችም፡ብዙ፡ያሳጡት፡ነበር፤ርሱ፡ግን፡ምንም፡አልመለሰም። 4፤ጲላጦስም፡ደግሞ፦አንዳች፡አትመልስምን፧እንሆ፥በስንት፡ነገር፡ያሳጡኻል፡ብሎ፡ጠየቀው። 5፤ኢየሱስም፡ከዚያ፡በዃላ፡ጲላጦስ፡እስኪደነቅ፡ድረስ፡ምንም፡አልመለሰም። 6፤በዚያም፡በዓል፡የለመኑትን፡አንድ፡እስረኛ፡ይፈታላቸው፡ነበር። 7፤በዐመፅም፡ነፍስ፡ከገደሉት፡ከዐመፀኛዎች፡ጋራ፡የታሰረ፡በርባን፡የተባለ፡ነበረ። 8፤ሕዝቡም፡ወጥተው፡እንደ፡ልማዱ፡ያደርግላቸው፡ዘንድ፡እየጮኹ፡ይለምኑት፡ዠመር። 9፤ጲላጦስም፦የአይሁድን፡ንጉሥ፡እፈታላችኹ፡ዘንድ፡ትወዳላችኹን፧ብሎ፡መለሰላቸው፤ 10፤የካህናት፡አለቃዎች፡በቅንአት፡አሳልፈው፡እንደ፡ሰጡት፡ያውቅ፡ነበርና። 11፤የካህናት፡አለቃዎች፡ግን፡በርባንን፡በርሱ፡ፈንታ፡ይፈታላቸው፡ዘንድ፡ሕዝቡን፡አወኳቸው። 12፤ጲላጦስም፡ዳግመኛ፡መልሶ፦እንግዲህ፡የአይሁድ፡ንጉሥ፡የምትሉትን፡ምን፡ላደርገው፡ትወዳላችኹ፧አላቸው። 13፤እነርሱም፡ዳግመኛ፦ስቀለው፡እያሉ፡ጮኹ። 14፤ጲላጦስም፦ምን፡ነው፧ያደረገው፡ክፋት፡ምንድር፡ነው፧አላቸው።እነርሱ፡ግን፦ስቀለው፡እያሉ፡ ጩኸት፡አበዙ። 15፤ጲላጦስም፡የሕዝቡን፡ፈቃድ፡ሊያደርግ፡ወዶ፡በርባንን፡ፈታላቸው፥ኢየሱስንም፡ገርፎ፡እንዲሰቀል፡ አሳልፎ፡ሰጠ። 16፤ወታደሮችም፡ፕራይቶሪዮን፡ወደሚባል፡ግቢ፡ውስጥ፡ወሰዱት፥ጭፍራውንም፡ዅሉ፡በአንድነት፡ጠሩ። 17፤ቀይ፡ልብስም፡አለበሱት፥የሾኽ፡አክሊልም፡ጐንጉነው፡ደፉበት፤ 18፤የአይሁድ፡ንጉሥ፡ሆይ፥ሰላም፡ለአንተ፡ይኹን፡እያሉ፡እጅ፡ይነሡት፡ዠመር፤ 19፤ራሱንም፡በመቃ፡መቱት፡ተፉበትም፥ተንበርክከውም፡ሰገዱለት። 20፤ከተዘባበቱበትም፡በዃላ፡ቀዩን፡ልብስ፡ገፈፉት፥ልብሱንም፡አለበሱት፥ሊሰቅሉትም፡ወሰዱት። 21፤አንድ፡መንገድ፡ዐላፊም፡የአሌክስንድሮስና፡የሩፎስ፡አባት፡ስምዖን፡የተባለ፡የቀሬና፡ሰው፡ከገጠር፡ ሲመጣ፡መስቀሉን፡ይሸከም፡ዘንድ፡አስገደዱት። 22፤ትርጓሜውም፡የራስ፡ቅል፡ስፍራ፡ወደሚኾን፡ጎልጎታ፡ወደተባለ፡ስፍራ፡ወሰዱት። 23፤ከርቤም፡የተቀላቀለበትን፡የወይን፡ጠጅ፡እንዲጠጣ፡ሰጡት፤ርሱ፡ግን፡አልተቀበለም። 24፤ሰቀሉትም፥ልብሱንም፡ማን፡ማን፡እንዲወስድ፡ዕጣ፡ተጣጥለው፡ተካፈሉ። 25፤በሰቀሉትም፡ጊዜ፡ሦስት፡ሰዓት፡ነበረ። 26፤የክሱ፡ጽሕፈትም፦የአይሁድ፡ንጉሥ፡የሚል፡ተጽፎ፡ነበር። 27፤ከርሱም፡ጋራ፡ኹለት፡ወንበዴዎች፡አንዱን፡በቀኙ፡አንዱንም፡በግራው፡ሰቀሉ። 28፤መጽሐፍም፦ከዐመፀኛዎች፡ጋራ፡ተቈጠረ፡ያለው፡ተፈጸመ። 29፤የሚያልፉትም፡ራሳቸውን፡እየነቀነቁ፡ይሰድቡት፡ነበርና፦ዋ፥ቤተ፡መቅደስን፡የምታፈርስ፡በሦስት፡ቀንም፡ የምትሠራ፥ 30፤ከመስቀል፡ወርደኽ፡ራስኽን፡አድን፡አሉ። 31፤እንዲሁም፡የካህናት፡አለቃዎች፡ደግሞ፡ከጻፊዎች፡ጋራ፡ርስ፡በርሳቸው፡እየተዘባበቱ፦ሌላዎችን፡ አዳነ፤ራሱን፡ሊያድን፡አይችልም፤ 32፤አይተን፡እናምን፡ዘንድ፡የእስራኤል፡ንጉሥ፡ክርስቶስ፡አኹን፡ከመስቀል፡ይውረድ፡አሉ።ከርሱም፡ጋራ፡ የተሰቀሉት፡ይነቅፉት፡ነበር። 33፤ስድስት፡ሰዓትም፡በኾነ፡ጊዜ፥እስከ፡ዘጠኝ፡ሰዓት፡በምድር፡ዅሉ፡ላይ፡ጨለማ፡ኾነ። 34፤በዘጠኝ፡ሰዓትም፡ኢየሱስ፦ኤሎሄ፥ኤሎሄ፥ላማ፡ሰበቅታኒ፧ብሎ፡በታላቅ፡ድምፅ፡ጮኸ፤ትርጓሜውም፡ አምላኬ፥አምላኬ፥ለምን፡ተውኸኝ፧ማለት፡ነው። 35፤በዚያም፡ከቆሙት፡ሰዎች፡ሰምተው፦እንሆ፥ኤልያስን፡ይጠራል፡አሉ። 36፤አንዱም፡ሮጦ፡ሖምጣጤ፡በሰፍነግ፡ሞላ፡በመቃም፡አድርጎ።ተዉ፤ኤልያስ፡ሊያወርደው፡ይመጣ፡እንደ፡ ኾነ፡እንይ፡እያለ፡አጠጣው። 37፤ኢየሱስም፡በታላቅ፡ድምፅ፡ጮኸ፡ነፍሱንም፡ሰጠ። 38፤የቤተ፡መቅደስም፡መጋረጃ፡ከላይ፡እስከ፡ታች፡ከኹለት፡ተቀደደ። 39፤በዚያም፡በአንጻሩ፡የቆመ፡የመቶ፡አለቃ፡እንደዚህ፡ጮኾ፡ነፍሱን፡እንደ፡ሰጠ፡ባየ፡ጊዜ፦ይህ፡ሰው፡ በእውነት፡የእግዚአብሔር፡ልጅ፡ነበረ፡አለ። 40-41፤ሴቶችም፡ደግሞ፡በሩቅ፡ኾነው፡ይመለከቱ፡ነበር፤ከነርሱም፡በገሊላ፡ሳለ፡ይከተሉትና፡ያገለግሉት፡ የነበሩ፡መግደላዊት፡ማርያም፡የታናሹ፡ያዕቆብና፡የዮሳም፡እናት፡ማርያም፡ሰሎሜም፡ነበሩ፥ከርሱም፡ጋራ፡ ወደ፡ኢየሩሳሌም፡የወጡ፡ሌላዎች፡ብዙዎች፡ሴቶች፡ነበሩ። 42፤አኹንም፡በመሸ፡ጊዜ፡የሰንበት፡ዋዜማ፡የኾነ፡የማዘጋጀት፡ቀን፡ስለ፡ነበረ፥የከበረ፡አማካሪ፡የኾነ፡ የአርማትያስ፡ዮሴፍ፡መጣ፥ 43፤ርሱም፡ደግሞ፡የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡ይጠባበቅ፡ነበር፤ደፍሮም፡ወደ፡ጲላጦስ፡ገባና፡የኢየሱስን፡ ሥጋ፡ለመነው። 44፤ጲላጦስም፡አኹኑን፡እንዴት፡ሞተ፡ብሎ፡ተደነቀ፥የመቶ፡አለቃውንም፡ጠርቶ፡ከሞተ፡ቈይቷልን፧ብሎ፡ ጠየቀው፤ 45፤ከመቶ፡አለቃውም፡ተረድቶ፡በድኑን፡ለዮሴፍ፡ሰጠው። 46፤በፍታም፡ገዝቶ፡አውርዶም፡በበፍታ፡ከፈነው፡ከአለትም፡በተወቀረ፡መቃብር፡አኖረው፥በመቃብሩ፡ ደጃፍም፡ድንጋይ፡አንከባለለ። 47፤መግደላዊትም፡ማርያም፡የዮሳም፡እናት፡ማርያም፡ወዴት፡እንዳኖሩት፡ይመለከቱ፡ነበር።

1፤ሰንበትም፡ካለፈ፡በዃላ፡መግደላዊት፡ማርያም፡የያዕቆብም፡እናት፡ማርያም፡ሰሎሜም፡መጥተው፡ሊቀቡት፡ ሽቱ፡ገዙ። 2፤ከሳምንቱም፡በፊተኛው፡ቀን፡እጅግ፡በማለዳ፡ፀሓይ፡ከወጣ፡በዃላ፡ወደ፡መቃብር፡መጡ። 3፤ርስ፡በርሳቸውም፦ድንጋዩን፡ከመቃብር፡ደጃፍ፡ማን፡ያንከባልልልናል፧ይባባሉ፡ነበር፤ 4፤ድንጋዩ፡እጅግ፡ትልቅ፡ነበርና፤አሻቅበውም፡አይተው፡ድንጋዩ፡ተንከባሎ፡እንደ፡ነበር፡ተመለከቱ።5፤ወደ፡መቃብሩም፡ገብተው፡ነጭ፡ልብስ፡የተጐናጸፈ፡ጕልማሳ፡በቀኝ፡በኩል፡ተቀምጦ፡አዩና፡ደነገጡ። 6፤ርሱ፡ግን፦አትደንግጡ፤የተሰቀለውን፡የናዝሬቱን፡ኢየሱስን፡ትፈልጋላችኹ፤ተነሥቷል፥በዚህ፡ የለም፤እንሆ፥ርሱን፡ያኖሩበት፡ስፍራ። 7፤ነገር፡ግን፥ኼዳችኹ፡ለደቀ፡መዛሙርቱ፡ለጴጥሮስም፦ወደ፡ገሊላ፡ይቀድማችዃል፤እንደ፡ነገራችኹ፡ በዚያ፡ታዩታላችኹ፡ብላችኹ፡ንገሯቸው፡አላቸው። 8፤መንቀጥቀጥና፡መደንገጥ፡ይዟቸው፡ነበርና፥ወጥተው፡ከመቃብር፡ሸሹ፤ይፈሩ፡ነበርና፥ለማንም፡አንዳች፡ አልነገሩም።እነርሱም፡ያዘዛቸውን፡ዅሉ፡ለጴጥሮስና፡ከርሱ፡ጋራ፡ላሉት፡በዐጪሩ፡ተናገሩ።ከዚህም፡በዃላ፡ ኢየሱስ፡ራሱ፡ለዘለዓለም፡ድኅነት፡የኾነውን፡የማይለወጠውን፡ቅዱስ፡ወንጌል፡ከፀሓይ፡መውጫ፡እስከ፡ መጥለቂያው፡ድረስ፡በእጃቸው፡ላከው። 9፤ከሳምንቱም፡በመዠመሪያው፡ቀን፡ማልዶ፡በተነሣ፡ጊዜ፥አስቀድሞ፡ሰባት፡አጋንንት፡ላወጣላት፡ ለመግደላዊት፡ማርያም፡ታየ። 10፤ርሷ፡ኼዳ፡ከርሱ፡ጋራ፡ኾነው፡ለነበሩት፡ሲያዝኑና፡ሲያለቅሱ፡ሳሉ፡አወራችላቸው፤ 11፤እነርሱም፡ሕያው፡እንደ፡ኾነ፡ለርሷም፡እንደ፡ታያት፡ሲሰሙ፡አላመኑም። 12፤ከዚህም፡በዃላ፡ከነርሱ፡ለኹለቱ፡ወደ፡ባላገር፡ሲኼዱ፡በመንገድ፡በሌላ፡መልክ፡ተገለጠ፤ 13፤እነርሱም፡ኼደው፡ለሌላዎቹ፡አወሩ፤እነዚያንም፡ደግሞ፡አላመኗቸውም። 14፤ዃላም፡በማእዱ፡ተቀምጠው፡ሳሉ፡ለዐሥራ፡አንዱ፡ተገለጠ፥ተነሥቶም፡ያዩትን፡ስላላመኗቸው፡ አለማመናቸውንና፡የልባቸውን፡ጥንካሬ፡ነቀፈ። 15፤እንዲህም፡አላቸው፦ወደ፡ዓለም፡ዅሉ፡ኺዱ፥ወንጌልንም፡ለፍጥረት፡ዅሉ፡ስበኩ። 16፤ያመነ፡የተጠመቀም፡ይድናል፥ያላመነ፡ግን፡ይፈረድበታል። 17፤ያመኑትንም፡እነዚህ፡ምልክቶች፡ይከተሏቸዋል፤በስሜ፡አጋንንትን፡ያወጣሉ፤በዐዲስ፡ቋንቋ፡ ይናገራሉ፤እባቦችን፡ይይዛሉ፥ 18፤የሚገድልም፡ነገር፡ቢጠጡ፡አይጐዳቸውም፤እጃቸውን፡በድውዮች፡ላይ፡ይጭናሉ፡እነርሱም፡ይድናሉ። 19፤ጌታ፡ኢየሱስም፡ከነርሱ፡ጋራ፡ከተናገረ፡በዃላ፡ወደ፡ሰማይ፡ዐረገ፡በእግዚአብሔርም፡ ቀኝ፡ተቀመጠ።

ክርስቶስ ከዐረገ በኋላ በአብ ቀኝ ተቀምጦ

20፤እነርሱም፡ወጥተው፡በየስፍራው፡ዅሉ፡ሰበኩ፥ጌታም፡ከነርሱ፡ጋራ፡ይሠራ፡ነበር፥በሚከተሉትም፡ ምልክቶች፡ቃሉን፡ያጸና፡ነበር፨

  1. ^ በPew የጥናት መዐከል መሠረት በ፳፻፲፭ ዓ.ም. በተደረገው ግምት የዓለም ክርስቲያን ሕዝብ በ፳፻፶ ዓ.ም. ወደ ፫ቢሊዮን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል
  2. ^ ታሪካቸው በኢትዮጵያ ሥንክሳር Ethiopian Synaxarium (ጉግል ፕሌይ ስቶር ይገኛል) በሚያዝያ ፴ የሰማዕታትና ቅዱሳን ታሪክ ውስጥ ይነበባል
  3. ^ ወንጌል አንድምታ Archived ጃንዩዌሪ 8, 2019 at the Wayback Machine ይመልከቱ