መጽሐፍ ቅዱስ
መጽሐፍ ቅዱስ ነብያት እና ታሪካውያን የጻፉት የክርስቲያኖች እምነት መጽሓፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን ተከፍሎ 81 መጻሕፍት ያሉት ሲሆን በአንዳንድ እምነቶች ደግሞ 73 እና 66 ክፍል ብቻ ነው አሉት ብለው ያምናሉ። ከነዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍትም ጋራ የመጻሕፍት ቁጥር 81 ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከመቶ 25% የአምላክ ንግግር፣ ከመቶ 25 % የነብያት ንግግር እና ከመቶ 50 % የታሪክ ጽሐፍያን ንግግር ይዟል። ነገር ግን በነብያት ውስጥም በቃሉም በታሪክም ተነገረ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ነው
በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተለመደው «ባይብል» የሚለው ቃል ከጥንቱ የኮይነ ግሪክኛ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን ቃሉ የተገኘበት τὰ βιβλία /ታ ቢብሊያ/ የሚለው ሀረግ «መጽሐፍቱ» ወይም «ትንንሽ መጽሐፍት» ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። የዚሁም ቃል መነሻ ከግሪኩ ስም Βύβλος /ቢውብሎስ/ (ፓፒሩስ ወይም ቄጠማ፣ የወረቀት ተክል) ሲሆን ይሄ ቃል «ፓፒሩስ» ከተነገደበት ከተማ ጌባል / ቢውብሎስ ስም መጣ።
መጽሐፍ ቅዱስ ለአይሁድና ክርስትና እምነት የእምነት መሰረት የሆኑ ትናንሽ መጽሐፍትን የያዘ አንድ ጥራዝ ነው። በተለምዶ «ብሉይ ኪዳን» በመባል የሚጠራውና በአይሁዳውያን በ24 እና በክርስቲያኖች በ39 መጽሐፍት የሚከፈለው የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ክፍል በመጀመሪያ በአብዛኛው የተጻፈው በጥንታዊው የዕብራይስጥ ቋንቋ ሲሆን የተጻፉበት ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተወሰኑ መቶ አመታት ቀደም ብሎ እንደሆነ ይነገራል። እነዚህን መጽሐፍት የጻፉት በወቅቱ የነበሩ የታመኑ አይሁዳውያን ወይም እስራኤላውያን ናቸው። የመጨረሻዎቹን 27 መጻሕፍት በግሪክኛ የጻፏቸው ክርስቲያኖች ሲሆኑ «አዲስ ኪዳን» በመባል በሰፊው ይታወቃሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ማስረጃም ሆነ በጣም ጥንታዊ የሆኑት ወጎች እንደሚጠቁሙት እነዚህ 66 መጻህፍት የተጻፉት ግብጽ ኃያል ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ ሮም የዓለም ኃያል መንግስት እስከ ነበረችበት ዘመን ባሉት 1600 ዓመታት ውስጥ ነው።
በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እምነት መሰረት ከ66ቱ መጽሐፍት በተጨማሪ የተካተቱ የተወሰኑ መጽሐፍት ሲኖሩ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እነዚህ ተጨማሪ መጻሕፍት (ዲዩቴሮካኖኒካል በመባልም ይታወቃሉ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱትን መጻሕፍት ቁጥር ወደ 81 ያደርሱታል።በ greek እና hibrew የተፃፈው 66 ነው::
ከክርስቶስ ስብከት ቀጥሎ ምዕመናን የሆኑት ለረጅም ዘመን ተጨማሪ መጻሕፍቱን ከነመጽሐፈ ሄኖክና ኩፋሌ ያንብቡ ነበር። በግሪኩ «ሴፕቱዋጊንት» ትርጉም እንዲሁም በሞት ባሕር ጥቅል ብራናዎች (50 ዓመት ከክርስቶስ በፊት) በዕብራይስጥ መጻሕፍት መኃል ይገኙ ነበር። የአይሁድ ሰንሄድሪን ረቢዎች በ100 ዓ.ም. አካባቢ በተለይም ረቢ አኪቫ በን ዮሴፍ እነዚህን ተጨማሪ መጻሕፍት ከዕብራይስጥ ቅጂ አጠፉ። እስካሁንም ድረስ በዕብራይስጥ ትርጉም አይታወቁም። አዲስ ኪዳን ከተጻፈ በኋላ፣ ብዙ አጠያያቂ ወንጌሎችና የሌሎች እምነቶች ጽሑፎች ደግሞ ሊሠራጩ ጀመር። ግኖስቲክ የተባለው እምነት ተከታዮች በተለይ ብዙ ሥነ ጽሑፍ ፈጠሩ፣ ይህ ግን ከኦርቶዶክስ ወንጌል የተዛቡ ትምህርቶች ነበር። በ170 ዓ.ም. በክርስትያኖች ዘንድ የቱ መጻሕፍት ትክክለኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ናቸው? የሚል ጥያቄ ይነሣ ጀመር። መሊቶ ዘሳርዲስ የተባለ ጳጳስ በዚያን ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም መጻሕፍት ቤት ጉዞ አድርጎ የ ዕብራውያን መጻሕፍት ምን ምን እንደ ነበሩ ዘገበ። ተጨማሪ መጻሕፍቱ ከዚያ በፊት ስለ ጠፉ አልተዘገቡም። ስለዚህ ከዚህ በቀር ምንም ያልተዘረዘሩት ብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ትክክለኛ አይሆኑም የሚል ሀሣብ በሮሜ መንግሥት ክርስቲያኖች ተነሣ። ይህም የአይሁዶች ቀኖና በንቅያ ጉባኤ (317 ዓ.ም.) በሮሜ መንግሥት ለክርስቲያኖች ጸና።
መጽሐፍ ቅዱስ የስነምግባር ጉዳዮችን በሚመለከት መመሪያ የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ እንደ ወንጀል፣ ረሃብና የአካባቢ መበከል ያሉት ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ ይገልጻል። ችግሩ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ የሚናገረውን ነገር ብዙ ሰዎች በቁም ነገር መመልከት ትተዋል። ከዚህ ቀደም ይህ መጽሐፍ ቢያንስ በምዕራቡ ዓለም እንኳ ትልቅ ተሰሚነት ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በሰዎች አማካኝነት ቢሆንም እንኳ ቀደም ባሉት ጊዜያት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች የአምላክ ቃል መሆኑንና መልእክቱም አምላክ በመንፈስ አነሳሽነት ያስጻፈው እንደሆነ ያምኑ ነበር።
ይሁን እንጂ ዛሬ እያንዳንዱን ነገር መጠራጠር የተለመደ ነገር ሆኗል። ሰዎች ባህላቸውን፣ የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦችን፣ የስነምግባር ደንቦችንና የአምላክን መኖር እንኳ ሳይቀር የጠራጠራሉ። በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስን ጠቃሚነት በተመለከተ ጥርጣሬ ገብቷቸዋል። አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ጊዜ ያለፈበትና አላስፈላጊ እንደሆነ አድርገው የሚያዩት ይመስላል። ከዘመናችን ምሁራን መካከል መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርገው የሚመለከቱት በጣም ጥቂት ናቸው። እንዲያውም አብዛኞቹ ሰዎች ከምሁሩ ጄምስ ባር አባባል ጋር ይስማማሉ፡- "ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልማዶች ያለኝ አመለካከት የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት ናቸው የሚል ነው። የሰው ልጅ የራሱን እምነት ያሰፈረበት መጽሐፍ ነው።"[1]
ይህ አመለካከት ወደ አንድ ነጥብ ያመራል፦ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች የጻፉት ተራ መጽሐፍ ከሆነ ለሰው ልጅ ችግሮች ምንም ዓይነት ግልጽ የሆነ መልስ አይገኝም ማለት ነው። የሰው ልጆች በገዛ እጃቸው በሚያመጡት ጣጣ ከህልውና ውጭ እንዳይሆኑ ወይም በኑክሊየር ጦርነት እንዳያልቁ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል በጭፍን መዳከር ይኖርባቸዋል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ከሆነ ግን ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ የሚያስፈልገን ዋነኛው ነገር እርሱ ይሆናል።
የታሪክ መዝገቦች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላሉ?
መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት ታትሞ በመሸጥና በሰፊው በመሰራጨት ረገድ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። ጊነስ ቡክ ኦቭ ወርልድ ሬኮርድስ የተባለው መጽሐፍ በ1988 እትሙ እንደገለጸው ከ1815 እስከ 1975 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ ወደ 2.5 ቢልዮን የሚገመቱ ቅጂዎች ታትመዋል። ይህ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ሊሰራጭ ይቅርና ወደዚያ ቁጥር የተጠጋ አንድም መጽሐፍ በታሪክ አልታየም።
ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመ መጽሐፍ አይገኝም። ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ከ1800 በሚበልጡ የተለያዩ ቋንቋዎች ይገኛል። በኢትዮጵያ እንኳን በአማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ኦሮምኛ፣ ወላይትኛ፣ ጉራግኛና ሌሎች ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ሆነ በከፊል ተተርጎሞ ይገናል። በአጠቃላይ ዛሬ 98 በመቶ ገደማ የሚሆነው የምድራችን ነዋሪ መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋው ማግኘት ይችላል።
ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ መጽሐፍ ቅዱስን "በታሪክ ዘመናት ከታዩት ጽሑፎች ሁሉ ይበልጥ ተደማጭነት ያለው የመጻህፍት ስብስብ" ሲል ጠርቶታል።[2] የ19ኛው ጀርመናዊ ባለቅኔ ሄንሪክ ሃይነ እንዲህ ብለዋል፦ "ይህን ሁሉ ማስተዋል ያገኘሁት ከአንድ መጽሐፍ ነው። . . . መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ። ቅዱስ መጽሐፍ መባሉ ይገባዋል። አምላኩን ያጣ ሰው ካለ በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ሊያገኘው ይችላል።"[3] በዚሁ መቶ ዘመን የኖረውና የጸረ-ባርነት እንቅስቃሴ አራማጅ የነበረው ዊልያም ኤች ሴዋርድ እንዲህ ብሏል፦ "የሰው ልጅ የመሻሻል ተስፋ የተመካው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሚሄደው የመጽሐፍ ቅዱስ ተደማጭነት ላይ ነው።"[4]
የዩናይትድ ስቴትስ 16ኛ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል፦ "አምላክ ለሰው ልጆች ከሰጠው ስጦታ ሁሉ የላቀ ስጦታ ነው። . . . መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖር ኖሮ መልካሙንና ክፉውን ለይተን ማወቅ ባልቻልን ነበር።"[5] የብሪታንያው የህግ ሰው ሰር ዊልያም ብላክስተን "ሁሉም ሰብዓዊ ሕጎች የተመሰረቱት በእነዚህ ሁለት ሕጎች ማለትም በተፈጥሮ ሕግና አምላክ ለሰው ልጆች በሰጠው ሕግ [በመጽሐፍ ቅዱስ] ላይ ነው፤ እንግዲያው ሰብዓዊ ሕጎች ከእነዚህ ሕጎች ጋር እንዲጋጩ ማድረግ አይገባም ማለት ነው።"[6] ብለው ሲናገሩ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ተደማጭነት እንዳለው ጎላ አድርገው መግለጻቸው ነበር።
በአንጻሩ ደግሞ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል የከረረ ተቃውሞ የገጠመው መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ከመካከለኛው ዘመን አንስቶ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ በአደባባይ ተቆልሎ እንዲቃጠል ተደርጓል። በዛሬው ዘመን እንኳ ሳይቀር መጽሐፍ ቅዱስን በማንበባቸው ወይም በማሰራጨታቸው ምክንያት የገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸው ወይም በእስራት የተቀጡ ሰዎች አሉ። ባለፉት መቶ ዘመናት እንዲህ ያለው "ወንጀል" ብዙውን ጊዜ አሰቃቂ ለሆነ ድብደባ አልፎ ተርፎም ለሞት የሚዳርግ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ውስጥ ያሳደረው ፍቅር ከዚሁ ጎን ለጎን የሚታይ ነው። ብዙዎች የማያቋርጥ ስደት ቢደርስባቸውም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባቸውን ገፍተውበታል። ለምሳሌ ያህል በ16ኛው መቶ ዘመን የኖረውንና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተምሮ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው አስተማሪ የነበረውን ዊልያም ቲንደልን እንመልከት።
ቲንደል ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ፍቅር ነበረው። ይሁን እንጂ በዘመኑ የነበሩት ሃይማኖታዊ ባለ ሥልጣናት መጽሐፍ ቅዱስ ሙት በነበረው በላቲን ቋንቋ ተወስኖ እንዲቀር ሽንጣቸውን ገትረው የሟገቱ ነበር። ቲንደል ግን የአገሩ ሶዎች መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ አጋጣሚ እንዲኖራቸው በማሰብ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመተርጎም ቆርጦ ተነሳ። ይህ ተግባሩ ከሕጉ ጋር የሚቃረን ስለነበር ቲንደል ጥሩ የማስተማር ስራውን ትቶ መሰደድ ግድ ሆነበት። የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ("አዲስ ኪዳን") እና አንዳንዶቹን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ("ብሉይ ኪዳን") ወደ አገሩ ቋንቋ ተርጉሞ እስኪጨርስ ኑሮውን በስደት ለመግፋት ተገዷል። ይሁን እንጂ በመጨረሻ በመያዙና መናፍቅ ነው ተብሎ በመወንጀሉ ተሰቅሎ እንዲሞትና በድኑም በእሳት እንዲቃጠል ተደርጓል።
ቲንደል፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ወይም ለሌሎች ሰዎች እንዲዳረስ ለማድረግ ሲሉ ብዙ መሥዋዕትነት ከከፈሉት በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው። ከሌላው ሰው የተለየ ምንም ነገር ያልነበራቸውን ብዙ ወንዶችና ሴቶች ይህን ያህል ድፍረት እንዲኖራቸው ያነሳሳ ሌላ መጽሐፍ በታሪክ ውስጥ አልታየም። ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም አቻ አይገኝለትም።
- ^ The Bible in the Modern World, By James Barr, 1973, p. 120
- ^ The New Encyclopædia Britannica, 1987, Vol. 2, p.194.
- ^ The Book of Books: An Introduction to Solomon Goldman, 1948, p. 219.
- ^ The Book of Books: An Introduction, p. 222.
- ^ Federal Register, Vol. 48, No. 26, February 7, 1983, p.5527
- ^ Chadman's Cyclopedia of Law, 1912, Vol. 1, pp. 86-91.
- መጽሐፍ ቅዱስ Archived ጁላይ 29, 2013 at the Wayback Machine
- መጽሐፍ ቅዱስ - ድምፅ
- መጽሐፍ ቅዱስ (PDF)
- መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት