Jump to content

አካድኛ

ከውክፔዲያ
(ከባቢሎንኛ የተዛወረ)
የአካድኛ ኩነይፎርም ሰነድ፣ የቢራ ተቀባዮች ዝርዝር ከሻርካሊሻሪ ዘመን (2030 ዓክልበ. ገደማ)

አካድኛ ወይም አሦርኛ ወይም ባቢሎንኛ በጥንት በመስጴጦምያ የተነገረ ሴማዊ ቋንቋ ነበረ።

በሥነ ቅርስ መጀመርያው የታወቀው አካድኛ ጽሑፍ ከመስኪአጝ-ኑና ዘመን (2314 ዓክልበ. ግድም) ነው። ከአካድ ንጉሥ ታላቁ ሳርጎን ጀምሮ የአካድ መንግሥት (2077-2010 ዓክልበ.) በመላው መስጴጦምያ፣ ኤላምሶርያ አስገደዱት። ከዚያ በኋላ ኤላም ወደ ኤላምኛ መለሰ፣ የሶርያም ቋንቋ ኤብላኛ ሆነ። በአሦርና በባቢሎን የአካድኛ አይነቶች ተነገሩ። አሦራውያን በአናቶሊያ (ሐቲ) የካሩም ንግድ እስከ 1628 ዓክልበ. ድርስ ያሕል ያካሄዱ ነበር፤ የአሦርኛ አካድኛ ጥቅም እንደ መደበኛ ወይም ይፋዊ ጽሑፍ ቋንቋ አስፋፉ።

በሚከተለው ዘመን በግብጽ የተገኙ የአማርና ደብዳቤዎች (1369-1339 ዓክልበ.) እንዳሳዩ፣ ጽሕፈት የነበራቸው አገራት ሁሉ አካድኛ እንደ መደበኛ ቋንቋ ይጠቀሙ ነበር። የጥንታዊ ግብጽ፣ የከነዓን፣ የሚታኒ፣ የኬጥያውያን መንግሥት፣ የባቢሎን (ካራንዱኒያሽ)፣ የአላሺያ ወይም የአርዛዋ ባለሥልጣናት ሁላቸው በአካድኛ ተነጋገሩ። እነዚህ አገራት ግን ለየራሳቸው ልሳናት ግብጽኛከነዓንኛሑርኛኬጥኛካሥኛሚኖአንኛ እና ሉዊኛ ነበሩዋቸው።

በ740 ዓክልበ. የአሦር ንጉሥ 3 ቴልጌልቴልፌልሶር አረማይስጥ ከአሦርኛ ጋር ይፋዊና መደበኛ ቋንቋ አደረገው። ከዚያ ጀምሮ የአረማይስጥ ጥቅም እየተስፋፋ የአካድኛ ጥቅም በየጊዜ ይቀነስ ነበር። ከአዲስ ባቢሎን መንግሥት ውድቀት በኋላ አካድኛ ባይነገርም አካድኛን መጻፍ የቻሉ ጥቂት ሊቃውንት እስከ 75 ዓም ያህል ቀሩ።

የአካድኛ ጽሕፈት ከሱመርኛ የተበደረው ኩኔይፎርም (ውሻል ቅርጽ) ጽሕፈት ነበረ። የቻይና ጽሕፈትን በመምሰል እያንዳንዱን ቃል ለማንበብ ብዙ ሺህ ምልክቶች መማር አስፈለገ። ከ200 እስከ 1850 ዓም ድረስ የኩኔይፎርም ማንበብ ችሎታ አልኖረም፤ ከ1850 ዓም በኋላ ብቻ ሊፈታ የቻለ ነው።