Jump to content

ጣይቱ ብጡል

ከውክፔዲያ
(ከጣይቱ የተዛወረ)

==

እቴጌ ጣይቱ ብጡል
ባለቤት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ
አባት ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም
እናት ወይዘሮ የውብዳር
የተወለዱት ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፪ ዓ/ም በደብረ ታቦር[1]
የሞቱት የካቲት ፬ ቀን ፲፱፻፲ ዓ.ም.
የተቀበሩት ታዕካ ነገሥት በዓታ ቤ/ክርስቲያን
ሀይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና

==

«ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ» በሚል ቅፅል ስም የታወቁት እቴጌ ጣይቱ ከአባታቸው ከጎንደርና ወሎ የሆኑት ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም እና ከጎጃም እናታቸው ወይዘሮ የውብ ዳር ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፪ዓ/ም በጌምድር ውስጥ ደብረ ታቦር ከተማ ተወለዱ። በየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓት መሠረት በተወለዱ በ ፹ ቀናቸው ጥቅምት ፳፯ ቀን ፲፰፻፴፫ ዓ/ም በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ክርስትና ተነሡ። በልጅነት ዘመናቸው በዚሁ ደብር ውስጥ ዳዊትን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በጊዜው ይሰጡ የነበሩትን ሌሎች የሃይማኖት ትምህርቶች በየታላላቁ አድባራት በመዘዋወር ያጠናቀቁ ስለመሆናቸው ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። የተማሩባቸውም መፃሕፍት ተጽፈው ይገኙ የነበረበትን የግዕዝ ቋንቋ አጣርተው ያውቁ ነበር። እናታቸው ወይዘሮ የውብዳር ከባለቤታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም ከሞቱ በኋላ በጅሮንድ መዩ የተባሉትን የዓፄ ቴዎድሮስን ባለሟል አግብተው ነበር። እሳቸውም ጣይቱ ብጡል ትምህርት እንዲቀስሙ ለማድረግ ልዩ መምህር ቀጥረውላቸው እንደነበር ይታወቃል። እቴጌ ጣይቱ በማኅደረ ማርያም ሆነው ሲማሩና መፃሕፍትን ይቀጽሉ በነበሩበት ጊዜ ለቤተክርስቲያን መጋረጃ መሥሪያ በትርፍ ጊዜያቸው ፈትል እየፈተሉ ያቀርቡ ነበር። በበገና ቅኝትና ድርደራም በኩል የታወቁ ባለሙያ እንደነበሩ ይተረክላቸዋል።

ሸዋው ንጉሥ ምኒልክ በሸዋ የዓፄ ቴዎድሮስ እንደራሴ ከነበሩት አቶ በዛብህ ጋር ነሐሴ ፲፯ ቀን ፲፰፻፶፯ ዓ/ም በጋዲሎ አካባቢ በተደረገው ጦርነት ድል አድርገው ወደ አንኮበር ገብተው በነሐሴ ፳፬ ቀን ነገሡ። በነገሡም በአሥራ ሁለት ዓመታቸው የፋሲካን በዓል በባሕር ዳር አቅራቢያ ሱሉልታ ላይ ዋሉና ደብረ መይ በጣይቱ ብጡል እናት በወይዘሮ የውብዳር ቤት ከጣይቱ ብጡል ጋር ተጫጭተው ስለጋብቻቸው ተነጋገሩ። ከዚያም ዋና ከተማቸው ወደነበረችው ደብረ ብርሃን ተመልሰው መጡ።

ከተጫጩ ከሁለት ዓመት በኋላ ወይዘሮ ጣይቱን ለማስመጣት በቤተ መንግሥቱ በተደረገው ምክር መሠረት አለቃ ተክለማርያም ወልደ ሚካኤል ደብዳቤ ተሰጥቷቸው ተላኩ። በዚያም አስፈላጊው ሁሉ በተፋጠነ ሁኔታ ተሟልቶ በጐጃም በኩል ደንገጡሮችና አሽከሮች አስከትለው ጉዞውን ጀመሩ። ደብረ ብርሃንም በገቡ ጊዜ ንጉሡ /ምኒልክ/ ታላቅ አቀባበል አደረጉላቸው። ከዚያም ጣይቱ ወንድማቸው ራስ ወሌ ብጡል ዘንድ ለጥቂት ዓመታት ተቀምጠው ከቆዩ በኋላ የጋብቻቸው ስነ-ሥርዓት የፋሲካ ዕለት ሚያዝያ ፳፭ ቀን ፲፰፻፸፭ ዓ/ም በአንኮበር መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን ተቀብለው ተጋቡ።

አፈወርቅ ገብረ ጊዮርጊስ “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፋቸው ገጽ ፴፱--፵፩ ላይ “ከልዢነት ጀምረው ሲመኟት እንደ ህልም ሲአልሟት ትኖር የነብረችው ጣይቱ ብጡል በ፲፰፻፸፭ ዓ/ም ደብረ ብርሃን ገባች ንግሥተ ሸዋ ሆነች ወዲያው የፋሲካ ለት አንኮበር መድኃኔ ዓለም ቆርበው ሁለቱ ተጋቡ። … ፀሐይቱ ለማለት ጣይቱ ተባለች ነገር ግን ከጣይቱ እጣይቱ ለመባል ይገባታል።”[2] ይላሉ

«ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ» ዘውድ ጫኑ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ንጉሡ «አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ» የሚለውን ስም በተቀዳጁ በማግሥቱ ጥቅምት ፳፯ ቀን ፲፰፻፹፪ አ/ም ወይዘሮ ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰየሙ። የስርዓተ ዘውዱ አፈፃፀም በከፍተኛ መሰናዶ የተጠናቀቀ በመሆኑ እጅግ ደማቅ እንደነበር ከተፃፉ ፅሁፎች ለማወቅ ይቻላል። እቴጌ ጣይቱም ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ የተቀበሉትን ዘውድ ደፉላቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በታወቁበት «እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ» በሚል የክብር ስም ማኅተም ተቀረፀላቸው። እነዚሁ ታሪካዊ ሂደቶች እቴጌይቱን በኢትዮጵያ ዱኛዊ፣ ወታደራዊና ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ከፍተኛና ብሩህ ሚና ለመጫወት የቻሉ አድረገዋቸዋል።

የዱኛ (ፖለቲካ) ተግባራት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

እቴጌ ጣይቱ በዱኛ አስተዳደር አንፃር የነበራቸው ችሎታና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በታሪክ አዋቂዎች ዘንድ ተደናቂነትን አትርፎላቸዋል። በየጊዜው ይነሱ በነበሩ የሀገር ጉዳዮች ላይ ይይዙት የነበረው አቋም፣ ይሰጡት የነበረው ውሳኔና ያስተላልፉት የነበረው ትዕዛዝ ተሰሚነትና ተቀባይነት እያገኘ እንደመሄዱ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይሄድ ለነበረው የዱኛ ሥልጣናቸው ዓይነተኛ ምክንያት ነበር።

እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ዱኛ ተሳትፏቸው የገነነውና በአገር አስተዳደርም ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት የጀመሩት ኢትዮጵያ ሚያዝያ ፳፭ ቀን ፲፰፻፹፩ ዓ/ም በውጫሌ ላይ ከኢጣሊያ ጋር በተፈራረመችው ውል ውስጥ በጣልያንኛው ትርጉም ሀገሪቷን ነፃነት እንደሌላት ጥገኛ በማስመሰል ዓላማ ላይ የተመረኮዘ ውንብድና መኖሩ ከታወቀ ወዲህ ነው።

ይህ ለአድዋ ጦርነት መነሳት ምክንያትና ዋነኛ መንስዔ የሆነው ጉዳይ ሊታወቅ የቻለው እቴጌ ጣይቱ የውጫሌው ውል አንቀፅ ፲፯ ላይ ዓለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ የተባሉት ቋንቋ አዋቂ ዓፄ ምኒልክ በሰጧቸው ትዕዛዝ መሠረት የውሉን ሰነድ በመመርመር የውሉ አስራ ሰባተኛው አንቀፅ የያዘውን የትርጉም መዛባት በመግለፅ ጉዳዮ ኢትዮጵያ የምትጐዳበት ስለመለሆኑ ጭምር በማስረዳት በሰጡት ቃል ሲሆን እቴጌ በዚህ ወቅት ነገሮችን በጥንቃቄ የሚከታተሉ ስለነበር ዓፄ ምኒልክ በመጀመሪያ ሳይረዱ ዓለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ እንዲታሰሩ ቢያደርጉም እቴጌ ጣይቱ ግን እኒህ ሰው ትክክለኛ የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆናቸውን ለዓፄ ምኒልክ በማስረዳት ከሦስት ዓመታት እስራት በኋላ ማስፈታቸው ይታወቃል። በዚህ በኩል ሲታይ እቴጌ ጣይቱ የምኒልክ የቅርብ አማካሪ በመሆን በፖለቲካ ተግባሮች ምን ያህል አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ መገንዘብ ይቻላል። እቴጌ እንደተናገሩትም «ዓፅመ ጊዮርጊስ ቢታሰር ቢፈታም ለሀገሩ የሚገባውን ሠርቶ ነው። ኧረ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ዮሴፍ፣ ጣሊያኖች በተንኮል ገብተው በማታለል ይህን የመሰለ ሥራ ሲሠሩ አነጋጋሪ ሆኖ ሳለ እንዴት ሳይስጠነቅቅዎ ቀረ?» በማለት የእቴጌ ጣይቱ የቁጣ መዓት ወደ ዮሴፍ ዞረ። ከዚያም ጨምረው «ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ፣ ሥር የሚነቅል፣ መሠረት የሚያፈርስ ጉዳዮን ሁሉ እኔ ሳላየው እንዳያልፍ ይፍቀዱልኝ» ብለው ለንጉሡ ባመለከቱት መሠረት ይኸው አንቺ ሳታይው ሳትመረምሪው አያልፍም በማለት ፈቀዱላቸው፣ ይህ እንደሚያመለክተው እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸውን ተገቢ ቦታ የሚያመለክት ነው። ውሉንም ለማስተካከል ዓፄ ምኒልክ ያደረጉት የዲፕሎማቲክ ጥረት ውጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ ሚኒስትሮች የጦር አለቆችና መኳንንት የሚገኙበት ጉባዔ እንዲጠራ አደረጉ።

እያንዳንዱ ሰው ስለተነሳው ችግር ያለውን አስተያየት ሀገር ፍቅር በተሞላበት አንደበትና የጋለ መንፈስ ሲገለፅ ቆየ። እቴጌ ጣይቱም በበኩላቸው «እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያድርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ» ብለው በታሪክ ቅርስነቱ በማንኛውም የሀገሪቱ ትውልድ ትተውት ያለፉት አባባል ዘመን ተለውጦ ዘመን እየተተካ በሄደ ቁጥር የሚነገር በመሆኑ የእቴጌን ጀግንነት የቁርጠኛ ኢትዮጵያዊ ልጅ ለመሆናቸው ሌላ ማረጋገጫ ማቅረብ አያስፈልግም። እቴጌ ጣይቱ ወንድማቸው ራስ ወሌን አተኩረው በማየት በታወቀው ጀግና አንደበታቸው የተሰበሰበውን ሕዝብ ስሜት ለመቀስቀስ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ማድረጋቸው ይነገራል። እሳቸውም፦ «መልኩ ከመልካችን የማይመሳሰል እግዚአብሔር በባህር ከልሎ የሰጠንን አገራችንን የሚቀማ ጠላት መጥቶ እንዴት ዝም እንላለን እንዋጋለን እንጂ» በማለት የሀገሪቱን ቁንጅና ልምላሜ የምታፈራውን የእህልና የከብት ዓይነት እየጠቃቀሱ በማንሳት «ኧረ ለመሆኑ ተራራው ሸለቆው ወንዛወዙ ጨፌው ሜዳው ማነው ቢሉት የማነው ብሎ ሊመልስ ነው እንገጥመዋለን እንጂ!» በማለት የተሰበሰበውን ሕዝብ ልብ የሚነካና ወኔውን የሚቀሰቅስ ንግግር በማድረግ የተዋጣ የቅስቀሳ ችሎታቸው በአገኙት መድረክና አጋጣሚ የሚጠቀሙ አንደበተ ርቱዕ ነበሩ።

ስለ እቴጌ ጣይቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በምሳሌነት ሊቀርብ የሚችል ሌላ ዓይነተኛ ታሪክ ዓፄ ዮሐንስ በሞቱ በአንድ ዓመታቸው በመጋቢት ፲፰፻፹፪ ዓ/ም ዓፄ ምኒልክ አገሩን ለማረጋጋት ሲሉ መሃል ትግሬን ለመጐብኘት በሄዱ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ ለሸዋም፣ ለወሎም፣ ለበጌምድርም፣ ለየጁም መካከል በሆነችው ደሴ ከተማ ሆነው አገሩን እንዲጠብቁ በማለት ትተዋቸው እንደሄዱ እዚያ ሆነው ያከናወኑት ተግባር የረጋ አስተዋይና የተዋጣላቸው ዲፕሎማት አሰኝቷቸዋል። በተለይም በሁለት የጦር አበጋዞች መሃል የሚፈጠር አለመግባባትን አግባብቶ በመፍታት በኩል ተወዳዳሪ አልነበራቸውም።

እቴጌ ጣይቱ ከሕዝቡ ጋር በነበራቸው ግንኙነት በተለይም ያሳዩት በነበረው ርህራሄና ልግስና በጣም የተወደዱና የተመሰገኑ በመሆናቸው በሚያውቋቸው ዘንድ በሰፊው ይወራላቸዋል። ግልፅ የሆነው የፖለቲካ አስተያየታቸውና ጽኑ የሆነው ተግባራዊ ውሳኔያቸው፣ ዘዴንና ሥልጣንን እንዲሁም ምክርን ኃይልን ምን ጊዜ በእንዴት ያለ መጠን መጠቀም እንዳለባቸው በትክክል የመገመት ችሎታቸው ሲታይ በዓለም ከታወቁት የፖለቲካ አርበኞች ውስጥ ሊወሳ የሚገባ ታሪካዊ ስፍራ እንዳላቸው አጠራጣሪ አይሆንም። ስመ ጥሩነታቸውን ለማትረፍ ካስቻላቸው ጉዳዮች ጽኑ በሆነ መንፈሳዊ ኑሮአቸው አኳያ የሚታየው የልግስናና የቤተ ክርስቲያን ነፃ ተግባሮች አንዱና ዓይነተኛው ነው። ይህ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ልዩ ግንኙነት ለመመስረት ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ የፖለቲካ ሥልጣናቸውን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ከሌሎች ታላላቅ የፖለቲካ ሰዎች ታሪካዊ አነሳስ ለመገንዘብ ይቻላል።

በዚህ በኩልም እቴጌ ጣይቱ ብጡል በማህበራዊ ህይወት ሲያደርጉ የነበሩት በጐ ተግባር በመንፈሳዊ ኑሮአቸው በእምነቱ ተከታዮች ያላቸው ተቀባይነትም እጅግ የጐላ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለየካ ቅዱስ ሚካኤል ሠላሳ ጋሻ መሬት፣ ለሐመረ ኖህ ኪዳነ ምሕረት አሥራ ስድስት ጋሻ መሬት የሰጡት ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ናቸው።

እቴጌ ጣይቱ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች መረጋጋት የሚያረጋግጥ የሀገር ግንባታ ተግባሮች በማከናወን ረገድና የአዲስ አበባ ከተማ መቆርቆር በእቴጌ ጣይቱ ከተጠናቀቁት የግንባታ ተግባሮች አንዱ ነው። በመሆኑም የአዲስ አበባ ስም በተጠራ ጊዜ እቴጌ ትዝ የሚሉን ሲሆን በዚሁ በአዲስ አበባ በከፍተኛ ቀበሌ ፲፪/ፒያሳ/ አካባቢ የሚገኘው የከተማዋ የመጀመሪያው ሆቴል «ጣይቱ ሆቴል» የቅርብ ትዝታችን ነው። ምንም እንኳን እቴጌ ጣይቱ የተቀረፀላቸው ሐውልትና ለትውልድ የሚተላለፍ ስማቸውን የሚያስጠራ ልጅ ባለመውለዳቸው /መሐን/ ቢሆኑም የዓፄ ምኒልክን ልጆች አክብሮታዊ ፍቅር ሳይለያቸው ቤተሰባዊ ፍቅርን የተላበሱ እንደነበረ ከተለያዩ መፃህፍት ለመረዳት ይቻላል።

የሕይወት ጓዳቸው የሕይወት ፍጻሜ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
ጣይቱ ብጡል

እቴጌ ጣይቱ ባለቤታቸው ዓፄ ምኒልክ በጽኑ በታመሙበት ዘመን ከጭንቀታቸው የተነሣ የሚከተለውን ረጅም ደብዳቤ ለጀርመን ንጉሥ እንደላኩ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በ፳፻፪ ዓ/ም "አስደናቂዎቹ የነገሥታትና የመሳፍንት ደብዳቤዎች" በሚል ርዕስ በታተመው መጽሐፍ ውስጥ የእቴጌ ጣይቱ ደብዳቤ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

"ይድረስ ከክቡር ወዳጃችን ከዳግማዊ ዊልሄልምጀርመን ንጉሠ ነገሥት፡፡ የተላከ ከእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ፡፡

ሰላምና ጤና ለእርስዎ ይሁን፡፡

በብዙ ማክበርና በትሕትና ይህንን ደብዳቤ ልጽፍልዎ አሰብሁ፣ ስለዚህ ይህንን የደረሰብኝን የሚያሳዝን ነገር ደፍሬ ልጽፍልዎ የግድ ሆነብኝ ልታገሰው አልተቻለኝምና፡፡ ስለ አጤ ምኒልክ ጤና መጉደል፤ ጌታዬን፣ ወዳጄን አጣቸው ይሆን ብዬ አጥብቄ ተጨንቄአለሁ፡፡ ለሴቶች ካባት ከናት ከልጅ ከወንድምም የጮኛ ነገር ጭንቅ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡

ስለዚህ የጀርመን መንግሥት ሐኪም የጥብቅ ረቂቅ ብልሃት ስመ ጥሩነቱ አስከኔ ደርሶ ንጉሠ ነገሥቱ ተፈውሰው እንደቀድሟቸው ሆነው ለማየት የተቃጠለ ምኞቴ እንዲፈጸምልኝና በብርቱ አጥብቆ ለሚወዳቸውም ሕዝባችን ንጉሡ በሕይወት እንዲቆዩለት ለመፈወስ የሚያስፈልግ ነገር ሳይደረግላቸው እንዳይቀር ብለን የጀርመንን ስመጥሩ የጥበብ ረቂቅ ብልኃት እረዳትነት ለመንን፡፡ ንጉሡ በቸርነትዎ ሐኪሙንም ምክር የሚረዳንንም ይስደዱልን ያልነውን ዶክቶር ዲንትግራፍን ጨምረው ሰደዱልን፡፡ እነሱም በመምጣታቸው እኛንም ሠራዊታችንንም እጅግ ደስ አለን፡፡ ነገር ግን እንደተመኘነው ሳይሆንልን ቀረ፡፡

አለመሆኑንም ለማስረዳት ከዚህ ቀጥሎ በሚጻፈው ቃል አስታውቃለሁ፡፡ ሐኪሙ ዶክቶር ስትይሂክለር በሚያዝያ ፳፪ ቀን ገቡ፡፡ ከዚያም አንስቶ እስከ ግንቦት ፲፭ቀን ጧት ማታ እየተመላለሱ፣ ለንጉሥ መድኃኒቱን ሲያደርጉ ሰነበቱ፡፡ በግንቦት ፲፭ቀን ግን በንጉሠ ነገሥቱ ደም የመርዝ ፍለጋ አገኘሁ ይጠንቀቁ ብለው ለኔ ነገሩኝ፡፡ እኔም ባጤ ምኒልክ መርዝ ማን ያደርግባቸዋል፡፡ ይህ ነገር አይጠረጠርም አልሁ፡፡ ሐኪሙም ከወጥ ቤት ዕቃም ከምንም ከምን እድፍ መጠንቀቅ ነው አሉ፡፡

የከበሩም እጮኛዬ ሕመምዎ ከጀመረዎ ቀን አንስቶ እስካሁን ድረስ የዛሬው ሰዓት በኔ ዘንድ የተወደዱ ስለሆኑብኝ፣ ያለዕረፍት በብርቱ ትጋትና ጥንቃቄ ከብቤ ጌታዬን የማስታምምዎ እኔው ራሴ ነኝና፣ የሐኪሙን ትእዛዝ ሁሉ መፈጸሙን ተደላድዬ ማስረዳት የሚቻለኝ ስለሆነ ይህንንስ እሺ የሚሰናዳውም ምግብ ሁሉ ከኔ ቤት ነው አልሁ፡፡

ከዚያም ወዲህ ዳግመኛ መርዝ አገኘሁ ብለው አልነገሩንም፡፡ እንደፊተኛው መድኃኒቱን ሲያደርጉ ቆዩ፡፡ ዶክቶር ዲንትግራፍም እሳቸው ያሉትን ሁሉ አድርገን ለሳቸው የሚመቻቸውን ማለፊያ የተሰናዳ ቤት ሰጥተን አክብረን አስመችተን አኑረናቸው ነበር፡፡

በሐምሌ በ፱ ቀን ግን ዶክቶር ዲንግራፍም ሐኪሙን ይዘው መጥተው የኛ መኳንንቶችና ሠራዊት ከተሰበሰበበት ላይ በንጉሡ ክፉ ነገር ተደርጎባቸዋልና በብርቱ የታመኑትን አገልጋዮቻችንን፣ እጃቸውን ተይዘው ይመርመሩ፡፡ ይህ ካልሆነ ሐኪሙ ገብተው መድኃኒት አያደርጉም ብለው ከለከሉ፡፡

በበነጋውም ዶክቶር ዲንትግራፍ ከንጉሥ ልገናኝ ብለው ላኩ፡፡ እኛም እሺ ብለን ፪ታችንም ፩ ላይ ሁነን ጠራናቸው፡፡ እሳቸውም እነዚህ ሰዎች እጃቸው ተይዘው ይመርመሩ አሉ፡፡ የታመኑ አሽከሮቻችን ናቸው፡፡ አይጠረጠሩም፡፡ እጃቸው ተይዘው የሚመረመሩት ምንድነው ብንላቸው ተይዘው ካልተመረመሩ ሐኪሙ አይገቡም አሉ፡፡

ደግሞ በበነጋው ምንስቲሩን ሙሴ ሽለርን ጠርተን እነዚህ ፪ቱ ሹሞቻችንን ይያዙ ያሉበት ምንድነው ነገሩ ብለን ብንጠይቃቸው በንጉሡ ምግብ ውስጥ መርዝ ተገኝቷል፡፡ በመብልና በመጠጥ ውስጥ ሆኖ ንጉሡን አልጎዳቸውም እንጂ ሐኪሙ አግኝተዋል፡፡ ብለው ነገሩን፡፡

እኔም ለምንስቲሩ ንጉሥ የሚመገቡት ሁሉ የሚሰናዳ ከኔ ቤት ነው የኔ ሹሞች ናቸው የሚያሰናዱ፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን በኔ ቤት በምንም በምን አይደርሱም ብዬ አስታወቅሁ፡፡

ንጉሡም እነዚህ ሰዎች በዚህ ነገር አይጠረጠሩም ሥራቸው አይደለም ብለው ተናገሩ፡፡

ሕዝቡም አጤ ምኒልክ እንደነፍሱ እንዲያውም ከነፍሱ አልቆ እንዲያፈቅረዎ ንጉሡም በሕዝቡ አክብሮትና አፍቅሮት መከበብዎን ተደላድዬ አውቃለሁና ይህኑን ሥራ በሕይወታቸው ላይ ሊሠራባቸው ማንም የሚችል ሰው የለም፡፡ ሚኒስትሩ ግን ምንም ቢሆን እነዚህ ሰዎች ካልወጡ አይሆንም ንጉሥን የሚጠብቅ ሐኪሙ ሌላ ሰው መርጠው ያግቡ አሉ፡፡ ሐኪሙም እንደዚሁ እነዚህ ሰዎች ካልወጡ አልገባም ብለው ቀሩ፡፡ እኔም በዚህ ነገር እኔን የሚጠብቅ ሌላ ሹም መቀበሉ ታላቅ ሸክም ሆነብኝ፡፡ በገዛ ሰውነቴ ላይ መርዝ በማድረግ መጠርጠር አይቻልምና፡፡ ደግሞ የዚያኑለት ማታ ዶክተር ዲንትግራፍ እነዚህ ሰዎች ካልተሻሩና ካልወጡ እኔ አልቀመጥም ብለው የሰጠናቸውን ቤት ለቀው ሄዱ፡፡ እዚያም ከሄዱ በኋላ እነዚህ ሰዎች ካልወጡ፣ እኔን አሰናብቱኝ ብለው ወደ ንጉሡ ወረቀት ጻፉ፡፡ ንጉሥም አንተም ልሰናበት ያልክበት፣ እነዚህስ ሰዎች የሚወጡበት ብልሃቱ ካልተገለጠ እንዴት ይሆናል አንተው ይመርመሩ ባልክበት ነገር በ፳ ሐምሌ ማክሰኞ እንድትመጡ ብለው ላኩባቸው፡፡

በዚያው ለነሱ ባስታወቅንበት ቀን አባታችን አቡነ ማቴዎስም በከተማም ያሉት ሐኪሞች የኛም መኳንንቶች ሁሉ ተሰብስበው ከ፬ እስከ ፯ ሰዓት ሲጠብቁ ውለው እነሱ ሳይመጡ ቀሩ፡፡

የተሰበሰበውም ሰው በየቤቱ ገባ፡፡ ዶክተር ዲንትግራፍም ዳኛውስ ማነው ስፍራውስ ወዴት ነው ብሎ ሳይመጡ ቀሩ፡፡

ሐኪሙም እነዚህ ሰዎች ፈጽመው ካልተከለከሉ እኔ አልገባም ደግሞም ስገባ እኔ የምወደውን አስተርጓሚ ይዤ ነው የምገባ ውሌ ይህ ነው ብሎ ወረቀት ጻፉ፡፡ በዚህ ምክንያት ወደፊትም እንዲያስታምሙልን እርዳታቸውን ለመፈለግ የማይመቸን የማይመስለን ሆነብን፡፡

ደግሞ ፫ተኛ እነዚህ ሰዎች ከዚህ ተከልክለው ወደሌላ አገር ካልሄዱ እኔ አልኖርምና አሰናብቱኝ ብለው በራስ ቢቶደድ ተሰማ እጅ ወረቀት ላኩ፡፡

ንጉሥም እኔም በነዚህ በሰዎች በሹመት ነገር ሌላ የተመቀኛቸው ሰው ተነስቶ አስወጡልን ያላቸው ሰው ይኖር ይሆን እነዚያማ ከመጡ ጥቂት ነው አገሩን አያውቁት ሰውን አለመዱት ከነሱም ጋር ጠብ የላቸውም ይህ ነገር ምን ይሆን ብለን ገረመን፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ካልሆነ አሰናብቱኝ ብለው ፫ጊዜ ወረቀት ላኩ፡፡

ከዚህማ ወዲያ አላሰናብትም አሉኝ ብለው ወደ መንግሥታቸው የላኩት እንደሆነ የከበሩ ንጉሠ ነገሥት ወዳጄ ይቀየሙኛል ብለው ለዶክተር ዲንትግራፍ ይመርምሩ ብትሉ እሺ ብለን ቀን ቆርጠን ብናስታውቃችሁ ሳትመጡ ቀራችሁ፡፡

እኔ የማምናቸውን ያሳደግኋቸውን የሾምኋቸውን ሹማምንቶቼን ከዚህ ወጥተው ወደ ሌላ አገር ካልሄዱ ከነሱ ጋራ ለመኖር አይሆንልኝም ብለህ መሰናበትህን ከወደድህ እሺ አሰናብቼሃለሁ ብለው ጻፉለት፡፡

በዚህ በኛ ዘንድ ያሉን ምንስቲሩ ሙሴ ሽለር ግን መልካም ሰው ናቸው ዳሩ ግን ነገሩን መርምረው ለኛ ባለማስታወቃቸው አዘንን፡፡

ስለሆነም የተመኘነውን ፈቃዳችንን ለመፈጸም ብለው በታላቅ ቸርነትዎ ላደረጉልን በጎ አድራጐት እኔው እራሴ በፍጹም ልቤ ግርማዊ ሰውነትዎን አመሰግናለሁ፡፡ ይህንን ሁሉ ነገር መጻፋችን እነሱን ለማዋረድ ብለን አይደለም። የንጉሡ ልቡና እንዳይቀየምብን ብለን ነው እንጂ፡፡ ዳሩ ግን አንድነት የማያዋህደንን ታላቁን ፍቅራችንን ለማሰናከል ይህ ትንሽ ነገር ምክንያት ይሆናል ተብሎ አለመጠርጠሩ ግልጥ ነገር ነው፡፡

የንጉሡ ፈቃድዎ ቢሆን ከዚህ በኋላ ሁሉንም ነገር ለሚጠይቋቸው ምላሽ የሚናገሩ ከኛ ዘንድ መልዕክተኞች ለመስደድ እንመኛለን፡፡

ነገሩ ብዙ ስለሆነ በወረቀት አይጠቀለልምና ፊት ከሙሴ ሮዝ ጋራ መጥተው የነበሩት ሐኪም ሀንስ ቮልብረሽት ለኔም መድኃኒት አድርገውልኝ አድነውኝ ነበርና ዛሬም ለጥቂት ቀን እንዲመጡልን እንመኛለን፡፡ የከበሩ ንጉሠ ነገሥትም በቸርነትዎ ይሰዱልናል በማለት ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ለእሰዎ እድሜና ጤና ለሕዝብዎም ሰላምና ዕረፍት እንዲሰጥልን እግዚአብሔርን እንለምናለን፡፡ ነሐሴ ፲፩ ቀን ፲፱፻፩ ዓመተ ምሕረት አዲስ አበባ ተጻፈ፡፡[3]

ደብዳቤው ማኀተም አለው፡፡ ማኀተሙ በግዕዝ እንደተቀረጸው ዝማኅተም ዘእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ ይላል፡፡

የሥልጣን ፍጻሜ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
እቴጌ ጣይቱ ከደንገ ጡራቸውና የእንጀራ ልጅ ልጃቸው ጋር

ባላቸው ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ከሞቱ በኋላ በልጅ እያሱና በደጃዝማች ተፈሪ መኮንን መካከል በተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ አማካኝነትና ባስከተለው በጦሩ መሃልም መከፋፈል በመታየቱ በልጅ ኢያሱ አስተዳደር ዘመንም እቴጌይቱ ከቤተ መንግሥት ተወግደው በግዞት ላይ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ከሃያ ሁለት ቀናት ተቀመጡ። ሆኖም ታማኝ አሽከሮቻቸውና መላው ሠራዊት የእቴጌነታቸውን ልዕልና አላጐደለባቸውም። መሳፍንቱ መኳንንቱና ወይዛዝርቱም ቢሆን ተገቢውን አክብሮት ሳይነፍጓቸው ዕለት በዕለት ይጠይቋቸው ነበር። አቤቶ ኢያሱም ቢሆኑ የተለያዩ ስጦታዎችን ይዘው በመሄድ ይጠይቋቸው ነበር። የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀበተ ጊዮርጊስ ዲነግዴም የተለያዩ እጅ መንሻ ይዘው ይጠይቋቸው ነበር።

ልጅ እያሱ ሥልጣን ብዙም ሳይቆይ ከላይ በተገለጸው ‘የሥልጣን ክርክር’ ተሸንፈው መስከረም ፲፯ ቀን ፲፱፻፱ ዓ/ም የሚኒስትሮች ካቢኔ ወይዘሮ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው መንግሥቱን በመምራት እንዲተኳቸው መደረጉ ለእቴጌ ጣይቱ ታላቅ ድል ሆነ። በመሆኑም የእቴጌም የእስራት ቀንበር ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ሊወድቅላቸው ቻለ። ንግስት ዘውዲቱ ሥልጣናቸው ተዳክሞ ትዕዛዛቸው እንዳይዛባ በማለት ከተጋዙበት ከእንጦጦ ሳይቀር ምክር መለገሳቸውን አላቋረጡም ነበር።

እቴጌ ጣይቱ የደረሰባቸውን ፈተና ሁሉ በትዕግስት ተቀብለው ጥቂት እፎይ ካሉ በኋላ ከዓፄ ምኒልክ ጐን ሆነው የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ ለማረጋገጥ ሲታገሉ ያለፉት ዘመን ከዕለታት አንድ ቀን ትዝ ስላላቸው ከሰገነት ላይ ብቅ ብለው «ያ ቤት የትኛው ነው» ብለው ሲጠይቁ ከደንገጡሮቹ አንዷ «የእመቤቴ እልፍኝ ግምጃ ቤት ነበር» አለች። እሳቸውም ትንሽ ተከዝ ብለው ከቆዩ በኋላ ቀበል በማድረግ «ነበር ለካስ እንዲህ ቅርብ ኖሯል» አሉ ይባላል።

እቴጌ ጣይቱ ሰኞ የካቲት ፬ ቀን ፲፱፻፲ ዓ/ም በመንፈቀ ሌሊት ህመም ፀንቶባቸው ከሚወዱትና ከሚወዳቸው ሕዝብ በሞት ተለዩ። የእረፍታቸውን ዜና የሀዘኑንም ሥነ ስርዓት ለማወጅ የቤተ መንግሥቱ መድፍ ሃያ አምስት ጊዜ ድምፁን አሰማ። በሀዘኑ ስርዓትም ላይ እቴጌ በአድዋ ጦር ሜዳ ላይ ያሳዩትን የቆራጥነትና የጀግንነት ሙያቸውን እየጠቀሱ በግጥም እየገለጡ በማሞገስ ይሸልሉ ይፎክሩና ያቅራሩ ነበር። የእቴጌም አስክሬን በወርቅ ሀረግ በተከበበ የእንጨት ሳጥን ተደርጐ በብረት ሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ በቀድሞ ቤተ ፀሎታቸው ውስጥ ሸራ ቤት እየተባለ ይጠራ በነበረው መንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም ቤት ውስጥ በታላቅ ክብር አረፉ። ለተሰበሰበው ሕዝብ ትልቅ ግብዣ ተደርጐ የቀብሩ ፍፃሜ ሆነ።

እቴጌ ጣይቱ ከማረፋቸው አስቀድመው ለንግሥት ዘውዲቱ «ልጄ ማሚቴ ሆይ አደራዬን ሰጥቼሻለሁ» ብለው መናዘዛቸው በታሪክ ይወሳል። በዚሁ መሠረት ንግሥት ዘውዲቱ በታሕሣሥ ወር ፲፱፻፳ ዓ/ም የዓፄ ምኒልክን ዓፅም ከቤተ መንግስቱ አስወጥተው ለማረፊያው በታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን አሳንፀው በነበረ ጊዜ የእቴጌንም ዓጽም እዚሁ እንዲያርፍ ቢፈልጉም የእንጦጦ ማርያም ካህናት እቴጌ ጣይቱ ለኛም እናታችን ናቸውና መታሰቢያነታቸውን እንሻለን በማለት የተቃውሞ ድምፅ አሰሙ። ቢሆንም የኑዛዜውን ቃል አብራርተው በማስረዳታቸው ፈቅደውላቸዋል። በመጨረሻም የእቴጌ ጣይቱ፣ የዓፄ ምኒልክና የንግሥት ዘውዲቱ መካነ መቃብር በታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን ምድር ቤት ውስጥ በመንበሩ ትይዩ ሳጥኖች ተፈልፍለው በተሰሩ እብነ በረድ ታሽገው እንደቆዩ በወለሉ ላይ መደዳውን ተቀምጠው ይገኛሉ።

እቴጌ ጣይቱ በሞት የተለዩዋቸውን የሕይወት ጓደኛቸውን ጥለው በግዞት እንዲቆዩ በተገደዱበት በእንጦጦ አፋፍ ላይ ሆነው አዲስ አበባ ብለው የሠየሟትን መዲና በዓይን በመቃኘት «ያ ቤት የትኛው ነው» ብለው የጠየቁት የምኒልክን መቃብር በዓይናቸው ሲፈልጉ ይሆን? የሰው ሕይወት ኃላፊ ነው፣ ታሪክ ግን ሠሪዋን ለዘላለም ታስታውሳለች። በዚያች ደቂቃ እቴጌ ጣይቱ ስማቸውን የሚያስጠራ ታሪካቸውን የሚያስታውስ አንድ የምኒልክ የደም ቋጠሮ ሀረግ ሳያሠሩ ማለፋቸው ሳያሳዝናቸው እንዳልቀረ መገመቱ ቀላል ነው። ይህንም ሀዘን ለግዞት ወደ እንጦጦ ከመውጣታቸው ጥቂት ጊዜ በፊት ሊሸኟቸው በተሰበሰቡት መኳንንትና ወይዛዝርት ፊት የገጠሙት ግጥም አንጀት የሚበላ ነበር።

«ተወዶ ከመኖር ተጠልቶ መውለድ ማን ያይብኝ ነበር ይህን ሁሉ ጉድ» ብለው ባሰሙት ግጥም ነበር።

  1. ^ ጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ ፣ ገጽ 75
  2. ^ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ(፲፱፻፩ ዓ/ም)
  3. ^ ጳውሎስ ኞኞ (፲፱፻፹፬ ዓ/ም)
  • ጳውሎስ ኞኞ፣ «አጤ ምኒልክ» (፲፱፻፹፬ ዓ/ም)፣ ገጽ ፬፻፹፫-፬፻፹፰
  • አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፣ «ዳግማዊ አጤ ምኒልክ»፣ (1901 ዓ/ም) ሮማ፣
  • ሪፖርተር፣ “እቴጌ ጣይቱን በዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ስናስታውሳቸው”
  • ጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ፣ «የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ» አንደኛ መጽሐፍ፣ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም.