Jump to content

ፋሲል ግቢ

ከውክፔዲያ
የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስ
ፋሲል ግቢ

ፋሲል ግቢ
ፊት ለፊት ፋሲል ግምብ፣ በግራ ቀዳማዊ ዮሐንስ ጽሕፈት ቤት
አገር ኢትዮጵያ
ዓይነት ባሕላዊ
መመዘኛ c(ii)(iii)
የውጭ ማጣቀሻ 19
አካባቢ** አፍሪካ
የቅርስነት ታሪክ
ቅርስ የሆነበት ጊዜ 1971  (3ኛ ጉባኤ)
ፋሲል ግቢ is located in ኢትዮጵያ
{{{alt}}}
ፋሲል ግቢ
ፋሲል ግቢ በኢትዮጵያ ካርታ
* በዩ.ኔ.ስ.ኮ ስሙ እንደሰፈረ።
** የዩ.ኔ.ስ.ኮ. ክልል ክፍፍል


ፋሲል ግቢ ወይንም ነገሥታት ግቢጎንደር ከተማ የሚገኝ የቤተመንግስታት ግምቦች ስብስብ ነው። ግቢው የተመሰረተው በ1628ዓ.ም. በዓፄ ፋሲለደስ ነበር። ማቀባበያ የሚሰኘው የግቢው አጥር 900ሜትር ርዝመት[1] ሲኖረው በውስጡ 70፣000 ስኩየር ሜትር የመሬት ይዞታ ያካልላል። አጼ ፋሲለደስ የመጀመሪያውንና ታላቁን ግንብ ያሰሩ እንጂ፣ ከርሳቸው በኋላ የተነሱት ነገሥታትም ለ220 ዓመታት የየራሳቸውን ህንጻ በመስራት ቦታው በቅርስ እንዲዳብር አድርገዋል። በግቢው የመጨረሻውን ህንጻ ያሰራችው ንግሥት ብርሃን ሞገስ ነበርች።

ግቢው ገናና በነበረበት ዘመን በሽወች የሚቆጠሩ ቤቶችና ሱቆችን በውስጡ ያቅፍ ነበር። በጥንቱ ዘመን የአስተዳደር ስርዓት ተቀርጾለት በጥንቃቄ የሚመራ ነበር። ስርዓቱም ስርዓተ መንግስት በመባል ሲታወቅ በመጽሃፍ መልኩ በግዕዝና በድሮው አማርኛ የተመዘገበ ነበር።

የሚከተለው ካርታ ላይ ማውስወን ቢያንሳፍፉ፣ እያንዳንዱ የግቢው ህንጻና በሮች ስም ወጥቶ ይታየወታል፡፡ ሲጫኑም ወደዚያ ክፍል ማብራሪያ ይወስደወታል።[2]

አደባባይ
ሰሜን ->



ፋሲል ግቢ በኢትዮጵያን እይታ፣ በ1622 እና 1722 መካከል
ትንሹ የፋሲል ግምብ

የግቢው ይዘት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ፋሲል ግቢ፣ የውሃ እጥረት እንዳይገጥመው በማሰብ በአንገርብ እና ቃሃ በተሰኙ ሁለት ምንጮች መካከል ነበር የተመሰረተው። ከግቢው በስተደቡብ የጎንደር አደባባይ ሲገኝ፣ ቦታው ለገበያነት፣ ለአዋጅ መንገሪያነት እና ለወንጀለኛ መቅጫነት ያገለግል ነበር [3] ። በአሁኑ ወቅት የጎንደር ከተማ መናፈሻ በመሆነ ያገልግላል። ማቀባበያ የሚሰኘው የግቢው አጥር ግምብ በዙሪያው 12 በሮች ሲኖሩት፣ እኒህ በሮች ግልጋሎታቸውን የሚወክሉ ስያሜ ነበሯቸው። አንዳንዶቹ በሮች ከውጨኛው አለም ጋር ይገናኙ የነበሩት በትላልቅ ድልድዮች ነበር። ምንም እንኳ አብዛኞቹ የግቢው ቤቶች በጦርነትና እሳት ቢወድሙም ዋና ዋናዎቹ ህንጻዎች ግን እስከ አሁኑ ዘመን ዘልቀው ይታያሉ። ከነዚህ ጉልህ ህንጻዎች መካከል የፋሲለደስ ግምብትንሹ የፋሲል ግምብ፣ የታላቁ እያሱ ግምብ፣ የዳዊት ፫ ዙፋን ቤትምንትዋብ ግምብ፣ የየምንትዋብ ቱርክ መዋኛ፣ የፈረሶች ቤት፣ የፈረሰኞች አለቃ ቤትአንበሶች ቤት፣ የበካፋ ግምብ፣ የበካፋ ሰገነት፣ የቀዳማዊ ዮሐንስ ጽሕፈት ቤትዮሐንስ ቤተ መጻሕፍትአዋጅ መንገሪያን፣ ክረምት ቤትቋል ቤት(የሰርግ ቤት) እና ግምጃ ቤት ማርያምአጣጣሚ ሚካኤል የሚሰኙ አብያተ ክርስቲያናት የግኙበታል። በተጨማሪ ከፋሲል ግቢ ወጣ ብሎ በስተሰሜን ራስ ግምብ ይገኛል።

ትንሹ የፋሲል ግምብ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋና መጣጥፍ፦ ትንሹ የፋሲል ግምብ

ትንሹ የፋሲል ግምብ ሌሎች ህንጻዎች ከመገንባታቸው በፊት ለሙከራ ያክል የተገነባ የፋሲል ግቢ የመጀመሪያው አንስተኛ ህንጻ ነው። ዋናው የፋሲል ግምብ እስኪገነባ ድረስ ዓፄ ፋሲለደስ ተቀምጠዉበት የነበር ህንጻ ነው።

ማቀባበያ ድልድይ ስር ሰዎች ሲዘዋወሩ
ፋሲል ግምብ

የፋሲል ግቢን ዙሪያ ጥምጥም የያዘው የግምብ አጥር ማቀባበያ በመባል ይታወቃል። ስሙ ከጥንት ጀምሮ የነበር ሲሆን በዓፄ በዕደማርያም ዜና መዋዕልም መቀባበያ የሚባል ህንጻ ተጠቅሶ ይገኛል[4]። ትርጎሜውም መዘጋጃ፣ ወይም መከላከያ ምሽግ መሆኑ ነው። በዚህ የግምብ አጥር ዙሪያ 12 በሮችና ከፍ ብለው የተሰሩ መተላለፊያ ድልድዮች ይገኛሉ።

የፋሲል ግቢ እንደሐዋርያት ብዛት 12 በሮች አሉት፣ 12ቱም እንደየተግባራቸው ስም ወጥቶላቸው ያገልግሉ ነበር። ልዕልት እንኳየ በር፣ በንግሥት ብርሃን ሞገስ እናት ስም የተሰየመ ነበር። ግምጃ ማርያም በር ወደ ግምጃ ቤት ማርያም ቤተክርስቲያን ግቢ የሚያሻግር ሲሆን ጃን ተከል በር(ፊት በር) የሚባለው ዋናው በር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የጎብኚዎች መግቢያ ነው፡፡ ከአደባባይ ፊት ለፊት ይገኛል። ወምበር በር (የዳኞች በር) የፍርድ መስጫ በር ሆኖ ዳኞች የሚገቡበትም ነው ፣ ተዝካር በር በድሮ ጊዜ ድልድይ የነበረው፣ ሆኖም ግን በዳግማዊ ኢያሱ ጊዜ በተነሳ ጦርነት የፈረሰበት በር ነው።የቀብርና የሙታን ሥርዓት ለማስፈጸም የሚገባበት ነው። አዛዥ ጥቁር በር በድሮ ጊዜ ከአደባባይ ተክለ ሃይማኖት ጋር በድልድይ ይገናኝ ነበር፡፡ አደናግር በር እንዲሁ በድሮ ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ተብሎ ከሚታወቀው የሸማኔዎች ሰፈር ቤተክርስቲያን ጋር በድልድይ ይገናኝ ነበር።የፈትል ባለሙያዎች የሚገቡበት ነበር። ቋሊ በርእልፍኝ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዘመናዊ መግቢያ አጠገብ የሚገኝ ሲሆን ስሙ የወጣው የንግሥት ደንገጡሮች በር መሆኑን ለመግለጽ ነበር። እምቢልታ በር የአዝማሪዎች በር ሲሆን እልፍኝ በር ወደ የግቢው የግል ህንጻዎች የሚወስድ ነበር። ባልደራስ በር እሚያመለክተው የፈረሰኞች አለቃ በር መሆኑን ሲሆን፣ ራስ በር በሌላ ስሙ ቋረኞች በር ተብሎ ይታወቅ ነበር። እርግብ በር ደግሞ ቀጭን አሸዋ በር በመባል በሁለተኛ ስም ይታወቅ ነበር– ለነገሥታት እጅ መንሻ የሚገባበት በር ነው።[5]

ዋና መጣጥፍ፦ ፋሲል ግምብ

ፋሲል ግምብ ፋሲል ግቢ ውስጥ ካሉት ግምቦች ትልቁና የመጀመሪያው ዋና ህንጻ ነው። ቤተመንግሥቱ 32 ሜትር ቁመት እና 25 ሜትር በ25 ሜትር የሆነ የጎንና ጎን ርዝመት አለው። ባለ ሦስት ፎቅ ሕንፃ ሲሆን 123 ደረጃዎች አሉት።አጼ ፋሲለደስ የአገሪቱ መዲናን ከቦታ ቦታ መዛወር በመሰልቸት በመጨረሻ ጎንደር ከተማ ላይ የረጋ ማዕከል በ1628ዓ.ም. አቋቋሙ። በ1640ወቹ መጀመሪያ ፋሲል ግምብን በከተማው ማዕከል አሰርተው አስጨረሱ። ከጣሪያው ላይ ባለው መመልከቻ በረንዳ እስከ ጣና ሐይቅ ድረስ መመልከት ይቻላል። በውስጡ 20 ክፍሎች አሉት። ግድግዳው ላይ የተሰሩ ብዙ ጌጦች የነበሩት ሲሆን እንደ ጣሊያናዊው አመዶ የ1930 ጥናት የማግኔት ኮምፓስ ወደ ግድግዳዊ ሲጠጋ ኮምፓሱ በሃይል ዘውሮ ወደ 80 ዲግሪ እንደሚጠጋ ይጠቃሳል። ከዚህ ተነስቶ ግድግዳው ከማግኔታይት ባዛልት እንደተሰራ ይዘግባል (ገጽ 26)። የየመኑ አምባሳደር ሃሰን ኢብን አል-ሃያሚ ይህን ግምብ በ1640ዓ.ም. ተመልክቶ «ድንቅ ህንጻ፣ ውብ የሆነ የድንጋይና ኖራ ውጤት» በማለት እንደሚገልጸው ታሪክ አጥኝው ስቱዋርት ሞንሮ-ሄይ ዘግቦት ይገኛል።

ከቤተ መንግሥቱ ጫፍ ላይ የንጉሡ- የአፄ ፋሲል የቅኝት ማማ ይገኛል። በሦስተኛው ፎቅ ላይ የንጉሡ መኝታ ክፍል አለ። በሁለተኛው ፎቅ ላይ ደግሞ ፊት ለፊት የአክሊል ቅርጽ ያለው በረንዳ ይገኛል። ይህ በረንዳ የንጉሡ አዋጅ መንገሪያ፤ ሕግና ትእዛዛት ማሳወቂያ ነው። አንደኛው ፎቅ በረንዳ ላይ እንደየማዕረጋቸው የሚቀመጡ ሹማምንትና አፈ- ቀላጤዎች ከንጉሡ አንደበት ተቀብለው በተዋረድ አዋጁን ያሰማሉ። እንዲህ እያለም- ነጋሪት እየተጎሰመ፣ እምቢልታ እየተነፋ፣ ከበሮ እየተደለቀ አዋጁ ከሕዝቡ ጆሮ ይደርሳል። በቤተ መንግሥቱ አራቱም ማዕዘናት የክብ ቅርጽ ያላቸው እና ላቅ ብለው የሚታዩ ግምቦች አሉ። እነዚህም አራቱን ወንጌላውያን- ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስን ወክለው የተገነቡ ናቸው። የማዕዘን ግንቦቹ እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት መስኮቶች አላቸው ( በአንደኛ ፎቅ ላይ አንድ፣ በሁለተኛ ፎቅ ላይ አንድ፣ በሦስተኛ ፎቅ ላይ አንድ መስኮት ማለት ነው) የመስኮቶቹ ብዛትም 12 ሲሆን፤ ሐዋሪያትን ይወክላል።

ወደ አንደኛ ፎቅ ለመውጣት 32 ደረጃዎች አሉ። ደረጃዎቹም አፄ ፋሲል በ17ኛው ክፍለ ዘመን በ32ኛው ዓመት (በ1632 ዓ.ም) በትረ-ንግሥና መጨበጣቸውን ያጠይቃል። በአንደኛው ፎቅ የእንግዳ መቀበያ ክፍልን ጨምሮ የሴትና የወንድ ማዕድ ቤቶች፣ በወርሃ ክረምት የእሳት መሞቂያ፣ ንጉሱ ከእንግዶች ጋር የሚነጋገሩበት ክፍል እና መፀዳጃ ቤቶች ይገኛሉ። ክፍሎቹ በዚያን ዘመን በተሰሩና ውበታቸው ባልጠወለገ ጠንካራ የእንጨት በሮች የተከፋፈሉ ናቸው። የቤተ መንግሥቱ መግቢያ በርም እንዲሁ ከግዙፍ ጣውላ የተሠራ ሁለት ተካፋች በር ነው።

ቤተ መንግሥቱ ከጥቁር እና ከቀይ ጥርብ ድንጋዮች የተሰራ ነው። ግድግዳው ለዓመታት በሚቦካ ኖራ የተለሰነና የተጣበቀ ሲሆን እስከ አንድ ሜትር ተኩል ውፍረት አለው። ይህ የኖራ ማጣበቂያ በየጊዜው እየጠነከረ የሚሄድ እንጅ የሚላላ አይደለም። ከቤተ መንግሥቱ ጀርባ ከግንቡ ጋር ተያይዘው የተገነቡ ሌሎችም ቅርሶች አሉ። የመታጠቢያ ቤቶች፣ የእስረኞች ማቆያ፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ይጠቀሳሉ። ግን አብዛኞቹ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የፋሲል ገንዳ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከፋሲል ግምብ አጠገብ ውሃ የነበረበት ገንዳ ይገኛል። ይሄ ገንዳ በጊዜው ለዋና እና ዓሣ ለማርቢያነት ያገለግል ነበር። ፋሲለደስ ዓሣ ተመጋቢ እንደነበር ይዘገባል (ገጽ 27)።

ታላቁ ኢያሱ ግምብ

ታላቁ እያሱ ግምብ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋና መጣጥፍ፦ ታላቁ እያሱ ግምብ

ታላቁ እያሱ ግምብ (አድያም ሰገድ ግምብ)፣ በንጉሱ ታላቁ እያሱ ዘመን ተገንብቶ በ1677 (ዘመነ ማቲዎስ) የተጠናቀቀ ነበር። የአናጢዎች መሪ ወልደ ጊዮርጊስ ግምቡን የሰራው ሲሆን በጊዜው ከጠቢቡ ሰለሞን ቤት የብለጠ ያምር ነበር በመባል የተደነቀ ነበር። [6] የግምቡ ጣሪያ በወርቅና በከበሩ ደንጊያወች ያጌጠ ነበር። ግድግዳዎቹ ከዝሆን ጥርስና ከቅጠላቅጥል ጌጦች የተሰራ ነበር።[7] ግምቡ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በእንግሊዝ የአውሮፕላን ቦምብ ድብድባ የተጎዳ ቢሆም አብዛኛው ክፍሉ ግን አሁን ድረስ ሳይፈርስ ይገኛል።

ዮሐንስ ቤተ መጽሐፍ በግራ በኩል የሚታየው ህንጻ ነው፣ ዮሐንስ ጽሕፈት ቤት በስተቀኝ ይታያል

ዮሐንስ ቤተመጻሕፍት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋና መጣጥፍ፦ ዮሐንስ ቤተመጻሕፍት

ዮሐንስ ቤተመጻሕፍትፋሲልደስ ልጅ በቀዳማዊ አጼ ዮሐንስ የተገነባ ቤተ መጻሕፍት ሲሆን በፋሲል ግቢ ይገኛል። አማዶ በ1930 ብዙ ጌጣጌጥ እንደነበረውና ውጭውም ጥሩ መልክ ባለው፣ ከኑግ ዘይት በተሰራ ቢጫ ፕላስተር የተለጠፈ እንደነበር ይዘግባል። በዚሁ ወቅት የዚህ ህንጻ ሁለት ጎኖች የመፍረስ አደጋ ገጥሟቸው እንደነበርም ጽፎት ይገኛል (ገጽ 27)። አንድ ፎቅ ያለው ይሄ ህንጻ ምድር ቤቱ 3 ሰፋፊ ክፍሎች አሉት ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ክፍል ከሁሉ የሚሰፋ የነበር ሲሆን ይህን ክፍል ከሁለት የሚከፍል ቅስት ነበረው። በተረፈ የፎቁ ክፍል ከሁለት የተከፈለ የነበር ሲሆን፣ ወደ ፎቁ የሚያወጣው ደረጃ ከቤተመጻህፍቱ በስተ ውጭ(ገጽ 27)።

ዮሐንስ ጽሕፈት ቤት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋና መጣጥፍ፦ ዮሐንስ ጽሕፈት ቤት

ዮሐንስ ጽሕፈት ቤትፋሲልደስ ልጅ በቀዳማዊ አጼ ዮሐንስ የተገነባ በፋሲል ግቢ የሚገኝ ያስገነባው ንጉስ ጽህፈት ቤት የነበር ነው። እንደቤተመጻሕፍቱ ሁሉ፣ ይሄም ህንጻ አንድ ፎቅ አለው። የምድሩ ክፍል እንግዶችን ለመቀበልና ሌሎች ህዝባዊ በዓላትን ለማክበር ይጠቅም ነበር። ፎቅ ቤቱ በአንጻሩ እንደ መዝገብ ቤት ሲያገለግል የግብር እና የፍርድ ቤት መዝገቦችን ይይዝ ነበር (ገጽ 28)። ትንሽ አንስተኛ በር ወደ አንስተኛ ሰገነት መወጣጫ ደረጃ ስታመራ፣ ሌላ ሰፊ በር ደግሞ ወደ ውጭ ያመራል።

የፈረሰኞች አለቃ ቤት - በ1920ዎቹ

የፈረሰኞች አለቃ ቤት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋና መጣጥፍ፦ የፈረሰኞች አለቃ ቤት

የፈረሰኞች አለቃ ቤት በፋሲል ግቢ ዋና በር ጎንና ጎን ያሉ ባለ አንድ ፎቅ ግንቦች ናቸው። እኒህ ፎቆች ከሌሎቹ ህንጻዎች ለየት ባለ መልኩ ሳይፈርሱ ብዙ ዘመን አሳልፈዋል። ጣሊያናዊው አሌሳንድሮ ኮርቴ በ1930 ጥናቱን ሲያካሂድ በእኒህ ህንጻዎች የአጣጣሚ ሚካኤል ቄስ ይኖሩ እንደነበር ሳይዘግብ አላለፈም (ገጽ 38)። ወደ ላይ የሚያወጣ የውጭ ደረጃ አለው።


አጣጣሚ ቅዱስ ሚካኤል በ1920ዎቹ

አጣጣሚ ሚካኤል

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋና መጣጥፍ፦ አጣጣሚ ሚካኤል

አጣጣሚ ቅዱስ ሚካኤል ፋሲል ግቢ ውስጥ በስተ ሰሜን ምስራቅ ክፍል ሲገኝ፣ ሰኔ ፲፪ ቀን ፲፯፻፰ ዓመተ ምሕረት ተመርቆ የተከፈተ ቤተ ክርስቲያን ነው። ወደቤተክርስቲያኑ የሚገባው በእልፍኝ በር አድርጎ ነው። በዓፄ ዳዊት ዘመን ይተገነባው ይሄ ቤተክርስቲያን የአራት ማዕዘን ቅርጽ የነበረውና መልካም ውድርን የተከተለ ነበር። ሁለት ሰገነቶች የነበሩት ሲሆን አንዱ ግን ወድቋል። ውስጡ ከ3 ክፍሎች ነበሩት (ገጽ 38)። የአጣጣሚ ሚካኤል ቄሶች በአለቃ ገነት ማዕረግ እስካሁን ይታወቃሉ።

የበካፋ ግምብ በ1920ዎቹ

ዋና መጣጥፍ፦ በካፋ ግምብ

በካፋ ግምብ ፋሲል ግቢ ውስጥ የሚገኝ በአጼ በካፋ የታነጸ ነው። ግምቡ በግቢው በስተሰሜን በኩል ሲገኝ፣ ከፈረሶች ቤት ጋር የተያያዘ ነው። ይህ የዓፄ በካፋ ቤተ መንግሥት ነው። በ 'V' ቅርጽ የተሠራ ሲሆን 30 ሜትር ርዝመትም አለው። መሲህ ሰገድ በካፋ በፋሲል አምባ ያኖሩት ቅርስ ለግቢው አምስተኛው ቤተ መንግሥት ነው፡፡ በጣም ረዥም ሲሆን ከሁሉም የአምባው አብያተ መንግሥታት የተለየ ቅርጽ አለው። በዚህ ህንጻ በስተግራ በኩል ረዥም ግድግዳ ይታያል። በስተቀኝ ደግሞ ዋናው የቤተመንግሥቱ ክፍል አለ። ብቻውን የቆመው ግድግዳውና ዋናው ቤተ መንግሥት በ30 ሜትር ርዝመት ላይ ይገናኛሉ። ከመግቢያው ጀምሮ ግድግዳዎቹ እስከሚገናኙበት ድረስ ያለው ክፍተት እየጠበበ ሄዶ የ'V' ቅርጽ ይኖረዋል። ብቻውን በቆመው ግድግዳና በዋናው የቤተ መንግሥቱ ግድግዳ መካከል የ'V' ቅርጽ ያለው ክፍት ቦታ አለ። ይህ ክፍት ቦታም ጣሪያ የሌለውና በልምላሜ የተሸፈነ ነው። በዘመኑ የነበሩ መኳንንትና የፈረሰኛ አዛዦች እንደየማዕረጋቸው ፈረሶቻቸውን የሚያቆሙት- በዚሁ ክፍት ቦታ ላይ ነበር። የቤተ መንግሥቱ በርና መስኮቶች እስካሁን ያሉ ጣውላዎች ናቸው፣ ከሁለት ተከፋች ናቸው። የቤተ መንግስቱ እልፍኝ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተዘረጋ ነው። እስከ 300 ሰዎችንም የማስተናገድ አቅም አለው።

አምበሶች ቤት -ፋሲል ግቢ

አምበሶች ቤት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋና መጣጥፍ፦ አምበሶች ቤት

አምበሶች ቤት በአጼ ሳልሳዊ ዳዊት የተሰራ በፋሲል ግቢ የሚገኝ አንበሶች ይኖሩበት የነበር ነው። እስከ 1984 ዓ.ም. አምበሶች ይኖሩበት የነበር ሲሆን በዚሁ አመት የመጨረሻው አንበሳ በሞት አለፈ።

ምንትዋብ ሐማም

ምንትዋብ መታጠቢያ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋና መጣጥፍ፦ ምንትዋብ መታጠቢያ

ምንትዋብ መዋኛ ወይም የምንትዋብ መታጠቢያበእቴጌ ምንትዋብ የተሰራ በፋሲል ግቢ ውስጥ ከምንትዋብ ግምብ አጠገብ የሚገኝ ቱርክ መታጠቢያ (ሐማም) ነበር። ስለሆነም ከህንጻው ስር ምድጃ ሲኖር፣ ውሃ በቱቦ ይገባለትና እንፋሎት እያተነነ የተለያዩ የሚሸቱ ቅጠሎች በላዩ ላይ እየተደረጉ ለህመም ፈውስ የሚገኝበት ክፍል ነበር። በዚህ መታጠቢያ ቤት የመጀመሪያው ክፍል እራቁትን ሆኖ ሰውነትን ለማሞቅ የሚያገለግል ሲሆን፣ ሁለተኛ የበለጠ ሰውነትን በማጋል ላብ የሚያስወጣ ነበር። ከዚህ ቀጥሎ በቅዝቃዛ ውሃ መታጠቢያ ክፍል ውስጥ መታጠብ ሂደቱን ያጠናቅቃል።


ምንትዋብ ግምብ

ምንትዋብ ግምብ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋና መጣጥፍ፦ ምንትዋብ ግምብ


ምንትዋብ ግምብ ወይንም አልፎ አልፎ ትንሹ ኢያሱ ግምብ በእቴጌ ምንትዋብ የተሰራ ሲሆን በፋሲል ግቢ ይገኛል።

ዳዊት ፫ ዙፋን ቤት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋና መጣጥፍ፦ ዳዊት ፫ ዙፋን ቤት

ዳዊት ፫ኛ ዙፋን ቤትቀዳማዊ እያሱ ልጅ በዳዊት ፫ኛ የተሰራ ነበር። የቀዳማዊ ዮሐንስ ግንቦች ከተገነቡ ከ15 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። የዙፋን ቤቱ በግቢው በስተሰሜን በበበካፋ ግምብ እና በአጣጣሜ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መካከል ይገኛል። [8] ይህ ሕንጻ በእርግጥ ቤተ መንግሥት ሳይሆን በዘመኑ የሚደረጉ ጉባኤዎች፣ ክብረ በዓላት የመዝሙርና የዝማሬ መርሐ ግብሮች፣ የሹመትና የሽረት ስነ ሥርዓቶች፣ የኪ ጥበብና የባሕል መዝናኛ ዝግጅቶችም የሚካሔዱት አዳራሽ ነው። ይህ አዳራሽ ሰፊና ጣሪያ አልባ ነው። አጼ ዳዊት ሦስተኛ አዳራሹን ሲያስገነቡት ለመዝሙርና ለዝማሜ አገልግሎት ይውል ዘንድ አስበው ነበር። ጣሪያ አልባ አድርገው ማሠራታቸው ዘማሪያን ሲያመሰግኑ ወደ ሰማይ ሲያንጋጥጡ -ሲመለከቱ የሚከልላቸው ጣሪያ እንዳይኖር ነው የሚሉ አሉ።

የአጼ ዳዊት መዝሙር ቤት በአብዛኛው በዓመታዊ የንግሥና ክብረ በዓላት፣ በዓውደ በዓላትና በሌሎችም ጊዜያት ዝማሬና ዝማሜ ይቀርብበት ነበር። ንጉሱም ፊት ለፊት ከሚገኘው ባለፎቅ መድረክ ላይ ሆነው ይህንኑ መንፈሳዊ ሥርዓት ይታደማሉ። የአቋቋም የቅኔና ሌሎች ሊቃውንት በንጉሱ እና በታዳሚው ፊት ሆነው በያሬዳዊው ዝማሬና ዝማሜ ይሳተፋሉ።

አጼ ዳዊት መዝሙር ቤቱን ያስገነቡት በዋናነት ለመንፈሳዊው ዝማሬና ዝማሜ የነበረ ቢሆንም ቅሉ አዳራሹ ለሌሎችም ግልጋሎቶች ይውል እንደነበር፤ ከእነዚህ አገልግሎቶቹ ውስጥ ደግሞ አንዱ የሙዚቃ እና የሌሎችም ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችን ማቅረቢያነትም ነበር። ኋላ መንፈሳውያኑ ዘማርያን እና ዓለማውያኑ ሙዚቀኞች ሊጣጣሙ ስላልቻሉ አዳራሹ ለሁለት እኩል እንደተከፈለ ይጠቀሳል። እንደሚወጣላቸው መርሐ ግብር መንፈሳውያኑ በቀኝ ሙዚቀኞቹም በግራ የአዳራሹ ክፍል ኪናቸውን ማቅረብ ጀመሩ። በእንግሊዝ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች የተመታው ይኸው አዳራሽ የተወሰነው ግድግዳው ፈርሷል። መንፈሳዊውን ከዓለማዊው ሙዚቃ የሚለየው የመካከል ግድግዳ ፈርሷል።

  1. ^ http://whc.unesco.org/en/list/19
  2. ^ Adapted from:Monti, Augsto,I castelli di Gondar , Societa Italiana Arti Grafiche Editrice, Rome 1938
  3. ^ Munro-Hay, Ethiopia, pp. 114f
  4. ^ የአጼ በእደ ማርያም ዜና መዋዕል
  5. ^ Munro-Hay, Ethiopia, pp. 118-120
  6. ^ Budge,( 1928) pp. 409
  7. ^ ሪቻርድ ፓንክኸርስት፣ The Ethiopians: a history፣ ገጽ 111
  8. ^ Stuart Munro-Hay, Ethiopia, the unknown land: a cultural and historical guide (London: I.B. Tauris, 2002), pp. 126-128