የኢትዮጵያ መላክተኞች በብሪታኒያ

ከውክፔዲያ
የዓፄ ዮሐንስ ጊዜያዊ መላክተኛ፣ መርጫ ወርቄ ከመቅደላ ዘማች እንግሊዞች ጋር

ታላቋ ብሪታኒያ መንግሥት በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ጉዳዩን የሚያስፈጽምለት ወኪል እና የብሔራዊ ምሥጢራዊ ጉዳይ ባለሙያ (‘አምባሳዶር’)፤ በጊዜያዊነትም ኾነ በቋሚ ሹመት ወደኢትዮጵያ መላክ የጀመረው በ፲፱ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ከዚያ በፊት በተለያዩ ጊዜያት መላክተኞችን የሰደደ ቢሆንም የነዚያ ተልዕኮ ግን ወደተለያዩት የክፍለ አገራት መሳፍንት እና ገዚዎች ነበር።

የኢትዮጵያም ነገሥታት ከዓፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ እስከ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ድረስ አልፎ አልፎ ጊዜያዊ መላክተኞቻቸውን ወደ ታላቋ ብሪታኒያ ልከዋል። ዳሩ ግን ከእነዚህ ልዑካን አብዛኞቹ የውጭ ዜጎች ነበሩ። ከነዚህ አንዱ ዓፄ ቴዎድሮስን ወክሎ ወደ ሎንዶን ያመራው ሚሲዮናዊው ማርቲን ፍላድ ሲሆን ከኢትዮጵያውያን ደግሞ የዓፄ ዮሐንስ ልዑክ መርጫ ወርቄ፣ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክን ወክለው ለንጉሥ ኤድዋርድ ፯ኛ የንግሥ በዓል የተላኩት ልዑል ራስ መኮንን እና ከንቲባ ገብሩ፤ እንዲሁም ንግሥት ነገሥታት ዘውዲቱን ወክለው በንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ የንግሥ በዓል ላይ የተገኙት ደጃዝማች (በኋላ ልዑል ራስ) ካሣ ኃይሉ በዋቢነት ይጠቀሳሉ። በቋሚነትም በ፲፰፻፷፭ ዓ/ም የዓፄ ዮሐንስ ቆንስላ ሄንሪ ሳሙኤል ኪንግ በሎንዶን የኢትዮጵያን ጉዳይ እንዲይስፈጽም ተሹሞ እንደነበር ታሪክ ይዘግባል።

በዚሁ በንግሥት ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን አልጋ ወራሽ እና ባለምሉ ሥልጣን እንደራሴው ራስ ተፈሪ መኮንን ከመሳፍንትና መኳንንቶቻቸው ጋር በብሪታኒያ እና ሌሎችም የአውሮፓ አገራት ያደረኡት ጉብኝት በዓይነቱ የመጀመሪያው ከመሆኑም ባሻገር፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያ በአጽናፋዊ ትሥሥር ሂደት ለመሳተፍ ያላትን ፍላጎት ያበሥራል። በዚህ ጉብኝት የተከፈተውንም ግንኙነት ለማጠናከርና የኢትዮጵያን ጉዳይና ጥቅም ለማስከበር ቋሚ መላክተኞችን በጊዜው ከነበሩት ከተማሩ ኢትዮጵያውያን መኻል እየተመለመሉ ወደሎንዶንፓሪስሮማ እና ዠኔቭ ተላኩ።


በብሪታኒያ የኢትዮጵያ ቋሚ መላክተኞች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን የተሾሙ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • የመጀመሪያውኢትዮጵያ ቋሚ መላክተኛ ነጋድራስ (በኋላ ራስ ቢትወደድ) መኮንን እንዳልካቸው ሲሆኑ፣ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለብሪታኒያው ንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ስም ኅዳር ፲ ቀን ፲፱፻፳፪ ዓ/ም በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት የተረከቧቸው አልጋ ወራሹ የዌልስ መስፍን (የወደፊቱ ንጉሥ ኤድዋርድ ስምንተኛ) ነበሩ። ነጋድራስ መኮንን በዚህ መደባቸው ሁለት ዓመት አገልግለዋል።

ብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚያዝያ ፳፮ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም ያወጣው “የኢትዮጵያ ትላልቅ ሰዎች ዝርዝር” (“Record of Leading personalities in Abyssinia…” ) ላይ በተራ ቁጥር ፹፪ ስለይነጋድራስ መኮንን እንዳልካቸው ሲተነትን፤ በጥቅምት ወር ፲፱፻፳፫ ዓ/ም ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንግሥ በዓል ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ሲገቡ፣ ያጋጠማቸው አዲስ አበባ ከተማ እንዳይገቡ የመታገድ ትዕዛዝ እንደነበረና ምክንያቱም ፓሪስ ላይ በወቅቱ የራስ ጉግሳ አርአያ ሚስት ከነበሩት የንጉሠ ነገሥቱ ታላቅ ወንድም ልጅ፣ ልዕልት የሻሸወርቅ ይልማ ጋር ባልገዋል በሚል እንደነበር፤ ራስ ጉግሳም በኋላ በዚሁ ምክንያት ሚስታቸውን እንደፈቱ እና ነጋድራስ የአሥር ሺ የኢትዮጵያ ብር ቅጣት እንደተጣለባቸው ዘግቧል። ወደሎንዶን ሥራቸውም ሳይመለሱ በዚያው እንደቀሩና በታኅሣሥ ወር ፲፱፻፳፬ ዓ/ም ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ ኾነው ተሾሙ።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተሾሙ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሁለተኛውኢትዮጵያ ቋሚ መላክተኛ ኾነው የተሾሙት ባለ ሥልጣን ደግሞ በጅሮንድ ዘለቀ አግደው ሲሆኑ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለብሪታኒያው ንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ሐምሌ ፲፮ ቀን ፲፱፻፳፫ ዓ/ም በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት አስረክበው፣ በዚሁ ሥልጣን ላይ እስከ ግንቦት ፫ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ/ም ቆዩ።

በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የተማሩት በጅሮንድ ዘለቀ፣ የዋና መላክተኛነት ሥልጣናቸው በሎንዶን፤ በፓሪስእና ዠኔቭ በሚገኘው የዓለም መንግሥታት ማኅበር ነበር። ይኼንን ተልዕኮ አጠናቀው ወደኢትዮጵያ ሲመለሱ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የእርሻ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።


  • በሦስተኛ ተራ ለዚህ ሥልጣን የተመደቡት ደግሞ በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም (ፊታውራሪ ) ነበሩ። እኒህ ሰው ሹመታችው በአንድነት ለፈረንሳይብሪታኒያ እና የዓለም መንግሥታት ማኅበር እንደነበር እና ሹመቱን እንዳልፈለጉት “ኦቶባዮግራፊ” (የሕይወቴ ታሪክ) በተባለው መጽሐፋቸው (ገጽ 416-419) ላይ በሰፊው ተንትነውታል። በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት የሹመት ደብዳቤያቸውን መጀመሪያ ለፈረንሳይ ፕሬዚደንት ካቀረቡ በኋላ ወደሎንዶን ተጉዘው በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ለብሪታኒያው ንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ግንቦት ፫ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ/ም አቅርበዋል። በሎንዶን ወደፊት በዋና መላክተኛነት የሚሾሙትን አቶ (በኋላ ብላታ) ኤፍሬም ተወልደ መድኅንን፤ በፓሪስ ደግሞ ዋና ጸሐፊውን አቶ ተስፋዬ ተገኝን ቋሚ ወኪሎች በማድረግ እሳቸው ሥራቸውን በሎንዶን፤ ፓሪስ እና በዠኔቭ በማፈራረቅ ሲሠሩ ቆዩ። በ፲፱፻፳፯ ዓ/ም የወልወል ግጭት ስለተነሳ እና በዓለም መንግሥታት ማኅበር ኃላፊነታቸው ብዙ ስለተወጠሩ በሰኔ ወር ላይ የሎንዶኑን ዋና መላክተኛነት እንዲለቁ ተደረገ።
  • በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያትን ተከትለው በአራተኛ ተራ የተሾሙት መላክተኛ፣ አዛዥ ወርቅነህ ነበሩ። አዛዥ ወርቅነህ/ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ የመቅደላ ጦርነት ጊዜ በእንግሊዝ የጦር መኮንን በሕጻንነታቸው ወደሕንድ አገር ተወስደው እዚያው ያደጉ፤ የኖሩ እና በቀዶ ጥገና ሙያ የተሠማሩ ሰው ሲሆኑ አሳዳጊ አባቶቻቸው በሰጧቸው ስሞች ቻርልስ (በወሰዳቸው መኮንን ስም)፤ ማርቲን (ባሳዳጊያቸው ሐኪም ስም) (Charles Martin) ይባሉ ነበር። አዛዥ ወርቅነህ በሎንዶን የኢትዮጵያ ዋና መላክተኛነቱን ሥልጣን ሲሾሙ የሹመት ማስረጃቸውን መጀመሪያ ለንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ሐምሌ ፲፰ ቀን ፲፱፻፳፯ ዓ/ም፤ በኋላ ደግሞ ለንጉሥ ኤድዋርድ ስምንተኛ ጥር ፳፯ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም አቅርበዋል። በዚህ ዕለት የኢትዮጵያን ግዛት ከ ግንቦት ፩ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ጀምሮ የምወክለው እኔ ነኝ ያለችው የኢጣሊያ መላክተኛም የሹመት ማስረጃውን አብሮ አቅርቧል። በሎንዶን ፲፯ ‘ፕሪንስስ ጌት’ (17 Princes Gate) የሚገኘውን የኢትዮጵያ መላከተኞች መኖሪያ እና መሥሪያ ቤትን በአገራቸው ስም የገዙትም ዋና መላክተኛ አዛዥ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ናቸው።


  • አምሥተኛው ዋና መላክተኛ የኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆች የፋሺስት ኢጣልያን ቀንበር ከአምሥት ዓመት ትግል በኋላ በ፲፱፻፴፫ ዓ/ም ሲያስወግዱ፤ ወደሎንዶን የታላኩት ብላታ አየለ ገብሬ ነበሩ። ብላታ አየለ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለንጉሥ ጆርጅ ስድስተኛ መስከረም ፯ ቀን ፲፱፻፴፭ ዓ/ም አቅርበዋል።
  • ስድስተኛው ዋና መላክተኛ፤ የኤርትራው ተወላጅ ብላታ ኤፍሬም ተወልደ መድኅን ነበሩ። ብላታ ኤፍሬም በሎንዶን እና በፓሪስኢትዮጵያ መላክተኞች መሥሪያ ቤቶች በዋና ፀሐፊነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፤ በዋሺንግቶን የኢትዮጵያን ቢሮ በዋና መላክተኛነት የመጀመሪያው ሹም ሆነው ጥቅምት ፳፱ ቀን ፲፱፻፴፮ ዓ/ም የከፈቱ ሲሆኑ፤ የሎንዶኑን ዋና መላክተኛነት ከብላታ አየለ ገብሬ ተረክበው የሹመት ደብዳቤያቸውን ለንጉሥ ጆርጅ ስድስተኛ ጥቅምት ፳፱ ቀን ፲፱፻፴፰ ዓ/ም አቅርበዋል።

ብላታ ኤፍሬም በቤይሩትአሜሪካ ኮሌጅ የተማሩ ሲኾን በአዲስ አበባተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የንግሊዝኛ ቋንቋ አስተማሪም ነበሩ። ከዚያም በ ፲፱፻፳፩ ዓ/ም በፓሪስኢትዮጵያ ቆንስላ ሆነው ተሾሙ። ከሁለት ዓመትም በኋላ በሎንዶን የኢትዮጵያ ጉዳይ አስፈጻሚ (Charge d’Affaires) ኾነው አገልግለዋል።


  • ብላታ ኤፍሬምን የተከተሉት ሰባተኛው መላክተኛ በሎንዶን ለሰባት ዓመታት ያገለገሉት አቶ አበበ ረታነበሩ። አቶ አበበ የሹመት ደብዳቤያቸውን መጀመሪያ፣ ጥቅምት ፬ ቀን ፲፱፻፵፩ ዓ/ም ለንጉሥ ጆርጅ ስድስተኛ፤ ወዲያው ግንቦት ፩ ቀን ፲፱፻፵፬ ዓ/ም ለዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ አቅርበዋል። አቶ አበበ አንድ ዓመት በዋና መላክተኛነት ካገለገሉ በኋላ ጥቅምት ፲ ቀን ፲፱፻፵፪ ዓ/ም በሹመት ዕድገት አምባሳዶርነት ተሹመዋል።
  • በስምንተኛ ተራ ከአቶ አበበ ረታ የአምባሳዶርነት ሥልጣኑን በ፲፱፻፵፰ ዓ/ም የተረከቡት አቶ አማኑኤል አብርሐም ሲሆኑ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ጥር ፲፭ ቀን ፲፱፻፵፰ ዓ/ም አቅርበው በሎንዶን አራት ዓመታት አገልግለዋል። አቶ አማኑኤል የአዛዥ ወርቅነህ ደቀ-መዝሙር ሲሆኑ፣ አዛዥ ወርቅነህ ወደሎንዶን የተላኩ ጊዜ ይዘዋቸው ሲመጡ ያለደመወዝ ለቀለባቸው ብቻ በጸሐፊነት እየሠሩ እንዲትዳደሩ አስማምተው እንዳመጧቸው ስለህይወት ታሪካቸው በተጻፈ ዘገባ ላይ ተተንትኗል። አቶ አማኑኤል በጠላት ወረራ ዘመናት አዛዥ ወርቅነህ ሥልጣናቸውን ለቅቀው ወደሕንድ አገር ሲሄዱ የኢትዮጵያን ሥራ በስደት ላይ በነበሩት ንጉሠ ነገሥት እና ተከታዮቻቸው አመራር መሠረት በሎንዶን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
  • ልጅ እንዳልካቸው የሎንዶኑን አምባሳዶርነት ያስረከቡት ለተከታያቸው፣ በአሥረኛ ተራ ቁጥር ለተመዘገቡት እና በደራሲነታቸው ለሚታወቁት አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ ነበር። አቶ ሀዲስ የሹመታቸውን ደብዳቤ ጥቅምት ፳፪ ቀን ፲፱፻፶፬ አቅርበው በጠቅላላው ለአምሥት ዓመታት አገልግለዋል። አቶ ሀዲስ ከሥነ ጽሑፍ ሙያቸው ከደረሷቸው መጻሕፍት በተለየ ትልቅ ዝና ያተረፈላቸው ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ አዲስ አበባ በታተመበት ጊዜ እሳቸው ኑሯቸው ሎንዶን እንደነበረና “አብሮ አደጋቸው” አቶ መሀሪ ካሣ እንዳሳተሙላቸው በመጽሐፉ የምስጋና ገጽ ላይ አስፍረውታል።
  • አቶ ሀዲስ በሎንዶን ቆይታቸውን ጨርሰው ሥልጣኑን ሲለቁ በአሥራ አንደኛ መደብ የተከተሏቸው አምባሳዶር ጥቅምት ፳፫ ቀን ፲፱፻፶፱ ዓ/ም ሹመታቸውን ለንግሥት ኤልሳቤጥ ያቀረቡት አቶ ገብረ መስቀል ክፍለእግዚ ናቸው።
  • በ፲፪ኛ ተራ ቁጥር ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፲፱፻፷፪ ዓ/ም በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ሥነ ሥርዓት ላይ ንግሥት ኤልሳቤጥን በመወከል የንግሥቲቱ እናት እና እህት የሹመት ደብዳቤያቸውን የተቀበሏቸው አምባሳዶር ሌተና ጄነራል ኢያሱ መንገሻ ነበሩ። ለብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤድዋርድ ሂዝ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለ ሥልጣናት ሰኔ ፮ ቀን ፲፱፻፷፬ ዓ/ም የተዘጋጀ አጭር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሌተና ጄነራል ኢያሱ ከኢትዮጵያ መንግሥት የመከላከያ ሚኒስትር ጋር እንደማይግባቡ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፀሐፊ-ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን የግልጽ ተቃዋሚ መሆናቸውን ይዘግባል። ወደ እንግሊዝ አገር በአምባሳዶርነት መላካቸውንም በአገር ቤት ከነበረው አለመግባባት እና ግጭት እንደተገላገሉ ይቆጥሩታል በማለት ይደመደመዋል።

በደርግ ዘመን የተሾሙ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • ሌተና ጄነራል ኢያሱ ወደአገራቸው ሲመለሱ ሎንዶን በአምባሳዶርነት የተኳቸው አቶ ዘውዴ መኩሪያ ሲሆኑ የሥልጣን ደብዳቤያቸውን ልንግሥት ኤልሳቤጥ ያቀረቡት ሰኔ ፲፰ ቀን ፲፱፻፷፰ ዓ/ም ነበር። አቶ ዘውዴ የደርግ መንግሥት የመጀመሪያው ሹም ቢሆኑም ቦሎንዶን የኢትዮጵያ ዋና መላክተኛነት ተራ ቁጥር ፲፫ኛው መሆናቸው ነው።
  • በ፲፬ኛ መደብ የተመዘገቡት አምባሳዶር አቶ አያሌው ወልደ ጊዮርጊስ ደግሞ የሹመት ማስረጃቸውን ያቀረቡት ታኅሣሥ ፮ ቀን ፲፱፻፸ ነው።


::ከአቶ አያሌው እስከ ዶ/ር በየነ ነገዎ ያሉትን አምባሳደሮች ዝርዝር የምታውቁ እባካችሁ ሙሉት

በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የተሾሙ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]


አቶ ፍስሐ በየካቲት ወር ፲፱፻፺፰ ዓ/ም የደረሳቸውን ወደአገር ቤት የመመለስ ጥሪ ሲደርሳቸው በሥራቸው ይሰሩ ከነበሩ ሌሎች ዲፕሎማቶች ጋር ወደ አሜሪካ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው ለቀዋል።


ዋቢ ምንጮች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • (እንግሊዝኛ) The London Gazette; p.p. 7532, 4940, 3281, 4909, 889, 4123, 5535, 5532, 5079, 2652, 566, 2365, 8031, 12047, 4759, 9295, 16165
  • (እንግሊዝኛ) P.R.O. [J 2157/2157/1] Record of Leading Personalities in Abyssinia,- (As amended by Addis Ababa Despatch No. 54 of March 18, 1937; Received May 4); Copy No. 8
  • ሀዲስ ዓለማየሁ፣ “ፍቅር እስከ መቃብር”፣ ፲ኛ እትም፣ ሜጋ አሳታሚ እና ማከፋፈያ ኃ/የት/የግ/ማህበር (፲፱፻፺፱)