Jump to content

ኪርታ

ከውክፔዲያ
የ00:27, 30 ኖቬምበር 2018 ዕትም (ከTil Eulenspiegel (ውይይት | አስተዋጽኦ) ተዘጋጅቶ)
(ለውጡ) ← የፊተኛው እትም | «የአሁኑን እትም ለመመልከት» (ለውጡ) | የሚከተለው እትም → (ለውጡ)

ኪርታ እንደሚታመን በሑራውያን ላይ የነገሡት የሚታኒ መሣፍንት መስራች ነበር። እንዲህ ከሆነ ዘመኑ ምናልባት 1512 ወይም 1507 እስከ 1497 ዓክልበ. ነበር።

ስሙ ኪርታ የሚታወቀው በአላላኽ በተገኘው በልጁ 1 ሹታርና ማኅተም ብቻ ነው፤ «ሹታርና የኪርታ ልጅ» ብቻ ይላል።

ሆኖም የያምኻድና የባቢሎን መንግሥታት በ1508-7 ዓክልበ. ለኬጥያውያን መንግሥት ንጉሥ 1 ሙርሲሊ በወደቁበት ጊዜ ያህል የሚታኒ መንግሥት በኪርታ እንደ ተመሠረተ ይታስባል። ወይም የጥንታዊ ግብጽ ፈርዖን 1 ቱትሞስ ከዚያ ትንሽ በፊት (1512 ዓክልበ.) ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በ«ናሓሪን» ላይ ዘምቶ ነበርና በአንዱ ጽሑፍ «መታኒ» ሲል ከዚህ ዘመቻ እንደ ሆነ ይታመናል፤ ቀደም-ተከትሉ እንዲህ ከሆነ ምናልባት ኪርታና የሚታኒ ባለሥልጣናት ከሙርሲሊ ዘመቻ ጥቂት አመታት በፊት በሑራውያን አገር ወይም ሐኒጋልባት ተመሠረቱ።

«ናሓሪን» የሚለው ግብጽኛ ስያሜ ደግሞ በእብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ አራም-ናሓራይም (አረማይክ ናሓራይን ወይም «ኹለት ወንዞች») ይታያል። እንዲሁም በኪርታ ዘመን ያሕል የአራም-ናሓራይም ወይም እንደ ግሪክኛው የ«መስጴጦምያ» ንጉሥ ኲሰርሰቴም እስራኤልን አሸንፎ ለስምንት አመት (1505-1497 ዓክልበ. ግ.) እንደ ገዛ ይለናል (መጽሐፈ መሣፍንት 3:8)። በመጨረሻ በዕብራዊው ፈራጅ ጎቶንያል ተሸነፈ። «ኲሰርሰቴም» የሚለው ከዕብራይስጥ ስድብ ስለ ተዛበ ትክክል የንጉሥ ስም አይታስብምና የዚህ «ኲሰርሰቴም» መታወቂያ በእርግጡ ገና አልተፈታም።

በተጨማሪ በኡጋሪት የተገኘው ኡጋሪትኛ ድርሰት «የከረት ትውፊት» (ከ1350 ዓክልበ. ያሕል) ስለዚሁ ንጉሥ ኪርታ እንደ ሆነ የሚል አስተሳስብ አለ። በዚህ ትውፊት ዘንደ «ከረት» «በባሕሩ አጠገብ ያለው የሐበር አገር ንጉሥ» ይባላል። ሆኖም ግን የከረት ወራሾች ሁሉ በሕጻንነታቸው አርፈው በጣም አዝኖ ለአምላኩ ኤል ይጮሃል። እንደ ተማከረ፣ በጎረቤቱ በ«ኡዱም» ንጉሥ ፐበለ ላይ ጦርነት አድርጎ የፐበል ለምለም ሴት ልጅ ሐረየ እንደ ሚስቱ እንድትሰጥ ያስገደዋል። ድል ለማድረግ ከረት ለሴት ጣኦት «አጢራት» ሲጸልይ ብዙ ወርቅና ብር ለመቅደሷ ለመስጠት መሃላ ይገባል። በኋላ ልጆቹ አድገው ከረት መሃላውን ስላልጠበቀ ጣኦቷ አጢራት ትቆጣበታለች። በመጨረሻም ከረት በኲሩን «ያጺብ» ስላመጸበት ያጺብን በ«አጋንንት አለቃ ሖሮኑ» ዕጅ ያስገድለዋል። መደምደምያው ያለበት የጽላቱ መጨረሻ ክፍል ተሰብሮ ጠፋ።

እነዚህ ሕዝቦች - «ሐበር» እና «ኡዱም» - እንዲሁም ትውፊቱን የጻፉት የኡጋሪት ሰዎች - በብዙ አማልክት ያመኑ አረመኔዎች ቢሆኑም እንደ እብራውያን በመምሰል የ«ኤል» አምልኮት በድረው ከአምላኮቻቸው መካከል ያኖሩት ነበር። ሴት ጣዖቷም «አጢራት» ብዙ ጊዜ «አሸራሕ» ተብላ በእብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ከጣዖታት ሲያስጠንቀቅ ትገኛለች፤ በአማርኛ ብሉይ ኪዳን ይች ስያሜ «አስታሮት» ሲሆን ብዙ ጊዜም እንደ «ማምላኪያ ዐፀዶች» ወይም በመሰለው ይተረጎማል። «ሐበር» እና ጎረቤቱ «ኡዱም» ደግሞ ሐቢሩ / እብራዊ እና ኤዶም(ያስ)ን በጣም በመምሰላቸው ይሄ ትውፊት በሥነ ቅርስ በተገኘው ጊዜ ብዙ ትኩረት አገኘ። የዛሬውኑስ ሊቃውንት ግን መጽሐፍ ቅዱሱን በምንም ማጽደቅ ስለማይወዱ አሁን ከሐቢሩና ኤዶም ሌሎች መፍትሄዎች አግኝተዋል።

ከሐቢሩ ወገን መካከል የሑርኛ ቋንቋ እስከዚያ ድረስ በሰፊ እንደ ተነገረ ይመስላል። ስለዚህ ለነዚህ ስምንት አመት የሚታኒ አረመኔ መስፍን ኪርታ የሑራውያንን ነገዶች እያዋኸደ እስከ ከነዓን ምድር ድረስ እንዳስፋፋ በቀላሉ ሊታሠብ ይቻላል።