እቴጌ ምንትዋብ
==
እቴጌ ምንትዋብ | |
---|---|
ባለቤት | ዐፄ በካፋ ምልምል ኢያሱ |
ልጆች | ዳግማዊ ዓፄ ኢያሱ ወይዘሮ አስቴር ወለተ እስራኤል ወይዘሮ አልጣሽ |
ሙሉ ስም | ንግሥት ብርሃን ሞገስ (የዙፋን ስም) ወለተ ጊዮርጊስ (የክርስትና ስም) |
ሥርወ-መንግሥት | ሰሎሞን |
አባት | ደጅአዝማች መንበር |
እናት | ልዕልት እንኳይ |
የተወለዱት | ፲፯፻፮ ዓ.ም. እ.ኤ.አ |
የሞቱት | ግንቦት ፳፯ ቀን ፲፯፻፸፫ ዓ.ም. እ.ኤ.አ |
የተቀበሩት | ደብረ ፀሐይ ማርያም |
ሀይማኖት | የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና |
==
እቴጌ ምንትዋብ በዙፋን ስሟ ብርሃን ሞገስ በ1698 ዓ.ም. ከአባቷ ደጅአዝማች መንበር እና እናቷ ልዕልት እንኮይ በቋራ፣ ጎንደር ስትወለድ የክርስትና ስሟ ወለተ ጊዮርጊስ ነበር። እናቷ ልዕልት እንኮይ ከዓፄ ሚናስ ዘር የምትወለድ እንደነበረች ይጠቀሳል[1]። ምንትዋብ በ18ኛው ክፍልዘመን ኢትዮጵያ ላይ ብዙ አሻራ ትታ የለፈች ንቁ፣ ሃይለኛና ተራማጅ መሪ ነበረች። ከባሏ ዓፄ በካፋ ዘመን ጀምሮ እስከ ልጇ ዳግማዊ ዓፄ ኢያሱ እና ልጅ ልጇ ዓፄ እዮዋስ ዘመን ድረስ ለ40 አመታት የአገሪቱ እኩል መሪ የነበረች ናት። በዚህች መሪ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የህንጻዎች ግንባታና የቤተክርስቲያን ድረሰት፣ እንዲሁም ስነ ጥበብ እድገት ታይቷል። በፋሲል ግቢ የመጨረሻውን ግንብ ያስገነባችው ምንትዋብ ነበረች። ከልጆቿ የእድሜ አናሳነትና እራሷም በሰራቻቸው አንድ አንድ ስህተቶች ምክንያት በስልጣን በነበረችበት ዘመን የነበረው እድገትና ሰላም እርሷ ስታልፍ አብሮ አለፏል። እንግዴህ አገሪቱ ወደ ዘመነ መሳፍንት የተሻገረችው ልክ እርሷ እንዳለፈች ነበር።
ዐፄ በካፋ በህዝብ ዘንድ ክብርን ካስገኘለት ስራው አንዱ ብዙ ጊዜውን በመሰዋት፣ እራሱን ደብቆ በግዛቱ ሁሉ እየተዘዋወረ ስህተት የተሰራውን ማቃናቱ ነበር። [2] በዚህ ሁኔታ አንድ ቀን ተደብቆ ከጣና ሃይቅ በስተ ምዕራብ ሲጓዝ ቋራ ላይ ወባ ታመመና ከአንድ ገበሬ ቤት አረፈ። የስኮትላንዱ ተጓዥ ሐኪም ይጋቤ ሲተርክ "ወጣቷ ምንትዋብ ከመጠን በላይ ቆንጆ፣ ተግባቢና ልዝብ" [3]የነበረች ሲሆን በካፋ ታሞ ያረፈበት ቤት ባለቤት ልጅ ነበረች[4]። ምንትዋብ ታማሚውን ንጉሥ ተንክባክባ ለጤንነት ስላበቃችው ጳጉሜ5፣ 1716 (እ.ኤ.አ) ላይ ወደ ጎንደር ከተማእንዳስመጣትና እንዳገባት ይዘግባል። በ1717 ዳግማዊ አጼ ኢያሱን ወለደች። ከዚህ በኋላ ለ2 አመት ጎንደር ከተማ ተቀምጣ በመካከሉ በ1718 ወደ ወልቃይት እንድትሄድ ተደረገ። ምንም እንኳ ከሁለት ወር በኋላ ብትመለስም ልጇ ግን ወደ ሰሜን ሽሬ፣ ትግሬ ተልኮ በዚያ እስከ 1730 መኖር ቀጠለ[5]።
አጼ በካፋ በ1722 ዓ.ም. ሲሞት የከተማው ህዝብ ሞቱን ሊቀበል አልቻለም። ለዚህ ምክንያቱ ከአሁን በፊት ንጉሱ ሳይሞት የሞተ በማስመሰል ህዝቡ ላይ ሽብር በመፍጠሩ ነበር። ምንትዋብም ባሏ ሲሞት የህዝቡን ጥርጣሬ በመጠቀም ውስጥ በማስገባትና ከቋራ አምስት ወንድሞቿ መጥተው የቤተመንግስት ስልጣን እስኪጨብጡና እስኪያረጋጉ ድረስ የንጉሱን ሞት ደብቃ ቆየች[6]። ከወንድሞቿ መምጣት በኋላ እርሷና ዘመዶቿ ሆነው የ 7 አመት ልጇን ኢያሱን ለማንገስ ቻሉ። ከ2 ወር በኋላ ታህሳስ 15፣ 1722 ላይ የልጇን ህጻን መሆን በማስታከክ እራሷ ላይ ዘውድ በመጫን በንግሥት ሥልጣን እንደራሴነቷን አሳወጀች[7]። ለሚቀጥሉት 40 አመታት እርሷና ወንድሟ ወልደ ልዑል ከንጉሥ ልጇና ልጅ ልጇ ጋር እኩል ተሰሚነት ኑሯቸው አገሪቱን ለማስተዳደር በቁ፡፡ አንዳንዶች ይህ በዝምድና የተተበተበ አመራርና ያስከተለው የዘር ፉክክር አገሪቱን ለዘመነ መሳፍንት ያበቃ ተግባር ነበር ሲሉ ይታዘባሉ[8]።
ምንትዋብና ልጇ ይከተሉት የነበረው ፖሊሲ ፊት ለፊት መጋፈጥ ሳይሆን እርቅንና መስማማትን ነበር። ለዚህ ተግባር እንዲረዳት፣ በጣም ቆንጆ የሚባሉ ሶስት ሴት ልጆቿን (ከበካፋ ሞት በኋላ ካገባችው ምልምል ኢያሱ የተወለዱ) በዘመኑ ኃይለኛ ለተባሉ የጎጥ መሪወች በመዳር (ወለተ እስራኤልን ለጎጃም ጦረኛ ደጃች ዮሴዴቅ ወልደ ሃቢብ (1751)፣ ወይዘሮ አልጣሽን ለሰሜን ባላባት ወልደ ሃዋርያት (የራስ Michael Sehul ልጅ)1747 እና ወይዘሮ አስቴርን ለትግሬ መሪ ራስማርያም ባሪያው1761) በመዳር በግዛቷ ስላም አስፍና ነበር[9]። ንግስቲቱ በማዕከላዊው መንግስት ሹም ሽረት ብታደርግም ራቅ ብለው የሚገኙት ክፍሎች ግን በራሳቸው እንዲተዳደሩ አድርጋ ነበር። የኦሮሞ ቡድኖች ወደ ሰሜን የሚያረጉትን ዘመቻ ስላቋረጡ በደቡብ በኩል መረጋጋት ተከስቶ ነበር። በሌላ ጎን፣ በደቡብ የተወሰዱ መሬቶችን ለማስመለስ ምንም አይነት ዘመቻ በዚህ ዘመን አልተካሄደም። ስለሆነም ከጊዜ ወደጊዜ ራቅ ያሉ ስፍራወች ኢ-ጥገኝነታቸው እየጎላ ሄደ። ከነበረው አጠቃላይ ሰላም አንጻር ልጇ እያሱ ወደ ሰሜን የሚያደርገው ዘመቻ የፖለቲካ ሳይሆን ለአደንና መሰል ክንውኖች ነበር[10]።
በልጇና በልጅ ልጇ ዘመናት ለ40 ዓመት ስትነግስ ያከናወናቸቻው ስራወች ብዙ ነበሩ። ምንትዋብ በባህሪዋ ተራማጅና ንቁ ነበረች። በቤተክርስቲያን ተነስቶ በነበረው የቅባት እና ተዋህዶ ክርክር ለማስታረቅ ያደረገችው ጥረት የተሳካ ነበር። ስለሆነም ከሞላ ጎደል በአስተዳደሯ ወቅት ሃይማኖታዊ ስላም ነግሶ ነበር።[11] ከሌሎች መንፈሳዊ ስራዎቿ ውስጥ ብዙ አብያተ-ክርስቲያናትንና ግንቦችን በማነጽ እንዲሁም በግሏ እየተከታተለች ድርሰቶችን በማስደረስ ስሟ ይጠቀሳል።
እቴጌ ምንትዋብ በተለያዩ ምክንያቶች እራሷን ከጎንደር ከተማ ለማራቅ ጥረት አድርጋለች። የዚህ ጥረት ውጤት ከጎንደር ከተማ 3 ኪሎሜትር ራቅ ብሎ በሚገኘውደብረ ፀሐይ (ቁስቋም) ያሰራቻቸው ህንጻወች ናቸው። የስኮትላንድ ተጓዥጄምስ ብሩስ (ሃኪም ይጋቤ) በኒህ ህንጻወች አንድ ክፍል ተሰጥቶት ይኖር ነበርና ስለቁስቋም ሲጽፍ 3 ፎቅ የሆነ ቤተመንግስት፣ ክብ የሆነ ቤተክርስቲያንና ብዙ የተለያዩ የሰራተኞችና ዘበኞች ቤቶች እንዲሁም ግብዣ ቤት በአንድ ማይል ዙርያ በታጠረ ግቢ ይኖር እንደነበር አስፍሯል[12]። እነዚህን ቤተመንግስቶችና ቤተክርስቲያኖች ከ1723 ጀምራ በማሰራት በ1732 ነበር ያስመረቀቻቸው[13]።
በግቢው ውስጥ የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን፣ ደብረ ፀሐይ ማርያም ይባላል። በጄምስ ብሩስ ግምት፣ ኢትዮጵያ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሃብታም የነበረና ብዙ ምርጥ ምስላትንና በወርቅና በብር የተሰሩ የቤተክርስቲያን መገልገያ ዕቃወችን የተመላ ነበር[14]። የተገነባውም በአናጢዎችመሪ በጅሮንድ ኢሳያስ እና አዛዥ ማሞ፣ አዛዥ ህርያቆሳና አዛዥ ናቡተ መሪነት ነበር። ቤተክርስቲያኑ በቀይ ሃር አሸብርቆ በዙሪያው 380 መስታውቶች ተተክለውት ብርቅርቅታው ጎንደር ከተማ ድረስ ይታይ ነበር[15]። ነገር ግን ቤተክርስቲያኑና ሌሎች በግቢው የነበሩ ህንጻወች በሱዳን ወራሪ መሃዲስቶች፣ በ1880 ተቃጠሉ። አሁን በጊቢው የሚገኘው ቤተክርስቲያን በዚህ ፍርስራሽ ላይ የተሰራ ነው።
የአቡነ እውስጣጢዎስን ቤተክርስቲያን ሐምሌ 1729 ላይ አሰርታ ለማስመረቅ ችላለች[16]።ጣና ሃይቅ በሚገኘው ደጋ ደሴት እንዲሁ የራሷ የሆነ ቪላ የነበራት ሲሆን በዚሁ ደሴት ለቅዱስ እስጢፋኖስ መታሰቢያ ያሰራችውን ቤተ ክርስቲያን በ1739 ለማስመረቅ ችላለች። በተረፈም በርሷ ዘመን በስዕል ያጌጡ ድርሳናትና አጠቃላይ ስነ ጥበብ የሚበረታቱ ስለነበር ከዚሁ ዘመን የሚመነጩ የስነ ጥበብ ውጤቶች እጅግ ብዙ ናቸው[17]።
ምንትዋብ እጅግ መንፈሳዊ ነበረች። ለዚህ ስትል ብዙ መንፈሳዊ ስራወችን በገንዘብ ትደጉም ነበር። ብዙ መጻህፍት በዚህ ዘመን ተጽፈዋል፣ ከአረብኛም ተተርጉመው ወደ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የተሰራጩት ብዛት ስፍር ቁጥር የለውም[18]። ለስነጥበብ ከነበራት ትኩረትና ከምታደርገው ድጎማ የተነሳ በዚሁ ዘመን በድንገት የተፈጠረ ልዩ አይነት የሥነ-ስዕል ስራ ተጀመረ። ይህ እንግዲህ በውጭ ሃገር የኪነት አጥኝወች ዘንድ ሁለተኛው የጎንደሪን የስነስዕል ስልት የሚባለው ነው። [19] በአዲሱ ስልት ሥነ ሰዕል የቀጥተኛ መስመሮች ጥንቅር መሆኑ ቀርቶ በጎባጣ መስመሮች ጥንቅር የሚሰራና በህብረ ቀለማት የደመቀ ሆነ። የእውነተኛ ሰወች የሚመስሉ ምስሎችም መታየት ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ በጣና ሃይቅ በአሰራችው ናርጋ ስላሴ ቤተክርስቲያን እና በቁስቋሙ ደብረፀሐይ ማርያም ግድግዳወች ላይ አይን የሚስቡ ምስሎች ተሰርተው ነበር። ሆኖም ብዙወቹ በመሃዲስት ሱዳኖች ሲወድሙ ንግስቲቱ በራሷ ክትትል ያስደረሰችው መጽሐፈ ራዕይ የትሰኘው በምስል ያሸበረቀ መጽሓፍ አሁን እንግሊዝ አገር ስለሚገኝ የአዲሱ የሥነ ሥዕል ስርዓት ቅርስ ከጥፋት ድኖ አሁን ቅርሱን መዝግቦ ይገኛል።
አጼ በካፋ ከሞቱ በኋላ ከተወሰኑ ወንዶች ጋር ለአጫጭር ጊዜያት ትወጣ ነበር ተብላ ትታማ ነበር። በመጨረሻ፣ ምንም እንኳ ግራዝማች እያሱን ብታገባም የአማቷ ልጅ ከሞሆኑም በላይ ከእርሷ በድሜ ስለሚያንስ "ምልምል እያሱ" በሚል የሽሙጥ ስም ይታወቅ ነበር። ከዚህ ምልምል እያሱ 3 ሴት ልጆችን ስታተርፍ እነርሱም ልዕልት አስቴር፣ ልዕልት ወለተ እስራኤልና ልዕልት አልጣሽ ይባሉ ነበር። [20]። ልጇ ዐፄ እያሱ ይህን ምልማል እያሱን ይጠላው ነበር፤ ስለሆነም አንድ ቀን ለሽርሽር እንውጣ ብሎት ጣና ሃይቅ አካባቢ በአሽከሮቹ ተገፍትሮ ገደል ውስጥ እንዲሞት እንዳደረገ ይጠቀሳል[21]።
ታሪክ ፀሐፊው ተክለ ጻድቅ መኩርያ እንደዘገበ፣ ሺህ ነዋ የሚለው ቀልድ ከምንትዋብ የግብዣ አዳራሽ ነበር የፈለቀው[22]። በተረፈ ንግስቲቱ በአንዱ ቅድም አያቷ ፖርቱጋላዊ ነበረች ተብላ ስለምትታማ ለካቶሊኮች ታደላለች የሚል ግንዛቤ በጊዜው ነበር[23] ።
በኢትዮጵያ ታሪክ፣ በተደጋጋሚ እንደሚታየው፣ የህጻናት ስልጣን ላይ መውጣት አገሪቱን ከጥንት ጀምሮ ለውድቀት የዳረገ ነበር። የዳግማዊ አጼ ኢያሱና የልጁ የኢዮዋስ በህጻንነታቸው መንገስ ከዚሁ እውነታ የተለየ አልነበረም። አጼ በካፋ ሲሞት ልጁ ኢያሱ መንገሱ ህጋዊ ቢሆንም ህጻን ስለነበር ሃይል ለማግኘት የግዴታ ከሌላ ቦታ የፖለቲካ መሰረት ማግኘት ነበረበት። ስለሆነም እናቱ እቴጌ ምንትዋብ የምትተማመንባቸው የቋራ ዘመዶቿን በቤተ መንግስት ሾመች። ለምሳሌ፡ ወንድሟ ወልደ ልዑልን በራስ ማዕረግ። በዚህ ስራዋ ቀደምት በጎንደር ከትማ ስልጣን የነበራቸው ባላባቶች በጣም ጠሏት። ስለሆነም ከ1735-1736 እርሷንና ልጇን ከስልጣን ለማስወገድ ባላባቱ ሞከርው አመጹ ስለከሸፈ ይብሱኑ የቋራ ዘመዶቿን በከፍተኛ ስልጣንና በሰራዊቱ ላይ ሾመች [24]። ስልጣኗ እንዳይናጋ፣ የባላባቱን ኃይል በየጁወች ሃይል ለማጣፋት በማሰብ[25] ልጇ አጼ ኢያሱን ለየጁ ባላባት ልጅ የሆነችውን ውቢት ( ክርስትና ከተነሳች በኋላ ወለተ ቤርሳቤሕ) ዳረች[26]። ሆኖም ግን ንጉሱ ክርስቲያን ያልሆነች የየጁ ሴት አገባ ተብሎ ይታማ ስለነበር ጋብቻው በከተማው እርሱን ያስጠላና ድብቅ እንጂ በግልጽ የሚካሄድ አለነበረም። በመካከሉ ቤርሳቤሕ ቀስ በቀስ የየጁ ዘመዶቿን ልክ ምንትዋብ የቋራ ዘመዶቿን በቤተመንግስት እንደሰገሰገች ታደርግ ነበር። በዚህ ሁኔታ በየጁዎችና በቋራዎች የለሆሳስ ፉክክር ተጀመረ። ዳግማዊ አጼ ኢያሱ በ1747 ሲሞትና ከቤርሳቤሕ የወለደው ልጁ እዮዋስ ሲነግስ ምንትዋብ መልሳ እንደራሴነቷን አጸናች።
ቤርሳቤሕ በበኩሏ ልክ ምንትዋብ የኢያሱ ሞግዚት እቴጌ እንደነበረች፣ እርሷ በተራዋ ለእዮዋስ እንደራሴነት(እቴጌነት) ይገባኛል በማለቷ በሁለቱ ጥል ተነሳ[27]። በዚህ ወቅት አጼ እዮዋስ አያቱን ምንትዋብን ከመደገፍ ይልቅ የቤርሳቤህና የየጁዎች ወገን ሆነ። ውዝግቡ በ1759ዓ.ም. ወደ የርስ በርስ ጦርነት አመራ። በዚህ ጦርነት፣ የየጁም ሆነ የቋራ ክፍሎች ሃይላቸው ስለተዳከመ፣ ከትግሬ ገዢ ራስ ሥዑል ሚካኤል እገዛ ፈለጉ። ሥዑል ሚካኤል መጀመሪያ የንጉሱና የጁወች ደጋፊ የሆነ ቢሆንም በምንትዋብ የዲፖሎማሲ ስራ ኋላ የርሷ አጋር በመሆን አቋሙን ቀየረ[28]። በስተመጨረሻ 1769 ላይ ሥዑል ሚካኤል፣ አጼ እዮዋስ የጁወችን በጦርነት ደግፏል በሚል ክስ እንዲገደል አደረገ። የንጉሱ መገደል በአገሪቱ ሲሰራበት የነበረውን ትውፊት የቀየረ እንግዳ ስራ ነበር። እንግዲህ እስከ ብዙ ዘመን ድረስ የነበረውን የንጉስ ክብር የነካ ስለነበር የሚፈራ አንድ ሃይል በመታጣቱ አገሪቱ ወደ ዘመነ መሳፍንት - ሁሉ በሁሉ ጦርነት ገባች።
ምንትዋብ፣ ምንም እንኳ የየጁዎች ዋና ተቃዋሚ የነበርች ብትሆንም፣ የልጅ ልጇን መገደልና የሥዑል ሚካኤልን መግነን በመጥላት 1762 ላይ ወደ ጎጃም ሸሽታ ከሄደች በኋላ 1763 ተመልሳ ከጎንደር 3 ኪሎ ሜትር ሰሜን-ምዕራብ በሚገኘው ቁስቋም ባሰራችው ቤተ መንግስት ኑሮ ጀመረች። ከዚህ በኋላ ሃይሏ በመዳከሙ አገሪቱ ቀስ በቀስ እየተከፋፈለች ወደ ዘመነ መሳፍንት ስትሻገርና በስልጣን ትሥሥር ያስቀመጠቻቸው ዘመዶቿ ሲዋረዱ ከማየት በስተቀር ምንም ማድረግ አቅቷት ግንቦት ፳፮ ቀን ፲፯፻፷፭ ዓ/ም አረፈች[29]።
ዓፄ ሚናስ | እቴጌ አድማስ ሞገሳ | ||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||
አቤቶሁን ይስሐቅ, ቆይቶ ዓፄ ሠርፀ ድንግል | አቤቶሁን ዘሃዋርያት | አቤቶሁን ወልደ ሃዋርያት | አቤቶሁን ፍቅጦር | ወይዘሮ ማርታ ወንጌል ዘ-ባድ | |||||||||||||||||||||||||||||||||||||||
ዘ ክርስቶስ ሠርፀ | ወይዘሮ ነጻይት | የላስታ እና ሰሜን ዋግሹም ገብረ ስዩም | ? | ||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||
አቤቶ ላዕከ ማርያም ዘብሔረ ገንዝ | ወይዘሮ ወለተ ማርያም | ||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||
አቤቶ ዛስላሴ ዘብሔረ ወለቃ | ወይዘሮ ቅድስተ ክርስቶስ | ||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||
አዛዥ ዳሞ | ወይዘሮ ክርስቶሳዊት | ||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||
አቤቶ ዋክሶስ የቡላው | ወይዘሮ ዮልያና | ||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||
ደጃዝማች መንበረ የደምበያው | ወይዘሮ እንኮየ | ||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||
ምንትዋብ | |||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||
- ^ ታሪክ ወንግሥት ብርሃን ሞገሳ
- ^ Edward Ullendorff, p. 81
- ^ James Bruce, page 599 - 611
- ^ Stuart C. Munro-Hay, page 158
- ^ Stanislaw Chojnacki
- ^ ተክለጻድቅ መኩሪያ፣ ገጽ ፫፻፶፮
- ^ Stanislaw Chojnacki
- ^ Stanislaw Chojnacki
- ^ ተክለጻድቅ መኩሪያ፣ ገጽ ፫፻፷፰
- ^ Stanislaw Chojnacki
- ^ James Bruce
- ^ Stuart C. Munro-Hay, page159
- ^ Stanislaw Chojnacki
- ^ James Bruce
- ^ Stuart C. Munro-Hay, page159
- ^ Stanislaw Chojnacki
- ^ Stanislaw Chojnacki
- ^ ተክለጻድቅ መኩሪያ፣ ገጽ ፫፻፷፪
- ^ McEwan, Dorothea, page 2
- ^ James Bruce
- ^ ተክለ ጻድቅ መኩርያ፣ ገጽ ፫፻፷፰
- ^ ተክለ ጻድቅ መኩርያ፣ ገጽ ፫፻፷፬
- ^ James Bruce
- ^ Harold G. Marcus, page 46
- ^ Harold G. Marcus, page 46
- ^ ተክለጻድቅ መኩሪያ፣ ገጽ ፫፻፷፰
- ^ Stanislaw Chojnacki
- ^ ተክለጻድቅ መኩርያ፣ ገጽ ፫፻፷፬
- ^ Stanislaw Chojnacki
- ^ ታሪክ ወንግሥት ብርሃን ሞገሳ
- Edward Ullendorff, The Ethiopians: An Introduction to Country and People, second edition (London: Oxford Press, 1965), p. 81 (እንግሊዝኛ)
- Harold G. Marcus, A History of Ethiopia, University of California Pres, Berkley, 1994 (እንግሊዝኛ)
- James Bruce, Travels to Discover the Source of the Nile, 3rd ed., vol II, Edinburgh, 1813 (እንግሊዝኛ)
- McEwan, Dorothea, Illuminated Manuscripts In Ethiopia: Origin, Meaning and Manufacture of two Manuscripts Illuminating the Apocalypse in Qwesqwam and Derasge Mariyam (እንግሊዝኛ)
- Stuart C. Munro-Hay, Ethiopia, the unknown land: a cultural and historical guide, (እንግሊዝኛ)
- Stanislaw Chojnacki, The Encyclopaedia Africana Dictionary of African Biography. Volume One Ethiopia-Ghana,1997, New York, NY. (እንግሊዝኛ)
- ተክለጻድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከዐፄ ልብነ ድንግል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ ፪/፪
- ታሪክ ወንግሥት ብርሃን ሞገሳ - ወይንም - የእቴጌ ምንትዋብ ዜና መዋዕል
-
እቴጌ ምንትዋብ
-
እቴጌ ምንትዋብ ለማርያምና ለልጇ ስትሰግድ
-
ቁስቋም የሚገኘው የምንትዋብ ቤተ መንግስት ውስጣዊ ክፍል (በሱዳኖች የፈረሰ)
-
የእቴጌ ምንትዋብ ቤተመንግስት በቁስቋም በአሁኑ ዘመን