Jump to content

ሚናስ

ከውክፔዲያ

==

ዓፄ ሚናስ
ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ግዛት ከ1559 እስከ 1563 እ.ኤ.አ.
ቀዳሚ ዓፄ ገላውዴዎስ
ተከታይ ዓፄ ሠርፀ ድንግል
ባለቤት እቴጌ አድማስ ሞገሴ
ሙሉ ስም ቀዳማዊ አድማስ ሰገድ (ዙፋን ስም)
ሥርወ-መንግሥት ሰሎሞን
አባት ዓፄ ልብነ ድንግል
እናት እቴጌ ሰብለ ወንጌል
ሀይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና

==


የአጼ ሚናስ ዜና መዋዕል እዚህ ላይ [1] በመጫን የመጽሐፉን ገጾች በግዕዝና በፖርቱጊዝ ማንበብ ይችላላሉ

ዓፄ ሚናስ በዙፋን ስማቸው ቀዳማዊ አድማስ ሰገድ ከ1559 እስከ መጋቢት 1፣ 1563 እ.ኤ.አ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩ መሪ ናቸው። የአጼ ገላውዲዎስ ወንድም ሲሆኑ የአጼ ልብነ ድንግል ልጅም ናቸው።

አህመድ ግራኝ ጦርነት ዘመን ህጻኑ ሚናስ በምርኮ ተያዘ። ሆኖም ግን ከሌሎች እስረኞች በተለየ መልኩ በግራኝ አህመድ ሚስት በድል ወምበሬ እንደተያዘ ታሪክ ያትታል። በእስር ዘመኑ ሚናስ የባቲ ድልወምበሬን ልጅ አግብቶ ይኖር ነበር። ሆኖም ግራኝ አህመድ በ1542 ከየመን እና መሰል እስላም አገሮች ለሚያደርገው ጦርነት እርዳታ ለማሰባሰብ ሲል ሚናስንንና ሌሎች ውድ ስጦታወችን ለየመኑ ሱልጣን ዘቢድ ፓሻ ላከ [1] ሆኖም ግን በወይናደጋ ጦርነትግራኝ አህመድ ጦር ሲሸነፍ የግራኝ ልጅ በሚናስ ወንድም በአጼገላውዲወስ ተማረከ። ይህን እስረኛ በመጠቀም ገላውዲወስ ወንድማቸውን ሚናስን ከየመን አገር በእስረኛ ልውውጥ እንዲመጣ አደረጉ። በዚህ ጊዜ በአገሪቱ ለብዙ ቀናት ከፍተኛ ደስታ እንደነበር ታሪክ ተመራማሪ ሪቻርድ ፐንክኽርስት መዝግቧል፡፡[2]

የአገዛዝ ዘመን

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አጼ ገላውዲወስ በስቅለት ቀን፣ 1559 ጦርነት ላይ ሲያርፍ፣ ጎጃም ውስጥ ከደብረወርቅ በደቡባዊ ምዕራብ በኩል በሚገኘው መንግስተ ሰማያት በተባለ ቦታ ሚናስ ወንድሙን ተክተው ነገሱ። በነገሰ ወዲያው ሰሞን ከእናቱ እቴጌ ሰብለ ወንጌል ቀድማ ሚስቱ እቴጌ አድማስ ሞገሴ (ስሉስ ሃይሌ) ተሰሚነት እንዳላት አወጀ። እቴጌ ሰብለ ወንጌል ግን በባሉዋ አጼ ልብነ ድንግል ጀምሮ ብዙ ውጣ ውረድን ያሳለፈችና በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ መወዳድ የነበራት ንግስት ስለነበረች ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ስራው ንጉሱ ውለታ እንደማያውቅ ግድየለሽ በህዝቡ ዘንድ እንዲታይ አደረገው። [3]

የካቶሊኮች ጥል

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከገላውዲወስ ጋር ግራኝን የወጉት ፖርቹጋሎች ቀስ ብለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በሮማው ካቶሊክ እምነት ስር ለማድረግ ሰበካ ማድረግ ጀመሩ። ይህ ሁኔታ ከንጉሱ ጋር ጥል ፈጠረ። በዚህ ምክንያት የካቶሊኮቹን ጳጳስ አንድሬ ኦቪዶአክሱምና በአድዋ መካከል ወደሚገኘው ማይ ጎጋ የተባለ ስፍራ ተባረረ። ይህ ቦታ በኋላ በጀስዩቶቹ ፍሪሞና (ከፍሪምናጦስ ስም የተወሰደ) ብለው የሰየሙት ክፍል ነበር። በፋሲለ ደስ ዘመን እንደገና ካቶሎኮች የተባረሩበት አገር ነው።

የሐማሴን ገዢ ይስሃቅ አመጽ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከካቶሊኮቹ ጋር የነበረው ጥል የበለጠ እንዲካረር ያደረገው እንዲህ ነበር፡ ሚናስ ከንገሰ ከአንድ አመት በኋላ የሃማሴን ገዥ የነበረው ባህር ንጉስ ይስሃቅ አመጽ በማነሳሳት የንጉሱ ወንድም ያዕቆብን ልጅ ተዝካረ ቃልን ንጉስ አድርጎ ሰየመው። በዚህ ወቅት ተዝካረ ቃል በፖርቹጋሎቹ የጦር መሪ ይታገዝ ነበር።[4] አመጹን ለማብረድ ሚናስ ወደ ላስታ ዘመቻ ቢያደርግም ይስሃቅ ወደ ሽሬ በማፈግፈጉ ሽሬ ላይ ጦርነት ተካሂዶ ይስሃቅ ተሸነፈ። ሐምሌ2፣ 1561 ላይ ወደ ደቡብ ያቀናው የሚናስ ሰራዊት የተዝካረ ቃልን ሰራዊት ወገራ ላይ በማጥቃት ተዝካረ ቃልን ማረከ። ወዲያውም ተዝካረ ቃል በሊማሊሞ ገደል እንዲወረወር ተደርጎ ሞተ።[5]

በህረ ነጋሽ ይስሃቅ የተዝካረ ቃልን ታናሽ ወንድም ማርቆስን ንጉስ ነው በማለት እንደገና አመጸ። በዚህ ወቅት የምጽዋ ገዥ የነበረውን የኦቶማን ቱርክ ፓሻ ኦዝሚር ድጋፍ አግኝቶ ነበር። ካቶሊኮቹ የንጉሱን ክርስቲያናዊ ደካማ ጎኖች በነዚህ ወቅቶች ሳይቀር ይሰብኩ ነበር። ስለሆነም ንጉሱ ሚናስ ከቀን ወደወቀን በነሱ ላይ ያለው ጥላቻ እያደገ ሄደ። ጳጳስ ኦቬዶ ሁለተኛ እንዳይሰብክ ቢያዘው እምቢ በማለቱ የቁም እንዲታሰር አደረገ። ፖርቹጋሎችም ኢትዮጵያውያንን ማግበት እንደተከለከሉ አዋጅ አወጀ። በኋላ ሚናስ ኦቪዶን እንደገና በማስመጣት ለምን እንዳመጸ እንዲያስረዳ እድል ቢሰጠው ጳጳሱ የሸሚዙን ኳሌታ በማውለቅ አንገቴን ቀንጥሰው አለው። ንጉሱም በንዴት ጎራዴውን ቢመዝ በእቴጌ ሰብለ ወንጌል እና በጊዜው በነበሩ መኳንንት አማላጅነት ጳጳሱ ከሞት ተረፈ። ወዲያውም የታሰሩት የፖርቹጋል ቄሶች ወደ ባህር ንጉስ ይስሃቅ ካምፕ አምልጠው ከአማጺውና ከህጻኑ ማርቆስ/ፋሲለደስ ጋር ተቀላቀሉ። የአጼ ሚናስ ንዴት በመቀጣጠሉ ወደ ሰሜን ዘመቻ አካሂዶ የባህር ንጉስ ይስሃቅን ሃይሎች ድል ቢያረግም የካቶሊኮቹ ቄሶች ግን ሽሽት ስላደረጉ ከሞት ተረፉ።

ከዚህ በኋላ ኦሮሞዎች ዶባ በተሰኘው የሸዋ ክፍል አመጽ በማስነሳታቸው ወደ ደቡብ ዘመቻ አደረገ። ሆኖም ግን በዚህ ዘመቻ ላይ የወባ በሽታ ስላጠቃው እ.ኤ.አ ህዳር 1፣ 1563 ላይ በሞት አረፈ። በተድባባ ማርያም የቀብሩ ስነ ስርዓት ተፈጸመ። [6] የተለያዩ የኦሮሞ ቡድኖች በዚህ ዘመን ወደአማራአንጎት እና በጋምድር ደረሱ። በወለጋ መስፈር የጀመሩት በዚሁ ዘመን ነበር (1562 -1570)[7]

ንጉሱ በሞተ ጊዜ ታላቅ ልጁ ሠርፀ ድንግል ንጉስ ሆነ።

የንጉስ ሚናስ ዜና መዋዕል

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ግዕዝ ተጽፎ በፖርቱጋልኛ የተተረጎመው የንጉስ ሚናስ ዜና መዋዕል እዚህ ላይ ይገኛል።


  1. ^ http://www.angelfire.com/ny/ethiocrown/minas.html
  2. ^ Richard K.P. Pankhurst, The Ethiopian Royal Chronicles (Addis Ababa: Oxford University Press, 1967), pp. 72f.
  3. ^ http://www.angelfire.com/ny/ethiocrown/minas.html
  4. ^ Letter of Emanuel Fernandez to James Leynez, dated 29 July 1562, cited in Baltazar Téllez, The Travels of the Jesuits in Ethiopia, 1710 (LaVergue: Kessinger, 2010), p. 142
  5. ^ http://www.angelfire.com/ny/ethiocrown/minas.html
  6. ^ http://www.angelfire.com/ny/ethiocrown/minas.html
  7. ^ Hubert Jules Deschamps, (sous la direction). Histoire générale de l'Afrique noire de Madagascar et de ses archipels Tome I : Des origines à 1800. Page 410 P.U.F Paris (1970);