Jump to content

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋዎች

ከውክፔዲያ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አርማ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተመሠረተበት ከታኅሣሥ ፳፩ ቀን ፲፱፻፴፰ ዓ/ም ጀምሮ በ፷፭ ዓመት ዕድሜው እስከ ፳፻፫ ዓ/ም ድረስ በጠለፋ፤ በብልሽት ወይም በአብራሪ ጥፋት ምክንያት ፷፩ አደጋዎችን አስመዝግቧል። በነዚህ አደጋዎች የ ፫፻፳፪ ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ በዓቢይነት የተመዘገቡት ጥፋቶች በ፳፻፪ ዓ/ም በሜድትራኒያን ባሕር ውስጥ የተከሰከሰውና የ፺ ሰዎች ሕይወት የጠፋበት የበረራ ቁጥር ፬፻፱ እና ፻፳፭ ሰዎችን ለሞት የዳረገው የየበረራ ቁጥር ፱፻፷፩ሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ መከስከስ ናቸው።

የብልሽት እና አብራሪ ጥፋት አደጋዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አየር መንገዱ በተመሠረተ በሁለት ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበው አደጋ፣ በዚህ ዕለት በክረምት ዝናብ ረጥቦ በነበረው የጎሬ አየር ዠበብ ማረፊያ ላይ ሲያርፍ ተንሸራቶ የተከሰከሰው ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47A-75-DL) አየር ዠበብ (ሰሌዳ ቁጥር ET-T-5) ነበር። ማኮብኮቢያውን ስቶ ደንጊያ ላይ ሲከሰከስ የደረሰበት ጉዳት አየር ዠበቡን ከበረራ ጥቅም ውጭ አውሎታል። ሆኖም ከዚህ አደጋ በኋላ የአየር መንገዱ የጎሬ ቢሮ ሆኖ አገልግሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ፫ (የሰሌዳ ቁጥር ET-T-35) ከግሪክ ርዕሰ ከተማ አቴና ስድስት አየር-ዠበብተኞችንና አሥራ አራት መንገድኞችን ጭኖ በካርቱም በኩል ወደአዲስ አበባ ለመጓዝ ከአቴና ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ ተነሳ። ካርቱም በሰላም ደርሶ ሐምሌ ፫ ቀን ሲነጋጋ የአዲስ አበባ በረራውን በጀመረ በአሥራ አምስት ደቂቃው ከጧቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ከአሥር ደቂቃ ሲሆን ሁለተኛው ሞተሩ በእሳት ተያያዘ። አብራሪዎቹ ይኼንን እሳት በመከላከያ ሊያጠፉ ሲሞክሩ ሞተሩ ፈነዳ። በዚህ ጊዜ አብራሪዎቹ በአስቸኳይ ማረፊያ ጎማዎቹን ሳያወርዱ፤ ከካርቱም ከተማ ፵፱ ኪ.ሜ. እርቀት በርሻ መሬት ላይ አሳረፉ። አየር ዠበቡ ለማረፍ ፩ሺ ጫማ ሲቀረው ሁለተኛው ሞተር ተገንጥሎ ሲወድቅ ያስከተለው መናጋት የአየር ዠበቡን የግራ ክንፍ ቁልቁል አዛብቶታል። አደጋው ያደረሰበት ጉዳት አየርዠበቡን ከጥቅም ውጭ ሲያውለው በተዓምር ግን ሁሉም ተሳፋሪዎች ተርፈዋል።

ካፕቴን መኮንን ስለዚህ አደጋ ባሠፈሩት ትንተና ላይ፤ «አይሮፕላኑ ገና በረሃው ላይ ለማረፍ ሲጠጋ አስተናጋጆቹ የአደጋ ጊዘ መውጫዎቹን መስኮቶች ከፍተዋቸው ስለነበረ፤ እንደቆመ በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ማለትም በ ፳ ሴኮንድ ውስጥ ፳ መንገደኞችና ዘጠኝ ሠራተኞች ምንም ሳይነካቸው ከሚቃጠለው አይሮፕላን ወጥተዋል። እንደ ዕድል ሆኖ ነፋሱ መንገደኞች ወደወጡበት በኩል ይነፍስ ስለነበረ የእሳቱ ወላፈን ሳይነካቸው ከአይሮፕላኑ ለመራቅ ቻሉ» በሚል አስፍረውታል። [1]

የአደጋው ምክንያት፣ አየር ዠበቡ ሲያርፍና ሲነሳ በ’ፍሬኖቹ’ መጋል ምክንያት እና የፍሬን ዘይት መፍሰስ ጎማው በመፈንዳቱ በሁለተኛው ሞተር ማዕቀፍ ውስጥ የተቀጣጠለው እሳት እንደሆነ ባለሙያዎች ገምተዋል። ካፕቴን መኮንን ደግሞ በመጽሐፋቸው ላይ ስለአደጋው የምርመራ ውጤት ባሠፈሩት መሠረት «ከካርቱም ሲነሳ የእግሮቹ ፍሬኖች እንደሞቁ ታጥፈው ኑሮ ጎማው ታፍኖ ስለቆየ ፈንድቶ ብዙ ነገሮች ስለጎዳ፣ ከፈሳች ነዳጅ ጋር ተገናኝቶ እሳት ስለተነሳ የአደጋው መነሾ መሆኑ ታወቀ።» በማለት አብራርተውታል።

በረራ ቁጥር ፫፻፸፪ (የሰሌዳ ቁጥር ET-T-18) የነበረው የ’ዳግላስ ሲ-፫ (Douglas C-47A-20-DK) አየር ዠበብ የአየር መንገዱ የመጀመሪያው የሰው ሕይወት ጥፋት የተመዘገበበት በረራ ነው። ከአዲስ አበባ ፭መቶ ፳ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደቡብ ክልል ጋሞጎፋ ዞን ጎፋ ወረዳ ውስጥ ከምትገኘው ቡልቂ አየር-ዠበብ ማረፊያ ሦስት ዠበብተኞት እና ስምንት መንገደኞች እንዲሁም የቡና ምርት ጭኖ ወደጅማ ለመብረር ከጧቱ ሦስት ሰዓት ላይ ከተነሳ በኋላ ከአየር-ዠበቡ የተላለፈው ድምጽ ሦስት ሰዓት ከአርባ ደቂቃ ላይ አብራሪው ቶማስ ሃሎክ የጅማ የራዲዮ ማስተላለፊያ እንዲከፍተለት ያስተላለፈው ጥያቄ ነበር። አየር ዠበቡ መድረሻውን በ፳፯ ተኩል ኪሎ ሜትር አልፎት ከጅማ በስተደቡብ ከሚገኝ ተራራ ጋር ፱ሺ ፬መቶ ጫማ ከፍታ ላይ ተጋጭቶ ተገኘ። በተዓምር ከዠበብተኞቹ አብራሪው ሃሎክ ብቻ ሲሞት ሌሎች አሥር ተሣፋሪዎች ተርፈዋል። አየር ዠበቡ በደረሰበት አደጋ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

የአደጋው ምክንያት (ሀ) አብራሪው፣ አሜሪካዊው ቶማስ ፒ ሃሎክ የአካባቢውን ዓየር ሁኔታ መጥፎ ቢሆንም አቃልሎ በመገመቱ እና (ለ) የአየር ዠበቡን ሽቅብ የመውጣት ችሎታ ባለማወቅ በቂ ፍጥነት ሳያገኝ የአለአቅሙ ሽቅብ ለማስወጣት መሞከሩ እንደሆነ የአደጋው ጥናት ደምድሟል።

በሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ቲ-፲፮ ተመዝግቦ የነበረው አየር ዠበብ (Douglas C-47A-25-DK ) ለአየር መንገዱ ሁለተኛው የነፍስ ጥፋት አደጋ የተከሰተበት በረራ ሲሆን፣ በግል ኪራይ ለዳሰሳ ጥናት ሦስት ዠበብተኞችንና አሥራ ስድስት መንገድኞችን ጭኖ ከአዲስ አበባ ልደታ ማረፊያ ተነሥቶ ወደ አስመራ በረራ ጀምሮ ነበር። ነገር ግን ሰንዳፋ አካባቢ ላይ የሞተሩ ተሽከርካሪ ሲያቆም አብራሪው ወደልደታ ለመመለስ ሞክሮ ነበር። ዳሩ ግን አየር ዠበቡ ወደመሬት ተከሰከሰና አስተናጋጇና አራት መንገደኞች ሕይወታቸው አልፏል።

ከፋ ጠቅላይ ግዛት (የአሁኑ ከፊቾ ሸኪቾ ዞን) ውስጥ ከሚገኘው የቴፒ አየር-ዠበብ ማረፊያ ተነስቶ ወደ ጅማ ለመሄድ ሦስት ዠበብተኞችንና አሥራ አምስት መንገደኞችን ጭኖ የነበረው ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47A-50-DL) - የሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ቲ-፩ - አየር ዠበብ ከማኮብኮቢያው ሊነሳ ሲንደረደር ባልታወቀ ምክንያት በአቅራቢያው ከነበረ ወፍጮ ቤት ላይ ተላግቷል። በዚህ አደጋ አንዲት ወጣት ስትሞት ሦስት እግረኞች ደግሞ ክፉኛ ቀስለዋል።

ሰሌዳ ቁጥሩ ኢቲ-ኤ ኤ ቲ የነበረው ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47A-25-DK) ከጥገና በኋላ በሦስት አብራሪዎች ለፈተና ከአዲስ አበባ ልደታ አየር-ዠበብ ማረፊያ ሊነሳ ሲንደረደር ወደግራ በመሳብ ከማኮብኮቢያው ጥሶ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። በጥገናው ሥርዓት ላይ የግራ እና የቀኝ መጠምዘዣ መሪዎቹ በስኅተት ተለዋውጠው መገጠማቸው የአደጋው ምክንያት ሆነዋል።

ዠበብተኞችንና ተሣፋሪዎችን አጠቃሎ አሥራ ሰባት ተሣፋሪዎችን ጭኖ ጎሬ አየር ዠበብ ማረፊያ ላይ በማረፍ አደጋ የጠፋው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቲ-ኤቢ አይ (Douglas C-47A-1-DK) አየር ዠበብ አሥራ ሰባቱም ተሳፋሪዎችና አብራሪዎች ሕይወታቸውን ያጡበት በረራ ነበር።

አዲስ አበባ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዓለም-አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሦስት አብራሪዎችና አንድ መንገደኛ ጭኖ ወደአስመራ የበረረው ዲ-ሲ- ፮ (DC-6 )የጭነት በረራ ሲሆን አስመራ ላይ ሲያርፍ የፊትም ዋናዎቹም ጎማዎች ሲገነጠሉ አየር-ዠበቡ በእሳት ተያይዞ ከማኮብኮቢያው አልፎ ሜዳ ላይ ተቀጣጥሎ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። በሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ኤ ኤ ዋይ የተመዘገበው ይኽ ዲ-ሲ- ፮ አየር-ዠበብ በአደጋው ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ ሲሆን አየር መንገዱ ዋና አብራሪውን ካፕቴን መኩሪያ በለጠን ሲያሳርፉ በስህተት/አውቀው የዓየር መግቻዎቹን (the reversers) አልተጠቀሙም ብሎ ስለፈረደባቸው ከማዕረጋቸው በሁለት ደረጃ ዝቅ ከማድረጉም በላይ ከአገልግሎታቸውም የሁለት ዓመት ቅነሳ እንዲደረግ በይኖባቸዋል።

ካፕቴን መኩሪያ በ፲፱፻፹፰ ዓ/ም በጠላፊዎች ማስገደድ በቆሞሮስ ደሴቶች አጥቢያ ሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ የወደቀው የዓየር መንገዱ በረራ ቁጥር ፱መቶ ፷፩ ምክትል አብራሪ የካፕቴን ዮናስ መኩሪያ አባት ነበሩ።

በሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ኤቢኪው (ET-ABQ ) የተመዘገበው ዲ-ሲ ፫ አየር ዠበብ ከአስመራ ተነስቶ በአክሱምጎንደር እና ባሕር-ዳር በኩል ወደአዲስ አበባ ሊሄድ የተነሳው በረራ ከአክሱም በተነሳ በ ፴፭ ደቂቃው ከጧቱ አራት ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ላይ የቀኝ ክንፉ ተገንጥሎ ሲወድቅ ተሣፍረው የነበሩት አሥራ አንዱም ሰዎች ሞተዋል። አየር ዠበቡም ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

በሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ኤቢኢ የተመዘገበው ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47B-25-DK) ሞጣ አየር-ዠበብ ማረፊያ ላይ ሲያርፍ ማኮብኮቢያውን ስቶ ሲከሰከስ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። በዚህ በረራ ላይ ስንት ሰዎች እንደነበሩ፤አደጋው በሰው አካል ወይም ነፍስ ላይ ያደረሰው ክስተት ምን እንደነበር መረጃ አልተገኘም።

በዚህ ዕለት ከወላይታ ሶዶ ተነስቶ በምዕራብ ወለጋ ዞን ወደምትገኘው በጊ ለመብረር ሦስት ዠበብተኞችንና ሃያ አንድ መንገደኞችን የጫነው ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47A-30-DL) ለመነሳት ሲያኮበክብ ተከስክሶ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። በዚህ አደጋ የዋናውና የምክትል አብራሪዎቹ ሕይወት ሲያልፍ አሥሩ መንገደኞች ቀላል የአካል ጉዳይ ደርሶባቸዋል። አስተናጋጇና የቀሩት አሥራ አንድ መንገደኞች ምንም ሳይሆኑ ተርፈዋል። በሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ኤ ኤ አር የተመዘገበው ይህ አየር-ዠበብ በዚህ አደጋ ጊዜ የ፴፩ ዓምት ዕድሜ የነበረው ሲሆን በጠቃላላው ፳፯ሺ ፰፻ ሰዓታት የበረረ አሮጌ አየር-ዠበብ ነበር።

ይህ በሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ኤቢ ኤክስ የተመዘገበው ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47-DL) ከባሕር-ዳር ወደ ደብረ ማርቆስ ስድስት መንገደኞች፤ አንድ አስተናጋጅ፤ ዋና እና ምክትል አብራሪውን ጭኖ ሲበር ከዳመና ሽፋን ውስጥ ብቅ ሲል ከፊቱ በቅርቡ ተራራ ያጋጠማቸው አብራሪዎች በሽቅብ እና ዙር በረራ ለማምለጥ በሚሞክሩበት ጊዜ የአየር-ዠበቡ ጭራ ዛፎችን ስለመታ አብራሪዎቹ ለመቆጣጠር አልቻሉም። በዚህ ጊዜ በረራው ጮቄ ተራራ ላይ በጀርባው ተከሰከሰ። ተሳፈሩትም ዘጠኝ ሰዎች መኻል አንድ መንገደኛ ብቻ ሲሞት ሌሎቹ ተርፈዋል። ኢቲ-ኤቢ ኤክስ ለ፴፫ ዓመታት በጠቅላላው ለ፳፫ሺ ፱፻፳፩ ሰዓት የበረራ አገልግሎት ከሰጠ በኋላ በዚህ አደጋ ከጥቅም ውጭ ሆነ።

በሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ኤ ኤ ኤስ ተመዝግቦ የነበረው ይህ ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47A-25-DK) አየር ዠበብ በተሠራ በ ሠላሳ ሁለት ዓመት ዕድሜው፤ ከ፴፫ሺ፻፸፪ ሰዓት የበረራ አገልግሎት በኋላ ምጽዋ አየር ዠበብ ማረፊያ ላይ በእሳት አደጋ ከአገልግሎት ውጭ ሆኗል።

በሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ኤ ዲ ሲ ተመዝግቦ የነበረው ይህ ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47B-5-DK) አየር ዠበብ በተሠራ በ ሠላሳ ሁለት ዓመት ዕድሜው፤ ከ፴፪ሺ፮፻፹፪ ሰዓት የበረራ አገልግሎት በኋላ ምጽዋ አየር ዠበብ ማረፊያ ላይ ለመነሣት ስያኮበክብ በፍንዳታ የተነሳ ተቃጥሎ ከአገልግሎት ውጭ ሆኗል።

አስመራ አየር ዠበብ ማረፊያ ሊነሳ በማኮበኮብ ላይ ሳለ የቀኝ ጎማዎች ተገንጥለው በመውደቃቸው ከአገልግሎት ውጭ የሆነው ዲ-ሲ ፮ (Douglas DC-6B)፤ ሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ኤ ኤ ዜድ አየር ዠበብ በአደጋው ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

በሰሌዳ ቁጥር ኢቲ-ኤኢጄ ተመዝግቦ የነበረው ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47B-20-DK) አየር ዠበብ አምሥት መንገደኞች፤ አንድ አስተናጋጅ እና ሁለት አብራሪዎችን ጭኖ በባሌ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ኦቦርሶ ላይ ሲያርፍ ጎማዎቹ ተገንጥለው በመውደቃቸው ከጥቅም ውጭ ሆኗል። አየር ዠበቡ ያለጎማ በሆዱ አርፎ ከንተሸራተተ በኋላ ከምስጥ ክምር ጋር ተጋጭቶ ቆመ።

ኢቲ-ኤ ኤ ፒ (ET-AAP0) ዲሲ ፫ ( Douglas C-47A-25-DK) አየር ዠበብ በኦጋዴን ውስጥ ቀብሪዳር ላይ ሲያርፍ ዋናው የግራ ጎን ማረፊያ ጎማ በመሰበሩ ከጥቅም ውጭ ውሏል።

ሰሌዳ ቁጥሩ ኢቲ-ኤቢኤፍ (ET-ABF) የነበረው ዲ-ሲ ፫ (Douglas DC-3 (R4D-1)) የተገዛው በየካቲት ወር ፲፱፻፶፬ ዓ/ም ሲሆን፤ ሁለት መንገደኞችንና ሦስት ዠበብተኞችን ጭኖ ከቲፒ ቀን ለአሥራ አንድ ሰዓት ሩብ ጉዳይ ላይ ተነስቶ የአርባ ደቂቃ በረራውን ወደ ጅማ ጀመረ። የዓየሩ ሁኔታ በዝቅተኛ ጉም የተሸፈነ ዝናባማ እና የሩቅ እይታም የተወሰነበት ነበር። አሥራ አንድ ሰዓት ከሃያ ላይ የጅማ አየር ዠበብ ማረፊያ ስለዓየር ሁኔታ ለአብራሪው የራዲዮ መልዕክት ካስተላለፈለት በኋላ ከበረራው ምንም የተሰማ ነገር አልነበረም። አየር ዠበቡ በስምንት ሺ ጫማ ከፍታ ላይ ከተራራ ጋር ተጋጭቶ አምስቱም ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ ተግኝቷል።

ሚያዝያ ፭ ቀን ፲፱፻፷ ዓ/ም አገልግሎት ላይ የዋለው ኢቲ-ኤሲዲ የመጀመሪያው የአየር መንገዱ ‘ቦይንግ’ ፯መቶ፯ (Boeing 707-360C) ነበር። በአደጋው ዕለት ሦስት ዠበብተኞችንና ሁለት መንገደኞችን ይዞ በጭነት በረራ ከሮማ ‘ፊዩሚቺኖ’ ማረፊያ ተነስቶ ሲያሸቅብ፣ ሰባት እና ስምንት ሜትር ከፍታ ላይ የዛፍ ቅርንጫፎችን በመምታቱ ወድቆ ተሰባብሮ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

በሰሌዳ ቁጥር ኢት-ኤጂኬ (ET-AGK) የተመዘገበው ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47B-10-DK) አየር ዠበብ ሦስት ዠበብተኞችንና ሃያ ዘጠኝ መንገደኞችን ጭኖ በበረራ ላይ ሳለ የዠበቡ የሃይድሮሊክ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በመክሸፉ አብራሪዎቹ በአስቸኳይ ለማረፍ ወደወላይታ ሶዶ አምርተው ሞተሩችን ካተፉ በኋላ ሲያርፉ አየር ዠበቡ ለሺ ሁለት መቶ ሜትር ከተንሸራተተ በኋላ የውሐ ቦይ ውስጥ ገብቶ ቆመ። ዳሩ ግን በዚህ ክስተት በተሳፋሪዎቹ ላይ ክፉ ጉዳት ባይደርስም አየር ዠበቡ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

ኢቲ-ኤጂኪው (ET-AGQ) በሰኔ ወር ፲፱፻፸ ዓ/ም ከሌላ አየር መንገድ የተገዛ ዲ-ሲ- ፫ (Douglas C-47A-5-DK) ነበር። ከነአብራሪዎቹ አሥራ ሦስት ሰዎችን ጭኖ በረዳት አብራሪው ቁጥጥር በሰሜን ኦጋዴን ደገሀቡር ላይ ሲያርፍ ያልተጠበቀ የነፋስ ኃይል መታው። በዚህ ጊዜ ዋናው አብራሪ አየር ዠበቡን ከምክትሉ ተቀብሎ ለማቆም ቢጥርም ማኮብኮቢያውን ስቶ የውሐ ቦይ ውስጥ ሲወረወር ማረፊያ ጎማዎቹ ተገንጥለው ወደቁ። በዚህ አደጋ በሰው ላይ የደረሰ ክፉ ጉዳት ባይኖርም አየር ዠበቡ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

የሰሌዳ ቁጥሩ ኢቲ-ኤጂፒ (ET-AGP) የነበረው ዲሲ ፫ (Douglas C-47B-10-DK) ለአየር መንገዱ አገልግሎት ላይ የዋለው በ፷ዎቹ ማገባደጃ ሁለት አመታት ውስጥ ሲሆን በአደጋው ዕለት ከአስመራ በስተ-ምዕራብ ባልታወቀ ምክንያት ወድቆ ሲከሰከስ ሦስቱም የአየር መንገዱ ሠራተኞች ሞተዋል። አየር ዠበቡም ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

የሰሌዳ ቁጥሩ ኢቲ-ኤጂዩ (ET-AGU) የነበረው ይህ ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47 A -20-DK) አየር ዠበብ ዋናውንና ምክትል አብራሪውን፤ አንድ አስተናጋጅ እንዲሁም አራት መንገደኞችን ጭኖኦቦርሶ ማረፊያ ላይ ሲያርፍ የማኮብኮቢያው ድንበር ላይ የተተከሉትን ድንጋዮች በመምታት የቀኝ ማረፊያ ጎማዎቹ በመሰበራቸው የጥገና ሥራ ከተደረገለት በኋላ ለጥቂት ወራት ወደአገልግሎት ተመልሶ ነበር። ዳሩ ግን በሌላ አደጋ ከጥቅም ውጭ ውሏል፡፡

በዚህ ኦቦርሶ ማረፊያ ላይ ኢቲ-ኤ-ኤ-ጄ ታኅሣሥ ፭ ቀን ፲፱፻፷፱ ዓ/ም በተመሳሳይ የጎማዎች መገንጠል አደጋ ከምስጥ ክምር ጋር ተጋጭቶ ከጥቅም ውጭ እንደዋለ ተዘግቧል።

ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፲፱፻፸፩ ዓ/ም - ኦቦርሶ ላይ በደረሰበት አደጋ ሰፊ ጥገና ተደርጎለት ወደአገልግሎት የተመለሰው ኢቲ-ኤጂዩ (ET-AGU) የነበረው ይህ ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47 A -20-DK) አየር ዠበብ በደቡብ-ምዕራብ ኤርትራ፣ ከባረንቱ ማረፊያ ሊነሳ ሲያኮበኩብ በአፍንጫው ተደፍቶ ሲከሰከስ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

በሰሌዳ ቁጥር ኢቲ- ኤ ኦ ፒ (ET-AOP) የተመዘገበው እና ልዩ ስሙ "ንግሥት ሣባ" የተባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አየር ዠበብ በዛሬው ዕለት በሎንዶን 'ሂዝሮው' ጥያራ ጣቢያ እንደቆመ የእሳት አደጋ ደረሰበት። ይኽ አደጋ የተከሰተው ጥያራው መንገደኞችን አሣፍሮ ከአዲስ አበባ ከገባ ከስምንት ሰዓታት በኋላ ነው። አየር መንገዱ ይኽንን ዠበብ ከቦይንግ ኩባንያ ተረክቦ አገልግሎት ላይ ያዋለው ከስምንት ወራት በፊት ኅዳር ፲፩ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ነው።

የአየር ጠለፋ እና የአመጽ ጉዳቶች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የሰሌዳ ቁጥሩ ኢቲ-ኤሲ ኪው (ET-ACQ) የነበረው የቦይንግ ፯መቶ፯ (Boeing 707-379C) Boeing 707-379C) አየር ዠበብ በአየር መንገዱ ታሪክ በሽብርተኞች የአየር ጠለፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰለባ የደረሰብት አየር ዠበብ ነበር። ከግሪክ ርዕሰ ከተማ አቴና ተነስቶ ፍራንክፈርት ዓለም አቀፍ የአየር ዠበብ ማረፊያ የደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አየር ዠበብ በቆመበት ሥፍራ ላይ በአውሮፕላኑ የቱሪስት ማዕርግ ክፍል ላይ ሁለት ፈንጂዎች ጉዳት አድርሰዋል። አየር ዠበቡን በማጸዳዳት ላይ የነበሩም ሴቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጉዳቱን ያደረሰው ‘ለኤርትራ ነጻነት-የአረባዊ ሶርያ እንቅስቃሴ’ የሚባለው ቡድን ነው ሲል የኤርትራ ነጻነት ግንባር ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገጠር ነዋሪ ኤርትራውያንን ለማጥቃት የሚላኩትን ወታደሮች ወደኤርትራ ስለሚያጓጉዝ የበቀል ጥቃት ያካሄዱት እነሱ እንደሆኑ አረጋግጧል።

ፓኪስታንካራቺ አየር ዠበብ ማረፊያ ላይ ሦስት የኤርትራ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች፣ በሰሌዳ ቁጥር ኢ.ቲ. - ኤ.ሲ.ዲ. (ET-ACD) የተመዘገበውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ ፯፻፯ - ፫፻፷ ሲ (Boeing 707-360C) አየር ዠበብ ላይ ፈንጂ ወርውረው ከፍተኛ ጉዳት አድርሰውበታል። ኦኖም አየር ዠበቡ ተጠግኖ አገልግሎት ላይ ውሏል።

መሐመድ ኢድሪስ፣ ፍስሐዬ አብርሃምና ዓሊ አብደላ የተባሉት ሦስቱም ታጣቂ አመጸኞች ሲያዙ በሰጡት መግለጫ፣ በኤርትራ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ መንግሥት አስተዳደር ተቃዋሚ መሆናቸውን ለማሳወቅ የወሰዱት የሸፍጥ ድርጊት እንደሆነ ገልጸዋል። ሦስቱም ሸፍጠኞት በድርጊታቸው ምክንያት ለፍርድ ቀርበው የአንድ ዓመት ጽኑ እሥራት ተፈርዶባቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የኤርትራ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባዮች ሐምሌ ፳፬ ቀን ፲፱፻፷፩ ዓ/ም ይፋ ባደረጉት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በ ኤርትራውያን ላይ ለሚያካሂደው የአየር ድብደባ በቀላቸውን በአየር መንገዱ ላይ ለመወጣት ሙከራቸውን ስለሚቀጥሉ በዚሁ ብሔራዊ አየር መንገድ የሚሣፈሩ መንገደኞች ለሕይወታቸው አስጊና አደገኛ እንደሚሆን በመጠቆም የአየር መንገዱን የገቢ ምንጭ ከማዳከም እንደማይመለሱ አስታውቀዋል።

በተማሪው ንቅናቄ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው፣ አንደበተ ርቱዕ የነበረው ብርሃነ መስቀል ረዳ፤ የሕግ ተማሪ የነበረው ኢያሱ ዓለማየሁ፤ ኃይለ ኢየሱስ ወልደ ሰማያት፤ ገዛኸኝ እንዳለ፤ አማኑኤል ገብረ ኢየሱስ፤ የመንግሥት ሠራተኛ የነበረው አ.አ.፤ በጠቅላላው ሰባት ሆነው ከ ባሕር-ዳር ተነስቶ ወደአዲስ አበባ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዓለም አቀፍ አየር-ዠበብ ማረፊያ (ቦሌ) ሊበር የታቀደውን ዲ-ሲ ፫ (Douglas DC-3) ወደ ካርቱም እንዲያመራ አስገደዱት። እነኚህ ጠላፊዎች የካርቱም ቆይታቸው ለደህንነታቸው ዋስትና እንደሌለው በመገንዘብ፤ የፖለቲካ ጥገኝነት በመጠየቅ ወደ አልጄሪያ መዲና አልጄርስ አመሩ።

አዲስ አበባ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዓለም-አቀፍ ማረፊያ ፴፱ መንገደኞችንና ፭ ዠበብተኞችን አሳፈሮ ወደ ጂቡቲ በመማራት ላይ የነበረው ዲ-ሲ- ፮ (Douglas DC-6) በረራ በሦስት ኤርትራውያን ተጠልፎ ወደ አደን እንዲበር ተገድዶ ወደዚያው ሲበር የአየር መንገዱ የጸጥታ ታጣቂ አንዱን አመጸኛ ተኩሶ አቁስሎታል። አደን ሲያርፉም የአገሪቱ የፖሊስ ኃይል ሦስቱንም ጠላፊዎች በቁጥጥር ሥር አዋላቸው። ጠላፊዎቹ የኤርትራ ነጻነት ግንባር አባላት እንደሆኑ ታውቋል።

እስፓኝ ርዕሰ ከተማ ማድሪድ ዘጠኝ ዠበተኞችንና አሥራ አራት መንገደኞችን ጭኖ በሮማ በኩል ወደአዲስ አበባ ጉዞውን የጀመረው ቦይንግ ፯መቶ፯ (Boeing 707) በረራ የየመን ተወላጅ የሆነ ጠላፊ ሽጉጡን መዝዞ በረራ ክፍል ውስጥ ከገባ በኋላ አብራሪውን ወደአደን እንዲያመራ ቢያዘውም ቅሉ፣ አብራሪው ለነዳጅ ሮማ ማረፍ ግድ እንደሚሆንበት አስረድቶ ነበር። የአየር መንገዱ የጸጥታ አስከባሪ በረራ ክፍል ውስጥ ገብቶ ጠላፊውን በሽጉጥ ገድሎታል። በዚህ ጊዜ ሁለተኛው ጠላፊ ጩቤውን ጨብጦ ወደበረራ ክፍሉ ሲሮጥ ሁለተኛው የአየር መንገዱ የጸጥታ አስከባሪ እርሱንም በሽጉጥ ተኩሶ ገድሎታል።

ከዚህ ክስተት በኋላ በረራው በሰላም አቴና ላይ አርፏል። የኤርትራ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ ደማስቆ ላይ ገለጻ ሲሰጥ ሁለቱ የግንባሩ አባላት ቢሆኑም ዓላማቸው አየር-ዠበቡን ለምጥለፍ ሳይሆን ስለድርጅቱ በራሪ ማስታወቂያዎችን ለማደል ነበር ብሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የ[[እስፓኝ ፖሊስ ታኅሣሥ ፩ ቀን ማድሪድ ዓለም አቀፍ ማረፊያ ላይ ሦሥተኛው አባል ነው ብለው የገመቱትን ሰው ፈንጂ ይዞ ሲገባ በቁጥጥር ስር አውለውታል።

አራት የኤርትራ ነጻነት ግንባር ሸፍጠኞች ከባሕር-ዳርጎንደር፣ ከነዠበብተኞቹ ሃያ ሰዎችን የጫነውን ዲ-ሲ፫ አየር ዠበብ በኃይል ወደ ቱኒዚያ ዋ ሁለተኛ ከተማ በንጋዚ እንዲበር ካስገደዱት በኋላ ለነዳጅ ቅጅ ካርቱም ላይ አረፈ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ፯መቶ፰ ከአዲስ አበባ ተነስቶ አስመራአቴናሮማ እና ፓሪስ ለመሄድ ከነዠበብተኞቹ ዘጠና አራት ሰዎች ጭኖ በተነሳ በአሥራ ሦስት ደቂቃዎች ከመንገደኞቹ መኻል ፭ ወንዶችና ፪ ሴቶች ሽጉጥ መዝዘው በአማርኛ ትዕዛዛቸውን ሲጮኹ የአየር መንገዱ የጸጥታ ሰራተኞች ተኩስ ከፍተው ስድስቱን ጠላፊዎች ሲገድሉ ሰባተኛው በኋላ ሆስፒታል ገብቶ ሞቷል። በተኩሱ ጊዜ ከጠላፊዎቹ አንዱ የያዘውን የእጅ ቦምብ ነቅሎ ሲጥለው ከመንገደኞቹ አንዱ ብድግ አድርጎ ሰው ወደሌለበት ሥፍራ ጥሎት ፈነዳ። ይኽ ፍንዳታ አንድ ሞተር እና የአቅጣጫ መቆጣጠሪያ ከጥቅም ውጭ ሲያደርገው የአየር ዠበቡን የመንገደኞች ክፍል በጢስ አፍኖት ነበር። ኣብራሪው ካፕቴን ቀጸላ ኃይሌ ያለምንም ድንጋጣ አየር-ዠበቡን ወደአዲስ አበባመልሰው በሰላም አሳርፈውታል። ካፕቴኑ ለዚህ ተግባራቸው ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጀግንነት ሜዳይ ከመሸለማቸውም ባሻገር በአየር ዠበቡ ተሣፍሮ የነበረውና ከእንግሊዝ ለወፎች ጥናት ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ቡድን፤ ከዚህ አደጋ ላተረፏቸው ለኚህ ካፕቴን ሎንዶን ከተማ ውስጥ ከፍ ያለ ግብዣ አድርገውላቸዋል። ጠላፊዎቹ የኤርትራ ነጻነት ግንባር አባላት ሲሆኑ መሪያቸውም በዚሁ ድርጊት የተገደለችው ማርታ መብርሃቴ ነበረች። [2]

ላሊበላ ሲያርፍ በአመጸኞች የጥይት እሩምታ የተመታው ዲ-ሲ ፫ (Douglas C-47-DL) አየር ዠበብ - ሰሌዳ ቁጥር ኢቲ- ኤቢአር - ከጥቅም ውጭ ሲሆን የአንድ ሰውም ሕይወት ጠፍቷል። አየር ዠበቡ በዚህ አደጋ ጊዜ የ፴፫ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን ለ ፴፫ሺ፮፻፳፮ ሰዓት በረራ አገልግሏል።

መቀሌ ወደ ጎንደር ሲበር ሁለት ሰዎች የከሸፈ የጠለፋ ሙከራ ያደረጉበት ዲ-ሲ ፫ አየር ዠበብ ጎንደር ላይ በሰላም አርፏል። ዳሩ ግን ሁለቱን ጠላፊዎች አጠቃሎ የሦስት ሰዎች ሕይወት አልፎበታል።

ኢቲ-ኤ-ኤፍ ደብልዩ (ET-AFW) ዲሲ ፫ (Douglas C-47B-10-DK) ለአየር መንገዱ አገልግሎት ላይ የዋለው በ፷ዎቹ ማገባደጃ ሁለት አመታት ውስጥ ሲሆን፤ በደቡብ-ምዕራብ ኤርትራ በምትገኘው ባረንቱ ላይ በቦምብ ፍንዳታ ተከስክሶ ሲወድቅ አምስቱም ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። አየር ዠበቡም ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

  1. ^ መኮንን (ካፕቴን)፤ "አቪዬሽን በኢትዮጵያ - ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ጥረትና ዕድገት፤ ገጽ ፪፻፩፤(፲፱፻፺፭ ዓ/ም
  2. ^ መኮንን (ካፕቴን)፤ "አቪዬሽን በኢትዮጵያ - ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ጥረትና ዕድገት" (፲፱፻፱፭ ዓ/ም) ገጽ ፫፻፳፯
  • ክፍሉ ታደሰ፤ ያ ትውልድ፤ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት (ዓ/ም የለውም)
  • (እንግሊዝኛ) Brief and Bloody (Time, Dec. 18, 1972)
  • (እንግሊዝኛ) The Age - Sep 15, 1969
  • (እንግሊዝኛ) Aircraft hijackings and other criminal acts against civil aviation : statistics and narrative reports / FAA
  • (እንግሊዝኛ) Brian M. Jenkins and Janera A. Johnson; International Terrorism: A Chronology (1968-1974)
  • (እንግሊዝኛ) <http://aviation-safety.net/database/record.php?id=19690311-0 Archived ማርች 21, 2016 at the Wayback Machine>. [Accessed 11 February 2011.]
  • (እንግሊዝኛ) http://www.ethiopianairlines.com/en/corporate/history.aspx Archived ሜይ 7, 2013 at the Wayback Machine
  • (እንግሊዝኛ) Criminal Acts Against Civil Aviation 1992 / U.S. Department of Tranport, FAA, Office of Civil Aviation Security