Jump to content

አቡነ ባስልዮስ

ከውክፔዲያ
ቀዳማዊ አቡነ ባስልዮስ

ቀዳማዊ አቡነ ባስልዮስ (፲፰፻፹፬ዓ/ም (ሚዳ ሚካኤል) - ፲፱፻፷፫ ዓ/ም (አዲስ አበባ)) የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና የመጀመሪያው ፓትርያርክ ነበሩ።

አቡነ ባስልዮስ ሲወለዱ የተሰጣቸው ስም ገብረ ጊዮርጊስ ሲሆን መጋቢት ፲፬ ቀን ፲፰፻፹፬ ዓ/ም ከደብተራ ወልደጻድቅ ሰሎሞንና ከወይዘሮ (በኋላ እማሆይ) ወለተማርያም ባዩ በሸዋ አውራጃ ሚዳ ሚካኤል ተወለዱ። ደብተራ ወልደጻድቅ የይፋት ቀውትጌስ ማርያም ተወላጅ ሲሆኑ፣ እማሆይ ወለተማርያም ደግሞ በመንዝ ላሎ ምድር የተወለዱ ነበር።

በሕጻንነታቸው ዘመን መንፈሳዊ ትምህርትን እየተማሩና የኮሶ ማርያምን ቤተ ክርስቲያን እያገለገሉ አድገዋል። አቡነ ባስልዮስ የአሥራ-አራት ታዳጊ ወጣት እያሉ በ፲፰፻፺፱ ዓ/ም ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገብተው ትምህርታቸውን ከመምህር ገብረ ኢየሱስ ሲከታተሉ ቆይተው በዚያው ገዳም መዓርገ-ምንኩስናቸውን እስከተቀበሉበት ድረስ ለሦስት ዓመታት በእርድና አገልግለዋል።

፲፱፻፱ ዓ/ም በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ትዕዛዝ በመናገሻ ግርጌ ለሚሠራው የማርያም ቤተ ክርስቲያን ለሚጠጉ መነኮሳትና ባሕታውያን የሚሠሩትን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳደር ረዳት እንዲሆኑ በተጠየቁት መሠረት፣ እያገለገሉና ቅዳሴ እያስተማሩ ለሦስት ዓመታት በመናገሻ ማርያም ደብር ቆዩ። [1] እዚሁም ገዳም መምህር (አበ ምኔት) ሆነው ሲኖሩ ወደሐዋርያዊነት ሥራ በመሠማራት ቆዩ።

አባ ገብረ ጊዮርጊስ (አቡነ ባስልዮስ) የኢየሩሳሌም ገዳማት አስተዳዳሪ (፲፱፻፳፭ ዓ/ም)

የመናገሻ አምባ ማርያምን ገዳም እያስተዳደሩ ሳሉ፤ ከዚህ ሥልጣናቸው በተጨማሪ የአዲስ አበባ መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም መምህርነት በየካቲት ፳፯ ቀን ፲፱፻፳፬ ዓ/ም ተሰጣቸው። ከዚያም ቀጥሎ መጋቢት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፭ዓ/ም በኢየሩሳሌም ያሉ የኢትዮጵያን ገዳማት በመንፈሳዊ መሪነት አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው ለሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ወደአገራቸው ተመለሱ። [2]


የካቲት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፯ ዓ/ም በአቡነ ተክለ ሃይማኖት መንበር፥ ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ዘነበረ በመንበረ ተክለ ሃይማኖት ተብለው፥ አምሣ-ዘጠነኛው ዕጨጌ ሆነውተሽሙ። በዚሁ በዕጨጌነታቸው ዘመን የፋሺስት ወረራ ኢትዮጵያን ባጠቃ ጊዜ፣ በጦርነቱ ግምባር ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተሰልፈው አብያተ ክርስቲያናትንና መጻሕፍትን የሚያቃጥል የምእመናንን ዘር የሚያጠፋ ጠላት መጥቷልና በሃይማኖት፤ በጸሎት፣ በምህላ በርታ እያሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያጽናኑ ቆዩ። በጦርነቱም ጊዜ የተቀመጡበት በቅሎ በአረር ተመቶ እስኪወድቅና የለበሱትም ካባ አምስት ላይ በጥይት እስኪበሳሳ ድረስ ከንጉሠ ነገሥቱ ሳይለዩ የቆራጥነት ሥራ ሠርተዋል።


ሠራዊቱም ድል ህኖ በተፈታ ጊዜ ክንጉሠ ነገሥቱ ጋር በስደት ወደኢየሩሳሌም አቅንተው እስከ ድል ጊዜ ድረስ በስደት ቆይተዋል። በዚሁ በስደት ዘመናቸውም ሳሉ በርካታ ሐዋሪያዊ መልእክቶችን ለአርበኞችም፤ ለሕዝቡም በመላክ የማጽናናትና የሃይማኖታዊ ጣምሮችን ያስተላልፉ ነበር።


ንጉሠ ነገሥቱ በስደት ከነበሩበት ከ’ባዝ’ (ብሪታንያ) ፥ ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም በጊዜው በስደት ኢየሩሳሌም ለነበሩት ወደ ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ አንድ ፅላትና ለአገልግሎት የሚበቁ አምስት መነኮሳትን ወደ እንግሊዝ አገር እንዲልኩላቸው በአባ ሐና ጅማ በላኩት ደብዳቤ መሠረት፣ ዛሬ ምስካዬ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም የተባለውን የመድኀኔ ዓለምን ጽላት ወደንጉሠ ነገሥቱ ወዳሉበት ባዝ የላኩት እሳቸው ነበሩ፡፡ [3]


ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴጥር ፲፪ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም በኢትዮጵያ ጠረፍ በኡም-ኢድላ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ-ዓላማ ሲተክሉ ዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስም አብረዋቸው ነበሩ። ከዚያም ንጉሠ ነገሥቱ በምድረ [[ጎጃም]፤ በቡሬ፤ በደብረ ማርቆስ፤ በደብረ ሊባኖስ እና በእንጦጦ በኩል አድርገው ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም አዲስ አበባ ሲገቡ ዕጨጌው ሳይለዩ አብረው ነበሩ።

ከዕጨጌነት ወደ ጵጵስና ወደ ፕትርክና

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከድል በኋላም ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር ፥ በጠላት ወረራ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት እንዲታደስና እንዲቀጥል ለማድረግ በየካቲት ወር ፲፱፻፴፬ ዓ/ም ንግግር ተጀመረ። ሆኖም የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የጵጵስና ማዕርግ የመስጠትን ልምዳዊ መብቷን ለኢትዮጵያውያን አልለቅም በማለቷ በድርድሩ ስምምነት እስከተደረሰበት እስከ ሐምሌ ፲፯ ቀን ፲፱፻፵ ቆይቶ፤ በቀድሞው ሥልጣናቸው ሲያገለግሉ የቆዩት ዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ፥ አቡነ ባስልዮስ ተብለው ከአቡነ ቴዎፍልስ፤ አቡነ ሚካኤል፤ አቡነ ያዕቆብ እና አቡነ ጢሞቴዎስ ጋር በእስክንድርያው ፓትርያርክ አቡነ ዮሳብ እጅ ተቀቡ። [4]

ግብጻዊው አቡነ ቄርሎስም ካይሮ ላይ ስላረፉ ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ጥር ፮ ቀን ፲፱፻፵፫ ዓ/ም ካይሮ ላይ በአቡነ ዮሳብ እጅ ተቀብተው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሊቀ-ጳጳሳት ሆኑ። የፓትርያርኩንም ፈቃድ ካገኙ በኋላ በሚቀጥለው ነሐሴ ወር ላይ አምሥት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳትን ሾሙ።

ግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጋር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ብዙ ጊዜ የወሰደ ድርድር ከተደረገ በኋላ ስምምነት ተደርጎ፥ እሑድሰኔ ፩ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ/ም፤ ንጉሠ ነገሥቱም በተገኙበት ሥነ-ሥርዓት ፓፓው አቡነ ቄርሎስ ፮ኛ በብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ላይ የሢመቱን ሥርዓተ-ጸሎት አድርሰው፤ የፓትርያርክነቱን ዘውድ ባርከው ደፉላቸው። ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ አቡነ ባስልዮስ በግብጽ ፓትርያርክ እጅ በዚህ ማዕርግ ሲቀቡ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ነው።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እስከ ፲፱፻፶፩ ዓ/ም ድርሰ አርባ ሁለት አብያተ-ክርስቲያነትን እንዳሠሩና አስራ ሁለት ትምህርት ቤቶችንም እንዳለሙ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ የፓትርያርኩን ሞት ተከትል ባወጣው የሐዘን ዘገባ ላይ ገልጾታል። ከነዚህም መኻል በተለይም፣ በደብረ ጽጌ ያለውን የእብነት ትምህርት ቤት በግል ገንዘባቸው ነበር የሚያስተዳድሩት (አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 3/1963 ዓ.ም.)።

ፓትርያርኩ በተወለዱ በ፸፱ ዓመት ዕድሜያቸው ጥቅምት ፪ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ/ም አርፈው ጥቅምት ፬ ቀን በደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ። አቡነ ቴዎፍሎስ ተተክተው ሁለተኛው ፓትርያርክ ሆኑ።

  1. ^ *”ዜና ባስልዮስ ሊቀ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ” (፲፱፻፶ ዓ/ም) ገጽ ፪፻፴
  2. ^ ”ዜና ባስልዮስ ሊቀ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ” ፤ (፲፱፻፶ ዓ/ም) ገጽ ፱
  3. ^ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት፣ (፲፱፻፶፱ ዓ/ም)
  4. ^ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (፲፱፻፶፮ ዓ/ም)፤ ገጽ ፳፬–፳፭