በላይ ዘለቀ

ከውክፔዲያ
በላይ ዘለቀ

[1]በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ ፦ በላይ ዘለቀ የተወለደው በጎጃም ክ/ሀገር በቢቸና አውራጃ፣ ለምጨን በተባለው ቦታ ነው። ዘለቀ ላቀው (የበላይ ዘለቀ አባት) የልጅ እያሱ አንጋች ነበሩ ። ልጅ እያሱ ሲገለበጡ ዘለቀ ላቀው ወደሚስታቸው አገር ወደ ለምጨን ሄደው ልጆቻቸውን ይዘው ወደአገራቸው ወደ ለምጨን (ቢቸና ወረዳ ) ተሻገሩ። (ቢቸና ጎጃም ውስጥ ጫቀታ ወሎ ውስጥ ከአባይ ወንዝ ማዶ ለማዶ ናቸው። ይገበያያሉም፡ ይጋባሉም።)
1916 አ.ም. ማለት በላይ ዘለቀ የ14 አመት ልጅ ሳለ ፊታውራሪ እምቢ አለ የተባለ የራስ ሀይሉ ሌባ አዳኝ (ጸጥታ አስከባሪ ) ዘለቀ ላቀውን ከበባቸው። ዘለቀ ላቀው እጄን አልሰጥም ስላሉ ተኩስ ተከፈተ። ዘለቀ ላቀውና አብረዋቸው የነበረ አለሙ መርሻ የተባሉ ወንድማቸው ከአስር ሰው በላይ ገድለው ብዙ ሰው አቆሰሉ።
«እኛ ልጆች ተኩስ ካባራ በህዋላ ተየጫካው ስንመለስ ሁለቱም ሞተዋል። የዘለቀ ላቀው ሬሳ እበቱ በራፍ ላይ ተሰቅሎዋል።» አሉ ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ። እንግዲህ በላይ ዘለቀና ተሻለ አለሙ እኩል አባቶቻቸውን አጡ ፡ አብረው የሀዘንን ጽዋ ቀመሱ ፡ እኩል በቀልን እያሰላሰሉ አደጉ ፡ በሁዋላም አብረው ጠላትን ተዋጉ።

ዘለቀ ላቀው ሲሞቱ ልጆቻቸው ወደእናታቸው አገር ወደ ጫቀታ ተመለሱ። በላይ ዘለቀ ያባቱን ደም ለመመለስ ተኩስ እየተማረ አደገ። አደገና ያባቱን «ናስ ማሰር» (ባለ ነሐስ ማሰርያ ) ውጅግራ ጠመንጃ ይዞ ወደ አባቱ አገር ወደ ለምጨን (ቢቸና)ተሻገረ።
አባቶቻቸው የተገደሉባቸው ጎረምሶች ዳኝነት እንዳይሹ ዳኛው ራስ ሀይሉ ሆኑባቸው ፡ የቀራቸው ምርጫ በቀል ነው ።
መሳርያ እየገዙ እየተዘጋጁ ለምጨን ቀንጦ ማርያም እያረሱ ፡ ቀን ይጠብቁ ጀመር። ...እንዲህ ሲል ጥልያን መጣ ...በሚያዝያ 28 ቀን (1928 አ.ም.) ለቀኛዝማች መሸሻ ጥልያን መሳርያ በአየር አወረደላቸው ። (ለጥልያን ገቡ ) ካለው ሰበካ ያዙ ። በረንታ ወረዳ (ቢቸና አውራጃ ) ደረሱ። የዱሀ ከተማ ሰፍረው ህዝቡን መሳርያ እየነጠቁ (ጥልያንን እንዳይወጋ ) ጥልያን ደግ መንግስት ነውና እንገዛለን እያሉ ይሰብካሉ (እንዲሾማቸው። )
«ልጅ በላይ ዘለቀ ግን እዋጋለሁ እንዋጋ እያለ እኛን ወንድሞቹን አነሳሳን» አሉ ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ «ቀሰቀሰን ከሰላሳ እስከ ሀብሳ ለምንደርስ ያንድ አያት ልጆች ...የገልገል ላቀው ልጆች ...ታጥቀን ተነሳን ። ከቀኛዝማች በላይ መሸሻ ሰዎች መሳርያ እየነጠቅን በረሃ ገባን።»
«ጦር ሲያሳድደን ...ስንሸሽ ...ቤት ሲያቃጥልብን ...ከሁዋላው ወይም ከጎኑ በድንገት እየመታነው መሳርያ ነጥቀን ስናመልጥ .....እንዲህ ስንል አንድ ቀን የማናልፈው ጉዳይ መጣ። ግንባር መግጠም ግድ ሆነ። ጠላት መሸሻ አሳጣና።»
«የዛሬን ጦር ማን ይምራው ?» አለን ልጅ በላይ
«አንተን መርጠናል ...እስከ መጨረሻው» አልነው።
"ሁላችሁም ወንድማማች ናችሁ።" ፊታውራሪ ተሻለን "በላይ ዘለቀን እርስዎ እንኳን በ4 አመት እበልጠዋለሁ ብለዋል። እንግዲያው በምኑ ነው አለቃችሁ እንዲሆን የመረጣችሁት?"
"እንዴ! በደግነቱ ፡ በጀግንነቱ! ጠባየ መልካም በመሆኑ! እኔ ይቅርብኝ ብሎ ለሌላው ስለሚያዝን!" (ያን ጊዜ ፡ 1928 አ.ም. ልጅ በላይ 3 ወልደዋል። ልጅ ተሻለ ግን ገና በታህሳስ ነው ያገቡ።)
ወይዘሮ ድንቅነሽ ሀይሉ (የራስ ሀይሉ ልጅ ) ጥልያን ሾመዋቸው የለም ጨጉ ጉልተ ገዥ ሆነው ሄዱ። ህዝቡን መሳርያ አግባ ብለው አሰባሰቡ። በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ በድንገት ገብተው መሳርያዎቹን ነትቀው ሴትየዋን ሳይጎዱ ሳያጎሳቁሉ ወደመጡበት መልሰው ላኩዋቸው። የነጠቁዋቸውን መሳርያ 35 ያህል ጠመንጃ ዋሻ ደበቁት። ለራሳቸው በቂ መሳርያ ይዘዋላ።

ከዚህ በሁዋላ ደብረ ማርቆስን ጥልያን እየያዘ በላይ ዘለቀን ያሳድነው ጀመር። ከ'28 አ.ም. ሚያዝያ እስከ ግንቦት 29 ቀን ድረስ ሁኔታው ተመሳሳይና ተደጋጋሚ ነበር ። ጦር ይመጣል ...ያስሳል .....እነ በላይ ዘለቀ ይሸሻሉ ...በሁዋላ ቀስ ብለው መጥተው ጥቂቱን ገድለው መሳርያ ነጥቀው ....እልም ! መሳርያ በየዋሸው ያከማቻሉ ።
እንደዚህ ብዙ አሰሳ ተሞከረ ። ባንዱ አሰሳ የበላይ ዘለቀ በትና የለምጨን ቤቶች በሙሉ ተቃጠሉ። ከብቱም ተዘረፈ። ጠላት ለምጨን 3 ጊዘ ነው ያቃጠለ።
"እስከ ታህሳስ 29 ቀን ድረስ አሰሳው የሚካሄደው በባንዳ ነበር።" በታህሳስ 8 ቀን 1929 ግብጣን ደቡብ የተባለ ጥልያን ቢቸና ገባ ቢሉን ከዱማ ገስግሰን ቢቸና አደጋ ልንጥል ስንል ካህናት ጽላት ይዘው ስእል መስቀል ይዘው "አገሩንና ታቦቱን ያቃጥልብናልና አትውጉት ። እሱን እኛ ተመለስ እንለዋለን።" ብለው መለሱን። ግብጣን ደበቡም በላይ ዘለቀ መጣብህ ቢሉት ወደማርቆስ ተመለሰ።"
የካቲት 29 ጥልያን አገሩን አስነስቶ ወረረን። ከያውራጃው ግብጣን ደበቡ አስከተተ። ጦር ሲመጣባቸው እነ በላይ ዘለቀ ሸሹ። አጥቷቸው ሲመለሱ እያደፈጠ በጎን አደጋ እየጣሉ ብዙ መሳርያ ነጠቁት።
"የግንቦት እርገት ለት ..በ29 ነበር የዋለ ..ጥልያን ራሱ መጣ" የበላይ ዘለቀን ዘመዶች ከለምጨን እየደበደቡ ወደ አርበኞቹ እንዲመሩዋቸው አስገደዱዋቸው። "ጦሩ ሲመጣ አሳለፍነው። ከጎን አደጋ ጣልንበት። በላይ ዘለቀ አንዱን ትሊንቲ ገድለው ኩረኔሉን አቆሰለው። ብዙ ባንዳዎች ሞቱ።"
ታስሮ እየተደበደበ ሲመራ የነበረው አዛዥ ቢያዝን ዱብዳ የተባለው የበላይ ዘለቀ ዘመድም ቆሰለ።
ሰኔ 29 (1929) ጠላት በቅምቧት በደጀን በገበያ በሽበል በበረንታ የነበረውን "ደንበኛ" በሙሉ አከተተው። (ደንበኛ የሚባለው "የመንግስት " የደንብ ብረት የያዘ ነፍጠኛ ነው ) ቀኛዝማች ስማ ነገዎ አዝማች ሆኖ ይህን ሁሉ አስከትቶ አባይ ወረደና አባራ ጂወርጂስ ሰፈረ። ሀሳቡ እነ በላይ ዘለቀ ወደ ጫቀታ እንዳይሻገሩ በር በሩን ለመዝጋት ነበር።
"እንውጋው" አለ በላይ ዘለቀ
"ጦሩ በጣም ብዙ ነው አንችለውም" አሉት ሌሎቹ

"ግድ የለም። ጦሩ በየመንደሩ ይመራል። አዝማቹ ላይ አደጋ እንጣልበት።"

እነ በላይ ዘለቀ ፡ ቀኛዝማች ለማ ነገዎ ያደረበትን በለሊት ከበቡት። ሲነጋ ለማ ነገኦን ከነወንድሞቹ ደመሰሱት። ጦሩ በሙሉ እጁን ሰጠ። መሳሪያውንና በቅሎውን ሁሉ አስረከበ። ድል አድራጊዎቹ መሳርያውን ዋሻ ውስጥ ደበቁት። በቅሎዎቹን ወደ ጫቀታ ልከው በጥይት ለወጡዋቸው።" ይሄ የሆነው ሰኔ 10 ነበር። ሰኔ 12አውሮፕላን ይደበድቡን ጀመር። በረንታ ጎይ ጂወርጂስ ላይ 12 ሰው ሞተብን። እኛም ተመልሰን ወደ በረሃችን ሸሸን።" ፊታውራሪ ለማ ሞገስ የጣልያን የጦር እንደራሴ ሆኖ ከማርቆስ ተልኮ ወጥቶ ዲማ አጠገብ ገድ ወንዝ ዋሻ ውስጥ እንዳለ ከበባቸው። ወጥተው ገጠሙ። ድል ነሱት።
ብዙ ሰው ሞተበት። እሱ ግን አመለጠ።
በላይ ዘለቀ 60 ያህል ምንሽርና አልቤን ማረከ። ምንሽርና አልቤን ሲያገኙ የመጀመርያ ጊዜያቸው ነበር። እስካሁን ግን ሲዋጉ በናስማስር ፡ በውጅግራ ፡ በለበን ብቻ ነበር።
"ድፍን ሀምሌን ተከበብን። ለምጨን አንድ ዋሻ ገብተን ተደበቅን። ኤኛን ሲያጣን ጊዜ የጎይ ጂወርጂስና ያካባቢውን ህዝብ ጎይ ላይ ሰብስቦ በላይ ዘለቀን ካላመጣችሁ ብሎ በመትረየስ ፈጃቸው።" በላይ ዘለቀ የቶክሱ እለት
ሞቶ ተቀብሯል ተብሎ ለጥልያኖች ተነገራቸው። ሰው ሰደው መቃብሩን ቢያስመረምሩት ሴት ሆና ተገኘች።
አንዱ አሳባቂ በላይ ዘለቀ ወደ እነብሰ አውራጃ ነው የሄደው ብሎ ለጥልያኖች ጠቆማቸው። የጥልያን ጦር ወደ እነብሴ ዘመተ። የእነብሴና የጎንቻ ህዝብ ገጠመውና ጨረሰው። አንድ ጥልያን ብቻ አመለጠ።

በላይ ዘለቀና አገሬው[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

እስከ ነሀሴ 1929 ድረስ የበላይ ዘለቀ ተከታዮች ከ30 እንከ 50 የሚደርሱ ወንድሞቹ ብቻ ነበሩ።
"ነሀሴ ጂወርጂስ በላይ ዘለቀ በረንታ ላይ አዋጅ አስነገረ። ኤኛን ምሰሉ ፡ እርዱን። አለዚያ ግን ይህ የጦር ሜዳ ነውና እንዳትጎዱ ሂዱ ልቀቁ ።"
"እናርጅ እናውጋ (የደብረወርቅ ወረዳ ) በረንታና ሸበል ፡ ጉበያ (ደጀን አጠገብ ) እነማይ (ቢቸና አውራጃ ) ...ይሄ ሁሉ አመነ ፡ ተባበረን።
"ከህዳር ማርያም (1930) እስከ መጋቢት ውድማትን ፡ አዋባልን ፡ ቅምብዋትን ፡ ሊበንን ፡ ባስን ፡ አነድድን ደጀንን ...እነዚህን ያዝን።"
"በየካቲት ትሊንቲ ከጫቀታ ዘመተብን አባይ ደረሰ። አገድነው። ብዙ ውጊያ ተደረገ። 80 ብረት (ከነሰው ) ማረክን። መለስነው። ወደደጀን ተመለስን።"
"ከሸዋ ሲዘምትብን አባይ ላይ አገድነው። ወር ካስራምስት ቀን ተዋጋነው። 3 መኪናዎች ሰበርን። ውስጣቸው የነበሩ ጥልያኖች ሞቱ።
"ጥልያን ሀይሉን አጠናክሮ በደጀን በኩል ከሸዋ መጣብን። 12 በጦለኔ በጀኔራል ማሊን አዝማችነት መጣ።
"መጋቢት 19 ቀን (1930) ውጊያው ማለዳ የጀመረ በአስራአንድ ተኩል አበቃ። መትረየስና መድፍ ከታች ፈረሰኛ በሻምላ (በጎራዴ )" ተጨምሮበት ከላይ አሮብላ ። ወንድሞቻችን አለቁ። የጦር አዝማች የነበረው የበላይ ዘለቀ ወንድም ደጃዝማች ታደለ ላወቅ ወደቀ። ተሰማ ላቀው ቆስሎ አመለጠ። 300 ያህል አለቅን። የተቀረውን ጨለማ ገላገለን።
"ጠላት ፆን ማርቆስ ገባ። እኛ ወደ በረሀችን ገባን። "
"ሚያዝያ 4 (1930) እበረሀችን አፋፍ ላይ እንደሰፈርን ጠላት ባራት ረድፍ ቢቸና ገባ። ሚያዝያ 6 ጦሩን ባራት ማእዘን አቀነባብሮ በረሀችንን በሙሉ ከበበው። በመካከሉ ደግሞ በግንባር እልፍ አእላፋት ጦር ይዞ ተሰለፈ።"
"ባለው ሀይላችን ገጠምነው።"
"ሊያፍነን ሞከረ በብዛቱ።"
"የቆላ ጫካ ነው ....እሳት ለቀቅንበት"
"ይገርማል እኮ የቀን ነገር !ልፋሱ እሳቱን እያንቦገቦገ ወደነሱ ወሰደው። ብዙዎቹን እሳት በላቸው። ብዙዎቹ አመለጡ። "የበላይ ዘለቀ ሚስት ወይዘሮ ሸክሚቱ አለማየሁ በመትረየስ ሞቱ (እንደወንድ ለብሰው ነበር ) ልጅ የሻሸወርቅ በላይ ተማረከች። የናትየዋ እናትም ተማረከች። "ከዚህ በሁዋላ አባይን ተሻግረን ጫቀታ ገባን። ያጌ ከተማ ግዛው ሰብስቤ የተባለው የጥልያን እንደራሴ ገድለን አገሩን አቃትለን የጎበዝ አለቃ ሾመን ... ፊታውራሪንና ቀኛዝማች እያሱ ልጅ በላይ ሾመው ...ተመልሰን ወደ ለምጨን በረሀ ገባን ።"
"ክረምቱን ከረምን።" (ያን ጊዜ ወንዞች ስለሚሞሉ እነ በላይ ዘለቀም ያርሳሉ ። ጥልያንም በየካምቦው ይከርማል )
ህዳር 27 / 1931 ጥልያን የዴንሳ አማኑኤልን ክልክል ሸንበቆ ሊቆርጥ (ሰፈር ሊሰራበት ) ይመጣል ማለትን ሰማን አርበኞቹ። ደፈጣ አድርገው መሽገው አደሩ። ማለዳ ሲመጣ ገጠሙት።
"ብዙ ባንዳ ገደልን። ብዙ መሳርያ ማረክን። ጥልያን ግን አመለጠ።"

በሶስተኛው ቀኑ ለምጨን ወዳዳ በሚባል ቀበሌ ኮረነል አጎረኔ አውግስቶ የተባለ ጥልያን ሁለት መድፍ ጠምዶ ገጠማቸው። ሰቀላ ገብሬልን አቃጠለ። ከሁለቱም በኩል ብዙ ሰው አለቀ። በዘጠኝ ሰአት ኮረነሉ ድል ሆኖ ወደ ካምቦ ተመለሰ።
"ይህ ሁሉ ሲሆን ለምጨን ውስት ፈላው በሚባል ቦታ ላይ ከትመን ከዚያ እየወጣን ነው ጦርነት የምናደርገው ። ፈላው ነበር ዋናው ምሽጋችን ። ከ30 እስከ 1933 እ.ም ድል ሆነን አናውቅም።"

ሰኔ 1931 እነ በላይ ዘለቀ ወደ ማርቆስ ልንዘምት ነው ክተት ብለው አወጁ። ጦሩ ከተተ። መነሻቸውን ወደ ደብረ ማርቆስ አስመስለው ለሊት አባይን ተሻግረው ወደ ጫቃታ ገቡ። ሲነጋ ደጋው ደርሰዋል።

"ሀይሌ ረዳ የተባለ የጥልያን እንደራሴ ያገ ላይ ገጠመን። ተሸንፎ ሸሸ። አመለጠ። ከተማውን አቃጠልን። ሽቅብ ወደ ወጊዲ አፋፍ ቀጠልን።
"በማግስቱ ወጊዲ ላይ ያለውን ካምፕ (ምሽግ ) በቦምብና በእሳት አቃጠልነው። ያልተተኮሰበት አዳዲስ አልቤንና ምንሽር በጭነት ወሰድን። የኛ ሰው እየገባ አራት አምስት ምንሽር አንግቶ አንዱን የደስ ደስ ወደ ላይ እየተኮሰ ወጣ ።" አገሩን ሹም ሽር አድርገነው ወደ ፈላው ተመለስን።"

ይህን ጊዜ ባንዳዎች የነበላይ ዘለቀ ይዞታ የሆነውን አገር መልሰው ለማሳመን ጥረት ያደርጉ ጀመር። በድለንታ መጀመራቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለበላይ ዘለቀ ከታማኞቹ ደረሰው ። እነ በላይ ዘለቀም በፍጥነት ሄደው ባንዳዎቹን ከድለንታ አስወጡዋቸው። እስከ ደብረ ማርቆስ ድረስ አባረሩዋቸው ። እከተማው ዳር ቤቶች ተቃጠሉ።" ኦ ! ሮማ ተቃጠለች! አለ ጥልያን ሲዘብት። እነ በላይ ዘለቀ ይዞታቸውን ከባንዳ ለማጽዳት አገሩን እያሰሱ ደብረ ወርቅ አካባቢ ደረሱ።"

ሰኔ 1ቀን /፲፱፻፴፪ዓ/ም። በዚህን ጊዜ እንደአጋጣሚ - ጥልያን ከደብረ ወርቅ ብዙ ጉዋዝና መሳርያ (ስንቅና ትጥቅ ) ይዞ ወደ ቢቸና ይጉዋዛል። እነ በላይ ዘለቀ ይህን አላወቁም። ማለዳ እንደተነሱ ጅብ ሲያዩ ጊዜ ብዙዎች ተኮሱበት።
የተኩሱን እሩምታ ወደ ቢቸና የሚጉዋዘው ጥልያን ሰማውና ቃፊር ቢልክ - እነ በላይ ዘለቀ ናቸው። አዙር እንወጋቸዋለን አለ። ጦር ወደአርበኞቹ በኩል ሲሄድ የአዛዥ በቅሎ ሶስት ጊዜ ጣለችው። አጠገቡ ያሉት ባንዳዎች "ምልኪው መጥፎ ነውና ዛሬ ጦርነት ባናደርግ ይሻላል" አሉት። እሱ ግን በቅሎይቱን ገረፋት ፡ ለቅጣት ጥይት ጫነባትና በለላ በቅሎ ተቀመጠ። አርበኞቹን አያልፋሽ እተባለ ተራራ ላይ ገጠማቸው።

ውጊያው ሲጀመር አርበኞቹ ከላይ በኩል ጠላት ከታች በኩል ናቸው። በላይ ዘለቀ አርበኞቹን "ጎበዝ ጥልያን ጥይቱን የሚያመጣው ከፋብሪካ ነው። እኛ ግን ገዝተን ነው። ስለዚህ ጥይት መለዋወጥ አያዋጣምና በጨበጣ እንግባበት "አላቸውና በመጀመርያ ዘሎ እየጮኸ ከጠላት መሀል ገባ።

"ይህ የደብረወርቁ ጦርነት ለኛ የመጨረሻው ትልቅ ውጊያ ነበር። ድል አደረግን። ዘጠኝ የውሀ መትረየስ (ከባድ ፤ በከብት የሚጫን ቁጥር የለለው ቀላል መትረየስ ጥይትና ጠመንጃ ለማንሳት እስኪያቅተን እና አስራ ሁለት ባንዲራዎች ማረክን። አስራ አንዱን ባንዲራ በላይ ዘለቀ በሁዋላ ለንጉሱ አስረከበ። አንዱ ባንዲራ አሁን የጎላ ጂወርጂስ (ደብረቀርቅ አጠገብ ) ይገኛል።


"የደብረ ወርቁ ጦርነት የተደረገው ሰኔ 1/1932 አ.ም. ነበር። በበነጋው አስራ ሁለት አሮብላ መጥቶ የተዋጋንበትን አካባቢ ደበደበው። እኛ ግን ያን ጊዜ ፈላው ምሽጋችን ገብተናል። በላያችን አልፎዋል እኮ ታድያ። በላይ ዘለቀ "ጂወርጂስ ያውቃል አይዟችሁ" አለን። "እንዳትነቃነቁ !" ሰውም በቅሎም ባለበት ቀጥ ብሎ ቆመ። አሮብላን በሙሉ አልፎን ሄደ።"

ክረምቱን አርበኞቹ በምችጋቸው ከረሙ። ታህሳስ 1933። አርበኖቹ የቢቸናውን ካምቦ (ምሽግ ) ለመክበብ ሲዘጋጁ ራስ ሀይሉ በላይ ዘለቀን መጥቼ ላነጋግርኽ ብለው ላኩበት ።" እሺ ግን ከጠላት ጋር የነበረ ባንዳ እንዳይከተልዎ ፎቶ አንሺም እንዳይመጣ " ብሎ ላከባቸው ። ሰቀላ ገብሬል ድረስ መጥተው አነጋገሩት።

"ከተዋጋችሁ አገሩም ይጠፋል ትልያንም እኔን ላያምነኝ ነው። ካልወጋኸው ግን እራሱ አገሩን ይለቃል ።"
"እሺ ይሁን "
"ጃንሆይም መጥተዋል "አሉት።
"እንግዲያው እሱንም አፍነን እናስቀረው። እሱስ ይዞት የመጣው እንግሊዝ ያው ነጭ አይደለምን ?" አላቸው ።
"አይሆንም "አሉት ።
ተቀየመ ። ግን መውጋቱን ተወ ።
"ነጭ እዚህ ግድም እንዳላይ" አላቸው ። ራስ ሀይሉን ፤ "እርስዎንም እንዳልደፍርዎት ቶሎ ይዘውልኝ ይውጡ "
ሌሊቱን ተነስተው ሄዱ ። ጥልያንም ቢቸናን ለቆ ሄደ ።
(ራስ ሀይሉ ደብረወርቅ ሲደርሱ ራስ ተመስገን ፈንታ ወግቶ ጉዋዛቸውን ብዙ ጠገራም አገኘ ። እሳቸው ግን አመለጡ ። )

በላይ ዘለቀና ምቀኞቹ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

መጋቢት 1933 አ.ም. ከበደ ተሰማ (ደጃዝማች )ወዳገራቸው ለመመለስ መንገድ ላይ ከነበሩት ንጉስ ተልከው መጡ ::ከሳቸው ጋር የነበረው ጀኔራል ሳንፎርድ በላይ ዘለቀን ለመጨበጥ እጁን ሲዘረጋ በላይ ዘለቀ "ለፈረንጅ እጄን አልሰጥም "ብለው ሳንፎርድን አግባቡት :: በሁዋላ ልጅ መርድ መንገሻና እንግሊዞች ወደ ደጀን መቱ ::ወደበላይ ዘለቀ ላኩባቸው ::ሄዱ ::"የደጀንን ምሽግ ለመስበር ተባበሩን "ተባለ :: "መድፍ ይዛችሁዋል ?ኤሮቢላ ይዛችሁዋል ?"አላቸው በላይ ዘለቀ :: "አልያዝንም ግን መክበብ ይበቃል "አሉት :: "አይበቃም "አላቸው ::"ከዚህ በፊት ወር ካስራ አምስት ቀን ሙሉ ሞክረን ብዙ ወንድሞቼ አልቀዋል ::መድፍና ኤሮብላ አምጡና ምቱት ሌላውን ለኛ ተዉልን ::አለዚያ ግን እኔ ወንድሞቼን በከንቱ አላስፈጅም ::" ሳይስማሙ ተለያዩ ::


ንጉሱ ደብረ ማርቆስ ሲገቡ አርባ አራት ሺህ የበላይ ዘለቀ ሰራዊት በፊታቸው በሰልፍ አለፈ ::ያውም ባንድ ቀን ጥሪ የደረሰው ነው እንጂ ሰራዊቱ በሙሉ አይደለም :: በላይ ዘለቀ እንግዲህ በሰላም አርሼ እበላለሁ ብሎ ንጉሱን "አገሩንም ሰራዊቱን ይረከቡኝ "አላቸው :: "የሰላም ጊዜ ስራ አለ ::አገርን ማስተዳደር አለ "አሉት :: "እኔ ተራ ሰው ነኝ ::ሀረግ የሚቆጥሩት ሰዎች አያሰሩኝም ::ከርስዎ ጋር ያጣሉኛል "አላቸው :: "እኛ የማንንም ወሬ አልሰማም ::እንደአባትህ ቁጠረን ::እነዚህ ልጆቻችንም ወንድሞች ናቸው ::..."

ንጉስ ሹም ሽር አደረጉ ::በላይ ዘለቀ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ በሁዋላም ከአገሬው ጋር ሆኖ ጠላትን ተዋግቶ ነጻ ያወጣው ጠቅላይ ግዛት ለራስ ሀይሉ ተሰጠ :: በላይ ዘለቀ ወዳዲሳባ ተጠርቶ ደጃዝማች ተብሎ የቢቸና አውራጃ ገዥ ሆኖ ተሾመ :: የቢቸና አውራዣ ገዥ ሆኖም ሊሰራ አልቻለም ::ከደብረ ማርቆስ ትእዛዝ እየመጣ ወረዳዎቹ ሁሉ ቀድሞ ባንዳ የነበሩ ሰዎች ተሾሙባቸው። ብስጭት በዛበት በላይ ዘለቀ። "ሊወጋን ነው ....እምቢ አለ ..."እያሉ ማስወራት ጀመሩ። በቂ ካስወሩ በሁዋላ ከራያ ኦሮሞዎች ጦር አስዘመቱበት። (ጎጃመማ በላይ ዘለቀን ወይ ይወደዋል ወይ ይፈራዋል።) በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ ከጥቂት ታማኝ ተከታዮቹ ጋር ሆነው ወደ ሳማ አምባ ሸሹ ::በላይ ዘለቀ ሸፈተ ተባለ :: ሳማ አምባ ያለ ሁለት በር የላትም ሁለቱንም በር ይዘው ሀያ አምስት ቀን ሌትና ቀን ተዋጉ :: "ምረነዋል ልቀቁት ይምጣ "የሚል መልእክት ከንጉሱ መጣ :: ከሳማ አምባ ከወረዱ በሁዋላ ተከበቡና መሳሪያቸውን ተነጥቀው እንደ እስረኞች ወደ አዲስ አበባ ተወሰዱ :: በላይ ዘለቀ ሞት ተፈረደበት ::ንጉሱ "ምህረት " አደረጉለትና ቅጣቱ ወደ እስራት ተለወጠለት ::

መስከረም 1936 አ .ም በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ በያገሩ ተበትነው ታሰሩ :: በላይ ዘለቀና ወንድሙ እጅጉ ዘለቀ ወሊሶ በበቀለ ወያ ጠባቂነት ታሰሩ :: የበላይ ዘለቀ ምቀኖች አሁንም አላረፉለትም ::በላይ ዘለቀ ከዳ ;አመለጠ ጠፋ እየተባለ ይወራ ጀመር ::በቀለ ወያ ተያዘና "ምን ቢሰጥህ ነው የለቀከው ?"ተባለ ::"እረ እኔ አልለቀኩትም አለ :::: በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀን ወደ አዲስ አበባ አመጡዋቸውና ከአንድ ሌላ ሰው ጋር አሰሩዋቸው :.ያ ሰው እናምልጥ እያለ እነ በላይ ዘለቀን ይጎተጉታቸው ጀመር :: አንድ ቀን "ጠባቂዎቻችንን የኛ ወዳጆች ገዝተዋቸዋልና እናምልጥ ::በንዲህ ያለ ስፍራ እነ እገሌ መኪና ይዘው እየጠበቁን ናቸው ::"አል :: "ወንድሞቸ በየቦታው ተበታትነው ታስረው እኔ ማምለጥ ምን ያረግልኛል ?" አለ በላይ ዘለቀ :: "ፈራህ እንዴ በላይ ዘለቀ ?"አለው :: "እኔ የዘለቀ ልጅ !" በላይ ዘለቀ ወንድሙን ላከው መኪናው እተባለበት ስፍራ መኖሩን ለማረጋገጥ ::ወንድምየው በተባለበት ስፍራ መኪና አየ ::እስረኞቹና ጠባቂዎቻቸው አብረው አመለጡ ::እመኪናው ቦታ ሲደርሱ መኪናው የለም ::እንግሊዝም የለም :: ጠባቂዎቻቸው ከዚያ ሮጠው አጠገባቸው ከነበረው ጫካ ገቡና ደጋግመው ተኮሱ ::ምልክት ነው :: በላይ ዘለቀ እጠላቶቹ ወጥመድ ውስጥ መግባቱን አወቀ :: በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀ ከዚያ እሮጠው አመለጡ :: ሰላሌ ደርሰው በቅሎ ለመከራየት ሲነጋገሩ ተከበቡ :: በላይ ዘለቀ በጦር ፍርድ ቤት ሞት ተፈረደበት ::ንጉሱ ፍርዱን አጸደቁት :: ጥር 1937:.በላይ ዘለቀ በስቅላት ሞተ ::እድሜው ሰላሳ አምስት አመት ነበር ::

ጥልያንን በመድፍ በመትረየስ በአውሮፕላን ሊገድለው ያልቻለውን ጀግና በቅናት የተነሳሱ መቀኞች የሸረቡት ገመድ ገደለው ::ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ ሰላሳ አምስት አመት ታስረው በለውጡ ተፈቱ :: በላይ ዘለቀ ፎቶ ተነስቶ አያውቅም ::መልኩን ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ እንዲህ ብለው ይገልሱታል :: "አፍንጫው ሰተት ብሎ ወርዶ ቅጠሉ ነፋ ነፋ ይላል ::ከንፈሩ ከበድ ይላል ::ጠጉሩ ክርክም ጎፈሬ ጺሙ ሙሉ ለስላሳ ረጅም ጣቱ መልካም ወተት የተነከረ ነው የሚመስለው ጣቱ ::እግረ ቀጭን ::"

በላይ ዘለቀ ደጃዝማች ተብሎ ካዲስ አበባ ወደ ደብረ ማርቆስ እንደተመለሰ ከባለስልጣኖች ጋር ለመገናኘት ወደ "ጠቅላይ ግዛቱ " ጽህፈት ቤት ሄደ ::ዘበኞቹም አጋፋሪውም ሲያዩት ጊዜ ሽሽታቸውን ለቀቁ ::ስምና ግርማው ያን ያህል ያስፈራ ነበር :: ከጽህፈት ቤቱ ወጥቶ ወደ ሚያርፍበት ቤት ሲገባ ወሬው ከተማውን ከመቼው እንዳደረሰው አይታወቅም ::ማርቆስ ያለ ሰው ሁሉ እንጀራውን ወጡን ጠላውን ጠጁን አረቄውን እየያዘ መጣ ::በላይ ዘለቀን ህዝቡ ሲወደው ያን ያህል ነበር ::ምግብና መጠጡ ከመብዛቱ የተነሳ ሰዎች ወደውጭ ተላኩና አላፊ አግዳሚውን "የራበኽ ስንቅ የለለኽ ና ብላ !በበላይ አምላክ ና ግባ "እያሉ ጋበዙት :: በበላይ ዘለቀ ሰራዊት ውስጥ መሪና ተከታይ አለቃና ጭፍራ ያለው በውጊያ ሰአት ነው እንጂ በምግብ ሰአት ሁሉም እኩል ነው ::ለሰራዊቱ የሚበቃ ምግብ ከሌለ ያለው ተቆራርሶ ለሁሉም እኩል ይደርሰዋል :: በላይ ዘለቀ መሶብ ሲቀርብለት "ሁሉም በልቷል " ይላል :: "አይ ዛሬ እጥረት አለ "ካሉት "እንግዲህ መልሱ ::እኔ አልበላም "ይልና ጦሙን ያድራል :: (አንዳንድ ጊዜ ሁሉም ባይበላም ውሸታቸውን ሁሉም በልቷል ይሉና ያበሉታል :: ) "አንድ ጊዜ ሁለት ቀን ጦም አድረን በላይ ዘለቀ ዛሬ ሶስት ድርብ (ሁለት ቁና ) ሽምብራ ላመጣልኝ ጠመንጃ እሰጠዋለሁ አለ ::አንድ ገበሬ ሽምብራውን አመጣ ;ጠመንጃውን ወሰደ ::ሽምብራውን በልተን አደርን " በላይ ዘለቀ የገንዘብ ፍቅር የለበትም ::እንዲያውም ብር በእጁ አያድርም :: "ራስጌዬ አታርጉብኝ ...ይጠቀጥቀኛል "ይላል :: ያቃዠኛል ማለቱ ነው በጎጃምኛ።

ንጉሱ ደብረማርቆስ የመጡ ጊዜ አስራ ሁለት ሺህ ብር ሰጥተውት ሄዱ። በላይ ዘለቀ ከማርቆስ ወደ ቢቸና ሲጉዋዝ አንዱ መጥቶ "ቤቴ ተቃጠለ "ገንዘብ ሲሰጠው ;ሌላው መጥቶ "ከብቴ ተዘረፈ " ሲል ገንዘብ ሲሰጠው እንዲህ ሲል ገና ቢቸና ሳይገባ አስራ ሁለት ሺ ብሩ አለቀ። "ጊዮርጊስ ያውቃል "ይላል በላይ ዘለቀ። በጊዮርጊስ በጣም ያምናል። ፍልሰታ ሲሆን ሁል ጊዜ ሱባኤ ይገባል። "እኔ የዘለቀ ልጅ !"ይላል ሲቆጣ። "በምድር በሰማይ የሚያስጉዘው !በላይ የወንዶች ቁና "ይላል ሲፎክር።

በላይ ዘለቀ ተኩሶ አይስትም። ፍጥነቱ ደሞ ሲደግንና ሲተኩስ እኩል ነው። ውጊያ ሊጀምር ሲል "እኔ ሳልተኩስ እንዳትተኩሱ "ብሎ ያዛል። አንዳንድ ጊዜ በውጊያ ሰአት "እርስዎ እዚህ ይቆዩን " ሲሉት "ምን ?" ይላል ቁጣ እየጀመረው። "እርስዎ ከወደቁ መሪ የለንም" ሲሉት "ወይድ! እኔ አሮጌ ነፍጠኛ ነኝ።"ይልና ግንባር ይጋፈጣል።

በላይ ዘለቀ እራሱ ሲዋጋ "ገምባው" ይተበባለው ጥሩንባው ይነፋል። "ገምባው "ባንዳን ያስበረግጋል። ጥልያንን ያብረከርካል።

በላይ ዘለቀ የዘመኑን አስተሳሰብ በማወቁ ህዝቡን ለማስተባበር "ትልቅ ሰው" ማስፈለጉን በመገንዘቡ እሱ እራሱ ግን ተራ ሰው በመሆኑ የንጉስ ተክለሀይማኖት ሀረግ ለሆኑት ለልጅ ሀይሉ በለው ደብዳቤ ጻፈላቸው።

የደብዳቤው ሀሳብ ባጭሩ "ህዝቡን ለማስተባበር እርስዎ የበላይ ሆነው እነን የጎበዝ አለቃ ይሹሙኝና ጠላትን እንቋቋመው። እኔም እዋጋለሁ። እርስዎ ወደጦር ግንባር መድረስ አይኖርብዎትም።" የሚል ነበር። ደጋግሞ ደብዳቤ ጻፈላቸው። ገጸበረከትም ላከላቸው።...ጠመንጃ ሽጉጥ ዝናር ከነጥይቱ ሶስት መቶ ብርና ካባ።

ልጅ ሀይሉ በለው ለደብዳቤዎቹ አንድም መልስ ሳይሰቱ አንድ ቀን አንድ የትእዛዝ ደብዳቤ ላኩበት። "ደብረወርቅ ገበያችንን ያለአግባብ ቀረጡብን ብለዋልና ከንግዲህ ቆቅ የሰገረ ወፍ የበረረ እንዳይደርስባቸው። የተወሰደባቸውም ቀረጥ እንዲመለስላቸው።"

በላይ ዘለቀ ተናደደ። አብረውት የነበሩትን "ጎበዝ እግዚአብሄር የወለደው ሰው አለ?" ሲል ጠየቀ። "እግዚአብሄር ይፈጥራል እንጂ አይወልድም " አሉት። "ንጉስስ?" "ንጉስም እግዚአብሄር ይቀባዋል እንጂ አይወልድም። ይፈጥረዋል እንደሌላሰው" "እኔንም ፈጥሮኛል። ሊቀባኝ አይችልም?" "የሱ ሀይል ካደረብዎ የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ።" "እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ ለማንም አልታጠቅም።" ተመስገን ፈንታ የበላይ ዘለቀ የቅርብ ጉዋደኛው ነበር። አንድ ቀን ከጠላት በፊት ተመስገን ፈንታ በላይ ዘለቀን "ሸዋ ሄደን ለትልቅ ሰው እንደር። እንሾማለን ;እንሸለማለን "አለው። "እኔ ሰው ሆኜ ለሰው አላድርም "አለ በላይ ዘለቀ። "ባንተ ተኩስ ;ባንተ ወኔ፤ ባንዳፍታ ትሾማለኽ። "ጀግንነት እደጃችን ድረስ ይመጣ እንደሆነ ማን ያውቃል?" አለው በላይ ዘለቀ። አመታት አለፉ።

ሞረድ እጀ ጠባብ ካስመራ እሚመጣ አፈ ሾሌ ሱሪና ተመሳሳይ ኮኮት ጥንግ ድርብ ጥበብ ኩታ በቅሎ እንደተጫነች ጠመንጃ ከነሙሉ ዝናር ጥይት ...በላይ ዘለቀ ይህንን ሁሉ አዘጋጀና ተመስገን ፈንታን ጠርቶ፥ "ያ የጌታ አዳር ሄደን እንሸለማለን ያልከው ይኸውና "ብሎ ሸለመው። በአርበኝነት ዘመን ጉዋደኛሞቹ አልተለያዩም። በላይ ዘለቀ መጀመርያ "ራስ " ብሎ የሾመው ተመስገን ፈንታን ነበር። "እኔንስ ራስ አልከኝ። አንተ ማን ልትባል ነው?" አለው ተመስገን ፈንታ። "እኔንማ እናቴ አንደዜ በላይ ብላኛለች " አለ በላይ ዘለቀ ::

[2]

ዋቢ ጽሁፍ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

Ethiopian History

  1. ^ Ethiopian History
  2. ^ ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ የ 74 አመት አዛውንት ናቸው ::"እኔና በላይ ዘለቀ የወንድማማች ልጆች ነን "አሉኝ ::"በእድሜ 4 አመት እበልጠዋለሁ ::"እንግዲህ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ይኼን ጊዜ 70 አመታቸው ነበር ማለት ነው :: ፊታውራሪ ተሰማ ላቀው 67 አመታቸው ነው ::"የበላይ ዘለቀ ያባቱ ትንሽ ወንድም ነኝ ::አሉኝ ::ፊታውራሪ ቀለመወርቅ መዝጊያ 62 አመታቸው ነው ::የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዋና ጸሀፊ ነበሩ ::የሚከተለውን ታሪክ የነገሩኝ እነዚህ 3 አዛውንቶች ናቸው :: የካቲት 3ኛ አመት ቁጥር 7 ሀምሌ 1972 ,ስብሀት ግ /እግዚአብሄር