የኖህ መርከብ
የኖህ መርከብ ወይም ሐመር (ዕብራይስጥ፦ תיבת נח /ተይባት ኖዋሕ/፤ ዓረብኛ፦ سفينة نوح /ሣፊና ኑህ/) በመጽሐፍ ቅዱስ (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 6—9)፣ በቁርዓንም (ሱራ 11 እና 71)፣ እንዲሁም በሌሎች «አብርሐማዊ» የተባሉ ሃይማኖቶች ጽሑፍ ዘንድ፤ ኖህን፣ ቤተሠቡንም፣ ከዓለም እንስሶችም ምሳሌዎች ከማየ አይኅ ለማዳን የተሠራ ታላቅ መርከብ ነበረች።
በዘፍጥረት የተገኘው መሠረታዊ ታሪክ እንደሚለው፣ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ክፋት አዝኖ[1] ብልሹውን ዓለም ለማጥፋት ወስኖ ነበር። ሆኖም ኖህ ጻድቅ ሆኖ እራሱን፣ ቤተሠቡንም የመሬት እንስሶችንና አዕዋፍንም የምታድን መርከብ እንዲገነባ አዘዘው። የጥፋት ውኃ ከዚያ ምድሩን አጥፍቶ ውሆቹ መልሰው የብስ እንደገና ታየና መርከቢቱ በአራራት ተራሮች ላይ ዐረፈች። በመጨረሻ እግዚአብሔር ከኖህና ተወላጆቹ ጋራ ቃል ኪዳን ገባ።
ለዚህ መተረክ ብዙ ጊዜ በአብርሃማዊ ሃይማኖቶቹ በኩል ሰፊ ዝርዝሮች ተጨምረዋል። እነዚህ ዝርዝሮች ከሥነ-መለኮታዊ ትርጉሞች ጀምሮ ለተግባራዊ ጉዳዮች የሆኑ መላምታዊ ፍቾች እስከሚነኩ ድረስ ሊሆኑ ይችላሉ። በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ላይ፣ በተለይ በምዕራብ ዓለም በብዙዎቹ የሳይንስና የሥነ ጽሑፍ ሊቃውንት አስተያየት፣ መተራረኩ አፈ ታሪክ ብቻ እንጂ በዕውኑ አይሆንም በማለት ተጠራጠሩ። ዳሩ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት የሚያምኑት ሰዎች እስካሁን አይነተኛና ዕውነተኛ ታሪክ መሆኑን ቆጥረውታልና እስከዚህ ቀን ድረስ ለመርከቢቱ ማረፊያ ተራራ አንዳንድ ፍለጋ ሲካሄድ ነው።
መርከቢቱ
በዘፍጥረት 6፡15 መሠረት፣ የመርከቢቱ ርዝመት 300 ክንድ፣ ወርድዋም 50 ክንድ፣ ከፍታዋም 30 ክንድ እንዲሆን ኖህ ታዘዘ። ቢሆንም በጥንት ዘመን «ክንድ» የሚባለው መስፈርያ (ዕብራይስጥ «አማህ») በየአገሩ ይለያይ ነበርና በልክ ርዝመቱ አይታወቅም። በግድም ግን አንድ ክንድ ምናልባት ግማሽ ሜትር የሚያሕል ነበር። የርዝመቱና የስፋቱ ውድር 6፡1 ሆኖ ይህ ለዛሬው መርከቦች እንኳን በጣም ጽኑና ጠቃሚ ቅርጽ ሆኗል። ደግሞ መርከቢቱ መስኮትና በር በጎኑ ነበራትና መገንባትዋ 100 አመት ፈጀ ይላል።
«ጎፈር ዕንጨት»
በዘፍጥረት 6፡14 መሠረት ኖህ መርከቢቱን ከጎፈር ዕንጨት እንዲሠራ ታዘዘ። ይህ ቃል በዕብራይስጥ (גפר) በሌላ ስፍራ ከቶ አይታውቅም። የአይሁድ መዝገበ ዕውቀት ቃሉ ከአሦርኛ «ጊፓሩ» (መቃ) የተተረጎመ ይሆናል በሚል ሀሣብ ግመቱን አቅርቧል። በግሪክ ብሉይ ኪዳን (70 ሊቃውንት) ዘንድ «ξύλων τετραγώνων» /ክሲውሎን ተትራጎኖን/ (አራት ጎን ያለው ዕንጨት) ይላል። እንዲሁም በሮማይስጥ ትርጉም «lignis levigatis» /ሊግኒስ ሌዊጋቲስ/ (የተለመጠ ዕንጨት) አለው። በሌሎች ግመቶች ዕንጨቱ ዞጲ፣ ዝግባ ወይም አርዘ ሊባኖስ ሊሆን ቻለ። ከዚህ በላይ 6፡14 «በቅጥራን ለቅልቃት» ሲል የቅጥራን ትርጉም በዕብራይስጡ «ኮፈር» ነውና አንዳንድ ተቺዎች «ጎፈር» ለ«ኮፈር» የተሳተ ይሆናል በማለት ገመቱ።
መተረኩ
በዘፍጥረት የኖህ መርከብ ታሪክ መጀመርያ፡ እግዚአብሔር የሰው ልጅ ክፉ ሥራ አይቶ ሕይወት በሙሉ የሚያጠፋ ጎርፍ ለመላክ ሀሣቡን ቆጥሮአል። ነገር ግን እግዚአብሔር አንድ ጻድቅ ሰው ኖህን አግኝቶ የአዳም ዘር በርሱ እንዲኖር አስቧል። ስለዚህ እግዚአብሔር ኖህ መርከብ እንዲሠራ አዝዞ ሚስቱን፣ ሦስት ልጆቹንም (ሴም፣ ካምና ያፌት)፤ ሦስት ሚቶቻቸውንም በድምሩም 8 ሰዎችን እንዲያሣፍራቸው አለው። በተጨማሪ ከንጹሕ እንስሶች 14፣ ንጹሕ ካልሆኑትም 4 ወይም 2 ናሙናዎች እንዲያሣፍር መብላቸውንም እንዲያመጣ ታዘዘ። ሁሉም ወደ መከቢቱም ገብተው እግዚአብሔር ዘጋት ይላል።
የጥፋት ውኃ
ዘፍጥረት እንደሚለው የኖህ ዕድሜ 600 አመታት ሲሆን በ2ኛው ወር በ17ኛው ቀን 'የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፣ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ'፤ ጎርፉ እንግዲህ ከዝናብና ከታችኛ ምንጮች አንድላይ ወጣ ማለት ነው። ውኃው ከተራሮቹ በላይ 15 ክንድ ነበረ (7፡20)፤ በምድር የሚኖር ሁሉ ሰመጠ። (በዕብራይስጥ መዝሙር 103፡8 ደግሞ፣ ውኆች በተራሮች ላይ ከቆሙ በኋላ ተራሮቹ ከፍ አሉ ቈላዎቹም ወረዱ ይላል።) ኖህና ከሱ ጋር በመርከቢቱ ላይ የነበሩ ብቻ አልሰመጡም።
ዘፍጥረት ስለጥፋት ውኃ የተወሰኑ ቀኖች ያመልክታል። በኖህ ሕይወት 600ኛው አመት በ2ኛው ወር 17ኛው ቀን ከጀመረ በኋላ ዝናቡ ለ40 ቀን ዘነበ። ውኆቹም እንደገና ለ150 ቀን ምድርን ሸፈኑ። ዝናቡ ከጀመረ 5 ወሮች በኋላ ሐመር በአራራት ተራሮች አረፈች (8፡4)። 2.5 ወሮች ከዚህ በኋላ፡ በአሥረኛው ወር መባቻ የተራሮች ጫፎች ታዩ (8፡5)። እንደገና 3 ወር አልፈው በኖህ ሕይወት በ601ኛው አመት በመጀመርያው ቀን፣ ኖህ የምድር ፊት እንደ ደረቀ ከመርከብ አየ (8፡13)። ሁለት ወር ከዚያም በኋላ፣ በ2ኛው ወር 27ኛው ቀን፣ ምድሪቱ ድርቅ ሆነች። በዚያን ጊዜ ኖህ፣ ቤተሠቡና እንስሶቹ ሁሉ ከሐመር ወጡ።
ማየ አይኅ በየትኛው አመት እንደ ደረሰ ለመገመት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑት መምህራን አብዛኛው ጊዜ የዘፍጥረት ትውልዶች በምዕራፍ 5ና 11 ያጥናሉ። በ17ኛው ክፍለ ዘመን የአይርላንድ ሊቀ ጳጳስ ጄምስ አሸር በዚህ ዘዴ በ2349 አክልበ. (እ.ኤ.አ.) እንደ ደረሰ ቆጠሩ። አንዳንድ ምዕመናን እስካሁንም ድረስ ይህን አቆጣጠር ይቀበላሉ። ነገር ግን በዕብራይስጥ (ማሶሬታዊው) ትርጉም፤ በግሪኩ ትርጉምና በሳምራዊው ትርጉም የአባቶች አመቶች ስለሚለያዩ፣ ሌላ ውጤት ማግኘት ይቻላል። በመጽሐፈ ኩፋሌ ዘንድ ማየ አይኅ በአመተ አለም 1308 ደረሰ፣ ባጋጣሚው የሳምራውያን ትርጉም ደግሞ ከኩፋሌ ጋራ በመስማማት ይህን አመት ያመለክታል። ኩፋሌው እንደሚለው የእስራኤል ልጆች ከግብጽ የወጡ በ2410 ዓመተ አለም ከሆነ፣ ከጥፋት ውኃ 1,102 አመታት በኋላ ነበር ማለት ነው። ለምሳሌ ከግብጽ የወጡ በ1661 አክልበ. ከሆነ፣ እንግዲህ ማየ አይህ በ2763 አክልበ. ሊቆጠር ይቻላል።
የክፉ ልጆችን ሁሉ ለማጥፋት የተገኙባቸው አገሮች ብቻ በውኃ መሸፍን አስፈላጊ ይሆን ነበር፤ ብዙዎች እንደሚያስቡ፣ ሰዎች ያንጊዜ ካልተገኙባቸው አሁጉራት ጭምር መላውን ዓለም መሸፈን አስፈላጊ አይመስልም።
ከጥፋት ውኃ በኋላ
ዘፍጥረት እንደሚተርከው፣ መርከቢቱ በአራራት ተራሮች አርፋ ተራሮችም ታይተው ኖህ ቁራን ላከና ወዲያ ወዲህ በርሮ የብስን አላገኘም ነበር። ቀጥሎም ኖህ ርግብን ሰደደና ምንም መሬት ሳታገኝ ተመለሰች። ከሳምንት በኋላ በተጨማሪ ርግቧን ልኮአት የወይራ ቅርንጫፍ ይዛ ተመለሰች። ሦስተኛ ላካትና አልተመለሰችም።
ኖህ በዚህ መሬት ደረቅ እንደ ሆነች አውቆ፣ እግዚአብሔር ሁላቸው ከመርከብ እንዲወጡ አዘዘና ቃል ኪዳን ገባ። ይህ ቃልኪዳን ምድርን በሙሉ ዳግመኛ በውኃ ከቶ እንዳያጠፋ የኖህም ተወላጆች በመሠረታዊ ደንቦች እንዲኖሩ ነበር። የሰው ልጅ ምንም እንስሳ ከነደሙ መቸም እንዳይበሉ የሚል ትዕዛዝ ተሰጠ። ለዚህ ቃልኪዳን ምልክት እግዚአብሔር በዚያን ጊዜ ቀስተ ደመናን ፈጠረ።
ከማየ አይህ አስቀድሞ የአንዳንድ ሰዎች ዕድሜ እስከ 1 ሺህ አመታት ድረስ ይደርስ እንደ ነበር ኦሪት ይለናል። ግን ከዚህ በኋላ የእድሜ መጠን እስከ 120 አመት ድረስ ቶሎ ይቀነስ ጀመር።
በኩፋሌ ውስጥ ኖህ እራሱ አራት መታሰቢያ በዓላት አዋጀ እነዚህም በዓላት በየአመቱ በ1ኛው፣ 4ኛው፣ 7ኛው፣ 10ኛውም ወሮች መባቻ እንዲከብሩ ትልቅ ቁም ነገር መሆናቸውን ያጠቁማል።
ሐመር በተለያዩ ልማዶች
በአይሁድ ልማዶች
በአይሁድ ረቢዎች ስነ-ጽሑፍ ዘንድ (በመጀመርያ ክፍለ-ዘመናት ዓ.ም.) ኖህ ከጥፋት ውኃ 120 አመታት በፊት አርዘ ሊባኖስ ተክሎ ሐመርን ከዚህ ዕንጨት ሠራት። መላዕክት እንስሶቹን ወደ መርከቢቱ ያመሯቸው ሲሆን እግዚአብሔር ቤተሠቡን ከክፉ ሰዎች ለመጠበቅ አንበሶች አኖረ። ኖህ ቀንና ሌሊት በማገንባት ላይ ኖረ፣ ደግሞ በመርከቢቱ ላይ ሲሆን ለአመቱ አላንቀላፋም ይባላል። ራባ የተባለው ሚድራሽ እንደሚል የጎርፉ ክልል አለም አቀፍ ሳይሆን እስከ ሞሮኮ ድረስ ብቻ ሸፈነ። ታልሙድ ሳንሄድሪን ደግሞ አንበሣው ኖህን እንደ ሰለበው ይተርካል።
በመርከብ ላይ ያሉት ሁሉ ከማርባት ቆዩ የሚል መረጃ በአይሁድ ጸሐፍት ይጨመራል። ቁራው ሲሰደድ ፈቃደኛ አልነበረም። ከሐመር ሦስት ፎቆች፣ ታቸኛው ለቆሻሻ፣ መካከለኛው ለሰዎችና ለንጹሐን እንስሶች፣ ላየኛም ለርኩስ እንስሶችና ለወፎች ነበር። (በሌላ የአይሁድ ጽሑፍ ግን ቆሻሻው በላይኛ ፎቅ ሆኖ ቀጥታ ወደ ባሕር ይጣል ነበር።) ብርቅ ድንጋይ በተዓምር ብርሃን ይሰጥ ነበር። ከኖህ ቤተሠብ 8 ሰዎች ጭምር አንድ ረጃጅም ሰው ወይም ናፊል፣ የባሳን ንጉሥ ዐግ በሐመር ከመሰጠም አመለጠ የሚል የአይሁዶች ልማድ ቢገኝም፣ ይህ ግን ለመጽሐፍ ቅዱስ ተቃራኒ ይመስላል፤ የዐግ ግዛት በኢያሱ ወልደ ነዌ ዘመን ይታወቅ ነበርና።
በሌላ የአይሁድ ታሪክ ዘንድ የሐመር ሣንቃ በአሦር ንጉሥ ስናክሬም ተገኝቶ ጣኦት ሠራበት። በሚድራሽ አባ ጊርዮን ዘንድ፣ ሌላ የሐመር ሣንቃ ደግሞ ለሐማን (ከመጽሐፈ አስቴር) ስቅለት ተጠቀመ።
በክርስትና
በወንጌል መሠረት ኢየሱስ መመለሱን እንደ ኖህ ዘመን አመስሎ መሠከረ። (ማቴ. 24:37-42) መጀመርያ የቤተ ክርስትያን ጸሐፍት ሐመርን እንደ ምልክት ቆጠሩት። 1 ጴጥሮስ መልእክት እንዳለ በሐመር ያመለጡት ሰዎች በጥምቀት ውኃ ለመረጡት ሰዎች ምሳሌ ናቸው።
ቅዱስ አቡሊድስ (200 ዓ.ም. ገዳማ) አንዳንድ ልማዶች ተረኩ። በሦስት ፎቆች ታችኛው ለአውሬዎች፣ መካከለኛው ለአዕዋፍና ለከብቶች፣ ላየኛው ለሰዎች ሲሆን ማርባት ለመከልከል ወንዶች ከሴቶች በችካል ተለዩ። የአዳም አጽም፣ ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ ተጫኑባት፤ ሐመርም በመስቀል ቅርጽ ሰፈፈች። የሰፈረችበት ተራራ 'ደብራ ካርዱ' «በምሥራቅ፣ የራባን ልጆች አገር፣ ምሥራቃውያንም 'ጎዳሽ'፤ ዓረባውያንና ፋርሳውያንም 'አራራት' ይሉታል» በማለት ጻፈ።[2].
ኦሪጊኔስ ስለ ሐመር ቅርጽ ራሱ እንደ ተቋረጠ ፒራሚድ ይመስል ነበር ብሎ ጻፈ። በሱ አስተያየት፣ በጫፉ ርዝመቱ አንድ ካሬ ክንድ ነበር፤ ይህም ክንድ ሙሴ በግብጽ ስላደገ የግብጽ ክንድ ሳይሆን አይቀርም መሰለው።[3] ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ቅርጹ ባለ-ጣራ ሳጥን እንደ ነበር ተቆጠረ። በ15ኛው ክፍለ ዘመን አልፎንሶ ቶስታዳ፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ዮሐንስ ቡቴዎ የሐመርን ቅርጽ ገለጹ።[4]
በአይርላንድ አፈ ታሪክ፣ የኖህ አራተኛ ልጅ «ቢስ» እንዳይሣፈር አልተፈቀደም፤ ወደ አይርላንድ ከ54 ሰዎች ጋራ ሸሽቶ ሁላቸው ሰመጡ።
በሞርሞን («የመጨረሻ ቀን ቅዱሳን») ሃይማኖት
ሐመር ደግሞ በመጽሐፈ ሞርሞን (መጽሐፈ ኤጠር) ትጠቀሳለች። በመጨረሻ ቀን ቅዱሳን (ሞርሞን) እምነት፣ የኖህ መታወቂያ በውነት መልአክ ገብርኤል ነበረ።
በእስልምና
ኖህ (ኑኅ) ከእስልምና አምስት ዋና ነቢዮች አንዱ ነው። በቁርዓን መሠረት ኑኅ ጻድቅ ሆኖ ጣኦት ለሚያምኑት ክፉ ሰዎች ሰብኮ 70 ወይም 72 አሳመናቸውና በድምሩ 78 ወይም 80 ሰዎች በመርከቢቱ ላይ አብረውት አመለጡ። እነዚህ 72 ሰዎች ግን ምንም ልጅ ስላልወለዱ የዛሬ ሰው ልጆች በሙሉ ከኖህ ቤተሠብ ተነሡ። የኖህ አራተኛ ልጅ እንዳይሣፈር እምቢ ብሎ ተሰጠመ፤ ባንዳንድ ምንጭ ስሙ «ያም» ወይም «ከንዓን» ይሰጣል።
በሱራ 11:44 ዘንድ የሠፈረችበት ሥፍራ ደብረ ጁዲ ሲሆን ይህ በተለመደው በሞሱል፣ ኢራቅ አካባቢ በጤግሮስ ወንዝ አጠገብ የሚገኝ ኮረብታ መሆኑ ይታስባል። ጸሐፊው አል-ማሱዲ (940 ዓ.ም. ያህል) እንደ ጻፈው፣ ሐመር ከኩፋ፣ ኢራቅ ተነሥቶ እስከ መካ ድረስ ሰፍፋ ካዕባን ዞረችና ወደ ደብረ ጁዲ ተመለሰች። በዚያም እስከ ሕይወቱ ዘመን ሊታይ ቻለ ብሎ ጻፈ። ያቁት አል-ሐርማዊ (1200 ዓ.ም. ዙሪያ) ኖህ በዚያ ያሠራው መስጊድ በዘመኑ እንደ ተገኘ ጻፈ። በቅርቡ ሌላ ተራራ በቱርክ አገር፣ ዱሩፒናር፣ በውኑ የደብረ ጁዲ ሥፍራ ነው የሚል ግመት አለ።
ከመርከብ በሙሐራም ወር 10 ቀን ወጥተው ሰዎቹ በጁዲ ግርጌ «ጣማኒን» (ሰማንያ) የተባለ መንደር ሠሩ። ኑህ መርከቢቱን ቆልፏት ቁልፉን ለሴም ሰጠ።
በሙሐመድ ዘመን የኖረው አብድ አላህ እብን አባስ በጻፈው ዘንድ፡ ኑኅ ዋንዛን ተክሎ ከ20 አመት በኋላ በቂ ዕንጨት ነበረው። [5]
አል-ባይዳዊ በጻፈው ታሪክ መጽሐፍ ደግሞ በሐመር ሦስት ፎቆች ታችኛው ለእንስሶች፤ መካከለኛው ለሰዎች፤ ላየኛውም ለአዕዋፍ ነበር። የአዳም ሬሳ ወንዶች ከሴቶች ለመለየት በመካከላቸው ተደረገ። ረጃጅሙ ዐግ ከውኆቹ ለማምለጥ እንደተፈቀደ የሚል ተረት ደግሞ ይገኛል።
በፋርስ ጸሐፊ አል-ታባሪ ጽሁፍ ተጨማሪ ዝርዝር አለ። መጀመርያው የተሣፈረ ፍጡር ጉንዳን ሲሆን መጨረሻው ሠይጣን የተሣፈረበት አህያ ነበረ ይላል። ደግሞ የኢየሱስ ሐዋርያት ስለ ሐመር ለመማር በፈለጉ ጊዜ፣ ኢየሱስ እንዲመልሳቸው የኖህ ልጅ ካምን ከሙታን አንሥቶት ካም እንዲህ መሠከረላቸው፤ ቆሻሻ በበዛበት ጊዜ ኑህ በተዓምር ዐሣማዎች ከዝሆን ኩምቢ አወጣ፤ እንደገና አይጥ ያለ ፈቃድ ስለ ገባ ድመት ከአንበሣ አፍንጫ ፈጠረ አላቸው።[6] እነዚህ ተረቶች በቁርዓን ስለማይገኙ ግን ብዙዎቹ እስላሞች አይቀብሉዋቸውም።
እስላሞች ዛሬ ቁርአን ትክክለኛ ታሪክ ሆኖ ይቆጥሩታል። አንዳንድ ተቺዎች ለምሳሌ ሃሩን ያህያ እንደሚያስቡ፣ ማየ አይህ አለም አቅፍ ሳይሆን የኖህን አገር ብቻ ያጠፋ ነበር።[7]
በባኃኢ እምነት
ባኃኢ እምነት የተባለው ሃይማኖት የሀመር ታሪክ እንደ ምሳሌ ይቆጥሩታል። የኖህ ተከታዮች በመንፈሳዊ ረገድ ሕያው የሆኑ፤ የሰጠሙትም በመንፈሳዊ ረገድ ሙታን የሆኑት ምሳሌ ናቸው። በባኃኢ ቅዱስ መጽሐፍ ኪታብ-ኢ-ኢቃን ዘንድ፡ ከኖህ ጋር 40 ወይም 72 ተከታዮች አመለጡ፤ ከማየ አይህ አስቀድሞ ኖህም ለ950 አመታት ያስተምር ነበር።
በሳብያን ሃይማኖቶች
በኩርዲስታን ተራሮች የሚገኘው የየዚዲ ሀይማኖት ትምህርት በመጽሐፋቸው ምስሐፈ ረሽ (ጥቁሩ መጽሐፍ) ይገኛል። በዚህ በኩል የጥፋት ውኃ ሁለት ጊዜ መጣ። ከመጀመርያው ጥፋት የካም አባት ናኡሚ አመለጠ፤ መርከቡም በሞሱል ዙሪያ በዓይን ስፍኒ ተቀመጠች። ከዚህ በኋላ ሁለተኛው ጥፋት ውኃ በየዚዲዎቹ ብቻ ደረሰ፤ ከዚህም ኖህ በሌላ መርከብ አምልጦ መርከቡ ከደብረ ስንጃር በላይ በዓለት ተወግቶ ከዚያ በደብረ ጁዲ ተቀመጠች።
በደቡብ ኢራቅ የሚኖሩ ማንዳያውያን ሃይማኖት ደግሞ ኖህንና ዮሐንስ መጠምቁን እንደ ነቢያት ሲቆጥሩ አብርሐምና ኢየሱስ ግን ሐሣዊ ናቸው ብለው ያምናሉ። ሐመር የተሠራ ከጀበል ሃሩን (ሖር ተራራ በዛሬው ዮርዳኖስ) በመጣ ሰንደል ዕንጨት ተሠራ፤ ርዝመቱ፣ ስፋቱና ቁመቱ ሁላቸው 30 ክንድ ነበሩ፤ ማረፊያው ደግሞ በግብጽ ነበር ይላሉ።
የተዛመዱ ተረቶች በሜስጶጦምያ ጽላቶች
በሜስጶጦምያ ጥንታዊ ተረት ጽላቶች አንዳንድ ተመሳሳይ ታሪኮች ተገኝተዋል። እነዚህ ከሱመር፣ ከአካድ፣ ከባቢሎንና ከአሦር በኩነይፎርም ጽሕፈት ተጽፈው ይታወቃሉ።
በሱመር አፈ ታሪክ የጊልጋመሽ ታሪክ፤ አማልክት ምድርን በውኃ ለማጥፋት ወስነው ኤንኪ ግን የሹሩፓክ ከተማ ንጉሥ ዚውሱድራን በመርከብ እንዲያመልጥ ይነግረዋል። ነገር ግን በዚህ ተረት የጥፋት ውኃ ለ7 ቀን ብቻ ነው። ጽሁፉ ቢያንስ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን አክልበ. የተጻፈ ቢሆን በጊልጋመሽ ታሪክ የሚጠቀሱት ነገሥታት ኤንመባራገሲና አጋ በ3ኛ ሺህ አክልበ. በውኑ እንደ ነገሡ ከስነ ቅርስ ይታወቃል።
የጊልጋመሽ ታሪክ በባቢሎን ትርጉም ተጽፎ የዚውሱድራ ስም በአካድኛ ኡትናፒሽቲም ሆኗል። ከ7 ቀን በዝናብና ከ12 ቀን በውሆቹ ላይ በኋላ፣ መርከቡ በደብረ ኒጺር ተቀመጠች፤ ከሌላ 7 ቀን በኋላ ኡትናፒሽቲም 3 ወፎች ይልካል። በመጀመርያ ርግብ ልኮ ተመለሰች፤ ሁለተኛ ጊዜ ጨረባ ትልካ ተመለሰች፤ ሦስተኛም ቁራ ግን አልመለሰም። በሌላ ትርጉም መርከብን የገነባው ሰው ስም አትራሐሲስ ይባላል።
በ300 አክልበ. ገዳማ የባቢሎን ቄስ ቤሮሶስ አንድ ታሪክ በግሪክ ጽፎ ይህን አይነት ተረት መዘገበ። በዚህ ትርጉም መርከብ የገነባው ሰው ስም ክሲሲውጥሮስ ተባለ። መርከቡም እስከ ቤሮሶስ ዘመን በአርሜንያ ተራሮች እንደ ተገኘ ጻፈ።[8]
በአንዳንድ ሊቃውንት አስተያየት የሜስጶጦምያ ተረት ለኦሪት ዘፍጥረት ምንጭ ነበረ፤ በሌሎች ሀሣብ ግን ሁለቱ በአንድ ድርጊት ተመነጩና ከሁለቱም የሜስጶጦምያ ተረቶች እጅግ የተዛቡ፣ የዘፍጥረት ግን ትክክለኛ የሆኑ ይመስላል።[9][10]
ሌሎች የአለም ጥፋት ውኃ ተረቶች
በአለም ዙሪያ በማናቸውም አሕጉር በማናቸውም ወቅት የማየ አይህ ታሪክ ይታወቃል። ለምሳሌ በግሪክ ተረቶች ዘንድ ከጥፋት ውኃ በመርከብ ያመለጡ ዴውካሊዮንና ሚስቱ ፒውራ ነበሩ።
በሕንዱ ሃይማኖት ጽሕፈት፣ ከጥፋት ውኃ በመርከብ ያመለጠው ቅዱስ ንጉስ ማኑ ተባለ፤ እሱም የማኑስምርቲ ሕገጋት ደራሲ እንደ ነበር ታመነ። ከቤተሠቡና ከ7 ሊቃውንት ወይም 'ሪሺዎች'ና የአለም እንስሶችና አትክልት ናሙናዎች ጋራ ተጉዞ መርከቢቱ በሂማላያ ወይም በካሽሚር እንዳረፈች ይባላል።
በርካታ ሌሎች ተመሳሳይ ተረቶች በአፍሪካ፣ በስሜን አሜሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በአውስትራላዚያ፣ በእስያና በአውሮጳ ኗሪዎች መካከል ተገኝተዋል። ስለዚህ በጥንት የሰው ልጅ ሁሉ ወላጆች ከጥፋት ውኃ እንዳመለጡና በኦሪት ዘፍጥረት ያለው ከሁሉ ይልቅ ትክክለኛ ታሪክ ነው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ።
ታሪካዊ አስተያየቶችና ትችቶች
የአይሁድ ታሪክ ጸሕፊ ፍላቭዮስ ዮሴፉስ (1ኛው ክፍለ ዘመን አ.ም.) የቀድሞ አሕዛብ ጸሕፍት ቤሮሶስ፣ ሂኤሮኒሙስ ግብጻዊ፣ ምናሴዎስና የደማስቆ ኒቆላዎስ ሁላቸው ሐመር በአርሜንያ ተራሮች ትገኛለች እንዳሉ ጠቀሳቸው። እንዲሁም ረቢው ዮናታን ቤን ዑዝኤል (1ኛው ክፍለ ዘመን አ.ም.)፣ ክርስቲያን ጸሐፍት አቡሊድስ፣ የአንጾኪያ ቴዎፊሎስ (2ኛው ክፍለ ዘመን)፣ ቅዱስ ሂኤሮኒሙስና ኤጲፋንዮስ (400 ዓ.ም. ገዳማ)፤ የእስላም ጸሓፍት አል-ማሱዲ (9ኛው ክፍለ ዘመን) ሁላቸው በዘመናቸው ሐመር በአርሜንያ ወይም በኩርዲስታን ተራሮች ልትታይ ቻለች አሉ። ቅዱስ ያዕቆብ ዘኒሲቢስ ከሐመር ሥፍራ የወሰደው የእንጨት ቅርስ በአርሜንያ ኤጭምያጺን ገዳም እስከ ዛሬ ድረስ እንደሚታይ ይባላል።
በ17ኛው ክፍለ ዘመን የሮማ ካቶሊክ ኢየሳስዊ ቄስ አታናስዮስ ኪርከር በግሪክ አፈ ታሪክ የሚገኙት ሲሬኖች የተባሉት ፍጡሮች (በከፊል ወፍ በከፊልም ሴት) በውኑ እንደሚኖሩ አስተማረ። ስለዚህ በኖህ መርከብ ልዩ ክፍል ነበራቸው ብሎ ገመተ። በዚህ ዘመን የሐመር ታሪክ ብዙ ሊቃውንት የአትክልትና የእንስሶችን ስርጭት ለማጥናት ነዳቸው።
በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ላይ፣ በተለይ በምዕራብ ዓለም በብዙዎቹ የሳይንስ ሊቃውንት አስተያየት፣ መተራረኩ አፈ ታሪክ ብቻ እንጂ በዕውኑ አይሆንም በማለት ተጠራጠሩ። ቢሆንም በዚህ ወቅት የኖሩ አንዳንድ መምህራን ለምሳሌ አውጉስት ዲልማን፣ ፍራንጽ ዴሊችና ፍራንሷ ለኖርማን ማየ አይኅ አፈ ታሪክ ወይም ተረት ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ታሪክ ነው በማለት ገመቱ። ለማስረጃ እያንዳንዱ ጥንታዊ ሥልጣኔ ለዚህ ታላቅ ፍዳ ትዝታውን ስለ ጠበቀ ነው የሚል ምስክር አቀረቡ።[11]
ከአሜሪካ (USA) ሕዝብ 2 ሢሶ ወይም 65 ከመቶ የሚያህሉ ማየ አይህ ዕውነተኛ ታሪክ እንደሚሆን ጽኑዕ እምነት አላቸው።[12][13][14] በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት የሚያምኑት ምእመናን አብዛኛው ጊዜ ጸሐፊው ሙሴ በ13ኛው ክፍለ ዘመን አክልበ. ሲሆን ማየ አይህ በ3ኛ ሺህ አክልበ. የደረሰ መቅሠፍት እንደ ሆነ ይቀበላሉ። የማየ አይህ ጥናት የጥፋት ውኃ አለም አቅፍ እንደ ነበር፣ በመሬትም ብዙ ማስረጃ እንዳለ (ለምሳሌ የባሕር እንስሳ ቅርስ በተራሮች ላይ ሲገኝ) ያስተምራል። ሆኖም አብዛኛው የዛሬውኑ ሳይንስ ሊቃውንት ይህ ጥናት ሀሣዊ ነው የምድርም ዕድሜ ብዙ ሚልዮን አመታት ነውና በማለት ተቃውመውታል።
ፍለጋዎች
የሐመር ሥፍራ ማግኘት ከጥንት ጀምሮ ታስቧል። ብዙዎች ፍለጋዎች በደብረ አራራት በዛሬው ቱርክ አገር ቢሆኑም፣ እንዲያውም ዘፍጥረት «የአራራት ተራሮች» ይላል። በኩፋሌ የጫፉ ስም ሉባር ይሠጣል። ሌላ የቱርክ ጫፍ ዱሩፒናር ላይ ወይም በኢራን በደብረ ሳባላን ላይ እንደምትገኝ አንዳንድ ጀብደኞች ይላሉ።
በ1999 አ.ም. (2007 እ.ኤ.አ.) አንድ የቱርክና የሆንግኮንግ ፍለጋ ወደ ደብረ አራራት ሂዶ በአንድ ዋሻ ውስጥ፣ ወደ ድንጋይ የተቀየረ የዕንጨት ግድግዳ እንዳገኘ ናሙናዎችም ከዚያ እንዳወረዱ ይላሉ። ይህ የሐመር ሥፍራ በደብረ አራራት ላይ ተገኝቷል ማለት ነው ይላሉ።[15]
ነጥቦች
- ^ ዘፍጥ. 6:6። እግዚአብሄርን ያሳዘነው ክፋት ምን አይነት እንደ ሆነ ዘፍጥረት ባይነግረንም፣ በዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍት መጽሐፈ ሄኖክና መጽሐፈ ኩፋሌ መሠረት ሰውን መብላት፣ ጥንቆላና ሌላ መረንነት በሰፊው መገኘቱ ነበር።
- ^ Exegetical Fragments[1]
- ^ Origen, Homilia in Genesim II.2 (quoted in Norman Cohn, Noah's Flood: The Genesis Story in Western Thought, p.38. Yale University Press, New Haven & London, 1996. ISBN 0-300-06823-9)
- ^ Cohn, loc. cit.
- ^ Legends of the Patriarchs and Prophets and Other Old Testament, by Sabine Baring-Gould - 1884
- ^ History of Prophets and Kings, al-Tabari
- ^ Perished Nations by Hârun Yahya, Mustapha Ahmad, Abdassamad Clarke, 1999 p. 11
- ^ "Information about Ziusudra and Xisuthros". Archived from the original on 2006-03-26. በ2009-01-14 የተወሰደ.
- ^ Nozomi Osanai, A comparative study of the flood accounts in the Gilgamesh Epic and Genesis (2005)
- ^ Robert M. Best, Noah's Ark and the Ziusudra Epic, 1999.
- ^ Encyclopedia Biblica, 1899, p. 1067
- ^ Surveyed Americans Believe in Biblical Truth. CBN News, December 22, 2007.
- ^ Jennifer Harper: Most Americans take Bible stories literally; Accounts more than lessons, poll reveals. The Washington Times, February 2004.
- ^ David Morris: Six in 10 Take Bible Stories Literally. ABC News, telephone poll February 6-10 2004.
- ^ Ark nestled on Mount Ararat January 19 2008፣ The Peninsula by Satish Kanady